Saturday, 12 February 2022 12:45

አዳም ረታ፤ በይነ-ዲሲፕሊናዊ ንባብ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(3 votes)

 ክፍል ሁለት
ከሰማይ የወረደ ፍርፍር በተሰኘው የአዳም የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ውስጥ የሚገኘው የሚያንፀባርቅ ጥርስ የተሰኘው አጭር ልብወለድ ሌላኛው እኩይ እሳቤን የሚዳስስ ሥራ ነው፡፡ በእዚህ ልብወለድ ውስጥ የምናገኘው ዋና ገጸባሕርይ፣ የራሱን እሴት ፈብርኮ ለመኖር ያልጣረ፣ በተቃራኒው በይሉኝታ እግር ብረት ተጠፍሮ የሚኖር ገጸባሕርይ ነው፡፡ ከእኛ ሥልጣን ውጭ ባሉ ሌሎች አካላት ቀድሞ የተበጀ እሴትን (readymade moral principle)  እንደ ፍፁማዊ መርሕ (a prori moral principle) አድርጎ መቀበል በእኩይ እሳቤ የመውደቅ ምልክት ነው (ማካንታየር፣ 1998: ገጽ 171)፡፡ ከላይ በጠቀስኩት ልብወለድ ውስጥ የሚገኘው ገጸባሕርይ በእኩይ እሳቤ የመውደቁን ሐቅ እንዲህ ሲል ራሱ ይተርክልናል፡-
…ምን ይጨቀጭቁኛል … ሴት … ሕፃናት … እኔ ትዳር የመሰረትኩት የኅብረተሰቡን ፈተና ለማለፍ ነው… የሚፈጥሩና የሚያጠፉ የሰው ሥልጣናት ፈላጭ ቆራጭ ወሬአቸው እንዳይቀስፈኝ …. ኃላፊነት የሚሰማኝ መኾኔን ለመፈተሽ ከአብራኬ ይጀምራሉ… ስለዚህ ሕፃናትን እንደ ማሸነፊያ አርማዬ አደባባይ አውጥቼ አውለበልባቸዋለሁ… ውፍረታቸው፣ ማማራቸው፣ ንጽሕናቸው ለእኔ ‘ሰብአዊ ነው’ የሚያሰኝ ስም ይሸልመኛል… የወንድነቴም ምስክር ነው (አዳም፣ 2007፡ ገጽ 10-11)፡፡
፩. ፪. ሐቀኝነት (authenticity)
ሐቀኝነት፣ በሳርተር የኀልዮአዊነት ፍልስፍና ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው ፍልስፍናዊ ጭብጥ ነው፡፡ ይኸ ጭብጥ፣ ሳርተር ጭንቀት (anguish) የሚል ስያሜ ከሰጠው ፍልስፍናዊ ጭብጥ ጋር በቀጥታ የሚቆራኝ ሲሆን እኩይ እሳቤን (bad faith) የሚቃረን ጭብጥ ነው፡፡ ከላይ እንደዳሰስኩት፣ ጭንቀት፣ የተጎናፀፍነውን ፍፁማዊ አርነት እውቅና መስጠታችን የሚፈጥረው ስሜት ነው፡፡ ሳርተር እንዲህ ጽፏል፣ “ it is by anguish that man becomes conscious of his freedom, or, in other words, anguish is the manner of existence of freedom as consciousness of existing” (ሳርተር፣ 1956: ገጽ 66)፡፡
ሐቀኝነት፣ ብቸኛው የሳርተር ኀልዮአዊ ፍልስፍና የሞራል ልዕልና  (existentialist ethical virtue) ነው፡፡ ሐቀኛ ግለሰብ፣ ሁሌም የሚኖረው ራሱ በቀየሰው የአኗኗር መንገድ ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ሐቀኛ ሰው፣ የሚኖረው የራሱን ትርጉም አበጅቶ ነው (አንደርሰን፣ 1993: ገጽ 58)፡፡ ለዚህ ሰው፣ የእሱ ተሳትፎ የሌለባቸው ነባር እሴቶች ዋጋ ቢስ ናቸው፡፡
ሐቀኝነትን የሚዳስሰው የአዳም የልብወለድ ሥራ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር በተሰኘው የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ውስጥ የቀረበው ሁለት ልጃገረዶች የተሰኘው አጭር ልብወለድ ነው፡፡ ይኸ ገጸባሕርይ፣ የራሱን እሴት ፈጥሮ የሚተዳደር ሐቀኛ ገጸባሕርይ (authentic protagonist) ነው፡፡ የዚህን ግለሰብ የሞራል እሴት በአሮጌው የማኅበረሰቡ የግብረገብ ድንጋጌ ስንመዝነው ፍፁም የተወገዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለዚህ ግለሰብ በርካታ ፍቅረኞችን እየለዋወጡ መዘሞትና በመጠጥ መስከር ሰናይ ተግባር ነው፡፡
በሕይወቴ ወጥ ውስጥ ትንንሽ የእብደት ቅርንፉድ፣ የልክስክስነት ኮረሪማ፣ የባለጌነት ነጭ ሽንኩርት፣ የደደብነት ጥቁር አዝሙድ… የመሳሰለ ልጨምርባት እፈልጋለሁ (አዳም፣ 2007፡ ገጽ 151)፡፡  
በግል ባሕሌ ሦስት ወይም አረት የሴት ጓደኞች ያስፈልጉኛል፡፡ ቢመችና ቢቻል በየወሩ ይቀያየራሉ (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 152)፡፡
ከሁሉ ነገር (ብዙ ጉዳይ የምፈፅም አይመስልም?) በመጀመሪያ የማደርገው ነገር ያለገደብ መጠጣት ነው፡፡ ቢራ ሳይሆን ጅንና ብራንዲ (ዝኒ ከማሁ)፡፡
ፀሐይ ስታቀዘቅዝ በየቡና ቤቱ እየገባሁ የምታምር ሴት እፈልጋለሁ፡፡ መበላሸት ምኞቴ ነው፡፡ የጥፋት ፍላጎትም ይሆናል። በቁርጡና በጅኑ እያላበኝ ሴት ለመኝታ እጠይቃለሁ (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 153)፡፡
…ዛሬ ግን አልተዋጣም፡፡ ደክሞኛል። አርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ ከሥራ ቀርቼ ያወጣኋት ባለትዳር አድክማኛለች፡፡ እኚህ ባለትዳር ባሎች ሚስቶቻቸውን ምን ያበሏቸዋል… ወይስ ያለመጥገብ ነው (ዝኒ ከማሁ)፡፡  
፩. ፫. ወለፈንዲ (absurdity)
በአዳም ከሰማይ የወረደ ፍርፍር በተሰኘው የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ውስጥ ከቀረቡ የአጫጭር ልብወለድ ታሪኮች መካከል አንዱ ከረሜሎች የተሰኘው አጭር ልብወለድ ነው፡፡ ይኸ የአዳም ሥራ፣ ወለፈንዲ (absurdity) የተሰኘውን የአልበርት ካሙን የኀልዮአዊነት ፍልስፍና ጭብጥ የሚዳስስ ሥራ ነው፡፡ አዳም እንደሚነግረን፣ የዚህ አጭር ልብወለድ ዐቢይ ጭብጥ በእየለቱ የምንገፋው ተመሳሳዩ ህልውናችን የወለደው ስልቹነት ነው፡፡ ይኸ ልብወለድ  ታሪክ ጥቂት ብቻ ለውጦች በማድረግ ተደጋግሞ የተጻፈ ነው፡፡ ደራሲው ይኸን በማድረጉ ኋላ ላይ በሥራው መደምደሚያ ላይ ያቀረበው ፍልስፍና የሰመረ እንዲሆን ረድቶታል፡፡  
አዳም፣ በዚህ ሥራው የሚያሳየን የሰው ልጅ የመኖር ኩነኔ፣ የምኞት ግዞተኛ አድርጐት በልማድ የሚጓዘው ጉዞ አዲስ መዳረሻ የሌለው ከንቱ ጉዞ የመሆኑን ሐቅ ነው፡፡ የከረሜሎቹ ውክልና የሰው ልጅ ህልውና ነው፡፡ እነዚህ ከረሜሎች በቀለም የተለያዩ፣ ተመሳሳይ ቅርፅ ያላቸው፣ በተለያየ ልባስ የተጠቀለሉ እና በተለያዬ ቄንጥ የተሸመለሉ ናቸው፡፡ የከረሜሎቹ በመልክና በሽፋን መለያየትና በተለያየ ቄንጥ መሸምለል በእያንዳንዱ ዕለት የምንኖረው ፈርጀ ብዙ ህልውና ተምሳሌት ነው፡፡ ይኸ የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን በደምሳሳው ስናስበው፣ አንዱ ከአንዱ የተለያየ ይመስላል። ነገር ግን፣ ይኸ ሕይወት ልክ በመልክና በሽፋን የተለያዩ ከረሜሎች ተራ በተራ ተገልጠው ሲቀመሱ ያላቸው ጣዕም ተመሳሳይ እንደሆነ ሁሉ አዲስነት የሌለው ሕይወት ነው፡፡ አዳም እንዲህ ጽፏል፡
ነገ የገና በዓል ዛሬ የገና ዋዜማ ነው። ከቢሮ ልወጣ ስል አንዲት ሴት የዋዜማን በዓል ከምሳ በኋላ ቢሮ ውስጥ እንድናከብር ከረሜላ ገዝተህ ና አለችኝ (እስዋንም እንደ ከረሜላ አልፎ አልፎ የሚሰራት፣ ከአፏና ከአይኖቿ ዕፁብ ጣዕም የተንዠረገገ)፡፡ መልእክቷን እንዳልረሳው ምሳ ከመብላቴ በፊት አንድ ሱቅ ጐራ አልኩና የተለያየ ቀለም ያላቸው ከ30 የሚበልጡ ከረሜላዎች ገዛሁ፡፡ ከረሜላዎቹ ሞላሌ ቅርፅ አላቸው። መጠቅለያዎቹም አንዱ ከአንዱ የማይመሳሰል ውብ አብረቅራቂ ወረቀቶች ናቸው፡፡ የተሸመለሉባቸውም ቄንጦች ሶስት ዓይነት ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱም ጫፎቻቸው የተጠመዘዙ፣ የሚቀጥሉት በሠፊው ጐናቸው በኩል የተጠመዘዙ ሲሆኑ፣ ሶስተኛዎቹ ደግሞ በአንድ ጠባብ ጐናቸው በኩል የተጠመዘዙ ናቸው። ጉንፋን ስላመመኝ አላማዬ ለምሳ ሾርባ ቢጤ /የበግ ሾርባ/ ልጠጣ ነበር፣ ግን ላገኝ አልቻልኩም። በምትኩ በቃሪያና የተጠበሰ የበግ ሥጋ በሚጥሚጣ ተምትሜ በላሁና ወደ ቢሮዬ መመለስ ጀመርኩ፡፡
የከረሜላዎቹ ልባስ በጣም ማራኪ ስለነበር አንጀቱና ጥርሱ ቢኖረኝ ሁሉንም ሳልበላቸው አልቀርም ነበር፡፡ ቢሮዬም ሳልደርስ አንዱን ከረሜላ ገልጬ አየሁት። ልክ ከውጭ ከሽፋኑ እንደ ሚገመተው ወደ እንቁላል የሚጠጋ ሞላላ ቅርፅ አለው። እላዩ ላይ አንዳንድ ጉርብጥብጥ ምስል ነገሮች ተሰርተውበታል፡፡ ትርጉማቸው አልገባኝም። ከረሜላውን ወደ አፌ አስገብቼ መጥባት ጀመርኩ፡፡ ድዴን ጐረበጠኝ። አይመችም፡፡ ለመቆረጫጨም ፈልጌ ደጋግሜ በጥርሶቼ ከላይና ከታች ሆድቃውን ተጫንኩት፡፡ በመጀመሪያ ትንሽ ታገለኝና ብዙም ሳይቆይ ተደረመሰ፡፡  ከውስጡ እንደ ማር ሙሙት የሚል፣ እንደ አረቄ ሽታ ሰንፈጥ የሚያረግ ጣፋጭ ነገር አፌ ውስጥ ፈሰሰ፡፡  ሽታው አደናብሮኝ ልተፋው ፈልጌ መጣፈጡ ግን ገታኝ፡፡ በቀስታ እየቆረጫጨምኩ እየሰባበርኩ እያባበልኩ እያንከላወስኩ ዋጥኩት፡፡ በአፌ ውስጥ የነበረው የጥብስና የሚጥሚጣ ሽታ ጠፍቶ እንግዳ ነገር ተሰማኝ፡፡ ሌላ ከረሜላ አውጥቼ ቆረጨምኩ፡፡ ያው ነው (አዳም ረታ፣ 2007: ገጽ 126)፡፡
በድግግሞሽ ዑደት እንዲጓዝ የተደነገገው ህልውናችን የወለደው ስልቹነት (boredom) የወለፈንዲነት (absurdity) ስሜት መገለጫ ነው፡፡ ወለፈንዲነት፣ የታዋቂው ፈረንሳዊ ደራሲና ፈላስፋ አልበርት ካሙ ፍልስፍና ዐቢይ ጭብጥ ነው፡፡ የወለፈንዲነት ስሜት አንዱ ምንጭ የሰርክ ደፋ ቀናችንን ፋይዳ ቢስነት መታዘብ ነው (ኮፕልስተን፣ 1956: ገጽ 97)፡፡ ካሙ እንዲህ ጽፏል፡-
It happens that the stage-sets collapse. Rising, tram, four hours in office or the factory, meal, tram, four hours of work, meal, sleep and Monday, Tuesday, Wednesday, Thursday, Friday and Saturday, according to the same rhythm–this path is easily followed most of the time. But one day the ‘why’ arises and everything begins in that weariness tinged with amazement (ካሙ፣ 1955: ገጽ 18).
እንደ ካሙ እሳቤ፣ የኑሮ ድግግሞሽ የሚወልደው የትርጉም ማጣት ወይም የወለፈንዲነት ስሜት ራስን ወደ መግደል ድርጊት ይመራል፡፡ ነገር ግን፣ ለካሙ ይህ ድርጊት የተወገዘ ነው፡፡ እንደ እሱ እሳቤ፣ ራስን መግደል ለወለፈንዲነት ስሜት ፈፅሞ መፍትሄ መሆን አይችልም፡፡ ካሙ እንደሚለው፣ ትክክለኛው የወለፈንዲነት መፍትሄ ራሱን ወለፈንዲነትን መቀበል (lucid recognition) ነው፡፡ በመሆኑም፣ ምንም እንኳ ሕይወት ፍፁማዊ የሆነ ፋይዳ የሌለው ቢሆንም፣ የሰው ልጅ ይህን ሕቅ ተቀብሎ ግላዊ ትርጉምን በመፍጠር የመኖር ኃላፊነት አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱ ሕይወት ለካሙ ትክክለኛ (authentic) ሕይወት ነው፡፡ ለካሙ ትክክለኛ ሕይወት የሲስፈዝ አይነት ነው፡፡ ሲስፈዝ በግሪኮች አፈ-ታሪክ ውስጥ የሚገኝ የኮሪንዝ ንጉስ ነው፡፡ ይኸ ንጉስ እጅግ ከባድ ጥፋት በመፈፀሙ ኃያላን አማልክት ተራራ ጫፍ ሲደርስ መልሶ ቁልቁል የሚንከባለል ግዙፍ ቋጥኝ ለዘላለም እያመላለሰ እንዲኖር ፈረዱበት፡፡ ይኸ ልፋቱ ግን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አይነት ከንቱ ነበር። ሲስፈዝ የሚወክለው የእያንዳንዳችንን ሕይወትና ዕጣ ነው፡፡ ቋጥኙ የሕይወታችን ሸክም ምሳሌ ነው፡፡ ሁላችንም ይህን ሸክም ተሸክመን ዘወትር ተመሳሳይ ጉዞ እንጓዛለን። መኖር ዕዳ ነውና ዕጣችንን ከመቀጠል ውጪ ሌላ አማራጭ  የለንም፡፡ ካሙ እንደሚነገረን፣ ምንም እንኳን የሲስፈዝ የኑሮ ዕጣ ፋንታ በሌለው ድግግሞሽ የተሞላ ቢሆንም፣ ይህን በድግግሞሽ የተሞላ ፋይዳ ቢስ ዕጣውን በፀጋ ተቀብሎ በጀግንነት በመጋደል፣ ሕይወቱ ፋይዳ ያለው እንዲሆን አድርጓል፡፡ ዴቪድ ዌስት የሚከተለውን ጽፏል።-
The myth of Sisyphus gives Camus a potent image of the futility of existence. Sisyphus is condemned to roll a heavy stone up a great hill, only to see the stone roll down again and face the prospect of the repetition of the same task for all eternity. Camus’s response is that only the ‘lucid’ recognition of the absurdity of existence liberates us from belief in another life and permits us to live for the instant, for beauty, pleasure and the ‘implacable grandeur’ of existence. Lucidity is that clarity and courage of mind which refuses all comforting illusions and self-deception. Lucidity, in other words, is the counterpart of the notion, common to both Kierkegaard and Sartre, of anguish as the self-conscious and unflinching apprehension of freedom. But in the end Camus is more positive than either Kierkegaard or Sartre. Though living with absurdity is ‘a confrontation and a struggle without rest’, Camus concludes his account of the mythical Sisyphus with defiance: ‘One must imagine Sisyphus happy’ (ዌስት፣ 1997: ገጽ 152).
እንደ ካሙ እሳቤ፣ በኑሮ ሂደት ውስጥ ወለፈንዲነትን መጋፈጥ በራሱ ታላቅ (ultimate) ፋይዳ ነው፡፡ ለኒሂሊስቶቹ ኤሚሊ ሚሃይ ቾራን እና አርተር ሾፐንአወር ግን በሕይወት ውስጥ ጨርሶ ፋይዳ ያለው ነገር የለም፡፡ ይኸ አይነቱ አቋም ነው ኒሂሊስቶቹን ከአብዘርዲስቱ ካሙ ጋር የሚያቃርነው፡፡
የአዳም የከረሜላ ፍልስፍና አንኳር ሐሳብ (central thesis) እንዲህ የሚል ነው፡ የቱንም ያህል የሰው ልጅ ህልውና በተለያየ ጎዳና ቢጓዝ፣ እንደ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ጨዋታ በአሰልቺ የድግግሞሽ ዑደት የሚነጉድ ነው፡፡ ባለፈው፣ በዛሬውና በመጪው ጊዜ መካከል መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ ሰው ይኸን ፈፅሞ ሊሸሽ የማይቻል ገሀድ ሲገነዘብ ነፍሱ የስልቹነትን ብሉኮ ትከናነባለች፡፡ ነገር ግን፣ አዳም፣ ካሙ እንደተናገረው፣ ስልቹነት ራስን የመግደል ሐሳብን ይጠነስሳል የሚል እምነት የለውም።

Read 1594 times