Sunday, 20 February 2022 16:54

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የባላንታይን ዋዜማ ወግ
                                  በእውቀቱ ስዩም


              ከብዙ ዘመናት በኋላ ከወዳጄ ምእዝ ጋራ ትናንት በስልክ ተገናኘን፤ ላንድ ሰአት ተኩል ያክል ስናወጋ የተረዳሁት ነገር፣ ጊዜ ብዙ እንዳልቀየረን ነው፡፡
“የት ልትጋብዛት ነው ያሰብከው?” ሲል ጠየቀኝ፥
“ራቅ ያለ ሰፈር ልወስዳት ነው ያሰበኩት፤ እኛ ሰፈር ያሉት ሬስቶራንቶች ሁሉ ያውቁኛል”
“በሬስቶራንቶች ውስጥ ያሉትን አስተናጋጆች ሁሉ ትጀነጅናለህ እሚባለውን ሀሜት እንዴት ታየዋለህ?”
“ከእውነት የራቀ አይደለም”
“ደግ አደረግህ፤ ፈጣን ሎተሪ የሚደርሰው ደጋግሞ በመፋቅ ነው” አለና አበረታታኝ፤
“አለባበሴ ምን ቢሆን ትመክረኛለህ?’ አልኩት፤
“ሮዝ ሸሚዝ ፤ ቀይ ክራባት”
“ሱሪስ?”
“ሱሪ መታጠቅም እንዳትዘነጋ”
“ከድዴ በቀር የቀላ ነገር የለኝም፤ ቀይ ነገር የግድ ነው?;
“ባላንታይንን ያለ ቀይ ማክበር ጥምቀትን ያለ ሎሚ እንደማሰብ ነው”
“ወይን ጠጅ ሹራብ አለኝ፤ በላዩ ላይ የቤትናም ባንዲራ ጣል ባደርግበት ይደብራታል?”
“አግኝታ ነው?! እንዲያውም በልክህ ካገኘህ፣ የቼ ጉቢራን ኮፍያም አድርግ! ሴቶች ጀግና ይወዳሉ፤ የጀግና መታሰቢያም ይማርካቸዋል! ትልቅ አናት ያለው ወንድማ፣ ልባቸውን ይነካዋል፥ "ትልቅ አናት የትልቅ ልብ ፍንጭ ነው" ትል ነበር፤ ዮዲት ጉዲት!"
“ሌላ ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል?“
“አውራት! ጁንታው፤ ኢኮኖሚው! ኖ ሞር ምናምን-- ከሚሉና የመሳሰሉ ርእሰ ጉዳዮች ለጊዜው በሰባት ክንድ ራቅ! መረቅ መረቁን አጫውታት፥ በመሀል በመሀል የሷንም አስተያየት አድምጥ! ታዲያ ጨዋታ አማረልኝ ብለህ ያንድ ሰው ተውኔት እንዳታደርግባት! አደራ በሰማይ አደራ በባህር! እጅ ካላት እጇን ያዝ! በጨዋታ መሀል ‘ደረቅ! አስቀያሚ! ሞዛዛ‘ ካለችህ፤ ጨዋታውን ቀጥል፤ እያወራሀት ካዛጋች ወይም  #በተረፈ; የሚል ቃል ካፏ ከወጣ፣ ቶሎ ብለህ ሂሳብ ከፍለህ ከፊቷ ጥፋ፤ ባስና ባቡር ብታጣ፣ የፍሳሽ መኪናም ቢሆን ተንጣልጥለህ አምልጥ፤ ብቻ፥ ፈጣሪ በተረፈ ከሚለው ቃል ያትርፍህ”
“አሜን!”
“የሚያስጎርር ነገር ካለህ ጎርርላት፤ አየህ! አባቶቻችን ከገደሉ ገዳይ ነን ብለው ለመደንፋት አያፍሩም ነበር! ብዙ የቀንድ ከብት የነበራቸው አርቢዎች፣ በህዝብ ፊት በወተት የተሞላ ገንዳ ውስጥ ይዋኙ ነበር፤ የከብት አንጀት አንገታቸው ላይ እንደ ሀብል የሚጠመጥሙም ዘላኖችም ነበሩ፤ አንጀባ ላባቶች ከሰራ ለልጆች እማይሰራበት ምክንያት የለም’፤ራስን ዝቅ ዝቅ ማድረግ ለጽድቅ እንጂ ለጠበሳ አይሆንም”
“ዘሬን ከጠየቀችኝስ ምን ልበላት?”
“ዘር ካለህ ዘርዝርላት! በዘር ስም ሀብት መቋጠር እንጂ ዘር መቁጠር ችግር የለውም” አለና ተፐላሰፈ፤
“እኔ የማውቀው እስከ ቅደመ አያቴ ድረስ ብቻ ነው” አልኩት፥
“ከቅደም አያት ባሻገር እሚቆጥር አለ እንዴ?”
“እንዳለ በቅርቡ ተረድቻለሁ”
“እስኪ አካፍለኝ”
ዝርዝሩን እንደሚከተለው አቀረብኩለት፤
- “እናትና አባት
- አያት
- ሲኤምሲ
- እንጀራ አያት
- ቅድመ አያት
- ድህረ አያት
- ምንጅላት
- ምንጅልናት
- ፍናጅ
-ቅናጅ
- ቅዳጅ
- አናዳጅ
- ማንትቤ
- ማንቴስ
- ሆሞ ኤሬክተስ ( Homo erectus )
ምኡዝ በረጅሙ ተነፈሰና፤
“በተረፈ”

________________________________________

                   ዳግማዊው No More ይጀመር
                          ኦሃድ ቤንዓሚ

              የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ መንግስት ሥልጣኑን ከተረከበት ቀን ጀምሮ፣ ባለፈው የገና በዓል ዕለት እንደወሰደው እርምጃ ያሳዘነኝ ነገር ብዙ የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ውሳኔያቸው ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው በወቅቱ ጽፌ ነበር፤ ውሳኔያቸው እነሆ 39ኛ ቀኑን ይዟል፤ አሜሪካኖቹም ቂማቸውን አልረሱም፡፡ አሁንም ዶ/ር ዐቢይን በተለያየ መንገዶች የማሸማቀቁን ተግባር ቀጥለውበታል፡፡ አዎ ዶ/ር ዐቢይ ለአሜሪካኖቹ ጥያቄ ሸብረክ ማለት አልነበረባቸውም፤ አንዴ ሸብረክ ካሉላቸው ምዕራባውያኑ ጫናቸውን ነው የሚገፉበት፡፡
መሸወድ የለብንም፤ ምዕራባውያን ሕዝብ የሚደግፈውን የታዳጊ አገር መሪ መነካካት አይፈልጉም፤ አንዴ ከሕዝብ ጋር ካጣሉት በኋላ ግን ለእኩይ ተግባራቸው መንገድ ይከፍትላቸዋል፤ ስለዚህ መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር ጉዳዩ ከዐቢይ ጋር ሳይሆን ከአገራችን ጋር መሆኑን ነው፡፡ ትላንት ለ27 አመታት በጥላቻ ዘመቻ አገራችንን ሲከፋፍልና ፈንጂ ሲቀብር የነበረውን፣ አሁንም የአሜሪካኖችን ትዕዛዝ ተማምኖ ሸዋ ሮቢት ድረስ ትውልድ አስጨራሽ ጦርነት የሚያካሂደውን ህወሓት፣ ወደ ሥልጣን ለማምጣት በግልጽ የጀመሩትን ዘመቻ ማስቆም አለብን፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ተሳስተው ይሆናል፤ግን የሚሳሳተው የሚሰራ ብቻ ነው፤ ለበጎ አስበውት ይሆናል፤ ውጤቱ ግን ጥሩ አልሆነም፤ አሜሪካኖቹ እንደሚፈልጉት ነው የሆነው፤ ውሳኔያቸው ከሕዝብ ጋር አቀያይሟቸዋል፡፡  
በጋዳፊ ላይ የሆነውም ይሄው ነው፤ መጀመሪያ ከሕዝብ ጋር አጣሏቸው፤ ከዛ ሕዝቡ ራሱ አሳዶ አስወገዳቸው፤ ይህ በኛ አገር ላይ እንዲፈጸም የሚፈልጉ አሉ፤ ዋነኛው ደግሞ ጁንታው ነው፤ ዐቢይን በሕዝቡ መበቀል ይፈልጋል፡፡ አሁን ለዚህ ሲል እባቡ ጁንታ፣ ሁሉንም የድርድር ቅድመ ሁኔታዎቹን አንስቶ ሰላም ወዳድ መስሎ መደራደር ይፈልጋል፡፡
ሕዝቤ አትሸወድ፤ ሁላችም በይቅርታ ከዐቢይ ጎን መቆም ይኖርብናል፤ ዳግማዊው NoMore መጀመር አለበት። ጉዳዩ አሜሪካ ግብጽንና ወያኔን ለማገዝ የሄደችበት መንገድ እንጂ ለኢትዮጵያ አስባ ወይም ዐቢይ ከወያኔ ጋር የሚመጣጠን እልቂት ፈጽመው አይደለም፡፡ ጦርነቱን የጀመረው ወያኔ ነው፤ የሕዝቡን ዕልቂት ያባባሰውም ወያኔ ነው፡፡ አሁንም አፋር ውስጥ ሰው እየገደለ ያለው ወያኔ ነው፤ ብሔራዊ ውርደትን አሜን ብለን መቀበል የለብንም፤ የራሳችንን ችግሮች ራሳችን እንፈታለን፤ እናውቅበታለንም፡፡

________________________________________


                   ባለቤት አልባ ሀገር እንዳያደርጉን!
                           ሙሼ ሰሙ



            በአገራችን  የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረት ታሪክ ውስጥ፣ ፓርቲዎች ሲዋሃዱ፣ ሲጣመሩ ወይም ግንባር ሲፈጥሩ እንጂ የፓርቲ አባላት እንደ ቁሳቁሱ ሲወረሱ አይተን አናውቅም።
ብልጽግና ይህንን ማድረግ የቻለ የመጀመርያውና ብቸኛው ፓርቲ ነው። ፓርቲው “ቆዳ” ሳይልጥና ተመላሽ ሳያደርግ፣ “በልኩ” ሳይቀድና (በእርግጥ ልኩ ምን እንደሆነ ማወቅ ያዳግታል) ሳይሰፋ በአባልነት ቅጽ ልክ ሁሉንም አባል መዋጡና መሰልቀጡ ከፓርቲው ችግርነት አልፎ ሀገራችንንም ስጋት ላይ እየጣለ ነው፡፡
ገሀድ ከወጣው ውስጠ ፓርቲ ግብ ግቡ የምንረዳው ነገር ቢኖር፣ ብልጽግና በፖለቲካ አመለካከት፣ በትግል ስልትና በአደረጃጀት ዙርያ መግባባት ላይ ሳይደርስ፣ ሊውጠው ከሚችለው በላይ የኢህአዴግ አባላትን በጅምላና በአፍ ስብከት ለውሶ ቢጎርሳቸውም፣ "ብልጽግና በፍጹም አይውጠንም አይሰለቅጠንም፤ እምቢኝ አሻፈረኝ” ያሉ ይመስላል።
ፓርቲው በውስጡ ሲብላላ የነበረው ቀውስም ቀስ በቀስ እያደገ በመሄድ፣ እሰጣ አገባው ፓርቲውንና ሀገሪቱን እንደ አሲድ እየሸረሸራቸውና እያሟሟቸው ይገኛል። ለዚህ መገለጫው አባላቱ ፓርቲያቸውን በሙስና በድርጅታዊ አሰራር ዝርክርክነት፣ በሕግ ጥሰት፣ በአሰራር መዛነፍና በአወቃቀር መፋለስ፣ በራዕይና በርዕዮተ ዓለም አልባነት እየከሰሱት መሆኑ ነው።
ያልተዋሃደው የብልጽግና ውህደት፣ ችግሩን በውስጠ ፓርቲ ትግል መፍታት ተስኖት፣ አባላቱ የፓርቲውን ብቻ ሳይሆን የመንግስትንም ምስጢር መደበቅ እያዳገታቸው መጥቷል፡፡ እርግጥ ነው፣ የፓርቲው ጉዳይ እዳው ገብስ ነው። ይልቅ  የሚያሰጋን፣ የውርስ አባላቱ ፓርቲያቸውን ባለቤት አልባ አድርገው ሲያበቁ፣ እኛንም ባለቤት አልባ ሀገር እንዳያደርጉን ነው!?

_____________________________________________

                       "አድብቶ ማድማት"
                             ረድኤት አሰፋ


            «ቀለል ያለች ሴት ትመቸኛለች» ሲለኝ ቀና ብዬ ዐየሁት። ይህ ቅፅበት የተደገመ ሁሉ መሰለኝ። እንዲህ ያለኝ ማን ነበር። ትዝ አልል አለኝ። ትዝ ያላለኝ ሁሉም ስላሉኝ ነው። መጀመሪያ እንዲህ የተባልኩ ሰሞን በድንጋጤ ራሴን ጠይቄያለሁ። “መቅለል” መልክ ሆነ ማለት ነው? መቅለል ቅላት ሆነ? ቅጥነት ሆነ? መቅለል ደም ግባት ሆነ? ብዬ። አሁን ግን በደንብ ገብቶኛል። ትርጉሙም አልጠፋኝም። ተስፋ የሌላት ሴት ትመቸኛለች ማለቱ ነው። የቆሰለች። ፍቅር እንደ አውሬ አድብቶ ልቧን ያደማባት፣ ሕመሟን ላለማዳመጥ ዳግመኛ ወደ ፍቅር የማታማትር፣ “ሰው አላምንም” ያለች። ቶሎ መድረስ የፈለገ ተራማጅ የሚያሳብርባት፣ መንገድ የሚያሳጥርባት አቋራጭ ኩርባ... መዳረሻ ሳትሆን ማለፊያ ሴት ማለቱ ነው።
አንሶላውን ከላዩ ላይ ገፍፌ ተከናነብኩ። ነፍሴን በረዳት መሰል አንዘፈዘፈኝ። ቀና ብዬ የያዝናትን ክፍል ቃኘኋት። ልብስ አልባ ቁምሳጥን፣ ቴሌቭዥን፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ አልጋ፣ ነጠላ ጫማ፣ መጋረጃ ... ኮርነሩ ጋር ...መቀመጫ፣ መስታወት፣ ገንዳና ፊት መታጠቢያ ያለው መፀዳጃ ክፍል። አለቀ። ነዋሪነታችንን የሚያሳብቅ ቅያሪ ልብስ የለም። ምግብ ማብሰያና ማስቀመጫ የለም።
 “እኔና ይቺ ክፍል ልዩነታችን ምንድነው?” ሁለታችንም ጊዜያዊ ነን፤ ግፋ ቢል ማደርያ። እንግዳ ለመቀበያ እንጂ ለመኖርያ አንሆንም። እልፍኝነታችን ማለፊያነታችንን ያሳብቃል። አመጣጤ ልቆይ ማለት እንዳልችል በጥንቃቄ የተበጀ ነው። አንኳኪ እጆች በደጅ አሉ። ፈልጎ መግባት፣ ቢፈልጉም ባይፈልጉም መውጣት። ማን እንደጠለፈው የማላውቀው፣ ያ ነው ዳንቴሌ።
ዞሮ አቀፈኝ። እርቃን ቅዝቅዝ ሰውነቱ ይሻክራል። አንሶላውን ገልጦ እየተጠጋኝ፤ “እንዳንቺ የሚ’ረ’ዳኝ የለምኮ” ይላል። መረዳት ሲል መርከስ መሆኑን አውቃለሁ። ሰዓት ሳይመርጥ ይደውላል። እምቢታዬ መሰበሩን ያውቃልና አይጠይቀኝም። ለመገናኘታችን ብቸኛው አረንጓዴ መብራት የርሱ መፈለግ ነው። ያዲሱ ዐለም ስርዐት እንዲህ ነውኮ። በትዕዛዝ እንደሚሹት አይነት ሞደፊክ ሴት ማሰራት። “ሁኚ” አይሉም። “የምወደው እንዲያ ነው” እያሉ በጎንታ ይቀርፃሉ። ስስ መስለው... እርዳታ ፈላጊ... ተጎጂና ቁስለኛ መስለው፣ በሀዘን የቀለጠ የሴት እናታዊ ሰብዕናን እንደየ ፍላጎታቸው ያበጃሉ።
የቀለለችን ሴት ማን አቀለላት? ጠማማ ፍቅር አይደል? መከዳት አይደል? መቁሰል አይደል? እምነት ማጣት አይደል? መበደል አይደል? ማን ቀሎ ተፈጠረ? ማሕፀኔ በራፍ እንቁላሎች አሉ። ጡቶቼ ውስጥ እስኪታዘዝ ያደፈጠ ወተት አለ። እድሌ ውስጥ ያልተጨፈረ ሀይሎጋ፣ ሕልሜ ውስጥ ያልተሰቀለ ባጥ አለ። ታዲያ ይሄ ሁሉ ማቅለል፣ ይሄን ሁሉ ተዐምር ለማራከስ አይደል? የረከሰውን እንደ ልብ ዘግኖ ለማሻመድ? አሻምዶ ለመትፋት። ደግሞ ለባሰበት ረሀብተኛ ሰፌዱን ለማቀበል... ከዛ ለማሻገት?
ወንዶች ተናብበው ነው የሚጫወቱት። ኳስ በዘዴ ይቀባበላሉ። የመጀመሪያዎቹ አፍቃሪ ነን ብለው ይመጡና ንጽህናን ያረክሳሉ። ይበድላሉ።  ይክዳሉ። ልብ ይሰብራሉ። እንደ ቡድን ሬስለር አቁስለው ይሄዱና እጃቸውን ተጨባብጠው፣ መሰሎቻቸውን ወደ መረቡ ያስገባሉ። በውሻ ጭንብል የቀደዱትን ጉያ፣ የጅብ መንጋ አሰልፈው ያስወርራሉ። ልብ ያጣችውን ሴት... በህመም የቀለለችውን... ተስፋ የቀበፀባትን፣ የሚያቋርጥና የሚተመትም የተራማጅ መንጋ ይሰለፋል። ከዚያማ ምኑ ይወራል? መቀባበል ነው። እስክትተነፍስ ድረስ? ቆዳዋ እስኪላላጥ። እስክትቀደድ። ይሄን የረቀቀ ክፋት ማን አስተማራቸው? አሰላለፋቸውንስ የት የት እየተገናኙ... መች መች እየተቀጣጠሩ ነው የሚመዳደቡት? አጥቂና አከፋፋዮቻቸውን የት ተሰብስበው ነው የሚወስኑት?
ተነሳሁ። አንሶላውን ጥዬለት በቅዝቃዜ ተቆልምሜ ወደ ገላ መታጠቢያው ስሄድ፣ “በርዶሻልኮ ነይ ልቀፍሽ” አለኝ። ያልተነፈሰ ስሜት ይቀረዋል። ለራሱ ማሰቡን የሚዘረጋልኝ፣ ለኔ በማሰብ ሽፋን እየጠቀለለ ነው። ራስ ወዳድነቱን፣ እኔን ወዳድነት ሊያስመስለው ይዳክራል። ሲኦል ውስጥ ተኝተን የብርሃን መልዐክ ለመምሰል መጣርን ምን ይሉታል? ክፋት ላይ ተጋድሞ መልካም ስም ምን ይሰራለታል? ለስጋም ለሕሊናም ትርፍ እንዴት ይታሰባል? አልዞርኩም። መጸዳጃ ክፍል ገብቼ ከውስጥ ቆለፍኩት። የራስ-ላዩን ቀዝቃዛ ውሃ ከፍቼ ወለሉ ላይ ተቀመጥኩ። ሞቀኝ። ምን ያኽል እንደቆየሁ አላውቅም። ከውጪ ያንኳኳል። ይሄኔ ስሜቱ ሳይረግብለት የመውጫችን ሰዐት መድረሱ አስግቶት ይሆናል።
ገላዬን ለታጠብኩት ልቤ ለቀቀች። ውሃው ስር አገኘኋት። ያለ ጥፋቷ ያሰርኳትን ከፍርግርጓ ፈንቅዬ አወጣኋት። ራሴ ተበድዬ ለምን ራሴን እቀጣለሁ? ባመንኩ ለተከዳሁ፣ ባፈቀርኩ እንደ ሞኝ ለተቆጠርኩ፣ አብሬ ልኑር ማለቴ ወህኒ ጠባቂ ላስመሰለኝ... እድል የሰጠኋቸው ፊት ለነሱኝ...  ቀና ብዬ አንገት ማስደፋት ሲኖርብኝ ራሴው አንገት የምደፋው ለምን?
በሩን እየቀጠቀጠ ይጠራኛል “ደህና ነሽ? በሰላም ነው?”። ሳቄ አመለጠኝ። በደህንነቴና በሰላሜ በኩል የተዘረጋ ስሜቱ፣ ጉያዬን ኮረኮረኝና እስካነባ ድረስ በሳቅ ፈረስኩ። ሰንሰለቱን የበጠሰ ጡንቻም ባሪያ ስሜት ተሰማኝ።
የባርያውን ጥያቄ ተዋስኩት።
 “እነዚህ የማይረቡ ልፍስፍሶች እንዴት ቅኝ ገዙኝ?”

_____________________________________________


                       ሁለት ቁም ነገሮች



               1.
ከአዳም ረታ “ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ” መጽሐፍ እንጀምር። መቼም፣ መቼት ገለጻውን ተክኖታል። አተራረኩ ውብ ነው። ከመሰጡኝ ውስጥ ጥቂቱን ላጋራ፡፡ ታሪኩ በመጽሐፉ የመጀመርያ ክፍል ውስጥ ያለ ነው። በ“መንግስቱ ነዋይ ጊዜ” በሚለው ምዕራፍ።
ተናጋሪው፣ አዛውንቱ አቶ እምቢበል ናቸው። “ከምሽቴ ጋር፣ አወራሽ” በሚልና በሌላም ምክንያት፣ ወይዘሮ ጉልላት ላይ እጁን የሰነዘረውን ብዙአየሁን ሲመክሩና ሲገስጹ ቆይተው ሲሰናበቱ፤
“በሉ ልጆቼ፣ አልረብሻችሁ ልሂድ”
የብዙአየሁ ባለቤት፤ “አረፍ በሉ እንጅ ምሳ እንብላ፤ ቤት ያፈራዉን እንቋደስ”
እሳቸውም መለሱ፤  
“ልሂድ፣ ጾም አለብኝ እስከ ማታ። አገር ተረብሾ፣ ምራቅ እንኳን አይዋጥልኝም። ልጆች ናችሁ እናንተ። እኔ ረብሻን አይቸዋለሁ። በሉ ደህና ዋሉ።”
እኔ፤
አገር ተረበሸ አልተረበሸ፣ ሰውን የሚውጥ ሰው በበዛበት በዚህ ዘመን፣ ራሱን በጾም የገዛ፣ የነፍስም የስጋም አባት አለን ይሆን ብዬ ራሴን ጠየቅኹት። እናንተንም። አለን ግን??
2.
I am also with Nelson Mandela’s autobiography “Long walk to freedom”. While opening the first few pages... this caught my eyes ...
In the middle of a playground with his friends, the young Madiba was trying to ride over the donkey back. However, he was unlucky and his friends laughed at him and was embarrassed and humiliated. With his wordings .. he said፡
“.... I jumped on and the donkey bolted into a nearby thorn bush. It bent its head trying to unseat met, which it did....but not before the thorns had pricked and scratched my face, embarrassing me in front of my friends. Like the people of the East, Africans have a highly developed sense of dignity, or what the Chinese call “face”. I had lost my face among my friends. Even though it was a donkey that unseated me , i learned that TO HUMILIATE ANOTHER PERSON IS TO MAKE HIM SUFFER AN UNNECESSARILY CRUEL FATE. EVEN AS A BOY, I DEFEATED MY OPPONENTS WITHOUT DISHONORING THEM.” LONG LIVE MADIBA!!!
አንዱ ሌላው ላይ እየተረማመደና እየረገጠ በሚከብርበትና በሚከበርበት በዚህ ዘመን፣ እንዲህ እንደ ማዲባ አይነት ሰው፣ በባትሪ አይደለም እንደ ሊቁ፣ በባውዛም አይገኝ!!

___________________________________________


                     ሬዲዮ እና ያ ትውልድ


            እየተከበረ ያለው የሬድዮ ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ ያ ትውልድ እና የኔ ትውልድ፣ ከሬዲዮ ጋር የነበረንን ታላቅ መልካም ቁርኝት፣ በመልካም ወግ ለመዳሰስ ወደድነ። ይነበብ
***
እኛ ቤት ሬድዮ ሙላው ነገራችን ነበር፣ መረጃ መቀበያ፣ ዘፈን ማዳመጫ፣ ትምህርት መማሪያ/ ትምህርት በራድዮ/፣ ሠዓት ማወቂያ--- እና ሌሎችም ነገሮች። ባለ 3 ባትሪ ጎራሽ የነበረውና ኋላ ላይ አባባ በኤሌክትሪክ እንዲሰራ ያደረገው ትራንዚስተር ሬድዮ፣ ከአገር ውስጥ ኢትዮጵያ ሬድዮ፣ ብስራተ ወንጌልንና ለገዳዲ ሬድዮን፣ ከውጭ ደግሞ የአሜሪካ ድምፅና የጀርመን ሬድዮ ይደመጥበት ነበር።
***
ኢትዮጵያ ሬድዮ፤ አብዛኛውን የቤተሰብ አባላት ቀልብ በሚስቡ ፕሮግራሞቹና በተሻለ የአየር ሰዓት ጊዜው የበለጠ ተደማጭነት ነበረው፡፡ ለጥቆ የለገዳዲው ትምህርት በሬድዮ፣ በተለይ በተማሪዎች የ15 ደቂቃ እረፍት ሰዓት ላይ በሚያስደምጠን የአረጋኸኝ ወራሽ “እኔስ ብቸኛ ነኝ” ዘፈን የተነሳ ተመራጭ ነበር፡፡
***
ከኢትዮጵያ ሬድዮ አይረሴ ፕሮግራሞች መካከል--- ከመፅሃፍት ዓለም፣ ዜና ፋይል፣ የኪነጥበባት ምሽት፣ ህግና ህብረተሰብ፣ “ጤና ይስጥልኝ እንደምን አመሻችሁ፤ ይህ የቅዳሜ ምሽት የምርጥ ሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ነው----;በማለት ጀምሮ oldies ያስኮመክመን የነበረው የታምራት አሰፋ ተወዳጅ ፕሮግራም፤ ቅዳሜን ከኛ ጋር እና ዕሁድን ለአንዳፍታ፣ ከለገዳዲ ሬዲዮ አይረሴዎች ናቸው።
***
በተለይ እሁድ ምሽት ከ3:00 ሰዓት ዜና በኋላ የሚቀርበውን ከመፅሃፍት ዓለም ፕሮግራም፣ አባባ VOA እያዳመጠ ከሆነ ለመከታተል ስለማንችል፣ ትረካው ጠዋት ስለሚደገም ትረካውን አዳምጠን መጨረስ ነበረብን፡፡ በዚህም ሳቢያ ት/ቤት ባንዲራ ከተሰቀለ በኋላ ስለምንደርስ፣ በአርፋጅ ተገርፈን የምንገባባቸው ሰኞዎች ብዙ ነበሩ።
***
የለገዳዲዎቹ ቅዳሜን ከኛ ጋር እና ዕሁድን ለአንድ አፍታ ለየት ያደርጋቸው የነበረው፣ ከፖለቲካ ወግና ስብከት የፀዱ፣ የመዝናኛና ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ብቻ ይቀርብባቸው የነበሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህም በወቅቱ የነበሩ የመንግስት ባለስልጣንን መልካም ጎን ማሳያ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
***
ዛሬ ላይ FM 101.1 ላይ “ቅዳሜን ከኛ ጋር” የሚል ፕሮግራም የሚሰራ አንድ አዘጋጅ፣ የፕሮግራሙን ስያሜ ከየት እንደወሰደው እንዲሁም ለገዳዲዎችን አግኝቶ፣ ስለጥንቱ "ቅዳሜን ከኛ" ጋር ዳሰሳ ቢሰራ መልካም ነው።
መልካም ወግ፣ መልካም ሬዲዮ


________________________________________


                     ‘ዘዋሪዋ’ ንግስት!
                           አለምነህ ዋሴ

            ጋዜጠኛ ንግስት ሰልፉ በራድዮ ጋዜጠኛነት የማይረሳ አሻራ ማሳረፍ ብቻ ሳይሆን በመቶዎች ባይባል እንኳ በደርዘን የሚቆጠሩ ወጣት ምሁራን ሴቶች ወደዚህ ዘርፍ በፍቅር ተስበው እንዲመጡ ለማድረጓ ጥርጥር የለውም:: በሬድዮ ቆይታዋ ሁለገብ የተሟላ ጋዜጠኛ ነበረች:: ዜና መርታለች፤ ዘግባለች፤ ፕሮግራም አዘጋጅታለች፤ ተንትናለች፤ ተርጉማለች:: “የንግሥት” ተብሎ የሚታወቅ የዜና አጻጻፍ --አጭር ገላጭና ገልባጭ! ምሳሌ:-”6 ሰዓት ከቀኑ!”  (ከቀኑ 6 ሰዓት ነው የምንለውን ሃሃሃሃ)፡፡ ሲጀመር የሥነፅሁፍ ምሩቅ ናት:: ሃሳቧን በቀላልና ግልፅ አማርኛ መግለፅ ይሳካላታል...”ሬድዮ ቃላት መደረት አይወድም!” ትላለች:: ናት፡፡ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን፣ ታሪኳን በድረገጽ ላይ አውጥቶላታል፡፡ ታሪኳን ስታነቡት በዕድገቷ ምንኛ “አገር- አካላይ”፣ በሙያዋ ደግሞ “ዓለም-አካላይ” እንደሆነች ትገነዘባላችሁ። የዚህ ታሪኳን ርዕስ እኔ ብፅፈው ኖሮ፣ “ዘዋሪዋ ንግስት!” ነበር የምለው!


Read 1652 times