Sunday, 20 February 2022 17:08

በካናዳ የኮሮና ክትባት የቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደሌሎች አገራት ተስፋፍቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የካናዳ መንግስት አገር አቋራጭ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የኮሮና ክትባት መውሰድ ግዴታቸው ነው በሚል በቅርቡ ያወጣው መመሪያ ከሳምንታት በፊት የቀሰቀሰው ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ፣ መንግስት በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ መዘጋጀቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ በሌሎች የአውሮፓ አገራት ከተሞችም ተመሳሳይ ተቃውሞዎች መጀመራቸው ተዘግቧል፡፡
ተቃውሞው ፖለቲካዊ ገጽታ መያዝና ለብሔራዊ ደህንነት አስጊ መሆን መጀመሩን ተከትሎ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ተቃዋሚዎች በአፋጣኝ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ ያስጠነቀቁ  ሲሆን ተቃውሞውን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚገባቸውን ያህል አልሰሩም ተብለው የተወቀሱት የኦትዋ ግዛት የፖሊስ አዛዥ፣ በፈቃዳቸው ከስራ መልቀቃቸውን ይፋ እንዳደረጉ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ፖሊስ መንገድ የዘጉ መኪኖችን በቁጥጥር ስር እንደሚያውል ያስጠነቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፤ ተቃዋሚዎቹ በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ የባንክ ሂሳባቸውን እንዳያንቀሳቅሱ እስከማገድ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችልም አሳስበዋል፡፡
አስገዳጅ የኮሮና ክትባት መመሪያው የዜጎችን ነጻነት የሚጋፋ ነው በሚል አደባባይ የወጡት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች "ፍሪደም ኮንቮይ" በሚል መሪ ቃል የጀመሩትን ተቃውሞ አጠናክረው መቀጠላቸውን የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፣ ተቃዋሚዎቹ አገሪቱን ከአሜሪካ ጋር የሚያገናኙ ሰፋፊ የንግድ መስመሮችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች በርካታ መንገዶችን ከመዝጋት ባለፈ ሃይል ወደተቀላቀለበት ተቃውሞ መግባታቸውንና የአገሪቱ መንግስትም ስርዓትን ለማስከበር ጠበቅ ያሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ መዘጋጀቱን እንዳስታወቀ አስነብቧል፡፡
በሳምንቱ መጀመሪያ በካናዳዋ ግዛት ኦትዋ ተቃውሞው መባባሱን ተከትሎ ሁኔታው ለነዋሪዎች ደህንነት እጅግ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተጣለ ሲሆን፣ በኦንታሪዮም ተመሳሳይ አዋጅ መጣሉና ተቃውሞው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ እየጎዳው እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡
አንደርሰን ኢኮኖሚክ ግሩፕ የተባለው ተቋም ባወጣው መረጃ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው ሳቢያ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከወደ 300 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ እንዳጣ የገለጸ ሲሆን፣ ከተጎጂዎች መካከልም ታዋቂዎቹ የመኪና አምራች ኩባንያዎች ጄኔራል ሞተርስ፣ ሆንዳና ቶዮታ እንደሚገኙበት መነገሩንም ሲኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ተቃዋሚዎች ወደ ድንበሯ መጠጋታቸውንና ሁለቱን አገራት የሚያገኛኙ መንገዶች በተቃውሞው መዘጋታቸውን ተከትሎ የካናዳ መንግስት ሰልፉን በአስቸኳይ እንዲያስቆም ጥሪ ያቀረበች ሲሆን፣ ተቃውሞው ከካናዳ የተለያዩ ከተሞችና ግዛቶች ባለፈ ፓሪስና ብራሰልስን ወደመሳሰሉ ሌሎች የአውሮፓ ከተሞች በተመሳሳይ መንፈስ መስፋፋት መጀመሩ እየተዘገበ ነው፡፡
ተቃውሞውን የሚደግፉ አካላት በተለያዩ ድረገጾች አማካይነት በሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን፣ ግማሽ ያህሉ ድጋፍ አድራጊዎች ካናዳውያን እንደሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡









Read 1105 times