Monday, 21 February 2022 00:00

በዚምባቡዌ ያልተከተቡ ደመወዝ ሲከለከሉ፤ በአልጀሪያ ስራ አጦች ሊከፈላቸው ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዚምባቡዌ መንግስት 96% የአገሪቱ መምህራንን ከስራ አግዷል

             የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት ዜጎቹን በስፋት በመከተብ ላይ የሚገኘው የዚምባቡዌ መንግስት፣ የኮሮና ክትባት ላልወሰዱ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ መክፈል እንደሚያቆም ከሰሞኑ ማስታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ የዘገበ ሲሆን ቢቢሲ በበኩሉ፤ አልጀሪያ ለስራ አጥ ዜጎቿ ወርሃዊ ደመወዝ ለመክፈል ማሰቧን አስነብቧል፡፡
የዚምባቡዌ መንግስት ከ1 ዓመት በላይ ከቢሮ ተገልለው በየቤታቸው ስራቸውን ሲያከናውኑ የቆዩና ክትባት የወሰዱ የመንግስት ሰራተኞች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቢያቀርብም፣ ያልተከተቡትን ግን ወደ ስራ እንዳይገቡ በመከልከል ደመወዝ መክፈል እንደሚያቆምና የተለያዩ ቅጣቶችን እንደሚጥል ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአልጀሪያ መንግስት በአንጻሩ ከመጪው መጋቢት ወር ጀምሮ ስራ ለሌላቸው ዜጎቹ በየወሩ ደመወዝ መልክ እንደሚከፍል የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱልመጂድ ቴቡኔ ሰሞኑን መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከ600 ሺህ በላይ ስራ አጥ ዜጎች የሚገኙባት አልጀሪያ፣ መንግስት ስራ ለሌላቸውና ስራ በማፈላለግ ላይ ለሚገኙ እድሜያቸው ከ19 እስከ 40 የሚሆን የአገሪቱ ወጣቶች ስራ እስከሚያገኙበት ጊዜ ድረስ በየወሩ 100 ዶላር ደመወዝ እንደሚከፍልና የጤና አገልግሎት በነጻ እንደሚሰጥ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የዚምባቡዌ መንግስት ከክፍያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት መምህራን የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ በህዝብ ትምህርት ቤቶች ተቀጥረው ከሚሰሩ የአገሪቱ መምህራን መካከል ከ96 በመቶ በላዩን ወይም 135 ሺህ ያህል መምህራንን ለ3 ወራት ከስራ ገበታቸው ማገዱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የዚምባቡዌ ትምህርት ሚኒስቴር በስራ ማቆም አድማ ተሳትፈዋል ያላቸውን መምህራን ለ3 ወራት ከስራ ማገዱን ባለፈው ሃሙስ ማስታወቁን ተከትሎ፣ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ኦና መታየታቸውንና የአገሪቱ የመምህራን ማህበር በበኩሉ፤ ውሳኔውን በመቃወም ክስ መመስረቱን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
የዚምባቡዌ መንግስት መምህራን በአሜሪካ ዶላር ሳይሆን በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ውሳኔ ያስተላለፈው ከ3 አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህ ውሳኔ አለመግባባትና ቀውስ መፍጠር የጀመረውም ከዚያ ጊዜ አንስቶ እንደነበር አክሎ ገልጧል፡፡




Read 9091 times