Monday, 28 February 2022 13:57

ለመገለባበጥም’ የነፍስ ጥሪ አለው እንዴ!?

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አሁን በጣም እየቸገረን ያለው አዳዲስ ሀሳቦችን ማመንጨት አይደል! እናማ...የድርሻችንን ለመወጣት ሀሳብ ቢጤ እናቅርብማ፡፡ እኔ የምለው...በኦሎምፒክ የምንሳተፍባቸውን የስፖርት አይነቶች ብዛት የማናሳድግሳ! ለምሳሌ ጂምናስቲክ፡፡ አሀ ምን እናድርግ...ሀገሩ ሙሉ እኮ በየጊዜው የምንገለባበጥ፣ ፌዴሬሽኑ እውቅና ያልሰጠን ጅምናስቲከኞች ሀገር እየመሰለ ነው እኮ! ወፍራሙ በሉት ቀጭኑ፣ ረጅሙ በሉት አጭሩ፣ ...ብቻ በምን ፍጥነት...አለ አይደል... ያቺ አሪፏን አፍሪካ አሜሪካዊት ጅምናስቲከኛ በሚያስንቅ ‹ታለንት› ግልብጥ ብለን ልውጥውጥ እንደምንል የሚገርም ነው፡፡
“ስማ ያ እንትና ምን ነካው!”
“ምን ነካው ማለት?”
“ይሄን ሰሞን እንዴት እንደተለዋወጠብኝ አልነግርህም፡፡ ልክ እኮ ዘለዓለም ዓለም የማያቀኝ ሰው ነው የሆነብኝ!”
“አያውቀህ ይህን ይሆናላ!”
“እኔ ቁም ነገር አወራለሁ አንተ ትቀልዳለህ፡፡ አፈር ስንፈጭ ያደግነውን ጓደኛዬን ነው አያውቅህ ይሆናል የምትለኝ?”
“ስማ... አንተ የምትለው አይነት ትውውቅ ቀርቷል፡፡  እንደውም ምን አለ በለኝ... ትንሽ ቆይቶ ወዳጅነት፣ አበልጅነት፣ አብሮ አደግነት ምናምን የሚሉ ነገሮች ቋሚነታቸው ይቀርና እንደ ንግድ ፈቃድ በየጊዜው ማሳደስ ሳይኖርብን አይቀርም፡፡”
“ምንድነው የምታወራው! ሰዉ ሁሉ ምን ነካው? ሁላችሁንም የሆነ እጸፋሪስ ያቀመሳችሁ አለ እንዴ!”
ጎሽ! “የተማረ ይግደለኝ!” እንዳንል ቸገረን፡፡ አንዳንዶች የምር እያደረጉት ነዋ፣ ሀገር ስትታመስ የኖረችው! ስለተቸገርን በቃ በዘመኑ ቋንቋ...ይመችህማ፡፡ አዎ... “ሰዉ ሁሉ በአንድ ጊዜ ጠባይ የሚያስለውጥ እጸፋሪስ ቀምሷል ወይ?” የሚያሰኝ ጊዜ ነው፡፡ እናማ ምን መሰላችሁ... “ኤለመንተሪና ሀይስኩል አብረን አንድ ትምህርት ቤት ነው የተማርነው፡፡” “ሰፈር አንድ ቡድን ውስጥ ነበር እግር ኳስ የምንጫወተው...” “በእናቴ በኩል የአክስቴ ልጅ ነው፣”  ምናምን እያሉ የአሮጌ ዶሴ አቧራ ማራገፍ የለም፡፡ ተዉ የድሮ ወዳጆች ግዴላችሁም! “እህ...” ብሎ አዳማጭ በሌለበት ዘመን፣ “ሻይ ልግዛልህ...” ስትሉት እንደ በፊቱ “በአንድ አፍ!” ብሎ ‹ውል ከማሰር› ይልቅ (ቂ...ቂ...ቂ...) “ያልለመደበትን ዛሬ ሻይ ልጋብዝህ ያለኝ ምን ተንኮል አስቦብኝ ነው!” የሚል በበዛበት፣ ቢሆንም ባይሆንም፣ የከረመ ወዳጅ አይከፋም፡፡ 
ለነገሩማ... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...በድንገት የመገለባበጥ ነገር ድሮም ነበር፡፡
እንደ ወንዝ ድንጋይ አሳ እንደላሰው
ሙልጭልጭ እያለ አስቸገረኝ ሰው
ይባል አልነበር፡፡ (ስሙኝማ... በፊት እኮ እንደዚህ ህብረተሰቡ ውስጥ የሚታዩ ማህበራዊ ህጸጾችን የሚያነሱ ብዙ ዘፈኖች ይወጡ ነበር፡፡ አሁን፣ አሁን በብዛት የማይወጡት ለክሊፕ አይመቹም ተብሎ ነው እንዴ?... አሀ... አሳ እንደላሰው ድንጋይ መሙለጭለጭ ምን ማለት እንደሆነ ለማሳየት፣ ለዳንስ ወይም በዳንስ ስም ለሚቀርቡ ‹የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች› ክሊፕ ላይመች ይችላላ! ወይ ደግሞ ሙዚቃ አድማጩ... “አሁን እኛ የምንጨነቅበት ነገር አጣንና ነው እንዴ ድንጋዩን አሳ ላሰው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሰዉ ተሙለጨለጨ እያለ ‹ቴረር› ሊለቅብን የሚሞክረው!” ብሎ ይቃወም ይሆናላ!)
እናላችሁ... ገልበጥበጥ ማለት እንደ አሁኑ በድንበር ተሻጋሪ ኢንዱስትሪ አቅም ባይሆንም  መኖሩን ነበር ለማለት ያህል ነው። የምር ስታስቡት ኮሚክ እኮ ነው...አሪፍ የምንላቸው አብረው የሚያኗኑሩ የጋራ ልምዶቻችን አንድ በአንድ ‹እየተሰወሩ›፣ በድንገት መተጣጠፍና መገለባበጥ የሚባሉ ነገሮች የተለቀቀ ባዶ ቤት አግኝተው ዘው ብለውላችኋል፡፡ (ይቺ “ባዶ ቤት” ምናምን የምትለዋ አባባል...አለ አይደል...በኋላ “ይህን ልብወለድ ለመጻፍ ያነሳሳህ ምንድነው?” ሲባል፣ እኛም እንዳይቀርብን... “ስነ ጸሁፍ ነፍሴን ጠራቻት!” ለማለት የሙከራ ልምምድ ቢጤ ነች፡፡) የምር ግን... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ጥያቄ አለን። ስነጽሁፍ የምትጠራቸው ነፍሶች ምን፣ ምን ማሟላት እንዳለባቸው ይነገረን፡፡ አሀ...ኦሪጅናል ማግኘት ቢያቅተን፣ ይሄ ተደብቆ የፈረንጅ ሀገሩን ፈረንካ የሚያበዛ፣ ምድረ ካሜሩን ምናምን፣ ነፍስ ፎርጀሪ ይሠሩ ይሆናላ!
“መሴ እከሌ... ነፍሴን ስነጽሁፍ እንድትጠራት የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች የምታሟላ ፎርጅድ ነፍስ ሥራልኝ፡፡ ደግሞ የአፍሪካ ዋንጫ ጊዜ የካሜሩን ደጋፊ ነበርኩ።”
“ሙሉ ነው ግማሽ ነፍስ የምትፈለገው?” ይሄ ምን ይላል!
“ሙሉ ነው እንጂ ግማሽ ነፍስ ብሎ ነገር አለ እንዴ!”
“እሱን ለእኛ ለባለሙያዎቹ ተውልን፡፡” (ቂ...ቂ...ቂ...)
“እንደምትለኝ ነፍስህ እንድትጠራ ማድረግ ነው የምትፈልገው፡፡”
“ነገርኩህ እኮ!”
“ግልጽ እንዲሆንልኝ ነው፡፡ እሺ... መጠራት የምትፈልገው በምድሩ ህግ ነው በሰማዩ?”
(ሂድ! ምን ይላል ይሄ፡፡ ጭራሽ ያሟርታል እንዴ! እንደውም ትቸዋለሁ፡፡)
ሀሳብ አለን...በአሪፍ አነጋገር ኮስተር ብላችሁ፣ “ነፍሴን ስነጽሁፍ ጠራቻት...” ማለት የምትችሉበት፣ ሰዎች በየሚዲያው ይደጋግሙልንማ! አሀ... ቦተሊካችን በምሳሌነት እንዲጠቀመው እንፈልጋለና! የሆነ በቃ... አለ አይደል... ቦተሊካው ክሬቲቪቲ ጠፍቶበት ወደ ችኮነት እየሄደብን ስለሆነ የነፍስ ጥሪ ቢያሰማምረው ብለን ነው፡፡
“የዛሬው እንግዳችን፤ ከልጅነታቸው ጀምሮ ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩት አቶ እከሌ ናቸው፡፡ እንግዳችን ጥሪያችንን አክብረው ስለተገኙ....” (ያው እንደተለመደው ይቀጥላል፡፡ ፈረንጅ “ብላ...ብላ  ብላ” የሚለው አይነት፡፡ እንግዳውም የተለመደውን “እኔም ስለጋበዛችሁኝ...” ምናምን ይላሉ፡፡
“አቶ እከሌ፤ ለመሆኑ ፖለቲካ ውስጥ የገቡት መቼ ነው?” (ይቅርታ..ግን “ከልጅነታቸው ጀምሮ፣” ብለሽ ነገርሽን እኮ!)
“እውነት ለመናገር ገና ነፍስ ካወቅሁ ጊዜ ጀምሮ ነው ማለት እችላለሁ፡፡” እሰይ! የአንዳንድ ቦተሊከኞችን ድፍረት አለማድነቅ...ስህተት ብቻ ሳይሆን ምቁነት ይሆንብናል፡፡
“እንደው ለመሆኑ መጀመሪያውንስ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ የገፋፋዎት ምን ነበር?”
“ነፍሴ! ነፍሴ ነቻ!”
“ቢያብራሩልን...”
“ፖለቲካ ነፍሴን ጠራቻት!”
በቃ... እንዲህ ቢሆን አሪፍ አይመስላችሁም? አሀ...“ፖለቲከኛ ነፍስ እንደሌለው ተረጋገጠ...” የሚል ነገር ገና ከሳይንቲስቶችም፣ ከአንድዬ ጋር “ቡና ስንጠጣ አመሸን...” የሚመስል ነገር ከሚነግሩን ተንባዮችም የሰማነው ነገር የለማ! ነገርዬዋ... አለ አይደል... “ታክሲ ላይ ምናምን ‘ቄንጠኛ’ ፎቶውን ስላዩት ብቻ “እኔም የቼ ጉቬራን ምሳሌነት ተክትዬ...” ወይ ደግሞ “ለዲሞክራሲ መስፈን ባለኝ ከፍተኛ ፍላጎት...” ምናምን እያሉ፣ ለሳይንስ ፊክሽን የተዘጋጁ በሚመስሉ ዝርዝሮች (ቂ...ቂ...ቂ...) መከራችንን ከመብላት ትንሽ ተንፈስ እንላለን፡፡ “ፖለቲካ ነፍሴን ጠራቻት!” አለቀ። “ኸረ ውሸቱን ነው!” እንዳንል ማረጋገጫ የለ፡፡ (የምር ግን ቦተሊከኞች የሚሉትን በተመለከተ “ኸረ ውሸቱን ነው!” ስንል “ተጨባጭ ማስረጃ አቅርብ፡፡ ካልሆነ በስም ማጥፋት ትጠየቃለህ...” የሚል ጣጣ የመምጣቱ አደጋ ባይኖር ኖሮ፣ አቤት ስንትና ስንት “ውሸቱን ነው..;. ይኖር ነበር፡፡
እኔ የምለው...‘አሜሪካ ጎት ታለንት’ ላይ ቢታይ ኖሮ ለሽልማት በሚያበቃ ችሎታ መተጣጠፍ፣ መጠማዘዝና መገለባበጥ የምንችል ሰዎች፣ የምር ግን የሆነ ዓለም አቀፍ የስልጠና ተቋም የማናቋቁምሳ! ልከ ነዋ... ራሱን የቻለ ችሎታ ነው እኮ! አሀ...ቅድመ ሁኔታዎች ምናምኖችማ አሉት! ከትንሽ ከፍ ያሉ ክፋት (የመጣለትን ማፈንዳት የሚወድ ”ከይሲነት፣” ይለው ነበር፡፡) ለምን መሰላችሁ... መተጣጠፍ ውስጥ ብዙ ጊዜ በዛኛው ወገን የሚጎዳ ይኖራል፡፡ ወደዛኛው ወገን ሲሻገሩ ስለዚህኛው ወገን የሆኑ ነገሮችን ሹክ ማለት ይጠበቃላ!
“ማነው እዛ መሀል ለእኛ የተለየ ጥላቻ ያለው?”
“እንትና ነዋ! መጥላት ብቻ አይደለም፣ ሰዋራ ስፍራ በአካል ቢያገኛችሁ፣ እኝኝ አድርጎ ባይሰለቅጣችሁ ነው!” ተገልብጦ ወይም ተጠምዝዞ ‘የዛኛው ወገን’ ሙሉ አባል ለመሆን ዋናው መመዘኛ ተሟላ ማለት ነው!
ጥያቄ አለን... ‘ለመገለባበጥም’ የነፍስ ጥሪ አለው እንዴ!?
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 1048 times