Sunday, 27 February 2022 00:00

አቶ ግርማ ሰይፉ - በአገራዊ ምክክሩ፤ በእስረኞች መፈታት፣ በም/ቤቱ ስብሰባ...

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው ማክሰኞ ወንጀል እየሰሩ ፖለቲከኛ ከሆኑ መፈታት ልምድ እንዳይሆኑብን ኢዜማ ለአገራዊ ምክከሩ በቂ ዝግጅት እያደረገ ነው ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፓርላማ ተገኝተው ከም/ቤቱ አባላት ለተነሱ በርካታ ወቅታዊና አወዛጋቢ ርዕስ ጉዳዮች ጥልቅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የህወኃት አመራሮች ከእስር መፈታ፣ የአገራዊ ምክክሩ ኮሚሽን ጉዳይ፣ በም/ቤቱ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡  የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በአጠቃላይ በምክር ቤቱ በተነሱ ጉዳዮች፣ በአገራዊ ምክክሩና በኢዜማ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-


             ጠ/ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ እንዴት ተመለከቱት?
እንዳየሁት ያው ጥያቄዎች ከአባላቱ ይነሳሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ይሰጣሉ። ጥያቄና መልስ ነው የሆነው፡፡ የምክር ቤቱ ድባብ እንዲለወጥ ካስፈለገ፣ አባላቱም ረዘም ያለ ጊዜ ተሰጥቷቸው የጥያቄና መልስ ሳይሆን የክርክር አይነት ድባብ ቢኖረው የፓርላሜንታሪ ፎርም ይይዛል ብዬ አስባለሁ። በዚሁ ከቀጠለ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሊሰጡባቸው የሚፈልጓቸውን አጀንዳዎች የምክር ቤት አባላት ያነሳሉ፡፡ በዚያ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ የሚሰጡበት ነው የሚሆነው፡፡ በፓርላማ ውስጥ ክርክር (ካውንተር ዲቤት) ከሌለ አሰልቺ ነው የሚሆነው፡፡
ለምሳሌ የአማራ ብሔራዊ ንቅናዌ (አብን) ተወካዩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ጠንከር ያለ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ በፓርላማ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ አካል በምንም መልኩ መፈታት እንደሌለበት የህግ አንቀፆችን እየጠቀሱ ሞግተዋል፡፡ (የህወኃት አመራሮችን ማለታቸው ነው) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን የአቶ ክርስቲያን የጠቀሷቸው አንቀፆች ሀሳቦች ብዙም እንደማስኬዳቸው በሚያሳይ መልኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ክስ ማቋረጥ የሚባል ነገር አለ፤ ክስ ማቋረጥ ይቻላል፡፡ መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች ክስ  ሊያቋርጥ ይችላል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ተፈቺዎቹ መንግስት ለከሰሳቸው ሰዎች ድጋፍ የሚሆን መረጃ እናቀርባለን ብለው ቃል ከገቡ እና  ያንን የሚያደርጉበት አግባብ ካለ፣ ክስ ሊቋረጥላቸው ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ ራሱ መንግስት ያለኝ ማስረጃ ፍርድ ቤት ብሄድ ላሸንፍ እችላለሁ ብሎ ካሰበ፣ ከዚያም ዘለግ ሲል በሚዲያው ሲባል እንደነበረው፣ ለአገራዊ ምክከሩ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላትን ወደ ውይይትና ድርድር ማምጣት ካቀደና የእነሱ ክስ መቋረጥ ለዚህ ያግዘኛል ብሎ ካሰብ ክስ ሊያቋርጥ ይችላል። ጥያቄው የታሰሩት ሰዎች ክሳቸው ሲቋረጥ ደስ  ብሏችኋል ወይ ከሆነ፣ በፍፁም ደስ አላለንም፡፡ ነገር ግን የሚደረጉት ነገሮች ሁሉ፣ እኛ ደስ የሚለን ብቻ መሆን አለበት ወይ የሚል ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅም ነገር  አምጥቷል-አላመጣም” የሚለውን ከውጤት አንጻር የምንለካም ከሆነ ገና ውጤቱን በደንብ እያየነው ባይሆንም ምልክቶች ግን አይተናል፡፡
ምን አይነት ምልክቶች አየን?
ለምሳሌ በምዕራቡ ዓለም ያለው ጫና ረገብ ማለትና መለሳለሶችን ስናይ… ጠቅላይ ሚኒስትሩም አንናገርም ያሏቸውን አንዳንድ ጥቅሞችን መገመት ይቻላል፡፡ ያው እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጥቅሞቹን ከምን አንፃር ነው ካውንት የሚያደርጉት የሚለውን ነገርም ማሰብ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል፣ ከብሔራዊ ደህንነት አንፃር ላይገለፁ የሚችሉም ነገሮች አሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሰዎች መፈታት አለመፈታት ብቻ ሳይሆን፣ ወንጀል እየሰሩ ፖለቲከኛ ከሆኑ መፈታት ልምድ እንዳይሆንብን ስጋት ሊያሳድር ይችላል። እኔ ጉዳዩን በዚህ መልኩ ነው የማየው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ እንዳነሱት በሀገራዊ ምክክሩ በአጀንዳነት ከሚነሱት ውስጥ የሰንደቅ አላማና የአንቀጽ 39 ጉዳዮች እንደሚኖሩበት ገልጸው “በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ በሀገራዊ ምክክሩ ከተግባባንባቸው እሰየው ካልሆነም ህዝበ ውሳኔ ይካሄድባቸዋል” ብለዋል። ከዚህ አንጻር ኢዜማ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ሊነሱ ይገባቸዋል የምትሏቸው አጀንዳዎች አዘጋጅታችኋል?
ኢዜማ ለሀገራዊ ምክክሩ በቂ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ራሱን የቻለ ግብረ ሀይል አቋቁሟል። ልክ የኮሚሽኑ አይነት ቁመና ያለው ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ አቋቁሞ ስራ ጀምሯል። ከሚሰራቸው ስራዎች አንዱ ከአባላትና ከሌሎችም የሀገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ሰዎች (ለናሽናል ዲያሎጉ) መቅረብ ያለባቸው ምን  አይነት አጀንዳዎች ናቸው የሚለውን እየሰራን ነው ያለነው። አጀንዳዎቹ  ምንድን ናቸው የሚለውን ጊዜው ሲደርስ ይፋ የምናደርገው ይሆናል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሷቸው ያልሻቸው አንቀጽ 39 እና የባንዲራም ጉዳዮች እውነት ነው አጀንዳዎች ናቸው። ነገር ግን በእኛ በኩል የምናነሳቸው በርካታ አጀንዳዎች በስምምነት ሳይሆን በህዝበ ውሳኔ እልባት ያገኛሉ ብለን እንጠብቃለን። ትክክለኛውም መንገድ ያ ነው የሚል እምነት አለን። ለምሳሌ ህገ-መንግስቱ ይሻሻል ወይስ አይሻሻል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጭ ብለው ሊወስኑት አይችሉም። አይሻሻል የሚል አንድ ሰው ቢኖር የእርሱ መብት መጨፍለቅ የለበትም። ጉዳዩ ለህዝበ ውሳኔ ቀርቦ ህዝቡ ይሻሻል ካለ፣ አንድ ቡድን አይሻሻል ስላለ ላይሻሻል የሚችልበት  ምክንያት የለም ማለት ነው።
ከብሄራዊ ምክክርና ውይይቱ ህዝበ ውሳኔ ይሻላል እያሉኝ ነው?
አይደለም! ሁለቱ የሚነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም ናሽናል ዲያሎጉ ብዙዎቹ ውጤቶች እኮ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ማድረግ ነው። ውይይትና ምክክር ይደረግና በምክክሩ መካከል እዛ የተሰበሰቡት 500 ያህል ሰዎች ሊወስኑት የሚችሉት ነገር ሊኖር አይገባም። እነሱ የደረሱበትን ውጤት አማራጭ ይዘው ቀርበው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው የሚወስነው። በጣም ብዙ ነገሮች አይደሉም አጀንዳዎቹ። ጋዜጠኞችን ጨምሮ አብዛኛው ሰው በጣም ብዙ ለብሄራዊ ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎች እንዳሉ አድርጎ ነው የሚረዳው።
ነገር ግን እንደዛ አይደለም። አንዳንዶቹ የፖለሲ ጉዳዮች ናቸው። ልዩነቶቹ የሚቀሩና በምርጫ ጊዜ ለምርጫ ውድድር የሚቀርቡ ናቸው እንጂ የብሔራዊ ምክክር አጀንዳ አይደሉም። የኢኮኖሚና የፍትሃዊነት ጉዳዮች የብሄራዊ ምክክር አጀንዳዎች አይደሉም። የምርጫ፣ የፖሊሲና የማኑፌስቶ ጉዳዮች ናቸው። ነገር ግን አገር የጋራ ሆኖ በሀገረ መንግስቱ ሊጤኑ የሚገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ሰንደቅ አላማ፣ የመገንጠል ጉዳይ፣ የሕዝብ መዝሙር፣ (በህዝብ መዝሙር ላይ እንኳን የተስማማን ይመስለኛል) ነገር ግን በዚህም አጀንዳ አለኝ የሚል ሰው አጀንዳ ሊያደርገው ይችላል። እናም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የሀገር ምሰሶ ሆነው በጋራ አንድ ላይ የምንቆምባቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረን የምንስማማበት ጉዳይ ነው-  የብሄራዊ ምክክር ጉዳይ ማለት ነው።
እስኪ ለሀገራዊ ምክር አጀንዳ ነው የተባለውን የሰንደቅ አላማውን ጉዳይ እናንሳው፡፡ ግማሹ “አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሆኖ ምንም አርማ የሌለው ልሙጡ ነው፤ የኔ ሰንደቅ አላማ” ይላል፣ ሌላው “የለም መሀሉ ላይ ኮከቡ አርማ ያለበት ነው ምክንያም የሃይማኖትና የብሄር ብሄረሶችን እኩልነነት የሚያሳይ ነው” ይላል። በሌላ በኩል፤ “ሁለቱንም ከነአካቴው አልፈልግም” የሚል አካል ይኖራል። ሃገራዊ ምክክሩ ይህንን ጉዳይ አጀንዳ ሲያደርግ አሁን ካለው ብሽሽቅና ውዝግብ የሚያወጣን ምን መላ ያበጃል ብለው ያስባሉ?
ነገሮችን ማወሳሰብ የሚፈልግ አካል ከሌለ በስተቀር አሁን ያነሳሽውን የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ስናነሳ ሁለት ነገር ነው ያለው። አንዱ ህገ-መንግስቱ ላይ ያለው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራችን ሆኖ አርማ ይኖረዋል ይላል። አርማው ይወክለናል አይወክለንም የሚሉ ሰዎች አሉ። ስለዚህ በባዲራው ጉዳይ ከተስማማን ከዚያ በኋላ አርማው ይኑረው አይኑረው
የሚለው ነገር ለህዝበ ውሳኔ ይቀርባል። አርማው ይኑረው የሚለው ህዝብ ቁጥር የሚበልጥ ከሆነ አርማው ይኖረዋል። ይኑረው የሚለው ላይ ከደረሰን በኋላ ደግሞ ምን አይነት  አርማ ይኑረው የሚለው ላይ እንነጋገራለን። ኮከብ ይሁን፣ አንበሳ ይሁን፣ ጦጣ ይሁን ሚለው ላይ በደንብ እንነጋገራለን። ነገር ግን ጉዳዩ ቀላል ሆኖ ሳለ ጽንፍ ድረስ የሚሄዱ አሉ። በነገራችን ላይ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የችግሮቻችን መነሻ አድርገን የምናነሳቸው ያን ያህል ከባድ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የክልልን ባንዲራ ከሀገር ባንዲራ ጋር እያነጻጸሩ ፉክክር ምን ይባላል?
የክልል ባንዲራዎች አያስፈልጉም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ይደመጣሉ። እርስዎ ክልሎች ባንዲራ ቢኖራቸው ይሻላል ብለው ያምናሉ?
አዎ፤ የክልል ባንዲራ ያስፈልጋል። የፌደራል ሚሊተሪ ስቴት እስካልሆነ ድረስ ፌደራል ስቴቶች ባንዲራ መለያ አላቸው። አሜሪካን ብትወስጂ፣ በየስቴቱ  ሃምሳ ምናምን ስቴት ባንዲራ አላቸው። ስለዚህ ይሄ አዲስ ነገር አይደለም። የፌደራል ስቴቶች የየራሳቸው መለያ አላቸው። ክልሎቹ የየራሳቸው ባንዲራ ቢኖራቸው ችግር የለውም፤ መኖርም አለበት። ነገር ግን ውድድራቸው ከሀገሪቱ ምልክት ጋር አይደለም። መሆን ያለበት፡፡ የራሳቸውንና የአካባቢያቸውን ምልክት ነው ማስቀመጥ ያለባቸው። አሁን እያየን ያለው ግን የሀገርን ባንዲራ ከክልል ባንዲራ፣ የሀገርን ባንዲራ ከፓርቲ አርማ ጋር እያወዳደርን የምንጋጨው ነገር የእውቀት ማነስ ነው። ይህንን እንግዲህ ማስተማር ነው የሚያስፈልገው።


Read 1386 times