Monday, 28 February 2022 17:34

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሒሞች ማህበር ESOG 30ኛውን አመታዊ ጉባኤ ከየካቲት 12-15 እ.ኤ.አ ከ Feb 19-22 በአዲስ አበባ አካሂዶአል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሒሞች ማህበር ESOG 30ኛውን አመታዊ ጉባኤ ከየካቲት 12-15 እ.ኤ.አ ከ Feb 19-22 በአዲስ አበባ አካሂዶአል፡፡


          የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ESOG በየአመቱ የሚያካሂደውን አመታዊ ጉባኤ ዘንድሮ ለሰላሳኛ ጊዜ ያከበረ ሲሆን የትኩረት አቅጣጫውም በግጭት ጊዜ የስነተዋልዶ እና የእናቶች ጤና አገልግሎት (Reproductive and maternal health services at time of conflict) የሚል ነበር፡፡  
በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ESOG የተካሄደው ጉባኤ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የካቲት 12-13 ለጽንስና ማህጸን ሐኪሞች የሙያ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን የካቲት 14-15 አጠቃላይ ጉባኤው ተካሂዶአል። በጉባኤውም የተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች በተለያዩ ተመራማሪዎች ቀርበዋል፡፡ እነዚህን ቁምነገሮች ወደፊት ለንባብ የምናቀርብ ይሆናል፡፡
ጉባኤውን በተመለከተ የኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ቦርድ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መቅደስ ዳባ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ማህበሩ የተመሰረተበትን 30ኛ አመት ማክበሩንና ከሌሎቹ ጉባኤዎች ለየት የሚያደርገው ሀገር በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ በመቆየትዋ እና እንዲ ሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ህብረተሰቡን በህመም የሚያሰቃይበት ወቅት በመሆኑ ይህ ጊዜ ለብዙዎች ጤና ማጣት ምክንያት በመሆኑ የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ምን ይመስላል የሚለውን የተመለከትንበት ወቅት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
እናቶች፤ ወጣቶች፤ ህጻናት፤ አዛውንቶች በጦርነቱ ይበልጥ ተጎጂ የሚሆኑበት መሆኑ እሙን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በተለይም በግጭት ላይ ባሉ አካባቢዎች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም እናቶች እና ህጸናት የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በምን መንገድ እያገኘ ነው የሚለውን ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በአካባቢዎቹ በመዘዋወር ለመመልከት ሞክሮአል። የሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት መጉዋደል ለብዙዎች ህይወት መበላሽት ምክንያት መሆኑ በግልጽ የታየበት ነው፡፡ በዚህም ብዙዎች የተገድዶ መደፈር ጥቃት ተፈጽሞ ባቸዋል፡፡ እርጉዝ የሆኑ እናቶች በስደት ረጅም መንገድ ከመጉዋዝ በተጨማሪ ምንም የህክምና አገልግሎት በሌለበት ደህንነታቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ ልጆቻቸውን መገላገላቸውን የሚያሳዩ ምስክርነቶች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በጋራ አብሮአቸው ከሚሰ ራባቸው አካላት ማለትም ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ ከክልል ጤና ቢሮዎች እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ግጭቱ በተስፈፋባቸው አካበቢዎች በመሆን የስነተዋ ልዶ ጤና አገልግሎቱ እንዳይ ቋረጥ ጥረት በማድረግ ላይ ነን ብለዋል ዶ/ር መቅደስ፡፡
ግጭቱ ከተጀመረ በሁዋላ በሰሜኑ የአገራችን ክፍሎች ከደብረብርሀን እስከ ቆቦ ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች የጤና ተቋማትን መልሶ ማብቃት በሚያስችል ሁኔታ ለማገዝ እና የወሊድ መሳሪያ ዎች፤የህክምና ግብአቶችን ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በየሆስፒታሎቹ የማድረስ ስራ ተሰርቶአል፡፡
የዛሬው የጉባኤ አሉ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ትኩረቱ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያለውን የስነተዋልዶ ጤናና የእናቶች ጤንነትን የሚመለከት እንደመሆኑ እናቶች እና ሕጻናት ምንም ችግር እንዳይደርስባቸው ሲባል ግጭቱ እንደተጀመረም ጭምር ከ6ወር በፊት በመቀሌ ካሉ የማህበሩ አባላትና የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር በስነተዋልዶ ጤናና በእናቶች ጤንነት ዙሪያ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ድጋፎችንም ማህበሩ አድርጎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ እስከ አፋር ድረስ በመዝለቅ በተለያዩ ጊዜያት በተለይም ወሩ የእናቶች ወር በነበረበት ወቅት እስከ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚገመት የስነተዋልዶ ጤና ሕክምናን እና የእናቶችን ጤንነት የሚረዱ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጎአል፡፡  
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በየአመቱ እንደሚያደርገው በዚህ ጉባኤም የሙያ አጋሮች በህክምናው አገልግሎት ከሰሩት ስራ አንጻር በመመዘን ሽልማት አበርክቶአል፡፡ ይህም ሽልማት አንደኛው ለረጅም ጊዜ በህክምናው ዘርፍ ማህበረሰብን በማገልገል ሲሆን ሌላው ደግሞ የህክምና አገልግሎት ለሚሹ ተገቢውን ሕክምና በማድረግ  እድሜን በመስጠት ወይም እንዲቀጥል በማድረግ በጎ ተግባር ለፈጸሙ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንትዋ ዶ/ር መቅደስ ዳበ፡፡    
ለረዥም ጊዜ በጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት ህብረተሰቡን ያገለገሉት የህይወት ዘመን ተሸላሚ ዶ/ር ፍጹም አርአያ ናቸው፡፡ ዶ/ር ፍጹም በአዲግራት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታ ቸውን ከተከታተሉ በሁዋላ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርታ ቸውን በማጠናቀቅ የተመረቁ ናቸው። ከዚያም በጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ት/ቤት ተመርቀዋል። በተጨማሪም ዩሮ ጋይኒኮሎጂስት Uro- Gynecology እና Pelvic Reconstructive የተሰኙትን ሙያዎች ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ቀስመዋል፡፡ ከአስር በላይ የሚሆኑ አገር አቀፍና አለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ሙያውን በሚመለከት ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ዛሬም በጅማ ዩኒቨርሲቲ አሶሽየት ፕሮፌሰር በመሆን በመስራት ላይ ናቸው፡፡
ሌላው ተሸላሚ በጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት በትእግስትና በቅንነት እንዲሁም ለታካሚዎች ቅድሚያ በመስጠት ሕይወት እንድትቀጥል በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ዶ/ር ብሩክ ጌታሁን ናቸው፡፡
ዶ/ር ብሩክ ወደህክምናው ዘርፍ ለመሰማራት የሚያበቃቸውን እውቀት በመጀመሪያ የቀሰሙት በጎንደር የህክምና ትምህርት ተቋም ሲሆን ወደ ጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት ለመዞር ወደ አዲስ አበባ በማቅናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት በመግባት ህልማቸውን አሳክተዋል፡፡ ዶ.ር ብሩክ በተለያዩ ከሙያው ጋር ተያያዥ በሆኑ እውቀቶች የበለጸጉ ሲሆኑ በስራም የተለያዩ ቦታዎችን ተዘዋውረው አገልግ ለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የጂንካ ሆስፒታል ተጠቃሽ ነው፡፡ ጂንክ ከአዲስ አበባ 900 ኪሎ ሜትር ያህል የሚርቅ ሲሆን እሳቸው የሰሩበት ሆስፒታልም በዞኑ ብቸኛው ሆስፒታል ስለነበር 14 ወረዳዎቸን ማገልገል ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ዶ/ር ብሩክ በዚያ ባገለገሉበት በአብዛኛው ወቅት በአካባቢው የመጀመሪያውና ብቸኛው የጽንስና ማህጸን ሐኪም ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከተመሰረተ እነሆ 30 አመት የሞላው ሲሆን ሰላሳኛውን አመታዊ ጉባኤ አካሂዶአል፡፡ በጉባኤው ላይ ከላይ ካስነበብናችሁ በተጨማሪ የቦርድ ፕሬዝዳንት በመሆን ያገለገሉት ዶ/ር መቅደስ ዳባ  ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠት አስቸጋሪ በሆነበት ወቅት ቦታና ጊዜ ሳይመርጡ ህብረተሰቡን ለማገል ገል ፈቃደኛ የሆኑ እና የፈጸሙ የማህበር አባላት ብቻ ሳይሆኑ በሙያው የተሰማሩ ሌሎች እስፔሻሊስቶች እንዲሁም በሕክምናው ዘርፍ ላይ ያሉ ግለሰቦችን ሁሉ በሆስፒታል ውስጥም ይሁን ከሆስፒታል ውጪ ግጭት በተከሰተባቸው ቦታዎች ሁሉ ላበረከቱት አተዋጽኦ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የላቀ ምስጋና ያቀርባል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በአገልግሎት ላይ ተሰማርተው ያሉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ቁጥር ከአንድ ሺህ በታቸ ነው፡፡ ይህ ቁጥር በመላ ሀገሪትዋ ላሉ እናቶች የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ለመስጠት በቂ ነው ባይባልም  ከጊዜ ወደጊዜ ግን ቁጥሩን ለመጨመር በርካታ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የዚህ ጉባኤም አንዱ አስተዋ ጽኦ ሙያው ቀደም ሲል የነበረበትን ሁኔታ ለማየትና ወደፊት ምን ቢደረግ ይሻላል የሚለውን ለመመ ካከር ነው። በጉባኤው ላይ የሚቀርቡ ሳይንሳዊ ወረቀቶች ወይንም ጥናቶች ከአገር ውስጥና ከአለም አቀፍ ዙሪያ ይዘታ ቸው ተመዝኖ የሚቀርቡ ሲሆን አገልግሎት በመስጠቱ ረገድ ምን ጉድለት እንዳለና መሟላት የሚገባውስ በምን መልኩ ነው መካሄድ ያለበት የሚለውን ለመምከር ይረዳሉ፡፡ ከዚህም በተ ጨማሪ የእናቶችን እና የህጻናቱን ጤና ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሳይንሳዊ ወረቀቶች ወይንም በአገልግሎት ዙሪያ የገጠሙ እውነታዎች ጭምር የሚቀርቡ ሲሆን ይህንን በወደፊቱ አሰራር በምን መንገድ ቢስተካከል ይበልጥ ህብረተሰቡን ማገልገል ይቻላል የሚለውን ለመወሰን የሚረዳ አመታዊ ጉባኤ በመሆኑ በአመት አመት አባላቱ በጉጉት የሚጠብቁትና የሚሳተፉበት ነው ብለዋል ዶ/ር መቅደስ ዳባ፡፡ አመታዊው ጉባኤ አዲስ የቦርድ ፕሬዝዳንት በመምረጥ ተጠናቆአል፡፡

Read 7951 times