Monday, 28 February 2022 17:37

"ምክክሩ ዋጋ የሚኖረው በሽብርተኝነት የተፈረጁ ሃይሎች ሲሳተፉበት ነው"

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ዓመት አገራዊ ምርጫ ሲካሄድ አባላቱ በመታሰራቸውና ቢሮዎቹ በመዘጋታቸው ሳቢያ ራሱን ከምርጫው ሂደት ያገለለው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በቅርቡ ከሚካሄደው የብሔራዊ ምክክር መድረክ ራሱን ሊያገል እንደሚችል ጠቁሟል - ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟላለት በመጠየቅ፡፡ ቅድመ ሁኔታዎቹ ምን ይሆኑ? ፓርቲው ራሱን ከማግለል ምን ይጠቀማል? የብሔራዊ ውይይት መድረኩ እንዴት ቢሆን ነው የሚመርጠው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከፓርቲው ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና ጋር በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በማተኮር እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል። እነሆ፡-

             ኦፌኮ ብሔራዊ የምክክር ሂደቱን እየተቃወመ ነው። ምክንያቱ ምንድን ነው?
እኛ እንዳየነው የምክክሩ ሃሳብ ሁሉን አካታች አይደለም። ሂደቱም የአንድ ፓርቲ ጨዋታ ነው። አንድ ቡድን የራሱን ዳኛ ይዞ ጨዋታ ውስጥ ከገባ ደግሞ የጨዋታው ውጤት ይታወቃል።
የአንድ ቡድን ጨዋታ ነው ስትሉ ምን ማለት  ነው? እስቲ ያብራሩልን?
ከልምዳችን ተነስተን የምንገመግመው ነገር አለን። ዝም ብለን አይደለም ይሄን ያልነው። ከደርግ ጀምሮ እንዲህ ያለ ኮሚሽን ነገር ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ ገለልተኛም አካታችም ባለመሆኑ፣ ችግሮችንም የማይፈታ ሆኖ  ይቀራል። አሁንም ይኸው አካሄድ ነው የተደገመው።
እናንተ ማስረጃችሁ ምንድን ነው፣ ገለልተኛና አካታች  አይደለም ስትሉ?
ለምሳሌ ጠመንጃ የታጠቁ ሃይሎችን ጠመንጃቸውን እንዲያስቀምጡ የሚያሳምናቸው ነገር አይደለም። አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ "ሽብርተኞች እዚህ ጨዋታ ውስጥ አይገቡም" እያሉ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ በመሰረታዊነት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመገዳደል ወደ መደራደር አልተሸጋገረም ማለት ነው። አንዱ ቡድን ሌላኛውን ሽብርተኛ በሚል ከፈረጀና “ከእነዚህ ጋር ድርድር አይካሄድም” ከተባለ፣ ምን አይነት ሰላም ነው እንዲመጣ የሚፈለገው? እነዚህ ሃይሎች በሂደቱ የማይሳተፉ ከሆነ፣ ጠመንጃቸውን አያስቀምጡም ማለት ነው። እንዲያ ከሆነ ደግሞ የመገዳደል ፖለቲካን ማስቆም አንችልም፡፡ ታዲያ ከዚህ ሂደት ምንድን ነው የምናተርፈው? ችግሮችን ዝም ብሎ ጊዜ ለመስጠት እንጂ  ከመሰረቱ ለመፍታት ያለመ አይደለም።
እናንተ የምክክር ሂደቱ እንዴት ቢሆን ነበር የምትመርጡት?
ቢያንስ ተቀናቃኝ ወገኖች ተቀምጠው፣ “እነ እገሌ ይዳኙን” ወይም “ኮሚሽነር ይሁንልን” ብለው በጋራ መክረው፣ የኮሚሽኑን አባላት መሰየም ነበረባቸው። የመደራደሪያ ፎርማሊቲውንም በጋራ ማዘጋጀት ይገባ ነበር። ይህ ባልሆነበትና አንድ ቡድን  ብቻ የፈለገውን አካሄድ መርጦ፣ ወደ ጨዋታው ሜዳ በጋበዘበት ሁኔታ የሚደረግ ውይይት ብዙም ውጤታማ አይሆንም። ቀባብቶና ያልሆነ ጨዋታ ተጫውቶ ለማለፍ የሚደረግ ጥረት የትም አያራምደንም። ስለዚህ በኛ በኩል የመጀመሪያ ሂደቱ ሁሉንም ወገኖች የሚያሳምን፣ የሚጋብዝ፣ ጠመንጃ ያነሱ ጠመንጃቸውን አስቀምጠው ለመነጋገር ፍላጎት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ መሆን አለበት። ይህን ኮሚሽን የሚመሩ ሰዎች የጋራ ስምምነት የተደረሰባቸው ናቸው ወይ? ሂደቱ በተለይ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እልቂት እያስከተለ ያለውን ጦርነት ማስቆም የሚችል ነው ወይ? የሚለውን የሚመልስ  ከሆነ ነው፣ ውጤቱ  የሃገራችንን ሰላም ማረጋገጥ የሚችለው። እኛ አሁን የተቸገርነው “እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው” ፖለቲካ ነው። ይሄ ላለፉት 50 ዓመታት የሰለቸን ዓይነት አካሄድ ነው።
ኦፌኮ ከአገራዊ ምርጫው ራሱን አግልሎ ነበር። አሁን ደግሞ የምክክር ሂደቱን እየተቃወመ ነው። ከሁሉም ሂደቶች ራስን ማግለሉ ፋይዳው ምንድን ነው?
እኛ ለኛ የሚመቸንን አካሄድ ነው የምንከተለው። ፍርፋሪ ፈልገን ወይ በፍርፋሪ ተታለን ያላመንበትን ነገር አናደርግም። የስልጣን ፍርፋሪ ብንፈልግ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ፣ አሁን ካለው መንግስት እኛም እንደ ሌሎቹ አናጣም ነበር። ዋናው ጉዳይ ግን የቆየንበት የፖለቲካ ቀውስ መሰረታዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል። ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ ስንሸጋገር ከርመናል። እኛ ለምሳሌ ከምርጫ የወጣነው የብልጽግና ካድሬዎች የህውሓትን የድሮ መንገድ ተከትለው ስለገፉን ነው። ይሄ ጨዋታ አያዋጣንም፤ እናስተካክል ብንልም አልሰሙንም። ስለዚህ በማይሆን ጨዋታ ውስጥ ገብተን አቋማችንን ማበላሸት አልፈለግንም። ከ2 መቶ በላይ ጽ/ቤቶች ተዘግተውብንና በርካታ አባላት ታስረውብን እያለ፣ ወደ ምርጫ መግባት የሚታሰብ አልነበረም።  በእንደዚያ ያለ ሁኔታ ወደ ምርጫ ብንገባ ኖሮ ፓርቲያችንን ይከፋፍልብን ነበር፤ ከህዝባችንም ያቀያይመን ነበር። ሁለተኛው ምክንያታችን ደግሞ በተመሳሳይ በኦነግ ላይ ይፈጸም  የነበረው ደባ ነው። እንዲህ የጨዋታውን ሜዳ ለማጥበብ ጥረት እየተደረገ በነበረበት ሁኔታ ወደ ምርጫ ብንገባ ኖሮ ስህተት ይሆን ነበር።
ስለዚህ እኛ ከምርጫ የወጣነው ተገፍተን ነው። በቂ ምክንያት ስለነበረን ነው። አሁንም ቢሆን ይህ የምክክር ኮሚሽን ዋጋ የሚኖረው፣ እነዚህ በሽብርተኛነት የተፈረጁ ሃይሎች ሲሳተፉበት ነው። ይሄ ካልሆነ ኮሚሽኑ የተሻለ ስራ መስራት አይችልም። እንደ ከዚህ በፊቶቹ ኮሚሽኖች ዋጋ የሌለው ስራ ነው ሰርቶ የሚያልፈው። ህውሓት ትግራይን ገንጥሎ ይሂድ ካላልን በስተቀር፣ ኦሮሚያ አካባቢም አሁን ካለው የበለጠ ደም ማፋሰስ ማስከተል ካልፈለግን በስተቀር፣ ከዚህ ቀውስ የምናተርፈው ነገር አይኖርም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ወደ መስመሩ ተመልሶ በሃቅ ላይ የተመሰረተ ድርድርና ምክክር መካሄድ አለበት።
እኛ እንዲህ ያሉ አቋሞችን የምንወስደው ተቸግረን ነው። ስልጣንም ፈልገን አይደለም። የሚያዛልቀው መፍትሄ እያለ፣ የማያዛልቅ ነገር ውስጥ አይናችን እያየ ላለመግባት ነው። መቼም ስልጣን ብንፈልግ፣ ዛሬ እነሱን የተጠጉት ያገኙትን ስልጣን፣ ብንጠጋቸው ይሰጡን ነበር። ነገር ግን የኛ ስልጣን ማግኘት፣ እንታገልለታለን የምንለው የኦሮሞም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብን መብት ማስገኘት አይችልም።
ኦፌኮ አሁን ያለበት  ሁኔታ ምን ይመስላል? ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግም ታዝዟል?
ኦፌኮ  አመራር ያጣ ድርጅት አይደለም። በእውቀትም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች የበታች ነው ተብሎ አይጠረጠርም፡፡  ምርጫ ቦርድ ያለውን በተመለከተ፣ ሁኔታው የሚያመች ከሆነ ጉባኤውን እናካሂዳለን፤ ካልሆነም ለቦርዱ በቃልም በደብዳቤም የገጠመንን ነገር እናስረዳለን። እንደሚታወቀው ኦሮሚያ ላይ የጸጥታው ሁኔታ ለእንቅስቃሴ ምቹ አይደለም። አባሎቻችን ከደምቢዶሎ፣ ከጉጂ፣ ከቦረና እንዴት እንደሚንቀሳቀሱ ማወቅ አለብን። ያው የጸጥታው ሁኔታ ይታወቃል። ምርጫ ቦርድና መንግስት ለዚህ ችግር  አስቸኳይ መፍትሄ መስጠት  አለባቸው።



Read 8264 times