Tuesday, 01 March 2022 00:00

ሐመልማል

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(4 votes)

 እነሆ በአርባ ቀን እድል ፈንታዬ እግር ብረት እንደተጠፈርኩ ዘመን ገስግሶ ሰላሳኛ አመቴን ደፈንኩ፡፡ የሚበቃኝን ያህል ዘመን ኖሬአለሁ፡፡ መኖር ዐቢይ ፋይዳ የሌለዉ ከንቱ ጉዞ ነዉ፡፡ አድካሚዉ የሕይወት ጉዞዬ በሞት ሲቋጭ ገላዬ የምስጥ ሲሳይ ይሆናል፡፡ ከዛ እንደማንኛውም ተራ ሰው ሳልውል ሳላድር እረሳለሁ፡፡ እንደ ሕይወት ሁሉ ሞትም ፋይዳ ቢስ ነዉ፡፡ ሞት ከመኖር በተቃራኒው ፋይዳ ቢኖረው ኖሮ ሳላወላውል ራሴን እገድል ነበር፡፡ ሕይወት እርግማን ነው፤ አለመፈጠር የተሻለ ነገር ነው፡፡ ሰው በመኖር የሚያተርፈው ነገር የለም፤ ሰርክ እየተፈራረቀ በሚደቁሰዉ የመከራ በትር ነፍሱን ከማጎስቆል በቀር፡፡
መኝታ ቤቴ ውስጥ አልጋ ላይ ተንጋልያለሁ፡፡ የመስታወቱ መስኮት እንደተከፈተ ነው፡፡ ከውጪ የሚገባው ነፋስ ቅዝቃዜ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ቢሆንም ተነስቼ ልዘጋው አልፈለግኩም፡፡ ደግሞም ደረቴና ክንዴ እንደተራቆተ ነዉ፡፡ ከሁለት ቀን በፊት ማንበብ ጀምሬ ሰልችቶኝ ያቋረጥኩት መጽሐፍ ፊቴ ግድግዳውን ታኮ ከተጎለተው ጠረጴዛ መሐል ተቀምጧል፡፡ ወርቃማው የጀንበር ፀዳል መስኮቱን ዘልቆ አልጋውንና ወለሉን አልብሶታል፡፡ የበጋውን ኃያል ነፋስ ቅዝቃዜ መቋቋም ባለመቻሌ ከተጋደምኩበት ተነስቼ ክፍቱን መስኮት በመጋረጃው ጋርጄ፣ ፊት ለፊቴ ከሚገኘው የቁም መስታወት ፊት ተገትሬ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የተጐሳቆለ መልኬን መገምገም ጀመርኩ፡፡ ጠይም ፊቴ ወዙ ነጥፏል፣ በአመዳይ ክፉኛ የተንገላታ ይመስላል። ጥርሴ መወየብ ጀምሯል፡፡ የሚያረግዱ ጡቶቼ ብቻ ከለበስኩት ስስ ሹራብ ስር በአትንኩኝ ባይነት ተኮፍሰዉ ይታያሉ፡፡ ተካልኝ ጥሎኝ ከሄደ በኋላ እየገፋሁት ያለዉ ሕይወቴ ባይተዋርነት የከበበዉ ነዉ፤ ዓለም ዉስጤ ከሞተች ከራርሟል፡፡ የይስሙላ ጉዞዬ ቀቢፀ ተስፋ ያጠላበት ነዉ፡፡ በአንፃሩ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች ሰርክ የሚጠቅሱት የኑሮ ስኬቴን ነዉ፣ ፈረንጅ አገር ተሰድጄ ድግሪ መሰብሰቤን፣ በአዱኛ ከደረጁ ቤተሰቦቼ መወለዴን፡፡ ሰዎች አልተረዱም እንጂ ይኸ ሁሉ ነገር ለእኔ ፋይዳ ቢስ ነዉ፡፡
ከወዳጅ ዘመድ ጋር የነበረኝ ጥብቅ ቁርኝት ከላላ ሰነባብቷል፡፡ የገጠመኝን ፈተና ብቻዬን መጋፈጡን መርጫለሁ፡፡ ደግሞም ሁሉም ሰዉ ብቻዉን ነዉ፡፡ ምንም እንኳ፣ ወዳጆቻችን ዙሪያችንን ቢከቡ የነፍሳችንን ስቃይ ግን መጋራት አይችሉም፤ የልባችንን ስብራት መጠገን አይችሉም፡፡ ጥላቻዬ እስኪሽር፣ የልቤ ቁስል እስኪጠግ ሰዎችን መሸሹን መርጫለሁ፡፡ ‘የሰዉ መድሃኒቱ ሰዉ ነዉ’ የሚለዉ ብሂል ፍፁም ቅጥፈት ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ የሰዉ ጠላቱ ማን ሆነና? የሰዉ ልጅ በወገኑ ላይ የሚፈፅመዉ ክፋት ከአዉሬ የከፋ ነዉ፤ ማለቴ በእሴት ያልተተበተበዉን ቱባ ተፈጥሮዉን ገልበን ካየነዉ፡፡
በናሁሰናይ ክህደት ቅስሜ ተሰብሮ ለዓለም ጀርባዬን ከመስጠቴ በፊት ፍፁም ደስተኛ ሰዉ ነበርኩ፣ ያ ሁሉ ደስታ በአንድ ጀንበር ከንቱ ሆነ እንጂ፡፡ ለሕይወት የነበረኝ አጠቃላይ ምልከታ የተቀየረዉ እጅግ አፈቅረዉ የነበረዉን ሰዉ አጥቼ ብቻዬን ስቀር ነዉ፡፡ ሕይወት በራሱ ግብ አልባ ዘፈቀዳዊ ዑደት መሠረት እንጂ የሰዉን ልጅ በጎ ትልም ተከትሎ የማይጓዝ መሆኑን የተገነዘብኩት በእዚህ ወቅት ነበር፡፡
የወለሉ ሴራሚክ ቅዝቃዜ ባዶ እግሬን ዘልቆ ስለተሰማኝ፣ መስታወቱ ፊት ተገትሬ ገፄን መገምገሙን ትቼ ሲጋራ አቀጣጠልኩና ወደ መስኮቱ ሄጄ አሻግሬ ከመንገዱ ማዶ ያለዉን መንደር መመልከት ጀመርኩ። መኖሪያ ቤቴ የሚገኘው መንደራችንን ለሁለት ገምሶ ከሚያልፈው ጠባብ የአስፋልት መንገድ ዳር ነው፡፡
ከእኔ ቤት ትይዩ ከሚገኘው ትልቅ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ አፀዱ ላይ አንዲት ፈረንጅና ሁለት ሐበሻ ልጆች እየተጯጯሁ ኳስ ይጫወታሉ፡፡ ከሁሉም ልጆች በቁመት የምትበልጠዉ ሴቷ ናት፡፡ ቀጭን ናት፣ ፀጉረ ረዥም፡፡ ሰማያዊ ሹራብና ነጭ ቁምጣ ለብሳለች፣ እስከ ጉልበቷ ድረስ ነጭ ካልሲ አጥልቃለች፡፡ በጨዋታዉ ዉስጥ የምታሳየዉ ዝቅተኛ ተሳትፎ የጨዋታዉ የአጨዋወት ቴክኒክ እንግዳ እንደሆነባት ያሳብቃል፡፡ በመሐል፣ ጨዋታዉን አቋርጣ (በጨዋታዉ ተሰላችታ ሳይሆን አይቀርም) ተነጥላ ወደ ቤቱ መግቢያ በር ታዛ በመሄድ እምነበረዱ ላይ ተቀምጣ፣ የጓደኞቿን ጨዋታ መመልከት ጀመረች፡፡
ልጆቹ ከሚጫወቱበት ሰፊ ቪላ ቤት ጎን የሚኖረዉ እንግሊዛዊ ጎልማሳ፣ ከነጭ ግዙፍ ዉሻዉ ጋር ግቢዉ ዉስጥ ይላፋል፡፡ የፈረንጁ ወጣት ሐበሻ የጥበቃ ሠራተኛ፣ ከቪላ ቤቱ ተነጥሎ ከተሠራዉ አነስተኛ ቤት ደጃፍ ላይ ተጎልቶ፣ ጎልማሳዉ ከዉሻዉ ጋር የሚያደርገዉን ልፊያ በአትኩሮት ይመለከታል፡፡ ከእኔ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚነፍሰዉ ነፋስ ኃያል ቢሆንም፣ ቀዝቃዜዉን ተቋቁሜ ትኩረቴን ወደ ልጆቹ ጨዋታ መለስኩ፡፡ ሴቷ ልጅ ከተቀመጠችበት ተነስታ ወንዶቹ ኳስ የሚጫወቱበትን ቀይ አሸዋ ሜዳ አቋርጣ አልፋ በአበቦች ከተከበበዉ ሐመልመል ሳር ላይ በጀርባዋ ተንጋለለች፣ እጆቿን ግራና ቀኝ ዘርግታ፡፡ የልጆቹን ጨዋታ መመልከቴን አቋርጬ መስኮቱን ዘግቼ መልሼ አልጋዬ ላይ ወጥቼ ተንጋለልኩ፡፡
ከሥራ መልስ ቤቴ እንደገባሁ የከፈትኩት የማይልስ ዴቪስ ሊፍት ቱ ዘ ስካፎልድ የተሰኘ ሙዚቃ፣ ለአምስተኛ ጊዜ መልሶ እየተጫወተ ነው፡፡ ሙዚቃዉን ለረዥም ጊዜ በተደጋጋሚ ስላዳመጥኩት እጅግ ሰልችቶኛል፡፡ ፊት ለፊቴ ግድግዳዉ ላይ አባቴ በሕይወት ሳለ ገዝቶ ያመጣዉ የአንድ ታዋቂ የአገራችን ሠዓሊ የሥዕል ሥራ ተሰቅሏል፡፡ የሥዕሉ የግርጌ ርእስ በመመለስ መንገድ ላይ ይሰኛል፡፡ ይህ ሥዕል ምድር ሳሎን ቤት ዉስጥ ከልጅነት እድሜዬ አንስቶ ለረዥም ዓመታት ተሰቅሎ የኖረ ነዉ፤ በቅርቡ ነዉ ከተሰቀለበት አዉርጄ እዚህ አምጥቼ የሰቀልኩት፡፡ ከሥዕሉ ጎን ከሁለት ዓመት በፊት ከናሁሰናይ ጋር ለጉብኝት ላንጋኖ ሐይቅ ሄደን ሳለ፣ ሐይቁ ዳር የተነሳነዉ ፎቶግራፍ በትልቅ የመስታወት ፍሬም ተሰቅሏል፡፡ ፎቶግራፉ ላይ ከወገቤ በታች ያለዉ አካሌ በወርቃማዉ የሐይቁ ዉሃ ተውጦ በፍርሀት (የዋና ክህሎት ስለሌለኝ) የናሁሰናይን ራቁት ወገብ አቅፌ እታያለሁ። ፎቶግራፉ፣ ልረሳዉ የምሻዉን ግን ከልቤ ሰሌዳ ላይ ፈፅሞ ያልተፋቀዉን ከናሁሰናይ ጋር በአብሮነት ሳለሁ ያሳለፍኩትን ረዥም የትዝታ ድር ጎተተብኝ፡፡ እዛ ቦታ የተካሄዱት ኩነቶች አንድ በአንድ ከአእምሮዬ ቋት እንደ ሰበዝ እየተመዘዙ ወጥተዉ፣ ተግተልትለዉ ብቅ አሉ፤ ነፍሴን በናፍቆት አለንጋ ሊገርፉ፡፡
ከወዳጅ ዘመድ መራቄ ብዙ አሉባልታዎች እንዲነሱብኝ ሰበብ ሆኗል፤ የእኔ አፀፋ ግን ቸልታ ብቻ ነበር፡፡ ብዙዎችም ከእነሱ ጋር ያሰናሰለኝን የወዳጅነት ገመድ ማላላቴን እንደ አልባሌ ወረት ቆጥረዉት ታዝበዉኝ ችላ ብለዉኛል፡፡ አበጁ፡፡ በወዳጅነት ሰበብ ላደረግሁት ችሮታ፣ ወሮታን የምሻ ግብዝ አይደለሁም፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሁሉም ነገር፣ ለየትኛዉም ሰዉ ደንታ ቢስ ነኝ፡፡ የእኔ ዓለም ናሁሰናይ ነበር፤ አሁን ብቻዬን ቀርቻለሁ፡፡
ከናሁሰናይ ጋር ከመለያየታችን በፊት አራት ዓመታትን አብረን በፍቅር ቆይተናል። በአንድ ጎጆ ልንጠቃለል ጫፍ ላይ ደርሰን ሳለ ነዉ፣ ሳይታሰብ የእህል ዉሃችን ገመድ የተበጠሰዉ፡፡ እሱን ከማወቄ በፊት ለፍቅር ባይተዋር ነበርኩ፡፡ ከእሱ ጋር በፍቅር ሳለሁ የነበረኝ ደስታ ወደር አይገኝለትም። በሕይወቴ ዉስጥ አዲስ ምዕራፍ የተጀመረዉ እሱን በማወቄ ምክንያት ነዉ፡፡ እናም፣ ፍቅሩ ዉስጤን በደስታ ማዕበል አጥለቀለቀዉ፤ በባይተዋርነት ተከብቤ ባሳለፍኩት ዘመን ተቆጨሁ፡፡
 * * *
 ከአንድ ዓመት በፊት ነዉ፡፡ በእዛ ዕለት፣ ረዥም መንገድ የእግር ጉዞ አድርጌ ነበር እቤቴ የገባሁት፤ ለገሀር ከሚገኘዉ መሥሪያ ቤቴ እስከ መኖሪያ ቤቴ ቦሌ ድረስ፡፡ ቤቴ ገብቼ የይድረስ ይድረስ የሠራሁትን ራት ቀማምሼ ብዙ ጊዜ ከምቀመጥበት ሶፋዬ ላይ ተጋድሜ ነበር፡፡ ፊት ለፊቴ ካለዉ የመስታወት ጠረጴዛ ላይ በመሥሪያ ቤቴ በኩል የደረሰኝ ናሁሰናይ የሰደደዉ በፖስታ የታሸገ ደብዳቤ ተቀምጧል፡፡ ፖስታዉን አንስቼ እላዩ ላይ የተለጠፈዉን የቴምብር ፎቶግራፍ ለአፍታ ተመለከትኩና በደካማ የማወቅ ጉጉት ፖስታዉን ከፍቼ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ደብዳቤው በእጅ የተፃፈ ነው፡፡ ከተለያየን ከዓመት በኋላ የላከው ደብዳቤ ነበር፡፡ መልእክቱን አንብቤ እንደጨረስኩ ወረቀቱን ጠረጴዛ ላይ ወረወርኩና ሲጋራ ለኮስኩ፡፡ በወቅቱ የአነበብኩት ነገር እጅግ አበሳጭቶኝ ነበር፡፡ ናሁሰናይ የሰደደዉ ደብዳቤ፣ እኔ ላይ ባደረሰው በደል በእጅጉ እንደተፀፀተና ይቅርታ እንዳደርግለት የሚያትት ነበር፡፡ ይሉኝታ ቢስነቱ እጅግ አናደደኝ፡፡ ያኔ ሁለመናውን የሰጠውን ሰው ገፍቶ ሲሄድ ፀፀት አልተሰማዉም ነበር፤ እናም በብጣሽ ወረቀት ጽፎ በሰደደው ደብዳቤዉ ረግጦ የሄደውን ፍቅር ዳግም መሻቱ በእጅጉ አበሸቀኝ፡፡ ይህን ያደረገው ምናልባት ለእሱ የነበረኝን ብርቱ ፍቅር ስለሚያውቅ፣ ዳግም ይቅርታ ታደርግልኛለች የሚል ከንቱ ተስፋን በልቡ ሰንቆ ይሆናል፡፡ ግን ምን ያደርጋል፣ ሁሉ እንዳልነበር ሆኖ ነበር፡፡ በክህደት የተሰበረዉ ልቤ ቂም አርግዞ እንደ አለት ደንድኖ ነበር፡፡ በእርግጥ በደልን መርሳት አስገራሚ ጉዳይ አይደለም፤ ነገር ግን የበደሉንን ሰዎች ይቅርታ ለመቀበልም ሆነ ለመቃወም የጉዳታችን መጠን ይወስነዋል፡፡
ከመለያየታችን አንድ ወር ቀደም ብሎ ነበር ናሁሰናይን በአካል ያገኘሁት፤ ብዙ ጊዜ ጎራ ከምንልበት መሐል ከተማ እሚገኘዉ ቬነስ ሆቴል ቀጥሮኝ የተገናኘን እለት። እዛ ሆቴል ዉስጥ፣ ለዘላለም ሳይለየኝ አብሮኝ ይዘልቃል ብዬ የተመካሁበት ሰዉ ግንባሩን ቋጥሮ በአጭር ቃል (በምን ሰበብ ሊለኝ እንደፈለገ እንኳን ሳይናገር) ፍቅራችን ማክተሙን አረዳኝ፡፡ ሰማይ ተደፋብኝ፡፡ ድንገተኛ መርዶዉ ልቤ ላይ ሊፈጥር የሚችለዉን የሐዘን ክብደት ፈፅሞ አላስተዋለም፡፡ ተነስቼ መፀዳጃ ቤት ገባሁና አለቀስኩ፡፡ መከዳት ለእኔ እንግዳ ነገር ነበር፣ እናም ሰዉ አማኝ ልቤ በሐዘን ክፉኛ ተሰበረ፡፡ አፅናኝ አልነበረኝም፡፡
እንቅልፍ በዐይኔ ሳይዞር ሌሊቱን እንዲሁ በከንቱ በሐሳብ ስብሰለሰል አነጋሁ፡፡ ማለዳ ላይ ጅስሜ በሐሳብና በእንቅልፍ እጦት እንደዛለ መኪናዬን አስነስቼ ከከተማ ዳር ወዳለ ሥፍራ ከነፍኩ፤ ምናልባት የቦታ ለዉጥ ክፉኛ የተናወጠ መንፈሴን ቢያሰክነዉ ብዬ፡፡
* * *
እንደ ምፃት ቀን እጅግ ለረዘሙ ቀናት በታላቅ ድብርት ተዉጬ፣ ብቻዬን ቤቴ ስቆዝም ከርሜ በአንዱ ቀን በቋፍ ወደ ሥራ ገበታዬ ተመለስኩ፡፡ የወትሮዉ የሥራ ሞራሌ ግን ሙት ነበር፡፡ ፊት ለፊቴ ተከማችተዉ ፍፃሜአቸዉን ከሚጠብቁ ሥራዎች መካከል አስቸኳይ ናቸዉ ያልኳቸዉን ሥራዎች መርጬ ሥሠራ ዉዬ አመሻሽ ላይ ከቢሮ ወጣሁ፡፡ መንፈሴም አካሌም እጅግ ዝሎ ነበር፣ እናም ቤቴ ገብቼ እስከማርፍ እጅግ ቸኩዬ ነበር፡፡ መስቀል አደባባይን አልፌ በቦሌ መንገድ ጥቂት እንደነዳሁ ድንገት መንገድ ላይ ለማመን የሚያዳግት ኩነትን በዐይኔ ተመለከትኩ፤ ናሁሰናይ ከሴት ጋር ተቃቅፎ ወደ ቡና ቤት ሲዘልቅ፡፡ እጅግ ደነገጥኩ፡፡ ክስተቱ ጥርጣሬዬን በተጨባጭ አስረገጠልኝ፡፡ ራሴን በመደለል አለባብሼ የተዉኩት እዉነት በገሀድ ጥርሱን አግጥጦ ፊቴ ተደነቀረ፡፡ ፍቅር ልቦናዬን አነሁልሎት አንዳንድ እንግዳ ተግባሮቹን (ቸልተኝነቴ ተደምሮ) በወጉ ማጤኑን ዘንግቼ እንጂ የናሁሰናይ ልብ ከእኔ መሸፈቱን የሚያሳብቁ ጥቂት ፍንጮች ነበሩ፡፡
በዐይኔ በብረቱ የተመለከትኩት ኩነት አዉኮኝ ከቀልቤ ርቄአለሁ፡፡ መኪናዬ ዉስጥ በድን ሆኜ እንደተጎለትኩ ነኝ፣ ልቦናዬ ባፈለቀዉ መንታ ምክር እየዋለልኩ፡፡ በአንድ በኩል ልቤ አካባቢዉን ጥለሽ ተሰወሪ እያለ ያጣድፈኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፍፃሜዉን መመልከት እንደሚገባኝ ይኸዉ ልቤ ይሞግተኛል፡፡ በመጨረሻ፣ መኪናዬን ጎዳናዉ ዳር ገትሬ ተከትያቸዉ ወደ ቡና ቤቱ ዘለቅኩ፡፡
ናሁሰናይ፣ የሴቷን እጅ እንደያዘ ወደ ዉስጠኛዉ የቡና ቤቱ ክፍል ይዟት ገባ። የገቡበት ክፍል ለጥንዶች ተብሎ የተሰናዳ ልዩ ክፍል ነዉ፡፡ እኔ ሬስቶራንቱ ዉስጥ ተቀመጥኩ፡፡ ናሁሰናይ ጀርባዉን ለሬስቶራንቱ ሰጥቶ በመቀመጡ ሬስቶራንቱ ዉስጥ የተቀመጠን ሰዉ ማየት አይችልም። በመሆኑም፣ ካለሁበት ሆኜ እያንዳንዱን እንቅስቃሴአቸዉን በግልፅ መከታተል እችላለሁ፡፡
ሴቷ ደርባዉ የነበረዉን ጥቁር ካፖርት አዉልቃ ቀይ ቦርሳዋ ጎን አስቀመጠችዉ፡፡ ናሁሰናይ ቡናማ ሙሉ ልብስ ነዉ የለበሰዉ፡፡ ፊቴ የቀረበዉን ቢራ መጠጣቱን ትቼ ሲጋራ አቀጣጠልኩና ፊቴ የሚካሄደዉን የጉድ ቴአትር መከታተሌን ቀጠልኩ፡፡ ናሁሰናይ እጆቹን በአስረጅነት እያወናጨፈ ያወራል፡፡ በተመስጦ ሲያወጋ እንዲህ የማድረግ ልማድ አለዉ፡፡ ሴቷ አፏን በእጇ ጋርዳ አብዝታ ትገለፍጣለች፡፡ ፀጉረ አጭር ነች፣ ብስል ቀይ። ፊታቸዉ የቀረበዉን ማዕድ እየተጎራረሱ መመገቡን ቀጥለዋል፡፡
ሰዎች እጅግ ግብዞች ናቸዉ፡፡ በብዙ ነገሮች የመዘንኩት ናሁሰናይ፤ እስከ ሕይወቴ ፍፃሜ ድረስ አብሮኝ የሚዘልቅ ፍፁም ታማኝ ሰዉ ይመስል ነበር፡፡ ወዳጅ ብለን የተቀበልናቸዉን ከማመን ዉጭ ምንስ የማድረግ ምርጫ ይኖራል? የሴቷ እጆች የናሁሰናይን አንገት አቅፈዉ፣ አፍ ለአፍ ገጥመዉ በመሳሳም ላይ ናቸዉ፡፡ በዐይኔ ያየሁትን ኩነት መቀበል አዳገተኝ፤ መሬት ተከፍታ እንድትዉጠኝ ተመኘሁ፡፡ የብቻ ይሉት የነበረ ሰዉ ከባእድ ጋር ሲወሰልት በዐይን ከመመልከት የከፋ ምን አይነት ልብን የሚሰብር ክስተት ይኖራል? ናሁሰናይን እጅግ አምነዉ ነበር፡፡ እንደዛ እጅግ አምነዉ የነበረ ሰዉ ድንገት በሌላ ሰዉ ይለዉጠኛል ብዬ ፈፅሞ አንድም ቀን አስቤ አላዉቅም፡፡ ዘግይቶም ቢሆን የተገለጠልኝ ታላቁ ስህተቴ ቀድሞ አለመጠርጠሬ ነበር፡፡ የሆነ ወቅት፣ ይወዱናል፣ ያፈቅሩናል በምንላቸዉ ሰዎች ልብ ዉስጥ ሌሎች ሰርገዉ እንደሚገቡና እኛ እንደምንሰለች፣ እንደምንዘነጋ፣ በሂደትም አንደምንረሳ፡፡ እንቆቅልሽ የሆነብኝ ጉዳይ ከእዚች ሴት ጋር መቼ ግንኙነት እንደ ጀመረ ማወቁ ነዉ፣ ፋይዳ ባይኖረዉም፡፡ ምናልባት ለሥራ ጉዳይ ምዕራብ አገር ሄጄ በነበረበት ወቅት ተዋዉቋት ሊሆን ይችላል፡፡ ቆይ ይቺ ሴት ማን ነች? ምንድን ነች? ይህን እንቆቅልሽ ለመፍታት በሐሳብ እየዳከርኩ ቡና ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ፡፡
* * *
ከናሁሰናይ ጋር ለመጀመሪያ ቀን የተዋወቅነዉ ብሔራዊ ቴአትር ቤት በራፍ ላይ ነዉ፡፡ ወሩን በደንብ አስታዉሳለሁ፣ ሚያዝያ ነበር፡፡ በእዛ ቀን ከእሱ ጋር የተመለከትኩት ቴአትር ዛሬ ድረስ ከመድረክ አልወረደም፡፡ ይሄ ቴአትር ብድራት ይሰኛል።
ከናሁሰናይ ጋር ፍቅር በጀመርኩ በሁለተኛዉ ዓመት (አሁን እምሠራበት መሥሪያ ቤት ከተቀጠርኩ ከወራት በኋላ) ባሕር ማዶ ለሁለት ዓመት ሥራ ተመድቤ ሄድኩ፡፡ ሆኖም፣ የናሁሰናይን ብርቱ ናፍቆት መቋቋም ስላልቻልኩ አንድ ዓመት ብቻ እንደቆየሁ ጓዜን ጠቅልዬ ወደ አገሬ ተመለስኩ፡፡
* * *
የናሁሰናይ ደብዳቤ ከደረሰኝ ከጥቂት ወራት በኋላ አንድ ቀን ምሽት ናፍቆቱ ተቀስቅሶ ክፉኛ አንገላታኝ፣ ትዝታዉ ከትዉስታዬ ማኅደር አንሰራርቶ ሰላም ነሳኝ። እናም፣ ከራሴ ጋር በብርቱ ስሟገት ቆይቼ ሄጄ ላገኘዉ ቆርጬ መኪናዬን አስነስቼ ወደ መኖሪያ ቤቱ ከነፍኩ፡፡
ከሰአታት ጉዞ በኋላ ናሁሰናይ መኖሪያ መንደር ደረስኩ፡፡ የሚኖርበት ግዙፉ ነጭ የአፓርታማ ህንፃ ከርቀት ይታያል፡፡ ወደ አፓርታማዉ የሚወስደኝን አቋራጭ መንገድ ተከትዬ ጥቂት እንደነዳሁ ግን እቅዴን የሚያፈርስ አስገዳጅ ዉሳኔ ከልቤ መነጨ። ወደ ትፋቱ የሚመለስ ዉሻ ብቻ ነዉ፣ እኔ ሐመልማል ብዙ ወንዶችን ሰርክ ደጅ የማስጠና ሴት ነኝ እንጂ ዉሻ አይደለሁም። ይኸን እዉነት ናሁሰናይ ማወቅ አለበት፡፡ አንዴ ሰዎች ከልባቸዉ አዉጥተዉ ከቀበሩን ሁሉም ነገር አብቅቷል። አሁን ናሁሰናይ የሌላ ሰዉ ነዉ፣ እናም ሁሉን ትቼ ወደ መጣሁበት ለመመለስ ቆርጬ፣ መኪናዬን አዙሬ በመጣሁበት አዉራ መንገድ ወደ መንደሬ ከነፍኩ፡፡
አድዋ አደባባይን ተሻግሬ ቁልቁል ወደ መኖሪያ መንደሬ ቦሌ የሚወስደዉን መንገድ ይዤ በፍጥነት እየከነፍኩ ነዉ፤ ከፊት ለፊቴ ከተቃራኒ አቅጣጫ (በቅርብ ርቀት) ግዙፍ ኮንቴነር የጫነ ከባድ ተሽከርካሪ አቅጣጫዉን ስቶ በሲሚንቶ የደደረዉን የአዉራ መንገድ መክፈያ ግንብና ብረት እየናደ ወደ እኔ ገሰገሰ፡፡ በገሀድ እየተፈጠረ ያለዉ ኩነት ሁሉ ቅፅበታዊ ቅዠት መሰለኝ፣ ከፊት ለፊቴ አስፈሪ መንጋጋዉን ከፍቶ በታላቅ ጭካኔ ሊዉጠኝ የሚገሰግሰዉ ሞት በብርቱ ፍርሀት አርበደበደኝ፡፡ እጅግ አስፈሪዉ ድራማ መካሄዱን ቀጥሏል፣ በጆሮዬ የሚተመዉ ድምፅ እጅግ ሰቅጣጭ ነዉ፡፡ ግዙፉ ተሽከርካሪ ያገኘዉን የብረት አጥርና የሲሚንቶ ግንብ እየደረመሰ ከእነ መኪናዬ ሊጨፈልቀኝ ወደ እኔ መገስገሱን ተያይዞታል፡፡ ሞት ይህን ያህል አስፈሪ መስሎ አይታየኝም ነበር፤ ድንገት ዐይኑን አፍጥጦ ስለመጣብኝ ነዉ መሰል ሁለመናዬ በታላቅ ቡከን ተንዘፈዘፈ፡፡ ተሽከርካሪዉ እየበረረ መጥቶ እላዬ ላይ ሲከመር የሰቀቀን ጩኸቴን ለቀቅኩት፡፡

Read 1080 times