Thursday, 03 March 2022 06:40

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ዓድዋ ቀኝ እጄ

ድምድምታ ነው እግሩ ያነሳል አቧራ
መብረቅ ነው ልሳኑ አባቴ ሲያጓራ
ጣቱ የእሳት ላንቃ ነጥሎ ሚመታ
ላይ በላይ ሚከምር አስከሬን በተርታ
ትኩስ ደመ ሞቃት የማያውቅ እርጅና
ቀልድ አያውቅም በሀገር ጥቁሩ ልበ
ጀግና!
ነፍሱን ቤዛ ሰጥቶ ልጁን ያስከበረ
አጥንቱን ደርድሮ ድንበሩን ያጠረ
ባንዲራ ታቅፎ ሞቱን የጨለጠ
የነፃነት ሐውልት
የእውነት ብራና መንፈሱ ያጌጠ
እንደተሞሸረ
ሞተ ሲሉት ኖሮ ዛሬ ላይ ሚያወራ
አባቴ መንፈስ ነው ኩራት ሚዘራ !
በሰው ጓዳ ቀንቶ ዓይኑ ማይቀላውጥ
መሶብ በእግሩ ረግጦ ወዳጁን ማይረግጥ
ለስሙ ሰም ሆኖ የነደደ ደርሶ
እብለት በአፉ ዙርያ የማይደርስ ጨርሶ
ኢትዮጵያ እያለ ምሎ ለአንድ እናቱ
በወርቅ ቀለም ጽፎ
ክብር አውርሶኛል አባቴ እንደ አባቱ!
ይሄ የእሳት ላንቃ ነጭነትን ገድሎ
ከጥቁር ቀለሙ መች ተገኘ ጎድሎ
ንሳ ብሎ ነግሮኝ እጅ ነሳሁ ዛሬ
የዓድዋ ዘር ወልዶኝ አላፍርም በሀገሬ!
ቡራኬው ደርሶኛል
ሞገስ አልብሶኛል
እሳት አጋርቶኛል
ብቃት አውርሶኛል
ማእረግ አቃምሶኛል
በጠላት ምድር ላይ የኔን ስም አንግሶ
ታሪክ እንዳይበርደኝ
ዓድዋ ቀኝ እጄ
አንቀባርሮ አኖረኝ ነፃነት አልብሶ
እንዲያው ቢነፃፀር
አልማዝ እንኳ አይደምቅም እንደኔ
ጨርሶ !
(ነፃነት አምሳሉ አፈወርቅ)




______________________

Read 1913 times