Saturday, 05 March 2022 12:02

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ እንዲያደርጉ ተልዕኮ የተሰጣቸው 3 ባለሙያዎች እነማን ናቸው?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፤ አሜሪካዊውን ስቴቨን ራተርን፣ ኬንያዊቷን ካሪ ቤቲ ሙሩንጊን እና ጋምቢያዊቷን ፋቱ ቤንሶዳን አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ባለሙያዎች አድርጎ ሾሟል።
ባለፈው ህዳር ወር 2014 ጉባኤው አከናውኖት በነበረው ስብሰባ፣ በኢትዮጵያ ሶስት አባላት ያሉት አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያዎች ለማሰማራት ውሳኔ አሳልፎ የነበረ ሲሆን በዚያ ውሳኔ መሰረት ኮሚሽኑ መቋቋሙ ተገልጿል።
የተቋቋመውን ኮሚሽን ጋምቢያዊቷ ቤንሶሱዳ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ሲሆን ዋነኛ ተልዕኮውም ከጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር ይሆናል ብሏል።
ኮሚሽኑ በዋናነት በርካታ አቤቱታ ሲቀርብባቸው የነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና ከስደተኞች ጋር የተያያዙ  የመብት ጥሰቶችን ይመረምራል ተብሏል።
ሶስቱ የኮሚሽኑ አባላት በዋናነት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በየፈርጃቸው እንዲለዩ፣ ጠንካራ ማስረጃ መኖሩን እንዲያረጋግጡ እንዲሁም ጥቃቱን ያደረሱ አካላት በተጨባጭ ማስረጃ እንዲለዩ ሃላፊነት እንደተሰጣቸው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ፕሬዚዳንት አርጀንቲናዊው አምባሳደር ፌደሪኮ ቮሌጋስ አመልክተዋል።
ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ተፈፅመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሙሉ እንደሚመረምሩ የ1 ዓመት ጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸው የተሾሙት ሶስቱ ባለሙያዎች የስራ ልምድ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
1. ፋቶ ቤንሶዳ፡- ጋምቢያዊቷ ቤንሶዳ ለ9 ዓመታት በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቢ ህግ ሆነው የሰሩ፣ በአለማቀፍ የወንጀለኞች ፍ/ቤት የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋን የዳኙ፣ የጋምቢያ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩ፣ የፍትህ ሚኒስትር የነበሩና የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ሆነው የሰሩ ጎምቱ የህግ ባለሙያ ናቸው፡፡
2. ካሪ ቤቲ ሙረንጊ፡- ኬንያዊቷ ሙረንጊ በተለይ በሴቶችና በህጻናት የመብት ጥበቃዎች ላይ ሰፊ የስራ ልምድ ያላቸው ናቸው ተብሏል። በአሁኑ ወቅትም የኬንያ ከፍተኛ ፍ/ቤት አማካሪና የሕግ  ባለሙያ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው።
ሙረንጊ በተለይ እ.ኤ.አ ከ2002 እስከ 2010 በነበረው የኬንያ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት የተቋቋመውን የእውነታ አፈላላጊና እርቅ ኮሚሽንን በምክትል ሊቀመንበርነት የመሩ መሆናቸውም ተጠቅሷል። በደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት የሕግ አማካሪ፣ እንዲሁም ከፍልስጤም ሉአላዊ ግዛት ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የተቋቋመው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አባል በመሆን አገልግለዋል።
3. ስቲቨን ራተርን፡- አሜሪካዊው ስቲቨን ራትነር በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ የህግ ፕሮፌሰር ሲሆኑ በተለይ በአለማቀፍ  የሰብአዊ መብት ህግ፣ በጸረ-ሽብር ስትራቴጂዎች የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ምርመራ ላይ የዳበረ ልምድ ያላቸው ናቸው ተብሏል።
በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጉባኤ በኩል በካምቦዲያ፣ ስሪላንካና የተለያዩ ሃገራት የተሰጣቸውን ተልዕኮ የተወጡ መሆናቸውም ተመልክቷል።

Read 9776 times