Saturday, 05 March 2022 12:03

በድርቅ ምክንያት 377 ያህል ትምህርት ቤቶች ተዘጉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 377 ት/ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መዘጋታቸውን የጀርመን ድምጽ ዘገባ ያመለክታል።
በሶማሌ ክልል 316 እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ቦረናና ምስራቅ ባሌ ዞን 61 ት/ቤቶች በድርቁ ምክንያት መዘጋታቸውን፣ በአካባቢዎቹ የሚገኙ ዜጎችም በድርቁ ምክንያት ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን የብሄራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አመልክቷል።
ድርቁ ባየለባቸው የኦሮሚያ 5 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 40 ወረዳዎች 8.4 ሚሊዮን እንስሶች ለጉዳት ተዳርገዋል ተብሏል። በምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ፣ በቦረና፣ በምዕራብ ጉጂ፣ በምዕራብ አርሲና  ባሌ  ዞኖች በሚገኙ 70 ወረዳዎች  የሚኖር 2.8 ሚሊዮን ህዝብ ለመጠጥ ውሃ እጥረት መጋለጡም ታውቋል።
ድርቅ ባጠቃቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች ብቻ 3.1 ሚሊዮን ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ይፈልጋሉ የተባለ ሲሆን በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል በ83 ወረዳዎች የሚኖር 3.1 ሚሊዮን ህዝብ ለውሃ እጥረት እንዲሁም 2.4 ሚሊዮን ለምግብ እጥረት መጋለጡ ታውቋል። በሶማሌ ክልል 864 ሺህ 43 እንስሳት በድርቁ ምክያንያት መሞታቸውም ተመልክቷል።
በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ 915 ትምህርት ቤቶች ከመደበኛ የመማር ማስተማር ተግባራቸው የተስተጓጎለ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 316ቱ ሙሉ ለሙሉ መዘጋታቸው ተጠቁሟል።
መንግስት በሁለቱም ክልሎች የድርቅ ጉዳት ላጋጠማቸው አካባቢዎች የውሃና የምግብ አቅርቦት እያደረሰ መሆኑም በሪፖርቱ ተገልጿል።

Read 11074 times