Saturday, 05 March 2022 12:36

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       የሩሲያ የሳይበር አቅም
                           ምህረትአብ ጂ. ደስታ


          NATIONAL INTEREST የሩሲያን የሳይበር አቅም በሚገልፅበት ፅሁፉ፤ አሜሪካን ከጥቅም ውጭ ለማድረግ የሚፈጅባቸው ጊዜ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ናቸው ይላል። ሩሲያውያን በአሜሪካ ላይ ከፍተኛ አቅማቸውን ተጠቅመው የሳይበር ጥቃት ቢፈፅሙ፣ የአሜሪካን የኤሌክትሪክ ሃይል ቋቶችንና ወሳኝ የመሰረተልማት ተቋማትን ማለትም ኢንተርኔትን፣ የፋይናንስ ስርአቱን፣ የትራንስፖርት ሲስተሙን፣ የምግብና ውሃ ማከፋፈያ ስርአትን፣ የመገናኛና የአደጋ ጊዜ አገልግሎቶችን ከመቅፅበት ያወድሟቸዋል።
ይህ የሩሲያ እጅግ የተራቀቀ የሳይበር አቅም ቢሰነዘር የአሜሪካን የቅድመ ጦር ማስጠንቀቂያ ሳይተላይቶችን ከጥቅም ውጪ ያደርጋቸዋል። ይህም በአሜሪካና በአጋሮቿ ላይ ለሚፈፀሙ ጥቃቶች ምንም መረጃ የሌላቸው እውሮች ያደርጋቸዋል።
የአሜሪካ ጦር መሪዎች ይህንን በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል ይላል። የአሜሪካው NATIONAL INTEREST መፅሔት፣ የጦር መሪዎቹ በተደጋጋሚ በሰጡት ማስጠንቀቂያ፤ “ከሩሲያ የሚፈፀምብን የሳይበር ጥቃት የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቻችንን እና ሲስተሞቹን እንዳንቆጣጠርና ማዘዝ እንዳንችል ሊያደርገን ይችላል” በማለት የኑክሌር ስርአቱ በነዚህ ሃይሎች ሊጠለፍ እንደሚችልም አሳስበዋል።
የሩሲያ የሳይበር ጥቃት የአሜሪካን ፕሬዚዳንት የአፀፋ ኑክሌር ጥቃት እንዲፈፀም እንዳያዝ እንኳ ያደርገዋል። የአሜሪካ ጦር ከመሪዎቹ ጋር መነጋገር እንዳይችሉ ፤ መሪዎቹ ጦሩን ለማጥቃትና መከላከል ማስተባበር እንዳይችሉና በዚህም በቀላሉ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል።
አሜሪካ ደግሞ እንደዚህ ያሉ ጥቃቶችን መመከት የሚያስችላትን ምንም አይነት Super Electromagnetic pulse (Super_EMP) አልታጠቀችም፤ ሩሲያና ቻይና ግን የዚህ ባለቤት ናቸው። ሩሲያ የ Super-EMP ወይንም የሳይበር ጥቃት አሜሪካ ላይ ብትፈፅም፣ አሜሪካ ያላት 94 የኑክሌር ማብላያ ጣቢያዎች በደቂቃዎች ውስጥ ይቀልጣሉ ይወድማሉ።
ይህም የradioactive አደገኛ ጨረሮችን ወደ ከተሞች ይለቃል። ይህ ጥቃት ቢፈፀም የአሜሪካ መሪዎች ማን ጥቃቱን እንደፈፀመባቸውም ሆነ ማንን መበቀል እንዳለባቸው አያውቁም። ይህም የአሜሪካን ህልውና እንዲያከትም ያደርገዋል ነው ተረኩ።
ሩሲያ በአሜሪካ ላይ የሳይበር ጥቃት መፈፀም ከጀመረች የቆየች ሲሆን አሜሪካ በአፀፋው በሩሲያ ላይ የሳይበር ጥቃት መፈፀም አልቻለችም። የአሜሪካን ምርጫ ጠልፋ ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፍ እስከማድረግ የቻለችው ሩሲያ፣ አሜሪካን ማንበርከክ የሚችሉ የሳይበር ቴክኖሎጂዎችን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገች ትገኛለች።
እናም የነዚህ ሀገራት የሳይበር ቴክኖሎጂ በዚህ ያክል ረቂቅነት ከዘመነ እያንዳንዱ ሀገር ያለውን ከኑክሌር እስከ ሚሳኤል መሳሪያ መቆጣጠርና ማዘዝ እንዳይችል ከማድረጉም በላይ በራሳቸው የታጠቁት ኑክሌር መጥፊያቸው እንዲሆን የሚያደርግ ነው ይላሉ። ለዚህም ነው የሳይበር ጦርነት ተወዳዳሪ የሌለው እጅግ አውዳሚው ጦርነት ይሆናል የሚባለው።
_____________________________________________

                 የግጥም ነገር ከተነሳ!
                      አበረ አያሌው


          ግጥም የሚል ቃል ሲጠራ አእምሮዬ ውስጥ ቀድመው የሚሣሉ ሰዎች አሉ። በውቄ ቀዳሚው ነው።
በረከት በላይነህ፣ ኑረዲን፣ ፀጋዬ፣ እና ሙሉጌታም እንዲሁ ግጥም ሲነሳ ጭንቅላቴ ላይ የሚመጡ ናቸው።
ዮኒ ብዙ ጊዜ ጣል ያደርገዋል እንጂ (አንዳንዴ ግጥምን ይጨክንበታል እንጂ) በዚኹ ልክ ግጥም ሲባል የሚመጣልኝ ሰው ነው። ይህን የሰሞኑን ግጥሙን ስንቴ እንዳነበብኩት!

ማመንታት ምንድነው?
ሄድ ብሎ መለስ
ከነባር ምንጭ ላይ አዲስ መከላለስ
ወንዞች ይዘልቃሉ፣
ውሆች ይደርሳሉ፣
በረዶም ያው ቁልቁል መሬት ይደልቃል
የዝናብ ነጠብጣብ
እንደ መሲህ ወርዶ
አዲስ ሰው፣
አዲስ ዛፍ፣ አዲስ ሰው ያመጥቃል።
ዛፉ ተቀልብሶ፣
ቁልቁል አያዘግምም፤
ዝናብ ተመልሶ፣
ዳመናን አይመስልም።
መሲህ ሳይገለጥ፣
ቀን አይቆጥርም ለርገት፤
የምን መዋለል ነው?
የምን መንገታገት።
ምሉዕ ነው ተፈጥሮ፣
ልክ እንደ ጨረቃ፤
ግማሽ ውበት ሰፍሮ
እይ አይልም በቃ።
ሁለንተና ዙሪያው አያምኑም በንጥል’ጥል
አምነህ፣ ፀንተህ ተነስ፣ ተስፋን ይዘህ ቀጥል።

_____________________________________

                          ነጮች በጥቁሮች ምህረት ስር ያደሩባት ኢትዮጵያ

           በአዲስ አበባ ሲደርሱ እያንዳንዱ ምርኮኛ ለባላደራ ቤተሰብ ተመደበ፡፡ ከከተማ ውጭ ቢወጡ የመትረፍ እድል እንደሌላቸው በመረዳትም ከተማ ውስጥ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ተፈቀደላቸው። የሚፈልጉት አይነት ባይሆንም ምግብና የኪስ ገንዘብ ሳይቀር ይሰጣቸው ነበር፡፡ ኋላ ላይም ከጣሊያን መንግስት ጋር ስምምነት ተደርጎ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ፣ ምርኮኞች “የደግነት ትዝታዎች” በሚል ርዕስ በአሳዳሪዎቻቸው የተደረገላቸውን ቅን መስተንግዶ ፅፈዋል፡፡
አንድ ምርኮኛ በወቅቱ በአንድ ገበያ የወደቀ ጓዱ መፅሄት ለሽያጭ ቀርቦ አገኘው። መጽሄቱን ለመግዛት ባለመቻሉም አሳዳሪው አቶ ገብርኤል ገዙለት፡፡ በኋላ ላይ ምርኮኛው ፍራንሲስኮ ፍሪሲና በምላሹ ለአቶ ገብርኤል ሳሙና፣ የታሸገ ፍራፍሬ፣ ሲጋራና መጠጥ ልኮላቸዋል፡፡ “እንደ አባት” ለተንከባከበው አሳዳሪው ብድሩን በሚገባ መመለስ እንደማይችል፣ አቶ ገብርኤል እስከ ዘለዓለሙ ከልቡ እንደማይፋቅም ተናግሮ ነበር፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከጣሊያኖች ጋር ጥብቅ ወዳጆችም ሆነዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ተፈቃሪ፡፡
“ይህ ክስተት የዘር ትርክት አቅጣጫ የታጠፈበትና ብዙ ነጮች በጥቁሮች ምህረት ስር ያደሩበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ሆነ። ሁኔታው ለቂም በቀል የተመቸ ቢሆንም፣ እንደዚያ አይነት ነገር አልደረሰባቸውም፣” ይላል ጆናስ በፅሁፉ፡፡ በጉዞው መጨረሻ ላይ የተፈጸመው ይህ ወዳጅነትና ፍቅር፣ ቀደም ሲል የተፈጸሙ በደሎችን የሚያስረሳ ነበር፡፡
በዲፕሎማሲ ደረጃም ምኒሊክ ከጣሊያን ጋር ይፋዊ ስምምነት ላይ መድረስ ቻለ፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 23 1896 አዲስ አበባ ላይ በተፈረመው የአዲስ አበባው ውል መሰረት፣ ጄኔራል ማቲዮ አልበርቶኒን ጨምሮ ሁሉም ምርኮኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የውጫሌ ውል ከዚያ በኋላ ውድቅ ስለመሆኑ ሁለቱ ጉልበታቸውን የተፈታተሹ ሀገራት ተስማሙ፡፡ ዋናው ነገር ደግሞ፣ ጣሊያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ግዛታዊ ነፃነት ፍጹም የሆነ እውቅና እንደምትሰጥ ሳትወድ በግድ ተናዘዘች፡፡
ኢትዮጵያ ለነፃነቷ ያላትን ክብር በድጋሚ አሳየች፡፡ አንድ ዝነኛ ጸሃፊ እንደመሰከረው፤ “በአለም ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ ለረጅም አመታት በነፃነት የቆየች ብቸኛዋ ክርስቲያናዊ ሀገር ናት፡፡” ብሏል።

____________________________________________

                    ዘይት እና ዳቦ
                        ዘከሪያ መሃመድ


           ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ እያንዳንዳቸው ከ4.5 ቢሊዮን እስከ 5 ቢሊዮን ብር ወጥቶባቸዋል የተባለላቸው ሦስት ወይም አራት ግዙፋን የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካዎች ተገንብተው ሲመረቁ (“ሪባን ሲቆረጥ”) ብናይም፣ የእነዚህ ፋብሪካዎች “የማምረት አቅምም የሀገሪቱን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ የሚያረካና ዋጋንም የሚያረጋጋ ነው” ተብሎ ቢነገረንም፣ … እነኾ #ዛሬ ከውጭ የገባ 5 ሊትር ዘይት ከብር 700.00 እስከ ብር 720.00 እየሸመትን ነው። በሀገር ውስጥ የሚመረተውም ቢኾን ዋጋው ከዚያ የራቀ አይደለም። “ምክንያቱስ?” ስንል “ያው ግብዓቱ (ድፍድፉ) ከውጭ ሀገር ነው የሚገባው” ይሉናል። …
የዘይት ፋብሪካዎቹ ግንባታና ማሽን ተከላ ሲከናወን በትንሹ አራትና አምስት ዓመታት አስቆጥሯል። ይህ ሁሉ ሲኾን፣ ማሽኑ ዘይት የሚተፋ ይመስል፣ [የቅባት እህል በሚያመርት ሀገር ውስጥ እያሉ] ለግብዓት የሚውለውን የቅባት እህል ስለማምረት ሳያስቡበት ኑረው ድፍድፍ ከውጭ ሀገር በዶላር በመገዛቱ፣ ፋብሪካዎቹ ወደ ሥራ ገብተዋል ከተባሉ በኋላም፣ በአቅርቦትም ኾነ በዋጋ ረገድ፣ ነገሮች ሲብሱ እንጂ ሲሻሻሉ አልታየም። …
በዚህ ሂደት ግን፣ ጥቂት የማይባሉ አነስተኛና መካከለኛ የዘይት አምራቾች ለወትሮው የምርት ግብዓት የሚሸምቱበት ሂደት በመዛባቱ፣ [በዋነኛነት የአኩሪ አተር ግብይት በምርት ገበያ (ECX) በኩል ብቻ በመደረጉ] በግብዓት እጦት ሥራ ለማቆምና አልፎም ለመዘጋት የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ ረገድ፣ የዚህ ሀገር የኢኮኖሚ አስተዳደር ቅጥ አምባሩ እየጠፋ ያለ ይመስላል።
በዘይቱ ላይ ያለው ችግር፣ በዳቦውም ላይ ይታያል። በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤትና በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ትብብር፣ በመላ ሀገሪቱ ከ10 በላይ እያንዳንዳቸው 80 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የዳቦና የዱቄት ፋብሪካዎች (በጠቅላላው በ800 ሚሊዮን ብር) በመገንባት ላይ ናቸው። የአዲስ አበባው እንዲያውም ግንባታው አልቆና ተመርቆ (“ሪባን ተቆርጦለት”)፣ ለአዲስ አበባ መስተዳድር ርክክቡ ተፈጽሟል - በጥቅምት 2014። ነገር ግን፣ እስካሁን ሥራ አልጀመረም። ዳቦ ኢንጂሩ፤ ዱቄት ኢንጂሩ። ማሽኑ ዳቦ አይተፋም!! አሁንም ስለ ግብዓት ሲወራ፣ ስንዴ ከውጭ ሀገር በዶላር ስለማስመጣት እየታሰበ ያለ ይመስላል። …
እርግጥ በሲዳማና በሌሎችም ክልሎች ስለሚካሄዱ የበጋ የመስኖ ስንዴ እርሻ ሥራዎች ሰምተናል። … እሰየው ነው። እነዚህን ነገሮች #የምር_አጥብቆ_መያዝ ያስፈልጋል። የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ሀብትንም እነርሱ ላይ በማፍሰስ፣ የዳቦና የዘይት ጥያቄን መመለስ የመንግሥት #ቀዳሚ_ሥራ መኾን አለበት። የሌሎችንም መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ምርት ማሳደግ የሚያስችል ፖሊሲ ቀርፆ ሥራ ላይ ማዋል የመንግሥት ግዴታ ነው። …

________________________________________________


                     ("የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግስተ ሳባ እስከ አዲስ አበባ" መጽሐፍ ላይ የተወሰደ)

                           ከምሉዕነቱ ይጎድል ዘንድ ከፍታው አይፈቅድለትም!
                               መላኩ አላምረው


          የማንችለው ላይ አንድከም! የዓድዋ ድል “የተንሸዋረረ ትርክት በፈጠረው የፖለቲካ ሴራ” ከምሉዕነቱ ይጎድል ዘንድ ከፍታው አይፈቅድለትም።
መግቢያ:-
በዚህች የዓድዋ መታሰቢያ ዕለት እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያን መላው አፍሪካና ሌላውም ጥቁር ዓለም ፈገግ ብሎ መዋል ይገባዋል:: ክብር ለአባቶቻችን ይኹንና እኛን በድል ጥቁር ዓለምን በነፃነት መንፈስ ያቆሙን በዚህች ዕለት ነበር:: ሕይወት ገብረው የቅኝ ገዥን መንፈስ ሰብረው የሰጡንን ዕድል የበለጠ አስተዋውቀን የዓለም ትልቁ ኩነት/በዓል ማድረግም ይቻለናል::
እኛ ኢትዮጵያውያን ሀዘንና መከፋት የሚገባን አልነበርንም:: እንኳን ለራሳችን ለሌላው ሀገርና ለጥቁር ዓለም በነፃነት ክብር ቆሞ በደስታ የመኖርን መንገድ የጠረግን ኾነን እያለ፣ እርስ በርስ በምንፈጥረው መገፋፋት ሁልጊዜ አጀንዳ መፍጠርና በራሳችን ላይ ሀዘንን ማምጣት ምን የሚሉት መርገምት እንደኾነ እንጃ:: የኹላችንም አባቶች ዘምተው ሞተው ያስገኙት ድል ነው የምንለውን ዐድዋን እንኳን የጋራ የደስታ ቀን ማድረግ ያልቻልነው እንዴት ብንረገም ነው? ዐድዋን የጋራ ማድረግ ካልቻልንስ ሌላ ምን ማድረግ እንችላለን? እንጃ:: በምኒልክ ዘመን የተፈጠሩ ስህተቶችን  (ወታደሩም ፈፀመው ወዝአደሩ) ዕዳውን ምኒልክ ይሸከም የሚል ፖለቲከኛም ኾነ ነፃ አውጭ ነኝ ባይስ በዓድዋ ድል ዕለት የንጉሠ ነገሥቱ ስም አይጠራ፣ ከሐውልቱም ራቁ ሲል በምን አመክንዮ/ሎጂክ ይኾን? ደግነቱ የሚሰማው የለም::
ሀ ተ ታ:-
(፩) ዓድዋን ያለ ዳግማዊ ምኒልክ ለመዘከር ማሰብ ወይም የድሉን ዘመቻ መሪና አዋጅ ነጋሪ ንጉሥ ስም ትቶ የጦር ሜዳውን ብቻ ለመጥራት መሞከር ድሉን ጎደሎ ብቻ ሳይሆን ያልነበረ ባዶ ያደርገዋል። ዓድዋን ያለ ምኒልክ ማሰብ የእስራኤላውያንን ባሕር የመሻገር ተዓምር ያለ ሙሴ እንደማሰብ ነው። የጦርነት ትዕዛዝ ሰጭውን ትቶ የጦር አዝማቾችን፣ አዝማቾችን ረስቶ ዘማቾችን ማሰብ የሥርዓተ መንግሥትንና የጦር አመራር ስልትን ያለመረዳት የዕውቀት/የግንዛቤ ክፍተትን ማሳያም ነው። ያን ጊዜ ጀግኖች ትዕዛዙን አክብረው ጦራቸውን ከየአቅጣጫው ያዘመቱለትን፣ ሕዝቡ አዋጁን ሰምቶ የዘመተለትን ንጉሥ እኛ ዛሬ ላይ ቁጭ ብለን ባልዋንበት ሜዳ የመፈረጅ ሥራን እንሠራ ዘንድ መብቱም የለንም፤ ተፈጥሮም አይፈቅድልንም።
*ዓድዋን ምኒልክ አልመራውም ማለት ሲጀመር ጦርነቱ አልታወጀም፤ አልተካሄደም፤ ድሉም የለም እንደማለት ነው።*
 (፪) ዓድዋን በእኛ ጥበት ልክ ልናጠበው፣ በዝቅታችን ልክም ልናወርደው ብንሞክር፣ የእኛን ታናሽነት ከመግለጥ ውጭ ሌላ ውጤት አይኖረውም። የዓድዋ ድልን እስከ ሙሉ ክብሩ ካላከበርን፣ ድሉን ከንጉሡ ከለየነው፣ በንጉሣቸው ስር በፍቅርና በአንድነት ለነፃነት የተዋደቁትን ጀግኖች የጦር አዝማቾችን ከረሳን ድሉን ሳይሆን ራሳችንን እናኮስሳለን። መስዋዕትነቱን ሳይሆን መንፈሳችንን እናረክሰዋለን።
ዓድዋ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ መሪነት፣ በእቴጌ ጣይቱ ብልህነት የተሞላበት ምክር፤ በእነ አሉላ አባነጋ፣ ንጉሥ ሚካኤል፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ባልቻ ሳፎ... ሌሎችም ለቁጥር የሚያታክቱ ጀግኖች ጦር አዝማችነት፣ በአዝማሪዎች ሞራል ሰጭነት፣ በሴቶች ጀግንነት የተሞላበት ዘመቻና ሃኪምነት፣ በአባቶችና እናቶች ጸሎት... በተባበረ ክንድ የተገኘ ሕያው ድል ነው። ለዓድዋ አይደለም ኢትዮጵያዊ ሰው እንስሳትም ዘምተዋል። ፈረሶች ፈረሰኞቻቸውን ይዘው ተዋግተዋል። አጋሰሶች፣ በቅሎዎች፣ አህዮች ስንቅ ተሸክመዋል። ለዓድዋ ድል ነፍስ ያለው ብቻ ሳይሆን ግዑዛን ተራሮች፣ ድንጋዮች፣ ገደላገደሉ ሁሉ ተባብረዋል። ከዚህ ውጭ ያለው ከፋፋይ እይታና የፈጠራ ተረት የተራቹን ጎደሎነት ያሳያል እንጅ ዓድዋን ከምሉዕነት አያጎድለውም።
*እኛ ዓድዋን ስንተርክ የምኒልክን ስም ብናስወጣው ምኒልክን ከዓድዋ ጦርነት መሪነት አያስቀረውም፤ ምክንያቱም ድሉ እኛ ልንቆጣጠረው በማንችል ባልነበርንበት ዘመን የተካሄደና ሕያው ታሪክ የዘገበው ነውና የእኛን ምስክርነትም ፈቃድም አይጠይቅምና።*
(፫) የዓድዋ ድልን “የየትኛውም ብሔር ብቻ” ለማድረግ መጣር አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን ግብዝነትም ነው። ድርሻው ይብዛም ይነስም ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘምቷል። ለዓድዋ ጦርነት ያልዘመተ ብሔረሰብም ሆነ ሕዝብ የለም። ባካል ያልዘመቱ ሽማግሎችና አቅመ ደካሞች እንኳን በንጉሥ ምኒልክ “በጸሎት አግዙኝ” በተባሉት መሠረት በጸሎታቸው ተዋግተዋል። የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ዓድዋ ዘምቶ ነው ድሉ የመጣው። ከዚህ ውጭ ያለው አረዳድም ሆነ አገላለጽ ለዓድዋ አይመጥንም።
በአንድ በኩል የመላው አፍሪካና የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ድል ነው እያልን በሌላ በኩል ወደ ብሔር አውርዶ #የእኛ ነው የእኛ ነው ዘመቻ; የለየለት ዕብደት ነው። መጠኑ ቢለያይም ሁሉም መስዋዕት ሆኗል። የሁሉም ድምር ውጤት ነው። ደግሞም አባቶቻችን የንጉሣቸውን ጥሪ አክብረው የዘመቱት በያኔው ስሜት ለኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነት ነው እንጅ ዛሬ እኛ በተከፋፈልንበት አግባብ ለብሔራቸው አይደለም። የዛሬው አልበቃን ብሎ እኛ ወዳልነበርንበት ዘመን ሄደን፣ ጀግኖችን ከመቃብር እየቀሰቀስን በብሔር የመደልደል ሥራ ውስጥ መግባት፣ የእኛን የዝቅጠት ጥግ ያሳያል እንጅ እነርሱን ከኢትዮጵያዊነት ወደየትም አይወስዳቸውም።
*እኛ በዓድዋ ላይ ያለን ብቸኛ መብት ከቻልን ድሉን አክብረን በክብርና በኩራት መቆም እንጅ ጦርነቱን የመሰረዝም ሆነ ድሉን የማንኳሰስ ወይም የድሉን ባለቤቶች በብሔር የመደልደል ወይም ንጉሡን ከጦር ሜዳው የማስወጣት መብቱም ዕድሉም የለንም። ባልኖርንበት ዘመንና ባልተሳተፍንበት ጦርነት የመፈትፈት ሥልጣኑን እናገኝ ዘንድ ተፈጥሮም አይፈቅድልንም።*
(፬) በዓድዋ ድል የተሸነፈው የቅኝ ገዥነት መንፈስ ነው። ያሸነፈው ነፃነት ነው። የተሸነፈው የነጮች የተንሸዋረረ ሰውን ከሰው ሀገርን ከሀገር የማበላለጥ የባርነትና የጌታነት እይታ ነው። ያሸነፈው እኩልነትና በራስ መተማመን ነው። የተሸነፈችው ጣልያን ናት። ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት። የዓድዋን ድል ማጣጣልም ሆነ ለማኮሰስ ወይም ከፍሎ ለማየት መሞከር ለቅኝ ግዛት፣ ለባርነት፣ ለጣልያን... ጥብቅና እንደመቆም ነው። ጣልያን ለምን ተሸነፈች ብሎ በጸጸት የመኖር የባንዳነትን መንፈስ የመውረስ ምልክት ነው።
*የዓድዋ ጦርነት በተካሄደበት በምኒልክ ዘመን ያልነበረን ሐሳብ አሁን እየፈጠሩ ማውራትና ምኒልክን የተበቀልን እየመሰለን በጥላቻ መዝመትም ሆነ ንጉሡን ከድሉ ለመለየት መሞከር የለየለት የበታችነት ስሜት ማሳያ ምልክት ነው።*
 (፭) ምኒልክ የመሪነት የውኃ ልክ ነው።
ጦርነትን መምራትና ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከድል በኋላ ምርኮኞችን ይቅር ማለትን፣ ቁስለኞችን ማከምን ያሳየን መሪ ነው። እንኳን ወዳጆቹ ሊወጉት የሸፈቱበት ጠላቶቹም ጭምር ተባብረው የዘመቱለት ምኒልክ ነው። ከፍ ባለ የራስ መተማመን መንፈስ የሚመራውን ሕዝብ በየጦር መሪው አደራጅቶ በማዝመት ነጭን በጥቁር እጅ ያንበረከከ ብቸኛው ጥቁር ንጉሥ ምኒልክ ነው። ይህ የማይቀየር የማይሻሻል ሐቅ ነው።
*ኢትዮጵያ የዓድዋን ድል ባስመዘገበችበት ዘመን ንጉሠ ነገሥቱ ምኒልክ ነበር፤ የዓድዋ ድል የመጣው ምኒልክ ያወጀውን አዋጅ “የንጉሣችን አዋጅ ነው” ብሎ ሰምቶ፣ የንጉሡን ቃል አክብሮ እምነትና ዘር ሳይገድበው በየተሰማራበት የጦር መሪ ስር ተደራጅቶ በዘመተው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጀግንነት የተመዘገበ ነው፤ የሁሉም የጦር መሪዎች አዛዥ ደግሞ ንጉሡ ምኒልክ ነበር። ይህ ሐቅ ቢጥመንም ቢመረንም ምንም ማድረግ አይቻልም።*
መደምደሚያ!
የዓድዋ ድል “የተንሸዋረረ ትርክት በፈጠረው የፖለቲካ ሴራ” ከምሉዕነቱ ይጎድል ዘንድ ከፍታው አይፈቅድለትም። ዓድዋ ከፍ ባሉ ልቦች ታስቦ ከፍ ባሉ ጭንቅላቶች በጥበብና በልዩ ልዩ ስልቶች ተመርቶ በአመራር ብቃት የመጣ እንጅ በግርግር የተገኘ ድል አይደለም:: የያኔውን የአባቶቻችንን አንድነትና ሕብረት የአመራርና የአደረጃጀት ጥበብና መገነዛዘብ ለመረዳት ከቆምንበት ጫማ መውጣት ያስፈልጋል:: ዓድዋን ከፍ አድርገው የሰቀሉት ከፍ ያሉ እጆች እንጅ እኛን መሳይ ድኩማን አይደሉም:: እናም የማንችለው ላይ አንድከም:: የዓድዋን ክብርም ኾነ የመሪዎችን የእነ ምኒልክን ዝና ማውረድ አይቻለንም:: የሚቻለን ይህንን ግሩም ዕድል መጠቀምና ሕዝብን አንድ ማድረግ ለማድረግ እነርሱ ይጠቀሙት የነበረን ስልትና ጥበብ አጥንቶ መተግበር ነው:: ይህንንም ካልቻልን ዝም እንበል:: ሲጀመር በዓሉ የሕዝብ እንጅ የፖለቲከኞች ስላልኾነ ኹሉንም ካልፈተፈትን አንበል:: አርፎ መቀመጥም  ወግ ነው::


________________________________________________


                   አንዳንድ ነገሮች.....
                     ኤርሚያስ በጋሻው ገሰሰ


           የአገሩን መሪ አምባገነን ነው ብሎ እየከሰሰ ሲያልፍም እያንጓጠጠ ይውላል፤ ዞር ይልና እልል ያለ የሩሲያ አምባገነን መሪን አፈቅራለሁ ይላል። (የአገርህን የጠላኸው በምትፈልገው ልክ አምባገነን ስላልሆነልህ ነው?!)
ስለ ሰው ልጆች ነጻነት የተከፈለ የገዘፈ ዋጋ በሚታሰብበት የዓድዋ በዓል ላይ የሩሲያን ባንዲራ ይዞ ይወጣል። በጦርነት ህዝብ እየቆላ የከረመ፣ ሶቪየት ህብረትን የመመለስ ቅዠት ያለበት መሪ ተግባር እኮ ልታከብር ከወጣኸው በዓል መንፈስ ጋር አይስማማም። (ነው ሩሲያ ዳግማዊ ምኒልክን በመሳሪያ አቅርቦት መደገፏን አንብበህ ነው ?!) ዘመኑም አላማውም ለየቅል ነው ጌታዬ።
*ይህ የሚመር የግርንቢጥ ሁነቶች መገኛዋ አገራችን እውነት ነው። ኢትዮጵያውያን የጣልያን ቅኝ ገዢን ድል ያደረግንበትን የአድዋን ድል በምናከብርበት ስፍራ ጉዳይ እየተቋሰልን በዋልንበት ቀን፣ ገንዘብ ሚኒስትራችን ከጣልያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር የአንድ ሚሊየን ዩሮ እርዳታ እየተፈራረሙ ነበር። ( ምነው ጋሽ አህመድ ከቻሉ ቀኑን ገፋ ቢያደርጉት፤ ካልቻሉ ዜና ባያሰሩት?!)
*ያሬድ ሹመቴን አንዳንድ ፈታላዎች ‘ምኒልክ ዛሬም ቢዝነስ ነው’ እያሉ ስሙን ሊያጠለሹ ቢሞክሩም፣ እኔ ግን አድዋን ከአድዋ ርቀን ማክበራችን እንደሚሰማው ሲናገር ስለሰማሁ ላደንቀው ተገድጃለሁ። አድዋ ላይ መስዋዕትነት ከፍለው አጽማቸው ስለተቀበረ ቀደምቶቻችን ስናስብ፣ አድዋ ላይ እትብታቸው ስለተቀበረ የዛሬ ሰዎችም እናስብ ነበር ያለው ያሬድ። (አገሩን ሰላም አድርጎት ከሶሎዳ ተራራ ስር ለማክበር ያብቃን። ለምን ካልከኝ አድዋ የአንድነት ቋንቋ ስለሆነ!)

Read 1186 times