Saturday, 29 September 2012 09:31

የመስቀል ደመራ በዓልና ቱሪዝም

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekle@gmail.com)
Rate this item
(2 votes)

አቡነ ጳውሎስ በመጨረሻ የሕይወት ዘመናቸው ከነበሯቸው ዕቅዶች መካከል የመስቀል ደመራ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረት ማድጋቸው ነው፡፡ ይህ ፓትርያርኩ  ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ከጣሉአቸው ምሰሶዎች እንደ አንዱ ይቆጠራል፡፡ የአሁኑ አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ይህንኑ አስመልክተው ባለፈው ረቡዕ በመስቀል አደባባይ ለበዓሉ ለተሰበሰበው ሕዝብ ሲናገሩ፤ “በዓሉ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መንፈሳዊ በዓል ቢሆንም ብሔራዊ በዓልና ዓለም አቀፍ እውቅና እያገኘ የመጣ በመሆኑ አገራችን ከዚህ በዓል ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን ትችል ዘንድ ቀደም ሲል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ የመስቀል በዓል በተባበሩት መንግስታት የባህልና ትምህርት ድርጅት ዘንድ እውቅና ተሰጥቶት በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የጀመሩት ጥረት ከግብ እንዲደርስ ሁላችንም እንረባረብ፡፡” ብለዋል፡፡

አቡነ ናትናዔል እንዳሉት ሁሉም አካላት ቢረባረቡ፣ የመስቀል በዓል በዓለም ቅርስነት ቢመዘገብ የጎብኚዎች ቁጥር በመጨመር ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ የትየለሌ በሆነ ነበር፡፡ይህ እንዲደረግ መንግስትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ትልቅ ድርሻ ቢኖራቸውም ኃላፊነቱ የእነሱ ብቻ እንዳልሆነ የበዓሉ ታዳሚዎች ይናገራሉ፡፡የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ሊቀጳጳስ እና የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ በዚህ ይስማማሉ፡፡ ሊቀጳጳስ ከመሆናቸው በፊትና በኋላ ለረዥም አመታት የመስቀል ደመራ በዓልን በመስቀል አደባባይና በሌሎች ስፍራዎች ታድመዋል፡፡ ይህን ኃላፊነት ቤተክርስትያናቸውና ብፁዕነታቸው እንደሚሸከሙ ከታሪክ በማጣቀስ “የመስቀል አደባባዩ በብሔራዊ ደረጃ ስለሚከበር ልዩ ስሜት ይሰጠናል፡፡ ሀገር ውስጥ ካለሁ ሁልጊዜ እመጣለሁ፡፡ እንደተባለው በዓሉ የኢትዮጵያ ብቻ መሆን የለበትም፤ የአፍሪካም የዓለም ቅርስ መሆን አለበት፡፡

“ለመስቀል በዚህ መልኩ መከበር ጉልህ ድርሻ ያላቸው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እና እናቱ ንግሥት እሌኒ ሲነሱ፣ የጴጥሮስ መንበር ሮም ትነሳለች፡፡ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ታላቅ አክብሮትና የእህትማማች መንፈስ ታሳያለች፡፡ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊና ቤኔዲክቶስ 16ኛ፣ አቡነ ጳውሎስን ጋብዘው በብዙ ጉዳዮች ተነጋግረው ነበር፡፡ አሁንም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ያላትን እምነትና ቅርስ ጠብቃ ብዙ ካቶሊኮች እንዲጎበኙት ለማድረግ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን መንገዱን ታመቻቻለች፡፡ እዚህ መስቀል አደባባይ ስመጣ ለዓለም አቀፍ ስብሰባ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ 40 ያህል ካቶሊካውያን አብረውኝ መጥተዋል፡፡

በሄዱበት ቦታ ሁሉ የዚህ ቅርስ አምባሳደሮች ነው የሚሆኑት፡፡ ለዚህም ነው በዓሉን እንዲታደሙ ፈቃድ የጠየቅነው” ብለዋል፡፡

ለአለምአቀፍ ስብሰባ የመጣው ነዋሪነቱን በናይሮቢ ኬንያ ያደረገው ኮንጎአዊው ጆን ካቱንጋ፤ በስብሰባ አጋጣሚ ነው የመስቀል በዓልን (ደመራ) ያየው፡፡ በሀገሩ እንዲህ ዓይነት በዓላት እንደሌሉና እዚህ አገር የትንሣኤና የገና በዓል አከባበር ይበልጥ እንደመሰጠው ጠቅሶ ይህንንም ናይሮቢ እና ኪንሻሳ ላሉ ጓደኞቹ እንደሚነግር ገልጿል፡፡

አዲሱ የካናዳ አምባሳደር ዴቪዲ አሸር፣ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ዕለት መስቀልን በማየታቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸውና ጥሩ አቀባበል እንደተደረገላቸው አውስተው “ምን ያህል እንደተደሰትኩ ማየት ትችላለህ” ብለዋል፡፡ ገና የሹመት ደብዳቤአቸውን ለፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ያላቀረቡት አምባሳደሩ፤ በመስቀል ደመራ በጣም በርካታ ሕዝብ በስርዓት መታደሙ አከባበሩን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸው፤ ያነሷቸውን ፎቶግራፎች ለቤተሰቦቻቸው እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል፡፡ አዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄስ ክሪስቶሞስ፤ በአገራቸው ገናን፣ ጥምቀትንና ትንሣኤን እንደሚያከብሩና መስቀልን በዚህ መልኩ እንደማያከብሩ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሕንዳዊው ባርሜንደር ብራር፤ ብዙ ሀይማቶች ያሏት ሀገራቸው ብዙ ትዕይንቶች እንደምታስተናግድ ተናግሯል፡፡

“በጋንጀስ ወንዝ ላይ ኩምባላ የሚባል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉበት በዓል አለ፤ በየዓመቱ ግን አይደለም፡፡ መስቀል ባህሉና ሐይማኖታዊ ስርዓቱ እንዲሁም አጠቃላይ ድባቡ፣ ቦታው እና የጧፍ መብራቱም ይለዩታል” ብለዋል፡፡ ይህን ልዩነት በዶክመንታሪ ፊልም ለማስቀረት የሚታትሩት “የሄሪቴጅ ኢትዮጵያ” ባለሙያዎች የመስቀል በዓልን ያካተተ ፊልማቸው ከሁለት ሳምንት በኋላ በኢትዮጵያ ለዕይታ እንደሚበቃ ተናግረዋል፡፡ ባለሙያዎቹ ከእንግሊዝ ነው የመጡት፡፡

ከአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የመጣው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቴዎድሮስ ኪዳኑ “መስቀል እንዳገሩ ይከበራል፡፡ እንደዚህ ባይደምቅም ችቦ በትንሹ ይኖራል፤ የእሳት አደጋ እንዳይኖር ስለሚሰጉ፡፡ የመስቀልን መገኘት አስመልክቶ እስራኤልን ጨምሮ የትም እንዲህ አይከበርም፤ ኢትዮጵያ ብሉይንም ሐዲስንም አጣምራለች፡፡” ብሏል፡፡ ከዚያው ከአሜሪካ ኒውዮርክ የመጣው ዴቪድ እና ባለቤቱ ለቅርሳቅርስ ግዢ እና ለአውሮፕላን የወጣውን ሳይጨምር በቀን ሁለት ሺህ ዶላር ለእያንዳንዳቸው ቢያወጡም ውድ እንደማይባል ተናግሯል፡፡ ፈረንሳዊቷ ሊዮ፣ ስድስት ጓደኞቿን ለጉብኝት ኢትዮጵያ ይዛ ስትመጣ ሆን ብላ መስቀልን የጉብኝቷ አካል አድርጋለች፡፡ ደመራው ተለኩሶ ከወደቀ በኋላ የደረሰው ፊሊፒናዊ ቱሪስት፤ ተቆጭቶ ለከርሞ ለመምጣት አልሟል፡፡

መስቀል ልዩ ነው ያለችው ጀርመናዊቷ ኬስተን፤ መንፈሳዊ መሆኑና ብዙ ሕዝብ መታደሙ ነው ልዩነቱ ትላለች፡፡ “ለጓደኞቼ ቆንጆ በዓል መሆኑን እነግራቸዋለሁ፡፡ ለሥራ ብመጣም አጋጣሚው ሰመረልኝ፡፡ ጓደኞቼ መጥተው መጐብኘት አለባቸው፡፡ ያነሳሁአቸውን ፎቶዎች ሲያዩ መቋመጣቸው አይቀርም” ብላለች፡፡

ሌላው በሕንፃ ኮሌጅ አርኪቴክቸር ሊያስተምር የመጣ ጀርመናዊ በበኩሉ፤ “እንዲህ እንደ መስቀል ብዙ ሰው ሲሰበሰብ ያየሁት ለሙዚቃ ብቻ ነው፤ በጣም ብዙ ሕዝብ በአንድነት በመምጣት ደመራው በችቦ ሲለኮስ ማየት ያስደስታል፡፡ ሆኖም በዓሉ በደንብ ባለመተዋወቁ  ጀርመን እያለሁ ስለመስቀል ሰምቼ አላውቅም፡፡ አዲስ አበባ ያሉ ጓደኞቼ ነግረውኝ ነው የመጣሁት፡፡

መስቀል በእርግጥም በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ይገባዋል” ብሏል፡፡

ከፊንላንድ ለስብሰባ የመጣችው አካል ጉዳተኛ ማርያን፤ መስቀል አደባባይ የሄደችው በተሽከርካሪ ወንበሯ ነው፡፡ አስተያየቷን ስትጠየቅ “ከሩቅ ሀገር ነው የመጣሁት፣ ይኼን የሚመስል ባህል አይቼ አላውቅም፡፡

የቀሳውስቱ አለባበስ፣ መዘምራት … ሁሉም ልዩ ናቸው፡፡ በደንብ ባለመተዋወቁ ስለመስቀል ካሁን በፊት አላውቅም ነበር፡፡

እንደ መስቀል አምባሳደር ሆኜ “ኢትዮጵያ በመስከረም ከሄዳችሁ የመስቀል ደመራ በዓል እንዳያመልጣችሁ እላለሁ” ብላለች፡፡

ለኢትዮጵያ ከፊላንድ የበለጠ ሩቅ ከሆነችው ከአውስትራሊያ የመጣችው ማርያንና ባለቤቷ ጆን፤ መስቀል አደባባይ የተገኙት ነጭ በነጭ ለብሰውና ነጠላቸውን አጣፍተው ነው፡፡ ለምን ይህን እንዳደረጉ ማርያን ስትጠየቅ፤ አክብሮቷን ለመግለፅ መሆኑን ጠቅሳ በጉብኝታቸው የመስቀልን ደመራ በአል ማካተታቸውን ተናግራለች፡፡

የባለቤቷን ጨምሮ በቀን አራት ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር እያወጣች መሆኑንም ገልፃለች፡፡  “በአውስትራሊያ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የምናውቀው ጥቂት ነው፡፡ በብዙ ሕዝብ የደመቀ ሃይማኖታዊ በዓል የለንም፡፡ ይህን ያመቻቸልንን ድንቅነሽ ቱር እና ትራቭል እናመሰግናለን፡፡ ኢትዮጵያ ለመምጣት አንዱ ምርጥ አጋጣሚ መስቀል ነው፡፡

በዓለም ላይ ከሚገኙ ቱሪስቶች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የሐይማኖት ተጓዦች ናቸው፡፡ ንግሥት እሌኒ ራሷ መስቀሉን ከተቆፈረበት ያስወጣችው ከሮም ወደ ኢየሩሳሌም በቱሪስትነት ከተጓዘች በኋላ ነው፤ አላማዋ ሃይማኖታዊ ቢሆንም፡፡  የዘንድሮውን መስቀል አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያሳተመችው “በዓለ መስቀል በኢትዮጵያ” መፅሄት ጥምር ቋንቋ መፅሄት ነው፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ብቻ ተዘጋጅቷል፡፡ መስቀልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በዓሉንና ታሪኩን ስፓኞልና ፈረንሳይኛን በመሰሉ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ማዘጋጀትና በውጭ ሀገራት መበተን እንዲሁም ተጨማሪ የማስተዋወቅ ሥራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ በዚሁ መፅሔት ላይ “መስቀልና ቱሪዝም” የሚል ፅሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ እስክንድር ገብረክርስቶስ፤ ባለፉት አራት ዓመታት መስቀልን ጨምሮ ሌሎች የቤተክርስትያኒቱን መስህቦችና ቅርሶች ለመጐብኘት ከመጡ ቱሪስቶች 4 ቢሊዬን 266 ሚሊዬን ብር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ ይህ አሃዝ ቤተክርስትያኒቱ እያሰራች ያለችውን የአክሱምን ቤተመዘክር ጨምሮ አብያተ መዘክር ብታስገነባና መስቀልን የመሰሉ ቅርሶቿን በመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት የባህልና ሳይንስ ተቋም ብታስመዘግብ፣ ከዚህ ገቢ እጅግ በጣም እንደሚልቅ ያላቸውን ግምት የመምርያ ኃላፊው ነግረውናል፡፡

 

Read 3757 times Last modified on Saturday, 06 October 2012 15:12