Saturday, 05 March 2022 12:55

የመጀመሪያይቱ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(8 votes)

ሌሊቱ ቀኑን ሊተካ ተካልቦ፣ ጀምበሯ ወርቃማ ቡሉኮዋን ተከናንባ አድማሱ ላይ ተንሰራፍታለች፡፡ የተጎለትኩበት ባሕር ዳርቻ፣ ከዳር እስከ ዳር ጀምበሯ በምትፈነጥቀዉ ጮራ ተጥለቅልቋል። አካባቢዉ ላይ የሚገኘዉ ነገር ሁሉ ወርቃማ መልክን ይዞ የተፈጠረ ይመስላል። አሸዋዉ፣ አለቱ፣ ባሕሩ፣ ከርቀት የሚታዩት ጎብኝዎችን ጭነዉ ባሕሩ ላይ የሚያዘግሙት ትናንሽ ታንኳዎች፣ ጠጠሩ፣ ባሕሩ ደርዝ ላይ የተተከሉት የጎብኝዎች ድንኳኖች፣ ሳሩ፣ ድንጋዩ እና ባሕሩ አጠገብ የተገነቡት የጎብኝዎች ማረፊያ ቪላ ቤቶች በጅምላ አንድ መልክ ካለዉ ቁስ የተፈበረኩ ይመስላሉ፡፡
የተጎለትኩት ባሕሩ ዳርቻ ላይ በዉሃ የታጠበ የመሰለ ግዙፍ ግራጫ ቋጥኝ ላይ ነዉ፡፡ ፊት ለፊቴ የሥዕል መሳያ ሸራ ተገትሯል፡፡ ባሕሩ የሚተነፍሰዉ ቀዝቃዛ ነፋስ፣ ነፍስን በደስታ ለመኳል የሚያባብል ነዉ፡፡ ለረዥም ጊዜ ተቆራኝቶኝ የነበረዉ መንፈሴን ያጠለሸዉ ታላቅ ድባቴ፣ ባሕሩን የከበቡት ትላልቅ ዛፎች ላይ ሰፍረዉ በሚዘምሩት አእዋፍት ዝማሬ ተጠራርጎ ተወስዷል፡፡ አካባቢዉ በታላቅ ፀጥታ የተዋጠ ነዉ፡፡ በጆሮዬ የሚሰርገዉ ድምፅ፣ ባሕሩ መሐል ጉብ ያለዉ ግዙፍ አለት በማዕበል ሲገጭ የሚፈጠረዉ ድምፅና የአእዋፍቱ ዝማሬ ብቻ ነዉ፡፡ እዚህ ቦታ፣ ፍጥረታት እርስ በእርስ  የተጋመዱበት ድር እጅግ ጠንካራ ነዉ፡፡ የእዚህ ሥፍራ ኩነት፣ የምልዓተ-ዓለሙን ዑደት ዉል ያረቀዋል፡፡    
ሁሌም እዚህ ሥፍራ ስመጣ የምትታወሰኝ ሐመልማል ናት፡፡ ዉቧ ሐመልማል፣ ፅልመትን የገሠሠች ብርሃን፡፡ መልካሟ ሐመልማል፣ ፍቅርን የምትዘክር ድርሳን፡፡ ምን ዋጋ አለዉ፣ ፈፅሞ ባልተጠበቀ ክስተት እንደ ሸክላ ተሰበረች፡፡ ወትሮም ሰዉ ከትቢያ የሚልቅ ዋጋ የለዉም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ይኸን ቦታ የረገጥኩት ከእሷ ጋር ነዉ፡፡ ታዲያ፣ እዚህ ስንመጣ ሁሌም የምንቀመጠዉ እዚህ ፊት ለፊቴ የተገተረዉ ግዙፍ ሾላ ሥር ነዉ፡፡ የዛፉ ግርማ የወትሮዉ አይደለም፤ በእርጅና ይሁን በሌላ ቅጠሎቹ ረግፈዉ ረዣዥም ቅርንጫፎቹ ርቃናቸዉን ቀርተዋል፡፡
የወትሮ የሥራ መንፈሴ ከድቶኝ እንደ ትቢያ በኖ ቢሰወርም፤ አሁንም በቀዘቀዘ ሞራልም ቢሆን በአእምሮዬ የሚንገዋለለዉን ፋይዳ ቢስ የሐሳብ ናዳ ሸራ ላይ ለመዘርገፍ መፍጨርጨሬ አልቀረም፡፡ ይኸ ልማድ (ሠዓሊነት) የተጣባኝ አፍላ ወጣት ሳለሁ ነዉ፡፡ ያኔ፣ ይኸ የሰርክ ተግባሬ አሰልቺነት ያልነበረዉ፣ ለነፍሴ ሐሴት የሚፈጥር ታላቅ ተግባር ነበር፡፡ ዛሬስ? ዛሬ፣ ዘወትር ነፍሱን በፀፀት ካራ የሚገዘግዝ ሰዉ ነኝ፤ ከራሴ ጋር የፈጠርኩትን ቁርሾ መፍታት የሚችል ሰበብ ማበጀት ያቃተኝ፡፡ በፍግምግም የፈበረኩት ሰበብም በወንጀለኝነት ጅራፍ ከመተልተል አልታደገኝም፡፡ ማምለጫ የለም፡፡
ሐመልማል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የብቸኝነት ቅጥሬን አፍርሳ ልቤ ዘዉ ያለች ሴት ናት። እኔ ግን፣ ዕድል ፈንታ የሸለመኝን ፍርቱና በወጉ መያዙን ችላ አልኩ፡፡ እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል በሚል ብሂል ተታለልኩ። በገፍ በተቀበልኩት ፍቅር ፈንታ ወረትን አለመለምኩ፡፡ በወደደኝ ላይ መሸፈቱ ጀብዱ መሰለኝ፡፡ አጥብቆ ከያዘኝ እቅፏ አፈገፈግኩ፣ በጉዳቷ ጥልቀት በልቧ ያለኝን ሥፍራ ለመገምገም፡፡
እኔና ሐመልማል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነዉ ብሔራዊ ቴአትር ነዉ፤ ብድራት የተሰኘ ቴአትር ለመመልከት ሄጄ፡፡ ቴአትሩን ለመታደም የመጣዉ ህዝብ ብዙ ስለነበር ቴአትሩ በራፍ ረዥም ሰልፍ ተሰልፌአለሁ፡፡ ከቢሮዬ ይዤዉ የወጣሁትን መጽሐፍ በግራ እጄ ይዣለሁ፡፡ ዐይኖቼን ጎዳናዉ ላይ ተክዬ አላፊ አግዳሚዉን በቸልታ እየተመለከትኩ ሳለ፡
“ወንድም” የሚል የሴት ጥሪ ከሐሳቤ አናጥቦኝ በፍጥነት ወደ ኋላዬ ዞርኩ፡፡ የጠራችኝ ሴት  
የቀይ ዳማ ናት፡፡
“ይቅርታ፣ መጽሐፉን ላየዉ እችላለሁ?” ድምጿ ለስላሳ ነዉ፣ ልክ እንደ አርጋኖን በጆሮ ዉስጥ
የሚፈስ፡፡   
“ይቻላል፡፡” መጽሐፉን ሰጥቻት መልሼ ዞርኩ፡፡
አእምሮዬ መዝግቦ የያዘዉን የእዚች ሴት ገፅታ በመጎልጎል ተጠምዷል። በአእምሮዬ የታተመዉ የሴቷ መልክ ይህን ይመስል ነበር፡ ዐይኖቿ የብር አሎሎ ናቸዉ፣ አፍንጫዋ ረዥም ሆኖ ከወደ ጫፉ ቀልበስ ያለ ነዉ፤ ልክ እንደ ንስር አፍንጫ፡፡ ደረቷ ላይ በትእቢት ጉች ያሉትን ክብ ጡቶቿን በጥቁር ቢትልስ ጋርዳቸዋለች፡፡ ከላይ ሐምራዊ ቀለም ኮት ደርባለች፡፡ በግራ ትከሻዋ ያነገተችዉ ቦርሳዋ ሉዊስ ቩቶን ነዉ፡፡ አእምሮዬ መዝግቦ የያዘዉን የሴቷን ተጨማሪ የመልክ ዝርዝሮች ከሰሌዳዉ ላይ እያገላበጠ ሳለ፡
“ርእሰ ጉዳዩ ምንድን ነዉ?” አለች፤ አንዴ እኔን አንዴ ደግሞ መጽሐፉን እያፈራረቀች እያየች፡፡
“ልብወለድ ነዉ፡፡”
“እንዴት ነዉ ታዲያ? ጥሩ መጽሐፍ ነዉ?” አለች፤ መጽሐፉ ጀርባ ላይ የሰፈረዉን ጽሑፍ
እያነበበች፡፡  
“እጅግ በጣም!”
“በቃ አነበዋለሁ፡፡” አለችና ድጋሚ የመጽሐፉን ፊትና ጀርባ አገላብጣ አይታ አመስግና
 መለሰችልኝ፡፡  
በመጽሐፍ የተጀመረዉ የእኔ እና የሐመልማል ወግ ደርቶ ብዙ ቁም ነገሮችን አንስተን ተራችን እስኪደርስ ድረስ  አወጋን። ረዥሙ ሰልፍ ተጋምሶ ወደ ዉስጥ ለመዝለቅ ተራችን ሲደርስ ትዉዉቃችንን ለማጠንከር በማሰብ ቀድሜ የሁለት ሰዉ መግቢያ ትኬቶች ገዛሁ፡፡
ከሐመልማል ጋር ወደ ቴአትር አዳራሹ ከዘለቅን በኋላ በእኔ መሪነት ሁለተኛዉ ረድፍ ላይ ቦታ መርጠን ጎን ለጎን ተቀመጥን፣ እኔ በቀኝ እሷ በግራ፡፡ ከፊሉ ቴአትር ታዳሚ ጎኑ ከተቀመጠ ሰዉ ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ ወግ በመሰለቅ ላይ ነዉ። ይኸን ሁካታ ፍልዉሃ ሆኖ፣ ለገሀር ሆኖ፣ ሰንጋተራ ሆኖ፣ ተረት ሰፈር ሆኖ መስማት ይቻላል፡፡ የቀረዉ ታዳሚ ደግሞ በዝምታ የቴአትሩን መጀመር በቋፍ የሚጠብቅ ነዉ፡፡ ሐመልማል ለብሳዉ የነበረዉን ኮት አዉልቃ ጭኗ ላይ አኖረችዉ፡፡ እኔ አካባቢዬን ቸል ያልኩ መስዬ ተጎልቻለሁ፤ ዐይኖቼ ግን አንዴ እሷን በስላቺ በመሰለል ሌላ ጊዜ ደግሞ የግል ስልኬን እያፈራረቁ በማየት ተጠምደዋል፡፡
“ታዲያ መቼ ነዉ ስቱዲዮህን የምታስጎበኘኝ?” ስለ ሥራ ሕይወት ስንጫወት ሠዓሊ መሆኔን
ነግሬአት ነበር፡፡ እሷ አርክቴክት ናት፡፡  
“ሁሌም በሬ ክፍት ነዉ፡፡ ሥነ-ጥበብ ወዳጅ ነሽ ልበል?”   
“አዎ በጣም!” ከቦርሳዋ ዉስጥ ባወጣችዉ ቀይ የከንፈር ቀለም ከንፈሮቿን አስዋበች፡፡
“የትኛዉን የአሣሣል መንገድ ነዉ የምትከተለዉ? ማለቴ፣ ሪያሊስት ነህ ወይስ አብስትራክት
ሠዓሊ?”
“ብዙዎቹ ሥራዎቼ አብስትራክት ናቸዉ።”
“አብስትራክት ሠዓሊ ነሃ?”  
“አዎ፡፡”
“ግሩም ነዉ፡፡ የአብስትራክት የሥዕል ሥራ አድናቂ ነኝ፤ ሸራ ላይ መገለፅ ያለበት ፍልስፍና መሆን
ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡”
“ግሩም ሐሳብ ነዉ፡፡ የሪያሊዝም የሥዕል ሥራን በተመለከተ ምን አይነት አተያይ አለሽ?”
“ሪያሊስቲክ የሆነ የሥዕል ሥራ ልክ እንደ አጥር ነዉ፤ የምናባችንን ወሰን የሚጋርድ፡፡”
“እንዴት ማለት?”
“እንዲህ አይነቱ የጥበብ ሥራ ፊትህ የሚያቀርብልህ በገሀድ የምታየዉን የዓለምን መልክ ነዉ፣
አለቀ፡፡”
ቴአትሩ መጀመሩን የሚያበስረዉ ቀዩ መጋረጃ በመከፈቱ የአዳራሹ ታዳሚያን፣ ሁካታቸዉን ገተዉ በዝና የሚያዉቋቸዉ ተዋንያን መድረክ ላይ ግጭት ፈጥረዉ ሲራኮቱ ለመመልከት አሰፈሰፉ፡፡ የመጀመሪያዬ ነዉ ከሴት ጋር ሆኜ ቴአትር ስመለከት፡፡
የተዋናዮቹ ትወና ድንቅ ነዉ፣ በተለይ የመሪዉ ገጸባሕርይ አተዋወን፡፡ ሐመልማል፣ እጆቿን ጭኖቿ ሲነባበሩ የፈጠሩት ስንጥቅ ዉስጥ ወሽቃ ቴአትሩ ላይ አተኩራለች። ቀሚሷ ስሪቱ አጭር በመሆኑ ጠይም ጠብደል ጭኖቿን ከዐይን መጋረድ አልቻለም፡፡ ነፋሱ ስቦ አምጥቶ የሚያዉደኝ ከገላዋና ከልብሷ የሚነሳዉ ምዑዝ ጠረኗ የፅጌ አፀድ ዉስጥ የተገኘሁ ያህል እንዲሰማኝ አድርጓል፡፡ ዐይኖቼን ከሐመልማል ሰዉነት ላይ አሽሽቼ፣ ቴአትሩን በትኩረት መመልከት ጀመርኩ፡  
በባላንጣዉ ሚስቱን እና ሴት ልጁን በሞት ያጣዉ ተሰማ የተባለዉ ዋናዉ ገፀ-ባሕርይ፣ ብድሩን ለመመለስ የባላንጣዉን ሴት ልጅ በግብረ አበሮቹ አማካኝነት አግቶ አምጥቶ ወዳሰረበት አንድ ጠባብ ክፍል ገባ። በቀኝ እጁ ሽጉጥ ይዟል፡፡ እጅና እግሯ ከተቀመጠችበት ወንበር ጋር የተጠፈረችዉ ልጃገረድ በታላቅ ስጋት ተዉጣ አጋቾቿን እያፈራረቀች ትመለከታለች፡፡ ዋናዉ ገፀ-ባሕርይ ልጃገረዷን ሲጠብቅ የነበረዉ ራሰ በራ ጎልማሳ እንዲወጣ በእጁ  ምልክት ሰጥቶ እየተንጎራደደ፣ ወደ ልጃገረዷ ቀረበና ጎንበስ ብሎ እንዳትጮህ አፏ ላይ ተደርጎ የነበረዉን ልጓም አነሳላት፡፡ ልጃገረዷ በታላቅ ቡከን እየተንዘፈዘፈች ፊቷ የተገተረዉ ሰዉ እንዳይጎዳት በዐይኖቿ ትማፀነዉ ጀመር፡፡
“እየዉልሽ  የእኔ ልጅ … አንቺ እንዳቺ በደል የለብሽም፡፡ ግን ዕጣ ፈንታሽ ሆኖ ከእዛ አዉሬ
አባትሽ ተወለድሽ!”
“አልገባኝም… ምንድን ነዉ ጉዳዩ?”
“ዝርዝሩ ለአንቺ የሚረባ አይደለም!”
“ምንድን ነዉ ከእኔ የምትፈልጉት? ልትገሉኝ ነዉ? እርዱኝ! ... ኡኡኡ …!”
“ዝም በይ!” ዋናዉ ገፀ-ባሕርይ እንደ መብረቅ አምባረቀ፡፡
“የትኛዉም ዋይታና ጩኸት ፈፅሞ ልቤ ለረዥም ጊዜ ተጠምቶ የኖረዉን በቀል ከመፈፀም
አይገታኝም፡፡”
በተዉኔቱ ቀስቃሽነት ከአእምሮዬ እየተመዘዙ የሚወጡ ሐሳቦች እያብሰከሰኩኝ፣ ቴአትሩን በተመስጦ እንዳልከታተል ማስተጓጎላቸዉን ቀጥለዋል። ሐመልማል ቴአትሩን በታላቅ አትኩሮት በመመልከት ላይ ናት፡፡ አእምሮዬ ዉስጥ የሚርመሰመሱትን ሐሳቦች ቸል ብዬ ትኩረቴን ወደ ቴአትሩ ትእይንት መለስኩ፡
“የአባትሽ እኩይ ሥራ ዳፋዉ ለአንቺም ተረፈ እንጂ ኃጢያተኛስ አይደለሽም፤ ግን የእኔም
ቤተሰቦች ደም በከንቱ ነዉ የፈሰሰዉ! ገባሽ?”
“የምትናገረዉ ነገር ግልፅ አይደለም፡፡”
“ያ እርኩስ አባትሽ እጅግ የማፈቅራትን ሚስቴንና የአብራኬን ክፋይ በአንድ ጀምበር ነበር  
የነጠቀኝ! እናም…”
“ተሳስተህ ነዉ፣ አባቴ እጅግ መልካም ሰዉ ነዉ!” አለች ታጋቿ ልጃገረድ፣ የሰዉዬዉን ንግግር  
አቋርጣ፡፡
“መልካም ሰዉ? አሃሃሃ… አሃሃሃ… መልካም ሰዉ አልሽ?”
“አዎ፣ አባቴ ፈፅሞ እንዲህ አይነቱን አረመኔአዊ ተግባር አይፈፅምም!”
“ዝም በይ!” ዋናዉ ገጸ-ባሕርይ እንደ አራስ ነብር ተቆጥቶ ሄዶ ፊቷን በጥፊ ደረገማት፡፡
አእምሮዬ ተዉኔቱ በሚያጭርበት ሐሳብ መዳከሩን ቀጥሏል፡፡ ብዙ ሰዎች ራሳቸዉን በጭንብል ጋርደዉ ስለሚኖሩ እዉነተኛ ማንነታቸዉን ፈፅሞ ማወቅ አንችልም፡፡ ለዚህም ነዉ እጅግ ባመናቸዉ የምንታለለዉ፣ እጅግ ባከበርናቸዉ የምንዋረደዉ፡፡ የሐመልማልን ገፅ ለማየት ወደ ቀኝ ስዞር፣ እሷም እኔን ለማየት ወደ እኔ ስትዞር አንድ ሆነ፡፡ እንደ ፀሐይ የደመቀ ፈገግታዋን ለግሳኝ ኮከብ ዐይኖቿን መድረኩ ላይ ተከለች፡፡ ፈገግታዋን ዘግኜ እንደገና ዐይኖቼን ወደ መድረኩ ትእይንት መለስኩ፡
“እናንተ እነማን ናችሁ? ለምንድን ነዉ እንደዚህ የምታሰቃዩኝ?” አለ ገዳሙ የተባለዉ የዋናዉ  ገጸ-ባሕርይ ደመኛ፡፡
“ምንድን ነዉ ከእኔ የምትፈልጉት? ገንዘብ ከሆነ የምትፈልጉት የጠየቃችሁትን ያህል ልስጣችሁ!”
“ዝም በል አንተ እርኩስ!” አለ ተሰማ በእርጋታ የፎቁን ደረጃ እየወረደ፡፡ ከዛ እየተንጎራደደ ወደ ባላንጣዉ ቀረበና፣ አድርጎት የነበረዉን ጥቁር የዐይን መነፅር አዉልቆ ፊቱ ቆመ፡፡
“እንዴ! በፍፁም ሊሆን አይችልም! ተሰማ! አንተ ነህ? በሕግ እድሜ ይፍታህ ተበይኖብህ
አልነበር እንዴ? በምን ተአምር ከስር ልታመልጥ ቻልክ?”
“አሃሃሃ…አሃሃሃ… ሕግ አልክ? አሃሃሃ… አሃሃሃ… አየህ፣ ቢዘገይም እዉነት ራሱን መግለጡ
አይቀርም፡፡ እናም እንደምታየዉ ጠላቴን እግሬ ሥር አንበርክኬ እንድቀጣ ሆነ!” ሽጉጡን አቀባበለ፡፡    
“አሻፈረኝ አልክ እንጂ፣ የከፋ እርምጃ ከመዉሰዴ በፊት ምርጫ ሰጥቼህ ነበር፡፡”
ሰዉ የዘራዉን ማጨዱ አይቀሬ ነዉ። ማን ነዉ ይኸ ሕግ እንዲፀና የደነገገዉ? መፍታት የተሳነኝ ታላቁ ምስጢርም ይኸዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ ዓለሙ ላይ ፍትሕ አንዲሰፍን ይሆን ይኸ ስርአት የተዘረጋዉ? ኃያሉ ፍጥረት ደካማዉን እንዳይጨቁነዉ አቅዶ ይሆን ተፈጥሮ ይኸን ስርአት ያረቀቀዉ? የሚያብሰከስከኝን ሐሳብ ሸሽቼ ቀልቤን ወደ ተዉኔቱ መለስኩ፡
“በፈጠረህ! እኔን እንዳሻህ አድርገኝ፤ ቤተሰቦቼን ግን አትንካብኝ?”
“አሃሃሃ… አሃሃሃ…” ተሰማ ጮክ ብሎ ሳቀ።
“አዝናለሁ፡፡ ለሁሉም ነገር እጅግ ዘገየህ፡።” አለ ተሰማ በባላንጣዉ ፊት እየተንጎራደደ።
“አይሆንም! አይደረግም!” በልጄና በሚስቴ ላይ እጅህን ካነሳህ …አለ ገዳሙ በጩኸት፡፡
“አየህ፣ የሚወድዷቸዉን አጥቶ የመኖርን ምሬት ማጣጣም አለብህ!”
“ጨካኝ ነህ!” ገዳሙ ጮኸ፡፡
“ጨካኝ አልክ? አሃሃሃ… አሃሃሃ…!”
“አዎ! አረመኔ ነህ!”
“አፍህን ዝጋ!” ተሰማ እንደ መብረቅ አምባረቀ፡፡
“አዉሬ ነህ! እንደምገልህ ደግሞ አትጠራጠር!” አለ ገዳሙ እንደ እብድ እየጮኸ፡፡
“ሴቶቹን ወዲህ አምጣቸዉ!” አለ ተሰማ ፊቱ ለተገተረዉ ግብረ አበሩ፡፡ እጃቸዉን ወደ ኋላ
የተጠፈሩ ልጃገረድና ቀይ ፀጉረ ረዥም ሴት ከታገቱበት ክፍል ሲወጡ ገዳሙን በማየታቸዉ
ለቅሶ ጀመሩ፡፡
“አባቴ! እህ … እህ …”           
“የእኔ ዉብ ደህና ነሽ?”      
“እባክህ በእነዚህ ንፁሀን ላይ አትጨክን?”
“ሃሃሃ … ሃሃሃ … አትጨክን አልክ? አንተ አዉሬ! ሞት ዋዜማ ላይ ሆነህም አትፀፀት?”
“እባክህ ለልጄ ልኑርላት?”
“ዝም በል!” ተሰማ ጮኸ፡፡
“በከንቱ የፈሰሰዉ የቤተሰቦቼ ደም እየጮኸ ነው፣ ደማቸዉ የሚመለስበት ሰዓቱ ደግሞ አሁን
ነዉ!”
“እባክህ?”
“አፍህን ዝጋ!” ተሰማ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ወደ ገዳሙ ተንደረደረና በያዘዉ ሽጉጥ ግንባሩ ላይ ሁለቴ ተኮሰበት፡፡  
ገዳሙ ወለሉ ላይ በጀርባዉ ተዘረረ፡፡
“ኡ … አባቴ! ኡ … ኡ ...”
ቴአትሩ አልቆ ከሐመልማል ጋር ብሔራዊ ቴአትርን ለቀን ወጥተን እስከ ሜክሲኮ አደባባይ እያወጋን በእግር ከተጓዝን በኋላ ወደ ሰፈሯ የሚወስዳትን ታክሲ አሳፍሬያት፣ አድራሻዋን ወስጄ፣ ዉስጤ በአንዳች እንግዳ ስሜት እየታመሰ ከዛንቺስ ገባሁ፡፡
* * *
በእኔና በሐመልማል መካከል ፅኑ መፈላለግ ስለነበር በተዋወቅን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ነዉ የፍቅር አክርማን መቅጨት የጀመርነዉ፡፡ ሐመልማል በልኬ የተሰፋች ሴት ነበረች፡፡ አለ አንዳንድ ጊዜ፣ ህልምና ገሀድ የሚቀናበሩበት፡፡
* * *
ታላቅ አወዳደቅ የወደቅኩት በተላላነቴ ምክንያት ነዉ፡፡ ሐመልማልን ገፍቼ፣ ማክዳን ተከትዬ የሄድኩት እጥፍ ድርብ ደስታን እዘግናለሁ የሚል ከንቱ ተስፋን ሰንቄ ነዉ። እናም፣ በማክዳ ሥጋ ተጠፍንጌ ሽፍትነትን ተማርኩ፡፡ ማክዳ፣ ድንገት ሐመልማል ተንሰራፍታ ወደ ተቀመጠችበት ልቤ ዘዉ ብላ ገብታ፣ ገብቼ ያልተንቦጫረቅኩበት ሌላ የደስታ ባሕር እንዳለ አሳየችኝ፤ ስስለቻት ትዝታዋን አስታቅፋኝ ባካበተችዉ ጥበብ ቀስ ብላ ልትሸሽኝ ነገር፡፡ እኔ ሞኙ፣ የያዝኩትን ጥዬ አጨብጭቤ ቀረሁ፡፡ የሚቆጨኝ ማክዳ ስለራቀችኝ አይደለም፣ ሐመልማልን ስለከዳሁ ነዉ፡፡ የሚበጀንን የማናዉቅ ግልቦች ነን፤ የሚወድኑን እየገፋን የሚሸሹንን እንከተላለን፡፡

Read 1334 times