Saturday, 12 March 2022 14:18

የአድዋ ድል - አተያይ አንድ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

   “በጣሊያን ወረራ ዘመን በ1928 ዓ.ም በሽሬ ግንባር ጉዞ ላይ ከድቶ ጎጃም መጥቶ ብጥብጥ የቀሰቀሰውን ደጃዝማች ገሠሠ በለውን (የጎጃም ነጋሲ ዞር የበላው ተክለ ሃይማኖት  ልጅ) ለጥቃት ከሰላሴ የመጣው ጦር ብዙ በደል ፈፅሟል። ብዙ ሰዎችም ተሰልበዋል። በመጨረሻ ገሰሰ በለው ተሰወረ፡፡”
“ያልታሰበው”
በሕይወቱ ፈታኝ ጉዞና በኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎ ብርሃኑ ባይህ (ሌ/ኮለኔል)
በንጉስ ዘመን ለዘጠነኛ ክፍል የእንግሊዘኛ ቋንቋ ማስተማሪያ ተብሎ የተዘጋጀ ኮንታክት” የተባለ መፅሐፍ ነበር፡፡ ለንባብ ትምህርቱ መለማመጃ አድርጎ ያቀረበው የትራፊክ አደጋ ሪፖርትን ነው፡፡ ትራፊክ ፖሊሱ ከቦታው የሚደርሰው አደጋው ከደረሰ በኋላ ነው፡፡ እንዴት እንደደረሰ የሚያሳይ ንድፍ  ካርታ ከሠራ በኋላ የጭነት መኪና ሹፌሩንና ረዳቱን፣አደጋው የደረሰበትን ታክሲ ሹፌርና ተሳፋሪውን፤አደጋ የደረሰባትን ሴትና  ሱቁ የተጎዳበትን ነጋዴ እንዲሁም በአካባቢው የነበረውን የቤንዚን ማደያ ሠራተኛ ይጠይቃል፡፡
የጭነት መኪናው ሾፌር “ፍጥነት አልነበረኝም፤ ከፊቴ የነበረው ታክሲ ድንገት አንድ ሰው አይቶ ሲታጠፍ እሱን ላለመጋጨት በኋይል ወደ ግራ  ስለጠመዘዝኩ ከመንገድ ወጥቼ ከሱቁ ጋር ተጋጨሁ አለ፡፡ ረዳቱ ታክሲውን አልፈነው ነበር፤ ከየት እንደመጣ እንጃ ታክሲው አንድ ሰው አይቶ ድንገት ሲቆም፣ እሱን ለማዳን መኪናውን ወደ ግራ ጠምዝዘው፡፡ እኔ ላለመወደቅ መታገል ጀመርኩ። ምን እንደሆነ አላየሁም” ሲል መለስ፡፡ ባለ ታክሲው ደግሞ፤     “የጭነት መኪናው በጣም ይፈጥናል፤ እሱ ነው ከመንገድ እንደወጣ ሴትየዋን  እንደገጫት ያደረገኝ” ሲል ቃሉን ሰጠ፡፡ የታክሲው ተሳፋሪ ደግሞ ሴትየዋን እንደሚያውቃት፤ በተገጨች ጊዜ በቦታው የነበረ ሃኪም ወደ ሆስፒታል እንደወሰዳት አስረዳ፡፡ ሴትየዋ ታክሲ እየጠበቀች እንደነበር አመልክታ፣ በደረሰባት ጉዳት የተፈጠረው ራስ ምታት እያሰቃያት መሆኑን ተናገረች፡፡ ባለ ሱቁ ደግሞ የጭነት መኪናው ውሻውን ገድሎ ወደ ሱቅ ሲመጣ  እንዳየ በጓሮ በር ወጥቶ ህይወቱን ማትረፉን አሳወቀ፡፡ የቤንዚን ማደያ ሠራተኛው ታክሲዋ አሮጌና በየደረሰችበት የምትቆም መሆኗን ጠቁሞ የጭነት መኪናው ሾፌር ጎበዝ ባይሆን ኑሮ ሁሉም ይልቁ እንደነበር አሳወቀ፡፡ ትራፊክ ፖሊሱ፤ ሃኪሙንና ሌሎችንም በቦታው የነበሩ ሰዎች አግኝቶ አነጋግሮ ቢሆን ምን ይሰማ ነበር? ብሎ ማሰብ ወይም መጠየቅ ይቻላል። ይህ  ቀጥዬ ለማቀርበው ታሪክ እንደ መመዘኛ ይታይልኝ፡፡
ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ልመለስ፣ ባለፈው ሳምንት በአደዋ ድል አከባበር ላይ የታዩ ልዩነቶቻችንን ማንሳቴን አስታውሳለሁ፡፡ የዛሬ ትኩረቴ ደግሞ በዚህ በዓል አከባበር ላይ  በመገናኛ ብዙሃን የተሰራጩ ወይም የተላለፉ ፕሮግራሞችን በመውሰድ ጉዳዩ  ላላጋጠማቸው ወገኖች “እንዲህም አለ” ለማለት ነው፡፡ መረጃውን ያገኘሁት ከዩቲዩብ ላይ ነው፡፡ መምረጥ ማግኘት እንጂ የተለየ መስፈርት የለኝም፡፡
“ሀበሻ እስታር መልቲ ሚዲያ 126ኛውን የአድዋ ድል በዓልን ለማክበር ባዘጋጀው የውይይት ፕሮግራም፣ የታሪክ ተመራማሪና  ፀሐፊ ተብለው የተገለጡት  አቡበከር መሐመድ፤ ብዕር ያገነናቸው የተባሉት አብዱል ጀሊል ሻይህ አሊ ካሳ እና  ኡስታዝ ጀማል በሽር (በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ይታወቃሉ) በፕሮግራሙ ላይ  ንግግር አድርገዋል፡፡ ከእነሱ በፊት ንግግር ያደረጉ ሰዎች እንደነበሩ የሚጠቁም  ቢኖርም ሀሳባቸውን ለማግኘት አልተቻለኝም፡
ጣሊያኖች (ነጭ ወራሪዎች) ዶጋሊ ጉንዳትና  አፋር ውስጥ በተደጋጋሚ መደምሰሳቸውን ያወሱት አቶ አቡቦከር መሐመድ፣ ለእሳቸው አድዋ የነበረችውን ኢትዮጵያን ለመጠበቅ የተደረገ ጦርነት ሳይሆን አዲስቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰረት የተጣለበት ነው፡፡ “”ድል አድርገን ድል  የተነጠቅንበት ነው” የሚሉት አቡቦበከር፤ ከጦርነቱ መንስኤዎች አንዱ የሆነው የውጫሌ ውል ችግር እንዳለበት አፄ ምኒልክ ከአንድ ዓመት በፊት  ያወቁ እንደነበር፣ወደ ሮም የላኳቸው ራስ መኮንንም ይህን ውል የሚያፀና ሌላ ውል መዋዋላቸውን አመልክተው፣ የጦርነቱ ሌላው ዋና ምክንያት ምዕራባዊያን  አፍሪካን በቅኝ ግዛታቸው ስር ለማስገባት መወሰናቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
“አፄ ዩሐንስን ለመውጋት ሙዚንገርን ወደ ኢትዮጵያ በአፋር በኩል  እንዲገባ ያደረገው ምኒልክ ነው፡፡ አፋሮች ግን አራት መቶ ከሚሆነው ጦሩ ጋር ደመሰሱት” የሚሉት አቶ አቡበከር፣ የአፋሩ ሱልጣን አንፍሬ ከሙዚንገር ሠራዊት ከማረኩት የጦር መሳሪያ ከፊሉን ለምኒልክ መላካቸውን በዚህ ንግግራቸው ሲጠቅሱ አላጋጠመኝም፡፡  ምኒልክ  አስመጥተዋቸው ቢሆን ኖሮ  ሲገደሉ ለምን ዝም አሉ የሚል ጥያቄም ያስነሳል፡፡
አፄ ሚኒሊክ ወደ አድዋ በዘመቱበት ጊዜ ውስጥ  በአዛዥ ወልደ ፃዲቅ የሚመራ ጦር ወደ አፋር መዝመቱን፣ ከሱልጣን አንፍሬ ጦር ጋር መዋጋቱን፣ በጦርነቱ ከስድስት እስከ ስምንት መቶ ሰዎች መምታቸውን የተዘረዘሩት አቶ አቡበከር፤ ምኒልክ ወደዚያ ጦር የላኩት ጣሊያኖች ስልጣን  አንፍሬን ከማዕከላዊ መንግስት ጋር የነበረውን ግንኙነት እንዲያቋርጥ ካደረጉ በኋላ ወደ አንኮበርና ሐረር ለመዝመት ማሰቡ በመታወቁ እንደሆነ አልገለጡም፡፡
አቶ አቡበከር ወደ አድዋ ከዘመቱ የጦር መሪዎች ውስጥ ለምኒልክ ሙሉ በሙሉ ታማኝ የነበሩት ራስ መኩንን ብቻ እንደነበሩ፤በሁለት ልብ የቆዩት የጦር መሪዎች ዘመቻውን በሙሉ ልብ የተቀላቀሉበት ከአምባላጌ ጦርነትና ድል መገኘት በኋላ እንደሆነ ዘርዝረው ጣሊያኖች መንገድ ይዘጋላቸው ዘንድ መሳሪያ የሰጧቸው ሺህ ጣላሃ ለምኒልክ ጦር እንቅፋት ለመሆን አለመፈለጋቸው ለአምባላጌ ድል መገኘት አስተዋፅ እንዳለው አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም አፄ ምኒልክ፤ “ጦልሃ ጃፋር እኔን ለመውጋት የተነሳው አገሩን ጠልቶ አይደለም” በማለት እንደመሰከሩላቸው አውስተዋል፡፡
ጦርነቱ ካለቀ በኋላ አፄ ምኒልክ በጦርነቱ ለሞቱ  ጣሊያናዊያን ክርስቲያኖች ሶስት የሀዘን ቀን ማወጃቸውን አቡበከር አውስተው፣በጦርነቱ ከጎናቸው ለነበረው የእስልምናና ሌላ እምነት ተከታይ የሀዘን ቀን አለማድረጋቸውን በአፀንኦት አውስተዋል። ሃሳባቸውንም የደመደሙት “የአድዋ ችግር የሚመነጨው ከጦርነት ሜዳ ነው፡፡ ድላችንን የነጠቁን መሪዎች የምናከብርበት ምክንያት የለንም” በማለት ነው፡፡
ሰባት ቤት ወሎና  የጁ በሱልጣን የሚተዳደሩ  እንደነበሩና ወሎ በአጠቃላይ በቦሩ ሜዳ  በጎ ስሜት እንደሌለው፣  የጅማው አባጅፋር ምንም ለምኒልክ ቢገብሩ የአላህ ባሪያ ነኝ ብለው እንደሚያምኑ፣ በሐረር ጨለንቆ ላይ በተደረገ ከፍተኛ ጦርነት መገበሩ፣ ወላይታ አካባቢ የሚገኙ ሙስሊሞች ለምኒልክ እንዲገብሩ በተደረገ ጊዜ “መስቀሉ ጨረቃን አሸነፈ” ተብሎ መፃፉን፣ የኢትዮጵያ ክርስትና ሲሶ መንግስት አገር መሆኗንና ሃይማኖቱ ባይፈቅድላትም ሙስሊሙ ወደ አድዋ የዘመተው ከንጉስ ጋር ይጓዝ የነበረውን የጊዮርጊስን ታቦት አጅቦ መሆኑን የዘረዘሩት አቶ አብዱ ጀሊል ሼህ አሊ ካሳ፤ “አጼ ሚኒሊክ ኢትዮጵያን አዋህደው እንደጨረሱ በተቀሰቀሰው በዚህ ጦርነት ሕዝቡ ቂሙን ረስቶ እንዴት በአንድነት ሊሰለፍ ቻለ” ሲሉ ይጠይቃሉ-በማድነቅ፡፡
አቶ አብዱ ጀሊል፣ አንድ ጣሊያናዊ ፀሐፊ ለእንግሊዞች ለፈረንሳዮችና ለጣሊያኖች “ኢትዮጵያዊያንን አትመኗቸው፤ ሁለት ውሾች በአጥንት ይጣላሉ፤ ጅብ በሚመጣ ጊዜ ግን ሁለቱም ወደ ጅቡ ይዞራሉ” ብሎ እንደመከሯቸው አስታውሰው፤ የጅማው አባ ጅፋር  ሃያ ሺህ ማርትሬዛ ብር  ለጦርነቱ ለአፄ ምኒልክ መስጠታቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከጣሊያን ለተበደረችው አራት ሚሊዮን ሊሬ የሐረር ገበያ መያዣ ተደርጎ እንደነበር፣ አፄ ምኒልክ በጋማና በቤት እንስሳት ላይ የጭራ ግብር በመጣል እዳው መከፈሉን፣ አቶ አብዱል  ጀሊል ጠቁመው፤ በከብት ሀብቱ  የሚታወቀው የቆላው አካባቢ ከፍተኛ ግብር ከፋይ እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡
“ሐረር ባትኖር ኑሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የአድዋን ጦርነት ለመሸከም የሚያችል አቅም አልነበረውም” የሚሉት አቶ አብዱል ጀሊል፣ ዘማቹ የአፄ ምኒልክ ጦር ወደ ግንባር የተጓዘባቸው አካባቢዎች ሙስሊሞች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው ሠራዊት በማቅረብ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ሁሉ በስንቅ አቅርቦትም ከፍተኛ ሚና መወጣቱን አስታውቀዋል፡፡
በንጉስ ሚካኤል ጦር ውስጥ ደጃዝማች ቃሲም መሐመድ፣ራስ በሽር የኮሬቡ ገዥ ደጃዝማች አመር በሽር፣በራስ ወሌ ጦር ውስጥ ደግሞ ቀኛዝማች ሃምዛ አበጋዝ፤ ቀኛዝማች መሐመድ በረንቶ፣ ፊውታራሪ አሊ ይማም፣ሺህ መሐመድ ሚያዊ የሚባሉ የጦር መሪዎች እንደነበሩ  የጠቀሱት አቶ አብዲል ጀሊል፤ የሌሎችንም ታሪክ በምርምር በማውጣት ሙስሊሙ በአድዋ ጦርነት የነበረውን ሚና ማሳወቅ በታሪክ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ  አስገንዝበዋል
“የአድዋ ጦርነት ብላችሁ ጎግል ስታደርጉ ከወታደሮች አናት ላይ የጊዮርጊስን ስዕል ታያላችሁ፡፡ ክርስቲያኑ ጊዮርጊስ ረዳኝ ማለቱ ስህተት አይደለም፡፡  ስህተቱ ሙስሊሙ እያለ  እንደሌለ መቆጠሩ ነው፡፡ እንደዚህ ያለው አገላለጥ ከአድዋ እንድንሸሽ አድርጓል፡፡ ከዚህ በኌላ አናኮርፍም፡፡ አድዋ የእኛም ነው የምንልበትን በጥናት አስደግፈን እናመጣለን” የሚለው በአቶ አብዱል ጀሊል ንግግር፣ እንደመዝጊያ ሃሳብ የሚቆጠርላቸው ነው፡፡
ሶስተኛው ተናጋሪ ኡስታዝ ጀማል በሽር፣ ንግግራቸውን የከፈቱት፤ “በዚህ ጉባኤ ላይ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና የመንግስት ባለስልጣናት እንዲያገኙ ተጋብዘው ነበር ወይ” ብለው መጠየቃቸውን በማውሳት ነው፡፡
አንድ ሰው የሚያደርገው በእውቀት ወይም በልማድ መሆኑን የጠቆሙት ኡስታዝ ጀማል፤ እኔን “እነዚያ አባቶች የተባለውን ሁሉ ያደረጉት አውቀው ነው ወይ?” ብትሉኝ መልሴ “አይደለም ነው” ሲሉ አስተረድተዋል።
“አያይዘውም “አንዱ የሌላውን ድካም ዋጋ በማሳጣት የሚገኝ በጎ ነገር ባለመኖሩ፣ የሌላውንም ድርሻ ጠብቆ በእውቀት ላይ  ተመስርቶ የሁሉንም  ድርሻ ማስገንዘብም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
መግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ታሪክ ከያዝኩት ጉዳይ ጋር በቀጥታ ላይገናኝ ይችላል፤ “በአድዋ ጦርነት ላይ የተሰለፉ ሙስሊሞች ቀብር አልተፈጸመላቸውም” የሚለው መረጃ የመጣው በቅርብ ነው፡፡ እንዲህ የምንሰማቸው  ብዙ ታሪኮች አሉ፤ ለማለትም ነው- መጥቀሴ። ለክፍል ሁለት ሳምንት እንገናኝ፡፡

Read 3608 times