Saturday, 12 March 2022 14:40

ልጅ የአለመውለድ ምክንያቶች፡፡

Written by 
Rate this item
(0 votes)


          በ2018 የወጣው የአለም የስነህዝብ ዳታ እንደሚያስረዳው በአለምአቀፍ ደረጃ የወሊድ መጠን በእያንዳንዱዋ ሴት 2.4 ልጅ መሆኑ ተመዝግቦአል፡፡ ይህ ማለት ከዛሬ 20 ወይንም 30 አመት ገደማ ጋር ሲነጻጸር በአለም ላይ አብዛኛዎች ሴቶች የሚወልዱትን ልጅ መጠን እያሳነሱ መምጣታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ መጠን ለሁሉም አገሮች እኩል ይሆናል ማለት አለመሆኑን የሚያስረዱ በርካታ መረጃዎች አሉ፡፡  ለምሳሌም በኢትዮጵያ በ2020 ባለው የወሊድ መጠን አመዘጋገብ መሰረት በአንዲት ሴት 4.109/ሲሆን ከ2019 እ.ኤ.አ ሲነጻጸር በ2.28 በመቶ ዝቅተኛ ሆኖ ይታያል፡፡  ለዚህም ብዙ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያን መውሰድ እንደ አንዱ አማራጭ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡
ልጅ ላለመውለድ በመፈለግ የተለያዩ መንገዶችን ተግባራዊ ማድረግ ከሚለው ሌላ ግን በዚህ እትም የምንመለከተው ልጅ መውለድ ሞክሮ መውለድ አለመቻልን ይሆናል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት እንደሚገልጸው ልጅ መውለድ አለመቻል Infertility አለም አቀፍ ችግር ነው፡፡ እስቲ አንድ ገጠመኝ እናስነብባችሁ፡፡
‹‹…እኔና ባለቤቴ ከተጋባን ወደ 18/አመት ሆኖናል፡፡ በፍቅርና በደስታ የመሰረትነው ትዳር እስከዛሬም ምንም ችግር አልገጠመውም፡፡ ነገር ግን ልጅ ለመውለድ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ብዙ ሞከርን፡፡ በጾም በጸሎቱም ሆነ በህክምናው ጥረት አድርገናል፡፡ አልተሳካልንም፡፡ ምናልባትም እኔም ሆንኩ እሱ በስራ ላይ በነበርንበት ወቅት በረሀው እና የስራው ጸባይ ጎድቶን ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ግን አለኝ፡፡ ሐኪሞቹ አይዞአችሁ…ችግር የለባችሁም ከማለት እና ከማጽናናት በስተቀር ተስፋ አያስቆርጡንም፡፡ ዛሬማ እንግዲህ እድሜውም እየነጎደ ነው፡፡ ምን ትሉናላችሁ?...››
ወ/ሮ አለም በሪሁን ከጀሙ ሶስት
WHO እንዳወጣው መረጃ በእንግሊዝኛ አጠራሩ Infertility በአማርኛው መካንነት ማለት እንደ አንድ የስነተዋልዶ ጤና ችግር የሚታይ ነው ፡፡ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በጋራ ወይንም በግል ልጅ ለመውለድ የቻሉትን ያህል ሞክረው ካልተሳካ እና ተስፋ ከቆረጡ ወደ ሳይንሳዊው ልጅ የመውለጃ ዘዴ እንደ IVF ወደመሳሰሉት መሄድ እየተለመደ መጥቶአል፡፡ በእርግጥ ይህ ዘዴ በመልማት ላይ ላሉ አገሮችና በተለይም አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ የሚተገበር አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን በላቦራቶሪ ልጅን ፈጥሮ ወደማህጸን በማስገባት ልጅ እንዲወለድ ከሚያስችለው ዘዴ በተለየ በተለያዩ የህክምና ዘዴዎች ልጅ እንዲወለድ መሞከር ይቻላል፡፡
ሴቶችንና መካንነትን በሚመለከት ይበልጥ ትኩረት መደረግ ያለበት በወር አበባ ተፈጥሮአዊ ኡደት ላይ ነው፡፡ መካንነት የገጠማት ሴት የወር አበባን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ በመከታተል እውነታውን ለሕክምና ባለሙያዎች ማስረዳት ይጠበቅባታል፡፡ የህክምና ባለሙያዎቹ መፍትሔ ወደሚያስገኝ እርምጃ የሚገቡት ከዚህ በመነሳት ሲሆን ይህ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያትም መካንነት ምናልባት በዘር የሚመጣ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ስለሚረዳ ነው፡፡ የህክምና ባለሙያዎቹ ሁኔታውን ከተረዱ በሁዋላ መካንነትን ለማስወገድ የሚረዱ መድሀኒቶችን ለሴትዋ የሚሰጡ ሲሆን ከሴትዋ የሚጠበቀው ደግሞ እራስዋን በአካልና በስነልቡና ዝግጁ ማድረግ እንዲሁም እራስን ከጭንቀት ማላቀቅ የመሳሰሉትን እርምጃዎች መውሰድ ነው፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ወይንም በዘርፉ ምርምር ያደረጉት እንደሚገልጹት ሴቶች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ምክንያቶች ልጅ መውለድ ሊያቅታቸው ወይንም እርግዝና ላይከሰት ይችላል ይላሉ፡፡  
በእድሜ መግፋት፤ ከበድ ያለ አልኮሆል ወይንም እንደቡና የመሳሰሉ መጠጦችን በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ መውሰድ፤ ሲጋራ ማጤስ፤
ከክብደት ጋር የተገናኙ በሕክምና ባለሙያዎች ሊገለጹ የሚችሉ ችግሮች፤
የአመጋገብ ችግር እና የተመጣጠነ ምግብ ያለማግኘት፤
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ (ከስፖርት ማዘውተሪያ አለመግባት ወይንም ከእለታዊ ኑሮ ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴ አለማድረግ ወይንም በእግር አለመሄድ…ወዘተ)
በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚፈጠሩ በሽታዎች ተከስተው የሚያውቁ ከሆነ ወይንም ከማህጸን እና ተያያዥ ከሆኑ አካላት ጋር በሚኖር ሕመም ምክንያት፤
እንደደም ግፊት ወይንም ስኩዋር የመሳሰሉ ሕመሞች ታማሚ ከሆኑ፤የአእምሮ ጭንቀት ፤የሆርሞን ችግር…ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ ሕክምና በሚደረግበት ወቅት የሚታዩ አንዳንድ ችግሮችም ልጅን ከመውለድ ወይንም ከማርገዝ ሴቶችን ሊያውኩዋቸው እንደሚችሉ የጤና ወረቀቶች ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌም በሕክምና ወቅት እንደሚታየው ከሆነ ከእንቁላል ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ችግር ልጅን መውለድ ላለመቻል ወደ 25 % የሚሆነውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የማህጸን ቱቦ መዘጋት ወይንም በማህጸን ውስጥ ከሚፈጠር ሕመም ጋር በተያያዘም መካንነት ሊከሰት ይችላል፡፡
መካንነት በሴቶች ምክንያት ብቻ የሚከሰት ሳይሆን የወንዶችም ጭምር መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ወንዶች  ለመካንነት ምክንያት ይሆናሉ የሚባልበት ዋናው ምክንያት የዘር ፈሳሽ ሁኔታ ነው፡፡ወንዶች በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት በቅድሚያ የሚኖራቸው ወተት መልክ ፈሳሽ እና semen የወሲብ  እርካታ በሚገኝበት ጊዜ የሚኖረው semen በትክክል እንደሚፈለገው ካልሆነ ወደ 75% የሚሆነውን የመካንነት ችግር ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ ችግሩ በተዋረድ ሲገለጽም፡- የወንድ የዘር ፈሳሽ sperm እንቅስቃሴ ወይንም ፍጥነት ዝቅተኛ ወይንም ደካማ መሆን
የወንድ የዘር ፈሳሽ sperm ቅርጽ፤ መጠን፤ ይዘት በትክክለኛው እንደሚፈለገው አለመሆን …ወዘተ
Semen በሚባለው ፈሳሽ ውስጥ የወንድ የዘር ፈሳሽ sperm በበቂ አለመኖር፤
የአንድ ወንድ ትክክለኛው የዘር ፈሳሽ sperm መጠን በ Semen ውስጥ 20 ሚሊዮን ሚሊሊትር ሲሆን የአንድ ወንድ የዘር ፈሳሽ sperm መጠን ከ10 ሚሊዮን ሚሊ ሊትር በታች ከሆነ እርግዝናን እውን ለማድረግ አቅም አይኖረውም፡፡ ይህ እንዲሆን ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚገለጹት ውስጥ ፡-
እንደ ሳኡና ባዝ የመሳሰሉ ሞቃት የገላ መታጠቢያዎችን በድግግሞሽ ወይንም ሁልጊዜ በሚባል ደረጃ መጠቀም፤
የወንድ የዘር ፍሬ ማምረቻ እና ማከማቻ Testicule ኢንፌክሽን ካጋጠመው፤
Testosterone የተባለው ሆርሞን እጥረት ካለ፤
የተለያዩ ከባድ የሚባሉ መድሀኒቶችን ለረዥም ጊዜ መውሰድ (chemotherapy/radiation፣Sulfasalazine, Anabolic steroids) …ወዘተ
ወንድ ልጅ ሲወለድ ብልቱ ትክክለኛውን የአፈጣጠር ሂደት አሟልቶ አለመወለዱ…ወዘተ ይገኙበታል፡፡
ሴትና ወንድ በትዳር ወይንም በጉዋደኝነት ተገናኝተው ልጅ ለመውለድ ፈልገው ካልቻሉ ወደህክምና ተቋም በመሄድ የምክር አገልግሎትና ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በግላቸውም አኑዋዋራቸውን፤አመጋገባቸውን፤የአካል ብቃት እንቅስቃሴአቸውን በመከታተልና አእምሮአቸውን በማዘጋጀት በተረጋጋ መንፈስ እንዲጠብቁ ይመከራሉ፡፡ ጭንቀትን ማስወገድ ሴቶች የሚፈልጉትን እርግዝና ለማግኘት ይረዳቸዋል፡፡

Read 11404 times