Saturday, 12 March 2022 15:22

የምናውቀው ኑሮና የማናውቀው ዳይኖሶር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ..እኔ የምለው ወይ የሆነ የተበተነብን ዱቄት ነገር አለ፣ ወይ ደግሞ የሆነ ቦታ ተሰብስበው ጥቁር ዶሮ አዙረውብናል ማለት  ነው... እንዴት ነው የኑሮው መክበድ እዚህ ደረጃ ሊደርስ የቻለው!?
መንገደኛው ጋዜጠኛ፤ ‘የአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን’ አስተያየት ለመሰበሰብ ከተማ ወጥቷል፡፡
መንገደኛው ጋዜጠኛ፡- “ካላስቸገርኩዎት አሁን ስላለው የኑሮ ሁኔታ አንዳንድ ነገሮች ልጠይቅዎ ፈልጌ ነበር፡፡”
እሳቸው፡- “ስለምን አልከኝ?”
መ.ጋ.፡- “አሁን...አሁን ስላለው የኑሮ ሁኔታ...”
እሳቸው፡- “ምን ሁኔታ ምናምን እያልክ ቀዝቃዛ ውሀ ትቸልስበታለህ! እንደው እናንተ ሰዎች መቼ ነው እንዲህ በቃላት ነገር ማድበስበሳችሁን የምትተዉት? እኛ መያዣው መጨበጫው ጠፍቶን ግራ ገብቶናል፣ ጭራሽ ሁኔታ ምናምን እያለ ይራቀቅብኛል!”
መ.ጋ.፡- “ወደዛው እኮ ልመጣ ነበር...”
እሳቸው፡- “ታዲያ በቀጥታው መንገድ አትመጣም? የምን ዙሪያ ጥምጥም ነው! ስማ እናንት ነገርን ከስር ከስሩ እንደመጨረስ እንዲህ ዙሪያውን ስትጠመጠሙ ነው፣ ኑሮ ዙሪያችን ላይ ተጠምጥሞ እግር ከወርች ያሰረን፡፡”
መ.ጋ.፡- “እሺ፣ ያሉኝን አስተካክላለሁ። ይቅርታ፤ በአሁኑ ጊዜ ስለሚታየው የኑሮ መክበድ የሚሉት ነገር አለ?”
እሳቸው፡- “ወይ ጣጣ! ስማኝ ጋዜጠኛው፣ እስቲ አንተን ልጠይቅህ... ለመሆኑ አንተ ኑሮ እንዴት ይዞሀል?”
መ.ጋ.፡- “ያው መቼስ እንደማንኛውም ሰው እኔም ከበድ ብሎኛል፡፡”
እሳቸው፡- “አየህ ጋዜጠኛው...አየህ አይደል!”
መ.ጋ.፡- “አልገባኝም፣ ምኑን?”
እሳቸው፡- አንተ እንደማንኛውም ሰው አልክ እንጂ የአንተ እንደማንኛውም ሰው አይደለም፣ ይለያል፡፡”
መ.ጋ.፡- “እኔ ምን የተለየ ነገር ይኖረኛል ብለው ነው...”
እሳቸው፡- “እሱንማ አንተው እወቀው። ኑሮ ከበደኝ አይደለም እኮ ያልከው! እኔ ከበድ ብሎኛል አይደል ያልከው? አየህ አይደል! አንተ ኑሮ ከበድ ነው ያለህ..፣”
መ.ጋ.፡- “ይቅርታ ግን ደፈረኝ አይበሉኝና፣ ሌላው ሰው ከሚለው ምን ልዩነት አለው?”
እሳቸው፡- “አየህ አንተ ማንኛውም ሰው ያልከው ሁሉ፣ አንተ እንዳልከው ኑሮ ከበድ አይደለም ያለው፡፡ አናቱና ትከሻው ላይ ነው የተከመረበት፡፡ መከመር ስልህ ይገባሀል አይደል! ከበድ ማለትማ ጨዋታ ነው፡፡”
መ.ጋ.፡- “እርስዎ መከመር አሉት እንጂ እኔም እኮ...”
እሳቸው፡- “ቆይ ቆይማ....ስላቋረጥኩህ ይቅርታ አይደል እሚባለው! ሁለት ኪሎ ሙዝም ይዘህ ስትሄድም እኮ ከበድ ይልሀል። ሦስት ወፈር፣ ወፈር ያለ መጽሐፍ ይዘህ ብትሄድም እኮ ከበድ ይልሀል፡፡”
መ.ጋ.፡- “እሺ እንዳሉት ይሁን፡፡ ግን እስካሁን እኮ በአጠቃላይ ስለ ኑሮ መክበድ ሀሳብዎን አልነገሩኝም፡፡”
እሳቸው፡- አየህ አንተ ኑሮ ከበድ ብቻ ያለህ ስለሆንክ፣ የማትኖረውን ብነገርህ ስለማይገባህ፣ የእኔንም የአንተንም ጊዜ አናጥፋ፡፡ ኑሮ ከበድ ማለት ሳይሆን እንደ እኛ የተከመረብህ ጊዜ ያኔ እነግርሀለሁ፡፡
(ጋዜጠኞች ‘ሶፊስቲኬትድ’ እንሆናለን እያላችሁ ነገር አታበላሹማ! አሁን ‘ሶፊስቲኬትድ’ እዚህ ውስጥ ድንቅር ያለችው ምን ለመሆን ነው!)
እሳቸው የጉልት ነጋዴ ናቸው፡፡ ከፈት ያለች ቦታ ሲያገኙ ያለቻቸውን ትንሽዬ ነገር ከተሳካላቸው እየሸጡ ቤተሰብ ለማስተዳደር የሚጥሩ፡፡
መ.ጋ.፡- “እማማ፣ ገበያ እንዴት ነው?” (ኸረ በህግ! ልክ እኮ...አለ አይደል... “ስሚ አንቺ፣ እዚህ ጋ ሁለት ጃምቦ ድራፍት...” እንደማለት አደረገው እኮ!)
(የጎሪጥ ያዩታል፡፡)
መ.ጋ.፡- “አጠፋሁ እንዴ እማማ?”
ጉ.ነ.፡- “ስለ ገበያ እኔን ነው የምትጠይቀው? ሂድና ከዚህ ተነሽ፣ እዛ ፍረጭ እያሉ ቁም ስቅሌን የሚያሳዩኝን ጠይቃቸው፡፡”
መ.ጋ.፡- “የእርስዎን ሀሳብ መጀመሪያ ላግኝ ብዬ ነው፡፡ እንደሚያውቁት ሰዉ ኑሮ በጣም እየከበደው ነው፡፡ አርሶ ደግሞ የጉልት ነጋዴ ስለሆኑ አሁን ስላለው ዋጋ...”
ጉ.ነ.፡- “ስማ፣ እኔ ገበያ ጠፍቶ አፌን ከፍቼ ተቀምጫለሁ፤በጠዋት የመጣኸው ልትነጅስኝ ነው እንዴ?”
መ.ጋ.፡- “ኸረ እማማ...እንደሱ አይደለም።”
ጉ.ነ.፡- “አሁን ይቺ የእኔም ኑሮ፣ ኑሮ ሆነችና ሂድና ሰልላት ብለው ላኩህ!”
መ.ጋ.፡- “እማማ...”
ጉ.ነ.፡- “እየው ሂድና ምን በላቸው መሰለህ፣ ኑና ሁሉንም ውሰዱት ብላለች በላቸው፡፡ የእኔ ነገር እንዲህ እንቅልፍ የሚነሳችሁ ከሆነ፣ ኑና ያለችኝን ቋጥራችሁ ውሰዷት ብላለች በላቸው፡፡ አሁን ሰው በዚች ድንችና ሽንኩርት ይቀናል!”
መ.ጋ.፡- “እማማ እባክዎ እንደእሱ አያስቡ። እኔ እኮ ስለዋጋ መወደድ...”
ጉ.ነ.፡- “እኮ ስለዋጋ መወደድ አስለፍልፋት ብለው አይደል የላኩህ! ከአፌ ለቅመህ ሄደህ ቱስ እንድትልላቸው!”
መ.ጋ.፡- “እማማ አንዴ ይስሙኝ፡፡
ጉ.ነ.፡- አሁን ከአጠገቤ ትሄዳለህ አትሄድም! ዋ! ኋላ ኡኡ ብዬ ሀገር እንዳልጠራ!”
መ.ጋ.፡- “እሺ እማማ፣ ደህና ይዋሉ፡፡”
ጉ.ነ.፡-  “ምን አይነቱን ሰይጣን ነው የላኩብኝ እባካችሁ!”
‘ወጣት የነብር ጣት’ የሚሉት ጎረምሳ...ተመችቶት እንደሁ፣ አልተመቸው እንደሁ ገጽታው ላይ የማይለይ ከተሜነት፣ገና ሜዳ ላይ ጥሎት ያልሄደ ወጣት፡፡
መ.ጋ.፡- “ስማኝ... አንተ ወጣት ነህ፡፡ እንደው እንደ ወጣትነትህ፣ አሁን ያለውን የኑሮ ሁኔታ ስታየው ምን ይመስልሀል!”
ወጣት፡- “ስታየው ነው ያልከኝ?”
መ.ጋ.፡- “አዎ፣ ስታየው... የምለው ገብቶሀል አይደል?”
ወጣት፡- “ገብቶኛል፡፡ አሁን ኑሮን ሳየው ምን ይመስለኛል መሰለህ...ዳይኖሶር፡፡ በቃ እንዲህ አፉን እንደ ስታዲየም በር ከፍቶ ሊበላኝ ወደእኔ እየመጣ ያለ ዳይኖሶር ይመስለኛል፡፡”
መ.ጋ.፡- “ግን እኮ በዚህ ዘመን ዳይኖሶር የሚባል ነገር የለም፡፡” (‘ሰበር ዜና!’ ቂ...ቂ...ቂ...)
ወጣት፡- “እሱን አይደል የምልህ! አሁን ተረዳኸኝ?”
መ.ጋ.፡- “አልተረዳሁህም...”
ወጣት፡- “ቆይ ዳይኖሶር የለም ብለሀል፣ አይደል!”
መ.ጋ.፡- አዎ ብያለሁ፡፡
ወጣት፡- “እኛ ደግሞ በየፊልሙ ይህን ይመስላል እያሉ ከሚያሳዩን ውጪ ምን ይመስል እንደነበር የምናውቀው ነገር የለም። ልክ ነኝ?”
መ.ጋ.፡- “ልክ ነህ...”
ወጣት፡- “አየህ አሁን እኖርን ያለነው ኑሮ መክበድ በህልማችን እንኳን አይተነው የማናውቀው አይነት አውሬ ነው፡፡
መ.ጋ.፡- "አገላለጽህን ወድጄዋለሁ፡፡”
ወጣት፡- “ቴንከ ዩ፣! .... ደግሞ ሳልነግርህ.... ቂማ እኮ እንደ ድሮው እንጨረግደው መሰለህ! እንደ ቆሎ እንዲች በእፍኝ ነው የምንቅመው፡፡ ምን አማረህ ብትለኝ...እውነተኛ ምርቃና ነው ያማረኝ! አየህ በፊት በምርቃና አንዴ ፏ ትልና እድሜ ለአስቱካ ‘ሰለ ሰው፣ ስለ ሰው ወደ ቀድጄ ልልበሰው’ ትል ነበር...ድራፍት እንኳን ሰርቲ ብር ገብቶ ዱካኩ ሊጨርሰን ነው! በል ይመችህ አቦ!”
እሷዬዋ የከተማችን ሸላይ...
መ.ጋ.፡- “እህቴ..ሰላም ነሽ?”
እሷዬዋ፡- (ከእግር እስከራስ ቄንጠኛ አስተያየት፡፡)
መ.ጋ.፡- “የሆነ ጥያቄ ልጠይቅሽ  ነበር...”
እሷዬዋ፡- (ሎካል ጫማ ነው እንዴ ያደረገው!  የሚል አስተያየት፡፡)
መ.ጋ.፡- አሁን በሀገራችን ስላለው የኑሮ መወደድ ሀሳብሽን...”
እሷዬዋ፡- (ሳቅ እየጀመራት ሳለ ሞባይሏ ያንጫርራል፡፡) “አንቺ...ቆይ ስሚኝ፣ እዚህ በሳቅ ልፈነዳልሽ ነው... ስለምን ጠየቀኝ መሰለሽ ...ስለ ኑሮ መወደድ... እማዬ ትሙት!...የኑሮ መወደድ እያሉ በሆረር ማስመጥ ተጀመረ እንዴ?”
እናማ... የምናውቀው ኑሮና የማናውቀው ዳይኖሶር ምንና ምን ናቸው? ቂ...ቂ...ቂ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1493 times