Saturday, 12 March 2022 15:19

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ባለስልጣኖቻችን እንደ ባለሃብቶች ሳይሆን-
                                  ፋሲል የኔአለም

               የኤርትራ ባለስልጣናት በአደባባይ ድህነትን ከህዝባቸው ጋር ተካፍለው እንደሚኖሩ ለማሳየት ይሞክራሉ። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተቃራኒው ስልጣናቸውንና ሃብታቸውን ለማሳየት ውድ መኪኖችን እየነዱ ከቦታ ቦታ ሲሽከረከሩ ይታያሉ።
የኤርትራ ህዝብ ኑሮው ሲገርፈው፣ “እኛን ብቻ ሳይሆን መሪዎችንም ነው የሚገርፈው” ብሎ፣ ችግሩን ዋጥ አድርጎ ይኖራል። የኢትዮጵያ ህዝብ በተቃራኒው፣ “ይብላኝ ለእኛ እንጅ እነሱማ ምን ይጎድልባቸዋል” እያለ በባለስልጣናቱ ላይ ሲያማርር ይሰማል።
በብልጽግና ዘመን በውድ መኪና መሄድና በተሽቆጠቆጠ ቢሮ ውስጥ መስራት፣ የብልጽግና መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። ጥሩ የስራ ከባቢ ጥሩ የስራ መንፈስ ይፈጥራል የሚለው አስተሳሰብ በስህተት እየተተረጎመ፣ ያለውን አጽድቶ ከማስዋብ፣ አፍርሶ መገንባት ቀዳሚ ተመራጭ ሆኗል።
ፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ቤተ መንግስት የሚሄደው በዓመት ሁለት ጊዜ ቢሆን ነው። አብዛኛውን የስራ ጊዜውን የሚያሳልፈው፣ እንደ አንድ ተራ ዜጋ አርባ ወይም ስልሳ ዚንጎ ባላት ቆርቆሮ ቤት ውስጥ ነው። ወደ ፕሬዚዳንቱ ጊዜያዊ ቢሮ በሄድኩበት ጊዜ፣ የለበስኩት ነጭ ሸሚዝ፣ በመንገዱ አቧራ አፈር ሆኖ መመለሴን አስታውሳለሁ።
የአንዳንድ የአውሮፓ ፓርላማ ባለስልጣናትን፣ የተመድ መሪዎችን እንዲሁም የሆላንድን ከፍተኛ መሪዎች የቢሮ ሁኔታ የማየት እድል አጋጥሞኛል። የቢሮአቸው መጠንና በውስጣቸው የያዙዋቸው እቃዎች “ አንቲክ” ከመሆናቸው በስቀር፣ አንድ የኢትዮጵያ ባለስልጣን ቢያያቸው “እነዚህን ቆሻሻ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች ከፊቴ አስወግዱልኝ” የሚላቸው አይነት ናቸው።
ባለስልጣኖቻችን እንደ ባለሃብቶች ሳይሆን፣ ከአብዛኛው ህዝብ ጋር ድህነትን ተካፍለው መኖር ካልተለማመዱ በስተቀር፣ ህዝብ አይከተላቸውም ብቻ ሳይሆን፣ በራሳቸውም ላይ አደጋን እየጠሩ እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። እውነት ለመናገር፣ መርዶ ነጋሪ አትበሉኝና፣ የሚቀጥሉት ሁለት አመታት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለም ህዝብ በሙሉ ፈታኝ ዐመታት ይሆናሉ። የኢኮኖሚ ችግሩን ተከትሎ ብዙ ማህበራዊ ቀውሶች በመላው ዓለም ሊከሰቱ ይችላሉ። ይህን ችግር ለመቋቋም ቢያንስ ያለጊዜውና ለታይታ የሚወጡ ወጪዎች ቢቀነሱ መልካም ይመስለኛል።

____________________________________________

                           9ኛ ክፍል . . .
                             ገመቹ መረራ ፋና


              ጩጬዎች ነበርን። ግን የጥጃ ቀንዳሞች። አረጋሽ ዳውድ የተባለች የክፍሌን ልጅ ወደድኩ። እርግት ያለች፣ ሂጃብ ከራሷ የማይጠፋ፣ የህፃን ልጅ የመሠለ አገጭ ያላት ልጅ ነች። ታላቄ ነች፣ ምራቃቸውን ከዋጡ ጎረምሶች ጋር ስትሳሳቅ አሻግሬ እያየሁ እቃጠላለሁ። ደፍሬ መቼም አልነግራትም።
አንድ ቀን ደብዳቤ ልፅፍላት ወሰንኩ። መፃፍ ጀመርኩ። አንድ ‘ኢትዮጵያ’? የሚል ርዕስ ካለው ቀጭን የግጥም መድበል ላይ ግጥም ሰረቅኩ። የጂጂ ‘የጎጃም ገበሬ ለሸዋ ካልሸጠ’ ምናምን የሚለው ግጥም ያለበት መድበል ነው። “ዳውድ ሴት ልጅ ወልዶ ለእኔ ካልሰጠ..” እያደረግሁ ቀያየርኩት።
ችግሩ . . . እኔ መፃፌን እንድታውቅ አልፈለግኩም። ያኔ ከምንም በላይ የምፈራው ነገር ጠይቆ እምቢ መባልን ነበር። ለምንም ነገር። እና ደብዳቤውን በስሜ ፅፌ እምቢ ብትለኝ ምን ሊውጠኝ ነው? ስለዚህ ደብዳቤውን አንድ ጊዜ ከለስኩት። እጅ ፅሁፌን ከኔ መደበኛ አፃፃፍ የተለየ እንዲሆን አደረግኩ። ‘ይ’ን ሁላ በዚያች ፌክ ‘ይ’ ቀያየርኩ። በማግስቱ እረፍት ስንወጣ ደብተሯ ውስጥ ደብዳቤዬን አኖርኩ። ስም የለው፣ ምን የለው።
በማግስቱ አረጉ ቀጥታ ወደኔ መጣች። ልቤ በአፌ ልትወጣ ”አማርኛ ደብተርህን አውሰኝ” አለቺኝ። ገባኝ። ተዘጋጅቼበታለሁ። ሰጠኋት። ሄዳ አስተያየች - መሠለኝ፣ ብቻ መለሰችልኝ። የጓደኛዬን የአዲሱ/ደመላሽን ደብተር ደግሞ ተውሳ ሄደች። ያኔ ከተጠርጣሪነት ማምለጤን አረጋገጥኩ። እፎይታ ተሰማኝ!
የጅል እፎይታ መሆኑን ለመረዳት ማደግ ነበረብኝ። መውደዴን ለመናገር ፈርቼ፣ ፅፌ ሳበቃ ደሞ ማንነቴ እንዳይታወቅ ጥሬ . . . ምን እያሰብኩ ነበር? በደብዳቤዬ ተመስጣ ቢሆንስ ኖሮ? ብቻ የፀሀፊው ማንነት ሚስጥር ሆኖ ቀረ።
ውድ አረጉ፣ ይሄኔ ባለትዳርና የልጆች እናት ሆነሽ ይሆናል። ምናልባት እንደኔ ነገር የማትረሺ ከሆንሽና የ9ኛ G ክፍል የተፃፈልሽ ደብዳቤ ፀሀፊ ማንነት ሆድ ሆድሽን የሚበላሽ ከሆነ፣ ያ ሰው እኔ ነኝ።

______________________________________________________

                             ላድንቅሽ እንዴ?
                                 አበረ አያሌው

ሄሄሄ…
ያንቺ ልብ እያለ - ብራ’ን ምን ይሠራል?
ለተሰበረ ሰው - ሌላው መች ያበራል?
ያ ፈገግታሽ አለ - ከልብሽ የባሰ፤
ሐሴት በቀኔ ላይ - እየነሰነሰ።
በዚያ ላይ ስታዪኝ - ልቤ ‘የዘለለ፥
እንደ እንጨት ፈላጭ - ሲያልበኝ ከዋለ፤
ልንሳ ለዓይኖችሽ - ነፍስን ለሚዘሩ፥
ያረገደች ነፍሴን - እያንዘረዘሩ።
ላድንቅሽ ወይ?
ቁመናሽ አይከስም - ውበትሽ አይዳምን፥
በሽንጥና ዳሌ - በመልክ በምናምን፤
ውጭ አይቆምም ዓይኔ - ላፍታ ብሎ “ወየው”፥
ለጊዜው አልሳብሽው - ከላይ በሚታየው፤
እንዳዲስ ከምንም - ፈጥረሽው ይመስል፥
ዝጉ ልቡናዬ - ባንቺ ሲያሰላስል፤
እንዴት አላደንቅሽ - እንደምን አልቀኝ፥
ሙት ኾኜ አይደል ወይ - ሰፈሩ የሚያውቀኝ?
ባደንቅሽ ምን አለ?...
“በኛ” ና “በነሱ” - የፍረጃ አጥር፥
ዙሪያችንን ጋርደን - ቀናት ስንቆጥር፥
ዝም ባለው ሰፈር - የጨዋታሽ ለዛ፥
ደርሶ ‘ያደመቀው - ሙቀት እየገዛ፥
“እነሱነት የለም - እኛነት ነው እንጂ”፤
ብለሽ ለሰፈሩ - አዚመሽ ስቴ’ጂ፥
ከሰፈሩ ተርፎ፥
ግድግዳዬን አልፎ፥
ዐዲስን ሕላዌ - ከለገሰው ቤቱን፥
መዳን ከጸናልን - ፈውስሽ ሲሆን ፍቱን፥
የእኛነት ፍቅርሽ - እንደዚህ ካከመን፥
ከውጥንቅጥ ኑሮ - ካዘመመ ዘመን፤…
ላድንቅሽ እንጂ!...

__________________________________________________

                   ጀነራል መርዕድ፣ ኮሎኔል መንግስቱና ሴቪንግ ፕራይቬት ሪያን
                              ኦሃድ ቤንዓሚ


              ኮለኔል መንግስቱ የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከጀነራል መርዕድ ንጉሴ ለሚቀርብላቸው ውትወታ የሚያቀርቡት ምክንያት “የሞቱት ምን ይሉናል? በታሪክ እወቀሳለሁ፤” የሚል ነበር፤ (ከተስፋዬ ገብረኣብ “የቲራቮላ ዋሻ” ገጽ 181 የተወሰደ)፤ ተስፋዬ አያይዞ “የሞቱት እንዳይወቅሱት ሌሎች ወጣቶችን በብዛት ወደ ሞት ላከ፤” ይላል፤
በሌላ አጋጣሚ አሜሪካኖቹ በሁለተኛው የአለም ጦርነት፣ አራት ልጆቿ ወደጦር ሜዳ የሄዱበትንና ሶስቱ መሞታቸው ሲረጋገጥ “አራተኛውን አትርፋችሁ አምጡላት፤” በማለት የጦርነቱ ፊልድ ማርሻል የሰጡትን ትዕዛዝ ተከትሎ አንድ በጓድ መሪ የሚመራ ቡድን ኖርማዲ ላይ ከዘመተው ጋር ተቀላቅሎ አስከፊውን የፈረንሳይን ኦማሃ የባህር ዳርቻ የናዚ ምሽጎች አልፎ ወደ አገሪቷ ውስጥ ጠልቆ ይገባል፤ አንድ ራያን የተባለ ወታደር ለማዳን የተሰማራው ቡድን በየምሽጉ በሚገጥመው ደፈጣ በርካታ አባሎቹን ማጣትን ተከትሎ የተልዕኮውን ጠቀሜታ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ውዝግብ ይነሳል፡፡
የአንዲት እናትን ልብ ለመጠበቅና አንድ ወታደር ለማዳን ስንት ሰው መሞት አለበት? (የዚህን መልስ ከቻላችሁ ለማወቅ (የ Steven Spielberg ን “Saving Private Ryan” የተባለውን ምርጥ ተሸላሚ ፊልም ይመልከቱ፤)
ኮለኔል መንግስቱ በዚህ ለታሪክና ለሞቱት የኢትዮጵያ ልጆች ኃላፊነት ተሰምቷቸው ከሆነ፣ በውሳኔያቸው የጸኑት በጣም የሚደነቅ ነው፡፡ ነገር ግን የጦርነቱን አዝማሚያ አለመገምገምና የድልን እውንነት ሳያረጋግጡ ወገንን ማጨራረስ በቀላሉ የሚታይ ጥፋት ወይም ወንጀል አይደለም፡፡
ጀነራል መርዕድ ንጉሴ የኮለኔሉ ልበ-ደንደናነት ሲበዛ፣ የግንቦት 1981ን መፈንቅለ-መንግስት ማቀናበራቸው የተሻሉ ሰው ያደርጋቸዋል፤ መፈንቅለ-መንግስቱ ባይሳካና በወቅቱ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ግብረ-አበሮቻቸው (በተለይም አስመራ ላይ የነበሩት እነ ጀነራል ደምሴ ቡልቲ፣ ሻለቃ ካሳ ፈረደ እና ሌሎችም) የውሻ ሞት እንዲሞቱ ቢፈረድባቸውም ያልተዘመረላቸው ጀግኖች ሆነው ይቀሩ ዘንድ ተገቢ አይደለም፤
ምንም እንኳን መፈንቅለ-መንግስቱ ቢሳካ ይዞት ሊመጣ የሚችለውን ትሩፋት በ“ቢሆን” አስቀምጦ መከራከር ባይቻልም፣ ጀነራሉና ጓዶቻቸው ሊዘመርላቸውና መታሰቢያ ሊቀመጥላቸው ይገባል፡፡
እነሱ ሞተውላት፣ ቀርተው በግፍ የገደሏቸውን ኮሎኔል እንደማወደስ የከፋ ማህበራዊ ስኪዞፌርኒያ የለም፡፡

____________________________________

                           ከመንግስት ምን እጠብቃለሁ?
                              Pace Negaa


              ኑሮ እየተወደደ ነው። የዚህ ዋና ምንጩ መንግስት ነው። የምርት መጠን ሳይጨምር ገበያ ውስጥ የሚዘዋወረውን ብር መጨመር የዋጋ መናር ያመጣል። መንግስት ብዙ ብር ወደ ገበያው ለቀቀ፤ ኑሮንም አስወደደ። እና ከመንግስት ምን እጠብቃለሁ? ምንም!
ከውጭ ሀገር የሚገቡ እቃዎች ተወደዱ። የምግብ ዘይት፣ ነዳጅ፣ ብረት፣ ምስር፣ ፕላስቲክ፣ መድሃኒት፣ መኪና፣ ማሽኖች፣... ተወደዱ፣ ዋጋቸው ናረ። ለዚህም ዋና ምክንያቱ መንግስት ነው። የምንዛሪውን መጠን ከነበረበት 22 ብር በዶላር ወደ 29፣ ከ29 ወደ 36፣ ከዚያ ወደ 42፣ ከዚያ ወደ 45። አሁን ላይ የዶላር ምንዛሪው በባንክ ቤት በዶላር 52 ብር ደርሷል፣ ገና ይጨምራል። ይህ ማለት መነሻው ላይ ከነበረበት እጥፍ ማለት ነው። ይህ ማለት ሁሉም ከውጭ የሚገባ እቃ ቢያንስ ዋጋው እጥፍ ሆኗል። አንዳንዱም ከእጥፍ በላይ! መንግስት ምንዛሪውን ባይጨምር እንዲህ አይሆንም ነበር። እና ከመንግስት ምን እጠብቃለሁ? ምንም!
የፀጥታ ችግር በየቦታው አለ። ህግ የሚከበረው በትልቅ ከተማ ብቻ ነው። በሌላው ቦታ ህግ ችላ ተብሎ ይዘረፋል፣ ሰው ይታሰራል፣ ይገደላል። ይህ ሲጀመር አንድ ተብሎ በጅጅጋ ተጀመረ፤ በሻሸመኔ ዳበረ፤ በወለጋ ከረረ፤ በትግራይ አመረረ። ጦርነት ተነሳ፣ ህዝብ ተፈናቀለ፣ መንገድ ተዘጋ፣ የሚታረሰው መሬት ቀነሰ። ምርት ቀነሰ፤ ኑሮ ተወደደ። ይህ ሁሉ ሲሆን ፀጥታ እንዲጠብቅና እንዲያስከብር ኃላፊነት የሰጠነው መንግስት ዝም አለ። እና ከመንግስት ምን እጠብቃለሁ። ምንም!
እኔ ለኑሮ ውድነቱ መፍትሔ አለኝ። እኔ የኑሮ ውድነቱ በግሌ እንዳያጠቃኝ መፍትሔ አለኝ። እኔ በግሌ የኑሮ ውድነቱ አያስቸግረኝም። እኔ ኑሮ ሳይወደድ በፊት ገቢዬን ለመጨመር እተጋለሁ። ገቢዬን ኑሮ ከመወደዱ በፊት ከነበረው አሳድጌያለሁ። ገቢዬን በአንድ መስመር ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ መስመሮች አገኛለሁ። አሁንም ለማሳደግ እተጋለሁ፤ ምርጫ የለኝም። ይህንን ላለማድረግ መቦዘን አልችልም።
እኔ ለቤተሰቤ መንግስት ነኝ። ልጆቼ እያደጉ ነው፤ አሁን ፍላጎታቸው ጨምሯል፤ ወጪያቸው ከፍ ብሏል። የቤተሰቤ የወጪ ዓይነት ተቀይሯል፣ ጨምሯልም። እኔም እድሜዬ እየጨመረ ነው። እና ከመንግስት ምን እጠብቃለሁ? ምንም!
እኔ ከራሴ ለራሴ ግን አንድ ነገር እጠብቃለሁ።
ህይወቴን በቻልኩት አቅም ነገሮችን አስቀድሞ በመገመት፣ በማቀድና ደስ የሚለኝን በመስራት መኖር። ታድያ ከመንግስት ምን እጠብቃለሁ?
ከመንግስት ግን አንድ ነገር ብቻ እጠብቃለሁ፤ ከመንገዴ ላይ ገለል እንዲልልኝ!
ከመንግስት የምጠብቀው ዋና ነገር መንገዴን እንዳይዘጋብኝ ነው። ከመንግስት የምጠብቀው ዋና ነገር እንቅፋትነቱን እንዲተው ነው። ከመንግስት የምጠብቀው ዋና ነገር ራሱን እንዲያይና ለዜጎቹ አባት እንዲሆን ነው፣ ለሚያምኑት ተስፋና እንጀራ እንዲሆናቸው ነው።
ጥያቄዬ መንግስት የዜጎችን ኑሮ ከማደናቀፍ እንዲታቀብ ነው፣ የማይችለውን ሥራ እንዲተው ነው።
መንግስት ይኸው ዛሬ ደግሞ የሀጫሉ ሁንዴሳን መንገድ እመርቃለሁ ብሎ መንገድ ዘግቷል። ይህ መንገድ ተመርቆ ሥራ ከጀመረ ቆየ። አሁን እንደገና ለመመረቅ መንገድ መዝጋቱ፣ ግርግርና ጫጫታ መውደድ ነው።
ሀጫሉ ሁንዴሳ ተወዳጅና ያለ ጊዜው የተቀጠፈ አርቲስት ነው። ሀጫሉ የፖለቲካ ማጫወቻ ካርድ ከተደረገ ቆየ። እስከ መቼ እንደሚቀጥል ግን እንጃ! ከዚያ ይልቅ የሀጫሉ ማለፍ የጎዳቸውን ቤተሰቦቹን ማሰብ የበለጠ ጠቃሚ ነው። ሌላው የፖለቲካ ንግድ ነው።
ወዳጄ:- መንግስትን ተውና ራስህ ለራስህ አስብ።
መንግስት ካስቸገረህ ሰፈር ቀይር ወይም አገር ልቀቅ! አገር አልለቅም ካልህ ግን ተደራጅና መንግስትን ሞግት፣ ጠይቅ፣ ከባሰና ከቻልህም ስልጣን አስለቅቅ።
እንጂ ከመንግስት የማይችለውን ጥሩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አመራር አትጠይቅ። እሱ ቅንጦት ነው። መንግስት የቻለውን ሠራ፤ የማይችለውን ምን ያድርግልህ?
መንግስት ኑሮ ውድነቱን ያስቁምልኝ፣ ሥራ ይፍጠርልኝ፣ ፀጥታ ያስከብርልኝ፣ ጉቦ ያስቁምልኝ፣ ፍትህ ይስጠኝ፣ መልካም አስተዳደር ያስፍንልኝ ብለህ አትጠይቅ፣ አትጠብቅ። ያንን አይችልልህም። የማይችለውን አትጠይቅ!
አንድ ነገር ግን በጋራ መንግስትን መጠየቅ ተገቢ ነው። መንግስትን የሚችለውን እንጠይቅ።
መንግስት ሆይ፤ በኑሯችን ላይ እንቅፋት አትሁን! ልምራችሁ ብለህ አታደነቃቅፈን።
ሌላ ጥያቄ አላችሁ?

Read 989 times