Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 September 2012 09:46

የቤት ስራው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአ.አ ዩኒቨርስቲ በማታው ክፍለ ጊዜ የሶስተኛ ዓመት የሥነ ጽሁፍ ተማሪ ነኝ፡፡

የመማሪያ ክፍላችን አየር በተማሪዎች የጭንቀት ትንፋሽ ዳምኗል፡፡ ውጥረቱ ከዕለት ወደ ዕለት እያየለ ሄዶ፣ ዛሬ የመጨረሻው ጡዘት ላይ ደርሷል፡፡ ለወትሮው መምህሩ እስኪመጡ የነበረው ድባብ እንዲህ የተቀዛቀዘ አልነበረም፡፡ከቀልደኛነቱ የተነሳ በፍልቅልቅ ሴቶች ተከቦ የሚያመሸውና ወደፊት የተዋጣለት የኮሜዲ ፀሐፊ እንደሚሆን የተማመንንበት ብርሃኑ ግንባሩን አኮማትሮ ከፊቱ የተዘረጋው ወረቀት ላይ አቀርቅሯል፡፡ አይደለም በዚህ ነፃ ጊዜ፤ በትምህርት ሰዓት እንኳ በነዛ ውብ አይኖቿ የምታጫውተኝ ሀና፣ ከነመፈጠሬም ረስታኝ ከዚያች የማትረባ ጓደኛዋ ጋር ወረቀቷን ትናበባለች፡፡

ተማሪው በሙሉ እርስ በርስ ይናበባል፣ ይሰርዛል፣ ይደልዛል፡፡ አንድም የቦዘነ ተማሪ አይታይም፡፡ እስከ ዛሬ በሰፊው መስኮት አሻግሬ ስመለከታት፣ በጠራ ሰማይ ላይ ፈክታ የነገን ብሩህነት የምትሰብከኝ ጨረቃ እንኳ ጸአዳነቷ በከፊል ወይቦ፣ ምሉዕነቷ በብጥስጣሽ ደመና ተከፋፍሎ ሳያት፣ በእኛ ያለማወቅ ሸራ ላይ የተሳለች የፍርሀት ምልክት መሰለችኝ፡፡

መምህራችን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውንና ይበልጥም ስነ ልቡናዊ የሆኑ የወል ድክመቶቻችን በማንሳት የችግሩን ምንጭና ስፋት እንዲሁም መፍትሄውን የሚጠቁም ጽሁፍ በተወሰነ ገጽና በዳበረ ቋንቋ እንድናቀርብ አዝዘውን ተሜ ሁላ መነሻ ሀሳብ ፍለጋ ሲራወጥ ነበር የከረመው፡፡

መምህር ደሬሳ በምናውቀው ኩሩ አረማመድ ወደ ክፍሉ ዘለቁ፡፡ ይህ የቤት ስራ ተማሪውን በሙሉ ያራወጠበትና ለጭንቀት የዳረገበት ሁለት ራሳቸውን የቻሉ ምክንያቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያ ግልፅና አካዳሚያዊ ምክንያት ውጤታችን በጽሁፉ አቅም ስለመሚዘን ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ግን የአስተማሪያችን የግል ባህሪ ነው፡፡ መምህሩ በተፈጥሯቸው እንከን ፈላጊ ናችው፡፡ ምንም ያህል ብንለፋና ብንጥር እኛን ማድነቅ አይፈልጉም፡፡

ለዚህ ትውልድ ጨለምተኛ አመለካከት ካላቸው ደካሞች አንዱ ናቸው፡፡ ሌላው ቢቀር ፊታቸው እንኳን ፈገግታ የራቀውና ጨፍጋጋ ነው፡፡

ይህን የተመለከተው ብርሃኑ በአንድ ወቅት ‹‹በኮማንደር ንዴት ስነጽሁፍ ያስተምራሉ›› ብሎኝ ነበር፡፡

አንድ ወንድይራድ የተባለ ጥላቢስ ተማሪ ወደ ፊት ለፊት በመውጣት፣ ለአፍታ በእጁ የያዘውን ወረቀት መልከት ካደረገ በኋላ፣ በዚህ ጽሁፌ ማህበረሰባችን ስለሴት ያለውን አመለካከት ከሀይማኖት፣ ከፍልስፍና፣ ከወንዱ ፍላጎትና በሁለቱ ጾታዎች መካከል ካለው ስነ አካላዊ ልዩነት እንዲሁም ከሴቷ ስነ ልቦና አንፃር… እያለ ማስተዋወቅ ጀመረ፡፡

እኔ በበኩሌ ላነሳቸው የምችላቸው ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ህፀፆች ቢኖሩም ከተሰጠኝ የገፅ ነፃነት ጋር የሚሰምር መነሻ ሀሳብ ለማግኘት ግን የአጋጣሚን ምትሀት መታደል ነበረብኝ፡፡ አንድ ማለዳ ቤቴ ተቀምጬ የስብሀትን እግረ መንገድ እያነበብኩ፣ እግረመንገዴንም እናቴና ጓደኛዋ የያዙትን የቡና ላይ ወግ በከፊል ትኩረት አዳምጥ ነበር፡፡ ታዲያ በጫወታቸው መሀል ተጫዋቿ እናቴ ሽበት የወረሰውን የጓደኛዋን ፀጉር ተመልክታ፤”እንግዲህ እርጅና መምጣቱ ነው መሰለኝ” አለች ይመስለኛል ቀድሞውኑ ብሶት ነበረባቸው፡፡ ምንም እንኳን እናቴ በሽበቱ የተነሳ ለጫወታ ያለችው ቢሆንም እሳቸው ግን ደባል ምክንያት ፈጥረው እርጅናቸውን አስተባበሉ፡፡

“ሽበት እንኳን ከዘራችን የመጣ ነው፡፡ ግን እንዲያው የዘንድሮ ልጆች፡፡

አጉል ደርሰው ሰውን ያሳጣሉ” በጣም የተማረሩ ይመስላሉ፡፡

“እንዴት ምን ማለትዎ ነው” እናቴ ግራ በመጋባት ጠየቀች፡፡ እኔም መጽሐፌን አጥፌ በጥያቄ አይን ተመለከትኳቸው፡፡ መቼም የዘንድሮ ትውልድ ፈርዶበታል፡፡ እሳቸውም በበኩላቸው ከጉዳያቸው ጋር አያይዘው እንዴት እንደሚያብጠለጥሉት ለመስማት ጓጓሁ፡፡ ፊታቸውን አስረዝመው ከቡናቸው ፉት ካሉ በኋላ “ምን እንዴት አለው ገና? በጠዋቱ ቁመታቸው ተመዝዞ ፂማቸው ጎፍሮ ቢታዩ ኮ ነው እኛን ወደ ላይ የሰቀሉን፡፡ እንደው በእመአምላክ እኔ እንደነተዋበች የፀጉር ቀለም መጠቀም ስለማልወድ ነው እንጂ እውነት አርጅቼ ይመስልሻል” አሉ፡፡

ሁለቱ ሴቶች በ”ተነቃቅተናል” ዓይነት ሳቁ፡፡ ሳቃቸው እያጀበኝ ወደ አእምሮዬ የመጣው ነገር ቢኖር መነሻ ሀሳብ የማግኘቴ ጉዳይ ነበር፡፡ የዕድሜ እውነት፡፡ ዛሬ ላይ ትንሽ ትልቅ ሳይል ሁሉም ሰው የእድሜው ነገር ክፉኛ ያሳስበዋል፡፡

በራሴ ልዩ ባህሪ መሰረት ይህን ሀሳብ በፅሁፍ ከማዋለዴ በፊት በከፊልም ቢሆን እድገቱን አእምሮዬ ውስጥ መጨረስ ነበረበት፡፡ ተራዬ በመድረሱ ጽሁፌን ይዤ ለመዳሰስ የምሞክረው በመጠኑ ሰውኛውን የዕድሜ ትርጉም፣ በስፋት ደግሞ ከዚህ የትርጉም እውነታ የሚደረገውን ቅዠት አከል ሽሸት ነው፡፡” ካልኩ በኋላ በቀጥታ ወደ ፅሁፌ ገባሁ፡፡

“እድሜን በምድራዊ ትርጉሙ ከተመለከትነው ከውልደት እስከ ሞት የተዘረጋ ቀጥተኛ መስመር ነው፡፡ የዘላለማዊነትን ወይም የህይወትን ምንነት የትርጉም ጣጣ ለፍልስፍናው የትምህርት ክፍል በመተው፣ ወደ ዋናውና የቁጥር ሽሽትን መሰረት ወዳደረገው እይታችን እንዘልቃለን፡፡

በዚህ የወፍ በረር ጥናት ስለ እድሜ ባለን እሳቤ ላይ መጠነኛ ጥቁምታ ለመስጠት ያህል መሰረታዊያን ሊባሉ የሚችሉ እውነቶችን በተሰጠኝ የገፅ ነፃነት መጠን ቀነበብኳቸው እንጂ ጉዳዩ ጠሊቅ ጥናት ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ ለማንኛውም ይህን የህልም እሩጫ ከመሰረቱ ለማየት እንነሳ፡፡

እድሜን መደበቅ ወይም መዋሸት አሁን ዘመን ላይ የተፈጠረ ነገር አይደለም፡፡ ከትላንት ወደ ዛሬ እንደሚተላለፉት መልካምና አይረቤ ነገሮች ሁሉ ስለ እድሜ ያለን ግንዛቤ ምንጩ ከአያቶቻችን ነው፡፡ በጊዜው የነበሩት ሰዎች እድሜያቸው ባሻቀበ ቁጥር ወደ ሞት እየተጠጉ እንደሆነ በማሰብ እንደ መፍትሄ የተጠቀሙት ነገር ቢኖር የእድሜያቸውን ቁጥር በመቀነስ ሞትን አታለው የምድር ላይ ቆይታቸውን ለማራዘም መሞከር ነበር፡፡

በተከታታይ የመጣው ትውልድም ይህንኑ በሞት ፍርሀት ላይ የተመሰረተውን ሽሽት ይዞ የራሱን ወቅታዊ ምክንያቶች በማከል መጠቀም ቀጠለ፡፡ ህላዌ አለም በጊዜ ሀዲድ ላይ በስውር እጅ እንደምትነዳ ባቡር ነች፡፡ የሰው ልጅ ህልውናው በዚህች ፈጣን ባቡር ላይ በውልደት ተሳፍሮ በሞት ይወርዳል፡፡

መላ ተፈጥሯዊ መስተጋብር የራሱን ቀመር ጠብቆ የሚጓዝ ነው፡፡ በሚገርም ሁኔታ ግን ይህ ቅንብር መሪ ተገኘለት፡፡ ሊፈጥን፣ ሊዘገይ፣ ካስፈለገ ደግሞ ሊቆም የሚችልበት ዋናው ማዕከልም የጠቢቡ የሰው ልጅ አእምሮ ነው፡፡ ሰዎች ከጭንቀታቸው ለመገላገል በዚህ መልኩ ፈረሱ በእጃቸው ሳይኖር ልጓም መጠቀም ነበረባቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከስራው መልካምና መጥፎ ተግባር፣ ከመውደቅና መነሳቱ፣ ይልቅ ደረቁን እድሜውን የሚሸሸውን ማህበረሰብ ከምክንያትና አላማው ጋር ከተለያየ አቅጣጫ ልመለከተው እወዳለሁ፡፡

የመጀመሪያዎቹ ለስንፈታቸው እንደ መሸፈኛ ይጠቀሙበታል፡፡ ይህም ማለት የህይወታቸውን መሰረት የሚጥሉበት ወሳኝ ጊዜ በዋዛ ፈዛዛ አልያም በፈለገው ምክንያት ሳይጠቀሙበት ይቀሩና ከራሳቸው ሳይሆን ከሰዎች ፍርድ ለመዳን እድሜያቸውን ይቀንሳሉ፡፡

ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው አንዳች ጠቃሚ ነገር ሲከውኑ በዙሪያቸው ካሉት ሰዎች የሚያገኙትን አድናቆትና ከበሬታ ለማሳደግ በመሻት፣ ፍጥነታቸውና ብቃታቸው የአእምሮ ብስለት ውጤት እንጂ የልምድ ጉዳይ እንዳልሆነ ለማስረዳት፣ እንዲሁም ገና የሻለ ብዙ እንደሚሰሩ ለመተንበይ በመፈለግ እድሜአቸውን ይቀንሳሉ” ይህን ተናግሬ ለቅፅበት ቀና ብዬ መምህሩን ተመለከትኳቸው፡፡

የንባብ መነፅራቸውን ለአመል ዝቅ አድርገው በትኩረት ይመለከቱኛል፡፡ ሀሳባቸውን ስገምተው “እሺ የኛ ፈላስፋ ተራቀቅ እስቲ” እያሉ የሚያፌዙ መሰለኝና በፍጥነት ወደ ፅሁፌ ተመለስኩ፡፡

“ዝርጉን ጊዜ በባህሪ እንደከፋፈሉት አራት ወቅቶች ሁሉ የሰው ልጅ የህይወት ዘመን አካላዊና አእምሯዊ ደረጃውን በሚወስኑ የእድሜ እርከኖች የተከፋፈለ ነው፡፡ ከእነዚህም በፀደይ ወቅት የሚመሰለውን ወጣትነት መመልከት ይቸላል፡፡

ይህን ወቅት ጋሽ ስብሀት በ ‹‹ትኩሳት›› መፅሃፉ

“ጥሩ ነው ወጣት መሆን

ገንዘብ ባይኖር ጤና ይኖርሀል

መልክ ባይኖርህ አንጐል ይኖርሀል

እውቀት ባይኖርህ ጉራ ይኖርሃል

ፍቅር ባይኖርህ ተስፋ ይኖርሀል

ደስታ ባይኖርህ ንዴት ይኖርሀል ወዘተ…”

እያለ ወጣትነት እንደምን ያለ ወሳኝ እርከን እንደሆነ ይጠቁመናል፡በእርግጥም ወጣትነት የማበቢያ ወቅት ነው፡፡ ሞት ከተራራው ጀርባ ሆኖ የማይታይበት፣ ደስታ ፈንጠዝያው ዘላለማዊ የሚመስልበት፣ በልብ ውስጥም የአድራጊ ፈጣሪነት ሀልዮት የሚገንበት ዘመን ነው፡፡ ግን ይሄም የሚያልፍ ነው፡፡

እናም ሽምግልና ለስለስ ባለ ፉጨቱ ሊጠራን ይጀምራል፡፡ ይህን ጊዜ እንባንንና ተሰናብቶን የሄደውን ወጣትነት በቁጥሮች ገመድ ጠልፈን ልናብተው እንሞክራለን፡፡ አንዳንድ ፈላስፎች በእንዲህ ያለው ሃሳብ ሲሳለቁ “ፈረሱ ከተሰረቀ ወዲያ ጋጣውን መዝጋት ለምን ይጠቅማል” ይላሉ፡፡

የተማሪዎቹ ሳቅ ጋብ እስኪል ትንሽ ጠብቄ ቀጠልኩኝ፤

“ያለፈው ትውልድ አካላት የሆኑ ሰዎች አሁንም ድረስ በጥንታዊ የሞት ፍርሀት ላይ ተመስርተው ሊዋሹ ይችላሉ፤ ሆኖም ግን በዚህ ባረጀ ሀሳብ የሚመራ ዘመናዊ ሰው ቢኖር ስያሜው አላዋቂ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በሂደት ስርዓቱ ተቀይሯል፡፡

በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንዲሁም ስፍር ቁጥር በሌላቸው በሽታዎች አጋዥነት ሞት ቀላልና ቅፅበታዊ ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡ የእድሜ ፍሰቱንም ሙሉ በሙሉ ባይሆንም የዘነጋው ይመስላል፡፡ እናም ሁኔታው በደምሳሳው ቢሆን ይህን ይመስላል፡፡

እንደ መፍትሔ የምጠቁማቸው ይህን አይነቱን ዋጋ ቢስ አስተሳሰብ ለመቅረፍ የሚያስችሉ አንዳንድ ነጥቦች ይኖራሉ፡፡ በቅድሚያ በእኔ እምነት ማንኛውም ሰው የራሱን ህይወት ለሌሎች ፍርድ ማቅረብ የለበትም፤ እሱ ራሱም ቢሆን የህይወት ተሞክሮውንና ውጣውረዱን ለህሊናው ፍርድ ሲያቀርብ መስፈርቱ ወቅታዊ ንቃቱ በፈቀደለት የእውቀት ሚዛን እንጂ በእድሜው ቁጥር መሆን የለበትም፡፡

እስር በእርስም ቢሆን በእድሜ ሚዛን ላለመሰፋፈር የዘመኑን ሂደትና ለውጦች በአግባቡ መረዳት ይጠይቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ተፈጥሮ ነገሮችን እያጣጣች ይመስለኛል፡፡ በቀደመው ዘመን ሰዎች እረጅም እድሜ ሲኖራቸው ንቃተ ህሊናቸው አዝጋሚ ነበር፡፡

በአንፃሩ ያሁኑ ዘመን ሰው ከእድሜው በማይስተካከል የላቀ እውቀት አጭር እድሜ ይኖራል፡፡ በተጨማሪም በአካዳሚያዊ እውቀትና በንባብ በመታገዝ ወጣቱ ህይወቱን ለመረዳት በእጅጉ ፈጥኗል፡፡ ከ20 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች ታሪካዊ መፅሀፍ የሚፅፉበት ጊዜ ነው፡፡ በሚገባ ከተስተዋለ ከጥቂት አመታት ወዲህ ትላልቅ የትምህርት ተቋማት በንቁ ህፃናት እየተሞሉ ነው፡፡

በዚህ የስልጣኔ ዘመን ከአንዳንድ አስገዳጅ ጉዳዮች (እንደወታደራዊ ቅጥር፣ ጤናና ጋብቻ ወዘተ…) በስተቀር ሰውን በእድሜው መመዘኑ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ይሆናል፡፡ በየትኛውም የእድሜ እርከን ላይ የሚገኝ ሰው መመዘን ያለበት የተፈለገውን ስራ በብቃት ከመፈፀም አንፃር ብቻ መሆን አለበት፡፡

ከዚህ በተረፈ የእድሜ ቁጥር አስፈላጊነት አንድም ከጤና ጉዳይ ጋር በተያያዘ በህክምና ተቋማት አልያም ደግሞ ከባቡሩ በሚወርድበት ጊዜ ከመቃብሩ ራስጌ ለሚውል ልኬት ጠቀስ ፅሁፍ ብቻ ነው፡፡ “አመሰግናለሁ” አልኩና በመገላገል ደስታና የመምህሩን አስተያየት ለመስማት በመጓጓት ስሜት ተወጥሬ ወደ መቀመጫዬ ተመለስኩ፡፡

መምህሩ ከተቀመጡበት ወንበር ላይ ማስታወሻቸውን ወርወር አድርገው በመነሳት መነፅራቸውን እያስተካከሉ “እንግዲህ ስነ ፅሁፍ ማለት የፅሁፍ ውበት ነው፡፡ ግን ይህ ውበት የማይጨበጥ፣ የሠውን ልጅ ከጉብጠቱ የማያቃናና ለጨለማ ጉዞው ፋና መሆን ካልቻለ ሙት ውበት ነው፡፡

በዚህም መሰረት አሁን የቀረበውን ፅሁፍ የጭብጡን ክብደት፣ የቋንቋውን ውበት፣ ያተራረክና ለዛውንና፣ በዋነኝነት ግን ጥበባዊም ሆነ ማህበራዊ ፋይዳውን በማንፀር ከስሜታዊንት የፀዳና የነጠረ ምሁራዊ ሂስ መስማት እፈልጋለሁ” አሉ፡፡ የመምህሩን አስተያየት ተከትሎ ብዙ እጆች ተቀሰሩ፤ ጉራማይሌ አስተያየትም ተሰጠበት፡፡ እኔ ግን መሰሎቼ ለሆኑ ተማሪዎች አስተያየት ቁብ አልነበረኝም፡፡ እኔ የምጠብቀው የመምህሩን ሂስ ብቻ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን ክፍለጊዜው በመጠናቀቁ የጓጓሁለትን ምሁራዊ ሂስ ለመስማት ሳልታደል ፍርዱ በቀጠሮ እንደተላለፈበት እስረኛ አይነት ስሜት እየተሰማኝ ባለሁበት ሁኔታ መምህሩ ወጥተው ሄዱ ……

 

 

 

Read 3033 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 10:04