Tuesday, 15 March 2022 09:29

በ”ግሪን ኢነርጂ” ፍቅር የወደቀው የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

  “ለምን በኤሌክትሪክ መኪና ፑቲንን ከዩክሬን አያስወጡትም?!”
               
             ራሺያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ ተከትሎ የምዕራቡ ዓለም የማዕቀብ ዶፍ እያወረደባት የምትገኘው የፑቲን አገር፤ በመላ አውሮፓ ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደ ደቀነች ቀጥላለች-ያውም የኒውክሌር! ሩሲያ ከተለመዱት የቪዛና የኢኮኖሚ ማዕቀቦች በተጨማሪ ሰሞኑን ደግሞ የነዳጅ ዘይት ማዕቀብ ተጥሎባታል። (በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማዕቀብ የተጣለባት አገር ተብላለች!)
የአሜሪካ መንግስት ከስንት ጩኸትና ግፊት በኋላ ባለፈው ሃሙስ ነው ከሩሲያ በሚያስገባው የነዳጅ ዘይት ላይ ገደብ (ማዕቀብ) የጣለው። የአውሮፓ አገራትም ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ከሩሲያ የሚገዙትን የነዳጅ መጠን በተወሰነ ፐርሰንት  እንደሚቀንሱ ገልጸዋል፡፡ በወረራው የተነሳ አያሌ ዓለማቀፍ ኩባንያዎች ከሩሲያ ወጥተዋል፡፡ (ፑቲን ከዓለም ተነጥለዋል!)
በዚህ ፅሁፍ ስለራሺያና ዩክሬን ጦርነትም ሆነ በሩሲያ ላይ እየተጣለ ስላለው ማዕቀብ  አይደለም ማንሳት ማንሳት የተፈለገው። ይልቁንም ትኩረቱን የማያደርገው የዓለማችን ቁጥር አንድ ልዕለ ሀያል አገር  በምትባለው ታላቋ አሜሪካ ላይ ይሆናል። ከአሜሪካም በላይ ደግሞ በስልጣን ላይ የፕሬዚዳንት  ባይደንና አስተዳደር ላይ ያነጣጥራል፡፡
በነገራችን ላይ አሜሪካ ከሩሲያ ስታስገባ የነበረውንና በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በግፊትና ጫና ብዛት ገደብ ያደረገችበትን የነዳጅ ዘይት ከሌላ አገር መተካት የግድ ነው፡፡ የፕሬዝዳንት ባይደን ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፣ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ዘመን፣ የነዳጅ ዘይት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዓለማችን ቀዳሚ አገራት አንዷ    ለመሆን በቅታ ነበር-አሜሪካ፡፡ ፕሬዚዳንት ባይደን ግን በምርጫ ዘመቻቸው ላይ በገቡት ቃል መሰረት፣ ዋይት ሀውስ በገቡ ማግሰት በመጀመሪያ ያደረጉት፤ ከአሜሪካ  የነዳጅ ዘይት የማውጣትና የማምረት ሥራ የሚገድቡ ህጎችና ደንቦች ማውጣ (ማፅደቅ) ነበር፡፡
የግል የነዳጅ አምራቾችን ተስፋ የሚያስቆርጥና የሚፈታተን ቢሮክራሲም ዘርግቷል- የባይደን አስተዳደርና ዲሞክራት ፓርቲያቸው። ይሄ ደግሞ አስተዳደሩ ከሚከተለው የግሪን ኢነርጂ (ፖሊሲ) ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው! ግሪን ፖሊሲ… ግሪን ኢነርጂ… የኤሌክትሪክ መኪና… ሶላር… ታዳሽ ሃይል…crimate change … ወዘተ የአሜሪካ ዲሞክራት ፓርቲ ዋነኛ መገለጫ እየሁነ መጥቷል፡፡
የባይደን አስተዳደር ዓላማውና ዕቅዱ፤ ለጊዜው ከእነ ሩሲያና ሳውዲ አረቢያ የሚፈልገውን የነዳጅ ዘይት እየገዛ በመጠቀም፣ ለዘለቄታው ግን ሙሉ በሙሉ በግሪን ኢነርጂ መተካት ነው፡፡ (ዜሮ የካርቦን ልቀትት ለማሳካት!) ከዚያም በነዳጅ የሚሽከረከሩ መኪኖች ከአሜሪካ አውራ ጎዳናዎች ላይ ተጠራርገው ወጥተው፣ በኤሌክትሪክ በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ይሞላሉ ማለት ነው (እንደ ቴስላ)።
ክፋቱ ግን አሜሪካ ቢያንስ አሁን ለግሪን  ኢነርጂ ገና አልደረሰችም። ስለዚህም ጆ ባይደን ከሩሲያ ያስገቡት የነበረውን የነዳጅ ዘይት የሚተካላቸው የክፉ ቀን ወዳጅ (ነዳጅ አምራች!) ሲያፈላልጉ ነው የሰነበቱት የተሳካላቸው ግን አይመስሉም፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ረቡዕ ወደ ሳኡዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (UAE) ስልክ ደውለው እንደነበር ተነግሯል-አገሪቱ ለአሜሪካ የነዳጅ ዘይት እንዲሸጡላት ለመጠየቅ፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ግን ስልኩን አላነሱላቸውም ተብሏል። እንዴት? (ሆድ ይፍጀው ነው!) ይሄ መረጃ ከተሰማ በኋላ ዋናው የመነጋሪያ አጀንዳ የነዳጅ ዘይት መሆኑ ቀርቶ የስልኩ አለመነሳት ሆኗል።  የአሜሪካ የቀድሞ ወዳጅ የነበሩት ሁለቱ አገራት አሁን የሩሲያ ወዳጅ መሆናቸው ተነግሯል (በባይደን የውጪ ፖሊሲ ስህተት!)
የአሜሪካ ሪፐብሊካኖችን ከምንም በላይ ያንጨረጨረው ግን የባይደን አስተዳደር  ራሱ በአምባገነንነት ከፈረጃቸው እነቬንዝዌላና ኢራን ነዳጅ ለመግዛት ድርድር ጀምሯል መባሉ ነው፡፡ ሪፐብሊካኖች፤ አሜሪካ ከኢራን ነዳጅ እንዳትገዛ የሚከለክል አዲስ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀታቸውም ታውቋል፡፡ የአሜሪካ ዲሞክራቶች ለግሪን ኢነርጂ ያላቸው ፍቅር ተነግሮ አያበቃም። ዋና አጀንዳቸው የአየር ንብረት (climate change) ሆኗል፡፡ በአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ምርቱን ከማሳደግና በኢነርጂ ራስን ከመቻል ይልቅ ከዓለም አምባገነኖች ጋር ታርቀው ውላቸውን ማደስ ይመርጣሉ፡፡)
(ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ገደል ገብተዋል!) ይህ በዚህ እንዳለ ታዲያ፤ በአሜሪካ የነዳጅ  ዘይት ዋጋ ከ2008 እ.ኤ.አ ወዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊትር ከ4 ዶላር በላይ መናሩ ተሰምቷል፡፡ ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችልም እየተነገረ ነው- በተለይ የሩሲያና -ዩክሬን ጦርነት ከቀጠለ። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ነው ይላሉ የአገሪቱ ታዋቂ የፖለቲካ ልሂቃን፡፡ ያለ ምክንያት ግን አይደለም፡፡ አሜሪካ ሞልቶ ከተትረፈረፉት የነዳጅ ሃብት ተጠቃሚ እንዳትሆንና በኢነርጂ ራሷን እንዳትችል የተደረገችው በፕሬዚዳዳንት ባይደን ግራ ዘመም የኢነርጂ  ፖሊሲ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። አሜሪካ የነዳጅ ዘይት እያላት እንደሌላት የተደረገችው በዲሞክራቶቹ “ግሪን ፖሊሲ” ምክንያት ነው። የነዳጅ ዘይት የማውጣትና የማምረት ሂደት የተስተጓጎለው አየሩ እንዳይበከል ነው ይላሉ- እነ ጆ ባይደን። ሌሎች አገራት አየሩን እየበከሉ የሚያመርቱትን የነዳጅ ዘይት ግን ይገዛሉ።
በነራችን ላይ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሚተቹትና የሚነቀፉት በፖለቲካ ባላንጣዎቻቸው- ብቻ አይደለም፡፡ ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካ ህዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ጥናቶች ይጠቁማሉ። (በአሁኑ ወቅት የ38% ድጋፍ (ተቀባይነት) ብቻ ነው ያላቸው።
ሪፐብሊካኖች፤ በአሁኑ ጊዜ እንደሚሳዬል እየተተኮሰ ላለው የነዳጅ ዋጋ ተጠያቂው ባይደን መሆናቸውን አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ግን፡- “ለነዳጅ ዋጋ ማሻቀቡተጠያቂው ፑቲን ነው” ብለዋል- ዓይናቸውን በጨው አጥበው፡፡
የአሜሪካ የነዳጅ ዋጋ መናር የጀመረው ሩሲያ ዬክሬንን ከመውረሯ በፊት መሆኑን የሚያስታውሱት ፖለቲከኞቹ፤ የአሜሪካ የኢነርጂ ቀውስ የጀመረው ጆ ባይደን ፕሬዚዳንት በሆኑ ማግስት ነው ሲሉ ተጠያቂ ያደርጓቸዋል፡፡ (ፕሬዝዳንቱ ክሱን ባይቀበሉትም!)
የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ዘግይቶም ቢሆን ከሩሲያ የነዳጅ ምርት መግዛቱን ማቆሙን በአዎንታ የተቀበሉት የአሜሪካ ፖለቲከኞች፤ አሁንም ፕሬዚዳንቱ ነዳጅ ፍለጋ ዓይናቸውን ወደ እነ  ኢራን፣ሳኡዲና ቬኔዝዌላ ማዞራቸውን ግን ክፉኛ ይኮንናሉ፡፡
ሰሞኑን አንድ ሪፐብሊካን ሴናተር ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት፤ የአገራችን የነዳጅ ዘይት ዋጋ ማሻቀብ ከፑቲን ወረራ ጋር ፈፅሞ የተያያዘ አይደለም-ፕሬዚዳንት ባይደን  ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የነዳጅ ዋጋ በ46% ገደማ ማሻቀቡን በመግለጽ። በተመሳሳይ የዓለም የነዳጅ ዋጋም በማይታመን ሁኔታ ማሻቀቡ ይታውቃል።
በዶናልድ ትራምፕ የፕሬዚዳንትነት ዘመን አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢነርጂ 100% ራሷን ችላ  እንደነበር በድል አድራጊነት መንፈስ የሚጠቅሱት ሪፐብሊካኖች፤ ጆ ባይደን ግን የሩሲያ የነዳጅ ዘይት ጥገኛ አድርጎናል ሲሉ ክፉኛ ይወነጅላሉ፡፡ “ፑቲን ለወረራ የተደፋፈረውም አሜሪካን ጨምሮ ብዙዎች የአውሮፓ አገራት የነዳጅ ምርት ከሩሲያ እንደሚገዙ በማወቃቸው ነው ይላሉ። (የኢነርጂ ፓወር ማለት የፖለቲካ ፓወር ሆኗል!)
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደሚደመጡት፤ አሜሪካ ያላት የነዳጅ ሃብት ለ100 ዓመታት ያለ ሃሳብ አንቀባሮ የሚያኖራት ነው።
ነገር ግን በፅንፈኛ የሶሻሊዝም (ተራማጅ) እሳቤ አቀንቃኞች ተፅዕኖ ስር ወድቀዋል የሚባሉት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሚከተሉት የተሳሳተ የኢነርጂ ፖሊሲ ሳቢያ አሜሪካ  በነዳጅ ዘይት ራሷን እንዳትችል ተደርጋለች ይላሉ- ቢሊየነሩ ትራምፕ።
 የጆ ባይደን አስተዳደርና ግራ ዘመው የዲሞክራት ፓርቲቸው የሚወቀሰው በዚህ ብቻ ግን አይደለም። ለአሜሪካ ቅድሚያ ባለመስጠት (እንደ ትራምፕ America first ባለመሆን)፣ ህገወጥ ስደተኞችን በገፍ ወደ አሜሪካ በማስገባት (Open boarder poliicy) የፖሊስና ፀጥታ  ሃይሉን አቅም በማዳከም (Defund the police)፣ በኮሮና ቫይረስ ሰበብ የማስክና ክትባት ግዴታን (ማስክ ማንዴት) በመጣል፣ የዘረኝነት እሳቤን በማቀንቀን፣ በነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ፣ በከፍተኛ በግሽበት (Inflation) ወዘተ…  ይጠቀሳሉ ይወቀሳሉ፤ ይከሰሳሉም። ፕሬዚዳንት  ባይደን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና አልተሳካላቸውም።
የአሜሪካንን ወታደሮች ከአፍጋኒስታን ያስወጡበት ስትራቴጂም (Exist strategy) በዓለም ፊት ነቀፌታን  አስከትሎባቸዋል። ከተጀመረ 16ኛ ቀኑን ባቆጠረው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነትም የፕሬዚዳንት ባይደን ስም በበጎ አይነሳም። ራሳቸው ትራምፕ እንኳን “ፑቲን ዩክሬን የወረረው የባይደንን አስተዳደር ልፍስፍስነት አይቶ እንጂ እኔ በስልጣን ላይ ብሆን አይሞክራትም ነበር” ሲሉ ይደነፋሉ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ቻይና ታይዋንን እንደምትወር በእርግጠኝነት ጠብቁ-ብለዋል (ፕሬዚዳንቱ ባይደን ነዋ!”)
ፕሬዚዳንት ባይደንና አስተዳደራቸው ትችቱን ባይቀበሉትም፣ የሚበዙት ሪፐብሊካኖች ግን የትራምፕን ሃሳብ መቶ በመቶ ይደግፉታል። ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ሲመጡ “አሜሪካ ተመልሳ መጥታለች” ብለው ለዓለም ቢያስተዋውቁም፤ እውነቱ ግን በተቃራኒው ነው ይላሉ ተቺዎቻቸው። የጆ ባይደን አሜሪካ የጠነከረች ሳትሆን የተዳከመች፣ የምትፈራ ሳትሆን የምትፈራ፣ የምትመራ ሳትሆን የምትመራ (ይጠብቃል) ወዘተ… ሆናለች ባይ ናቸው- የቀድሞው ፕሬዚዳንትና ሪፐብሊካኖቹ። እኔም የአሜሪካንን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተል ሁሉ ከዚህ ብዙም የተለየ እምነት አይኖረውም ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰላም ለዓለም የነገ ሰው ይበለን!!
ብዙ ማዕቀቦች የተጣለባቸው አገራት
ሩሲያ- 5534
ኢራን-3616
ሶሪያ-2608
ሰሜን ኮሪያ-2077
ቬኔዝዌላ-651
ሚያንማር-510
ኩባ-208


Read 1469 times