Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 29 September 2012 09:53

ሤራዎችን የወለደው “ሤራ”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“አፄ ኃይለሥላሴ በ1953 ዓ.ም. ለተደረገባቸው መፈንቅለ መንግሥት ምክንያቱ ራሳቸው ንጉሡ ናቸው” የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ መጽሐፍ ስላገኘሁ ለዛሬ ዳሰሳና ቅኝት መርጬዋለሁ፡፡ በ2003 ዓ.ም ታትሞ ለአንባቢያን የቀረበው መጽሐፍ “ሤራ! በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት” በሚል ርዕስ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተፃፈ ልቦለድ መሆኑን ደራሲው ወርቅአፈራሁ ከበደ ገልፀዋል፡፡

“አደራ ሳላቀብል

አልሞትም” ያለች ነፍስ

ወ/ሮ ተዋበች በአሜሪካን አገር በሜሪላንድ ክፍለ ሀገር የሚኖሩና ዕድሜያቸው በ70ዎቹ የሚገመት ኢትዮጵያዊት ሲሆኑ፣ ለአፄ ኃይለሥላሴና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የቅርብ ሰው ስለነበሩ በዚያ አጋጣሚ ካዩትና ከሰሙት ተነስተው ያዘጋጁትን ጽሑፍ አጠናቆ ለአንባቢ የሚያደርስላቸው ሰው በማፈላለግ ላይ ነበሩ፡፡ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ /ቪኦኤ/ በጋዜጠኝነት ይሰሩ የነበሩትና Borderless love: An Ethiopian – Eritrean Love Story በሚል ርዕስ መጽሐፍ ያሳተሙት ወርቅአፈራሁ ከበደን ያስጠሩና በእጃቸው ያለውን ሰነድ “መጽሐፍ ለመሆን የሚጠቅምህ ከሆነ፣ ወስደህ ልትጠቀምበት ትችላለህ” በማለት ሰጧቸው፡፡ በካንሰር በሽታ ይሰቃዩ የነበሩት ወ/ሮ ተዋበች፤ ለመጽሐፍ ይሆናል ያሉትን ሰነድ ለደራሲው በሰጡ በሶስተኛው ቀን ሞተው፣ ቀብራቸው እዚያው አሜሪካን ተፈፀመ፡፡

ከጉራጌ ዘር የተወለደችው የንጉሡ ገድ

በሶዶ ጉራጌ አይመለል ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት አቶ ደንቦባና ወ/ሮ ዘቢደሩ “ቡጡ” ብለው ስም ያወጡላትን ልጅ ከመውለዳቸው ጥቂት ወራት በፊት በአካባቢው በትንቢት ተናጋሪነታቸው የሚታወቁት አባ ገብረማርያም የሚባሉ የሀይማኖት አባት “አልጋ ወራሽ ተፈሪ በሚነግሱበት ዕለት አንቺም ሴት ልጅ ትወልጃለሽ፤ እርሷም ለአዲሱ ንጉሥና ለቤተሰቦቻቸው በክፉም ጊዜ ሆነ በደጉ ጊዜ በረከትን ታመጣለች፤ ስለዚህ ልጅሽን ከወለድሽ ከመንፈቅ በኋላ ወደ ቤተመንግሥት ወስደሽ ለንጉሡና ለእቴጌ ገጸ በረከት አቅሪቢላቸው፤ ልጅቷም በቤተመንግሥት እንድታድግ መስጠት አለብሽ፤ ባትሰጪ ግን በእርሷም ሆነ በሌሎች ላይ ብዙ የአበሳ ዘመን ይከተላል” ብለው ነገሯቸው፡፡ አባ ገብረማርያም እንዳሉትም የቡጡ የውልደቷ ቀን ጥቅምት 23/1923 ዓ.ም ንጉሡ ዙፋን የደፉበት ዕለት ሆነ፡፡

ንጉሡና እቴጌይቱ

የወደዷት ልጅ

በትንቢቱ መሠረት አቶ ደንቦባና ወ/ሮ ዘቢደር ልጃቸውን በወለዱ በ6ኛ ወር ወደ አዲስ አበባ ቤተመንግሥት አምጥተው ስለ ትንቢቱ በመንገር፣ ቡጡን ለንጉሡና ለእቴጌይቱ ሰጡ፡፡ እቴጌም በልጅቱ ቁንጅና ተማርከው እንደሚያሳድጓትም ቃል ገብተው የወላጆቿን መጠሪያ በመቀየር “ተዋበች” የሚል ስም አወጡላት፡፡

የተዋበች ከንጉሣዊያን ቤተሰብ ጋር መሰደድ

ጣሊያን በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወርር፣ ተዋበች የ6 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ ከንጉሡና ቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ እንግሊዝ የተጓዘችው ተዋበች፤ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ጠላት ከተባረረ ከስድስት ዓመት በኋላ ከእቴጌ ጋር በመቆየት ነበር፡፡ ተዋበች በአገር ውስጥ ብዙ አልቆየችም፡፡ ወደ ስዊድን ለትምህርት ተልካ ከ11 ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ አገሯ መጣች፡፡ በጃንሆይና በእቴጌ ትዕዛዝ የጽሕፈት ሚኒስትር ለነበሩት ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ልዩ ረዳት ሆና ስራ እንድትጀምር ተደረገ፡፡

ንጉሡ የጠነሰሱት ሤራ

አፄ ኃይለሥላሴ ዘውድ የጫኑበትን 25ኛ የብር ኢዮቤልዩ በዓል በ1948 ዓ.ም ሲያከብሩ በአገሪቱና በአገዛዛቸው ውስጥ “ህዳሴ” እንዲጀመር የፈለጉ ይመስላል፡፡ ህዳሴን የሚያስመኝም ዝብርቅርቅ ነገር በዙሪያቸው ነበር፡፡ በጠላት ወረራ ወቅት የንጉሡን ወደ እንግሊዝ መሰደድ አጥብቀው የተቃወሙትን ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለማርያምን መሰል ሰዎች የዘውድ ሥርዓት እንዲያበቃ ይመኛሉ፡፡ እንደ ራስ እምሩ ያሉት ደግሞ የንጉሡ አስተዳደር እንዲሻሻልና መሬት ላራሹ ተከፋፍሎ እንዲሰጥ ይሟገቱ ነበር፡፡በሌላ ጎን በጣሊያን ወረራ ወቅት፣ የንጉሡ ተቃዋሚ ሆነው ከወራሪው ጎን የቆሙና በፋሽስቱ መንግሥት የወር ቀለብ ይሰፈርላችው የነበሩ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከነፃነት በኋላም በአገሪቱና በንጉሡ አስተዳደር ውስጥ መኖራቸው ቀጥሎ ስለነበር፣ ወዳጅና ጠላትን መለየት ማስቸገሩ የዝብርቅርቁ አካል ነበሩ፡፡ጣሊያን ቀለብ ይሰፍርላቸው ከነበሩት መሐል ልዑል ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት፣ ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሣ፣ ሼህ ሆጀሌ፣ ራስ ስዩም መንገሻ፣ ደጃዝማች አያሌው ብሩ፣ ሡልጣን መሐመድ ሃንፍሬ፣ ደጃዝማች ሆሣዕና ጆቴ፣ ደጃዝማች ዮሐንስ ጆቴ፣ ራስ ጌታቸው አባተ፣ ሱልጣን አብዱላሂ አባ ጅፋር፣ አቡነ አብርሃም፣ ሡልጣን አባ ጆቢር አብዱላሂ፣ አቡነ ይስሓቅ፣ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ አቶ ይልማ ዴሬሳ፣ አቶ ከበደ ሚካኤል፣ አቶ አየለ ገብሬና ነጋድራስ ወዳጆ አሊ እንደሚገኙበት “ሤራ! በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት” መጽሐፍ በዝርዝር ያስረዳል፡፡

ከዚህም ባሻገር በንጉሡና በአስተዳደራቸው ላይ በነበራቸው ቅሬታ ምክንያት በጠላትነት ተፈርጀው በግዞት እንዲኖሩ ከተፈረደባቸው መሐል ቢትወደድ ነጋሽ በዛብህ፣ የልጅ ኢያሱ ልጅ ዮሐንስ ኢያሱ፣ በጅሮንድ ፍቅረሥላሴ፣ አፈ ንጉሥ ገብረመድህን፣ አቶ ተፈሪ ሻረው፣ ሐኪም ዓለመወርቅ እና ሌሎችም ነበሩ፡፡

በውጭ አገራት ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጡትና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተመድበው መስራት የጀመሩት ወጣቶችም የጀመሩት እንቅስቃሴ ሌላኛው የንጉሡ ራስ ምታት ነበር፡፡ ለምሳሌ ገርማሜ ንዋይ በአገር ግዛት ሚኒስቴር ተመድቦ በሚሰራበት ወቅት አድራሻውን ራስ እምሩ ግቢ ያደረገ “የወጣቶች ማህበር” መስርቶ እንደነበር የወርቅ አፈራሁ ከበደ ታሪክ ቀመስ ልቦለድ መጽሐፍ ያመለክታል፡፡ንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ የጫኑበትን የብር ኢዮቤልዩ በዓላቸውን ከማክበራቸው በፊት እንዲህ ዓይነቶች ዝብርቅርቅ ነገሮች ማጥራት በመፈለጋቸው፣ በ1946 ዓ.ም ለጸሐፌ ትዕዛዝ በአምስት ዓመት ተግባራዊ የሚሆን ምስጢራዊ የፖለቲካ ፕሮግራም እንዲነድፉ አዘዟቸው፡፡ የሤራው ዓላማ “ዘውዳዊው ሥርዓት ከርሱም ጋር የተጎዳኙ ባህሎችና ሥርዓቶች እንዳሉ ሆነው… ኋላ ቀር አመለካከት አሉዋቸው የተባሉትን ወገኖች በዘዴ አስወግዶ፣ የዘውዳዊ ሥርዓቱን አሜን ብለው ተቀብለው ነገር ግን አገሪቷን ወደ ሥልጣኔ ለመምራት እገዛ ለማድረግ የሚችሉትን የተማሩ ወጣቶችን ለማቅረብ የሚያስፈልጉትን ሁኔታዎች” ማመቻቸት ይገባል የሚል ነበር፡፡

ለሤራው የተመለመለው አለማየሁ ኒኮላስ

“የጽሕፈት ሚኒስትር፣ ጸሐፌ ትዕዛዝና የታላቁ ማሕተም ጠባቂ” የሚል ማዕረግ የነበራቸው ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ፤ (ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመውም) ሁሉንም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በበላይነት የሚቆጣጠሩ የንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ ሰውና ቀኝ እጅ ነበሩ፡፡ በንጉሡ የተጠነሰሰውን ሤራም እንዲመሩ በዋነኛነት ኃላፊነቱ የተሰጠው ለጸሐፌ ትዕዛዝ ሆኖ “ከንጉሡ ዕድል ጋር የተያያዘ ነገር አላት” ተብላ ከጉራጌ አገር መጥታ በቤተመንግስሥት ያደገችው ተዋበች ለምስጢራዊ ሥራው በቀዳሚነት ከተመረጡት አንዷ ሆነች፡፡ በሁለተኛነት ተመልምሎ የመጣው አለማየሁ ኒኮላስ ነበር፡፡

የግሪክ ደም ያላቸው ወ/ሮ ማሪያ፣ ከባለቤታቸው ሶስት ልጆችን ወልደዋል፡፡ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን በቤተመንግሥት ውስጥ በባልትና ሙያ ምክትል ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ባለቤታቸው በሞት ከተለዩዋቸው ከሶስት ዓመት በኋላ የወለዱት አለማየሁ (አባቱ አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው ተብሎ ይታማል፡፡) የአሜሪካን አገር ትምህርቱን አጠናቆ ሲመለስ፣ የምስጢራዊው ፖለቲካ ሥራ አካል ሆኖ የተመረጠውም በንጉሠ ነገሥቱ ጠቋሚነት ነው፡፡ በዘመኑ አለማየሁ ኒኮላስ፣ ከተማ ይፍሩ፣ ገርማሜ ንዋይ በዕድሜ የሚቀራረቡ ጓደኞሞች ነበሩ፡፡ ወጣቶችና በውጭ አገራት የመማር ዕድል ስላገኙ ሲገናኙ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ይነጋገሩሉ፡፡ በዚህ መሐል ነበር አለማየሁ ለምስጢራዊው ሤራ የተመረጠው፡፡

የአምስት ዓመት ዕቅድ የተያዘለት ሤራ

ዕቅዱ በ1948 ዓ.ም ጀምሮ በቀጣዩ አምስት ዓመታት ተግባራዊ በመሆን ፍፃሜውን እንዲያገኝ ነበር የታሰበው፡፡

የንጉሠ ነገሥቱንና የዘውዳዊ ሥርዓቱን ጠላትና ወዳጅ ለመለየት ደግሞ አንዱ መፍትሔ ሆኖ የተገኘው ንጉሡ ለጉብኝት ወደ ውጭ አገር የሚሄዱበትን ወቅት የማይሳካ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማድረግ የሚል ሆነ፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱን ከጀርባ ሆነው የሚመሩት የሤራው አራማጆች ስለሚሆኑ፣ በድርጊቱ ጠላትና ወዳጃቸውን ከለዩ በኋላ ሙከራውን በማክሸፍ ዓላማችንን እናሳካለን በሚል መርህ እንቅስቃሴው ይቀጥላል፡፡

ከሤራው ጀርባ ያሉት ሤራዎች

ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ በዕቅዳቸው ዙሪያ ለልዩ ረዳታቸው ለተዋበች ደንቦባ “ይህ በእኔና በአንቺ መካከል የሚቀር ጉዳይ ነው፡፡ አየሽ ዓላማችን ከተሳካ፣ ጃንሆይን የፖለቲካ ጠላቶቻቸውን ቢያስወግዱም እንኳ አሁን የያዙትን ፍፁም ሥልጣን ይዘው እንዲቀጥሉ መፈቀድ የለበትም፡፡ ስለዚህ ከእርሳቸው ጋር በሚደረግ ድርድር፣ የዘውድ ሥርዓት ሳይገረሰስ ነገር ግን መልኩ የተለወጠ ይሆናል” የሚልና ጃንሆይ የሚያውቁትን ሀሳብ ያካፍሏታል፡፡ ሆኖም ተዋበች ሀሳቡ እንዳልተዋጠላት ታስታውቅ ነበር፡፡

“ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል” የተባው ሤራ ሳይጀመር ሚያዝያ 17 ቀን 1947 ዓ.ም ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ በድንገት 14 ዓመት ከቆዩበት ከፍተኛ ስልጣናቸው እንዲነሱ ተደረገ፡፡ በመጽሐፉ መደምደሚያ ላይ ተዋበች ለአለማየሁ “ይህ ሹም ሽር የአምስት ዓመቱ የረጅም ፕላን መነሻ እንጂ መጨረሻው አይደለም” ትለዋለች፡፡ የተዋበችና አለማየሁ ግንኙነት ወደ ጾታዊ ፍቅር ከፍ ብሎ እንደነበርም በጽሑፉ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ለጸሐፌ ትዕዛዝ መሻር ዋነኛው ምክንያት የንጉሡ የቅርብ ሰው በመሆናቸው ይጠሏቸው የነበሩ ባለስልጣናት ደባ፤ በተለይ አክሊሉ ሀብተወልድ በተደጋጋሚ ያቀረቡባቸው ክስ ቢሆንም ከንጉሡ ሤራ ጀርባ ሌላ ሤራ ማቀዳቸውን ያልወደደችላቸው ተዋበች ደንቦባ፣ ለንጉሡና መንግሥታቸው “ገድ ናት”  የተባለውን ትንቢት በዚያ አጋጣሚ ፈጽማው ይሆን? ያሰኛል፡፡ የ1953 ዓ.ምቱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራስ ከዚህ ታሪክ ጋር ምን ግንኙነት ይኖረው ይሆንም? ያስብላል፡፡ ግንኙነታቸው ወደ መሳሳም ደረጃ አድጎ የነበረው የተዋበችና የአለማየሁ ፍቅር መጨረሻስ ምን ላይ ደርሶ ይሆን? የሚለው ጥያቄም ያጓጓል፡፡

መጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል እንደሚኖረው ስለተመለከተ ቀጣዩ ክፍል ሲታተም ምላሽ እንደምናገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በመግቢያዬ ላይ እንዳመለከትኩት መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ “የ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሊደረግ የቻለው ንጉሡ ያኖሩትን የመሠረት ድንጋይ መነሻ አድርጎ ነው” የሚል ግምት እንዲኖረን የሚገፋፋ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡

 

 

 

Read 4832 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 09:59

Latest from