Saturday, 19 March 2022 10:43

የጦርነቱ ተፈናቃዮች ትኩረት እንዲሰጣቸው እናት ፓርቲ ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

      በአማራና አፋር ክልል ለሚገኙ የጦርነቱ ተፈናቃዮች ህዝቡ አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርግ የጠየቀው እናት ፓርቲ፤ ከትግራይ ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል እየገቡ ያሉ ዜጎችን የየአካባቢው ህብረተሰብ በአግባቡ ተቀብሎ ወገኖቹን እንዲንከባከብና እንዲያስተናግድ ጥሪ አቅርቧል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ የዜጎች ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ አሰቃቂ ግድያዎችና መፈናቀል ወሬዎች ለጆሮ እየተለመዱ መምጣታቸውንና ትኩረት እንደተነፈጋቸው ያስታወቀው የእናት መግለጫ፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው ያሉ ዜጎችም ከህዝቡ ተገቢውን ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑን አውስቷል።
በአሁን ወቅት በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላምና አካባቢው ከተለያዩ አካባቢዎች በተፈናቀሉ ዜጎች መጨናነቁን እንዱሁም በዚያው በአማራ ክልል ራያ ቆቦና ሰቆጣ አካባቢም በተመሳሳይ ከትገራይ ተፈናቅለው እየመጡ ባሉ በመቶ ሺህ ተፈናቃዮች መጨናነቃቸውን እናት ፓርቲ በመግለጫው አመልክቷል።
በተመሳሳይ በአፋር ክልል በጦርነቱ የተፈናቀሉ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም በየበረሃው በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁሞ፤ በአንጻሩ እነዚያን ዜጎች ለመደገፍ የሚያደርገው ህዝባዊ ርብርብና ድጋፍ መቀዛቀዙን ተቅሷል።
“እነዚህ ከሞቀ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ያሉ ወገኖች ከህዝብ እንክብካቤና ድጋፍን ይፈልጋሉ፤ የአካባቢው አመራሮችም የአካባያቸውን ሰላም በማረጋገጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ሊያመቻቹ ይገባል” ብሏል እናት ፓርቲ በመግለጫው።


Read 11189 times