Monday, 21 March 2022 00:00

አሉላ አባ ነጋ - ጀግናው ኢትዮጵያዊ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 "-አሉላ አባነጋ፣ ባንድ ዐይቸው እንባ፣ በሌላ ዐይናቸው ተስፋ እያነበቡ፣ ንጉሰ ነገስቱን አርክተው፣ ሕዝባቸውን አኩርተው፣ ባንዳዎችን እያሳፈሩ ቀጥለዋል። ዐፄ ዮሐንስም ከመኳንንት ቤት አልመጡም ብለው የሚገባቸውን ክብርና ሹመት አልነፈጓቸውም።…"
          
            ታላቁ የጦር መሪ አሉላ አባ ነጋ፣ እንደ ናፖሊዮን  ቦናፓርት፣ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ አትንኩኝ ባይ ነበሩ። ከቄስ ትምህርት ቤት፣ አንጋች  እስከነበሩበት የደጃዝማች አርአያ ቤት ያሳዩት ይህንኑ ጠባይ ነበር።
በኋላም ካሳ ምርጫ  (ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዮሐንስ) ጋ ገብተው፣ ብዙ መኳንንት ድፍረታቸውን  አይወዱላቸውም ነበር። “ቀስ በል! እኛ እያለን” የሚል የበላይነት ማንጸባረቅ ይሻሉ፡፡ ዐፄ ዮሐንስ ግን አሉላን መስማት ይፈልጋሉ። ምክንያቱም አሉላ ሁሌ የተናገሩትን ያደርጋሉ። ለጦርነትም ቢሆን ግንባር ላይ ይቆማሉ። ፈሪ አይወዱም፣ ጥቃት አይቀበሉም። ነፃነታቸውንና የሀገራቸውን ክብር ማስነካት ያማቸዋል።
በተደጋጋሚ በጉንዳጉንዲትና በጉራሪ ግንባሮች የጦር አዝማች ሆነው ያሳዩትም ይህንኑ ነበር። በዕብሪትና በኩራት አብጦ የመጣውን የግብፅ ጦር ከአፈር የቀላቀሉት በዚሁ ወኔ ነበር። ተከታታይ ሹመት፣ ማለትም ሻለቃ፣ ሊጋባ፣ በኋላም ራስ የተባሉት በሰሩት ወደር የሌለው ጀብድ ነው።
በመጀመሪያ በመረብ ወንዝ አካባቢ በጉንዳጉንዲት የተካሄደው ጦርነትና የግብፃውያን ሽንፈት ዜና የደረሰው ዲቭ እስማኤል፣ እጅግ ተበሳጭቶ፣ እጥፍ ለመበቀል በመሐመድ ራጢብ ፓሻና በልጁ ልዑል ሐሰን ካዲቭ እስማኤል የሚመራ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀና ዘመናዊ ስልጠና ያለው ሰራዊት  ከስድስት የጦር መሪዎች ጋር ልኮ በጉራሪ ግንባር አሰለፈ። ይሄኔ አጼ ዮሐንስ  በጉንዳጉንዲት ላይ ጠላትን አንበርክኮ ያሳያቸው ጀግና መሪ አሉላ አባነጋ አጠገባቸው ስለነበር ስጋት አልተሰማቸውም። ይልቅስ በልበ ሙሉነት ጦራቸውን እንዲመራ ሰጡት።
 አሉላም፡-
“አያቴ ወታደር ናቸው። አባቶቼም  እንዲሁ ወታደሮች ናቸው። እኔም ወታደር ነኝ። ያገርን ዳር ድንበርና ሉዐላዊነት ከወራሪ ጠላት የምመክት ወታደር ነኝ። እኔ በህይወት እያለሁ አገሬ በውጭ ወራሪ ሀይሎች አትደፈርም!...” በማለት ቃል ገቡ።
ይሁንና አሉላ በጀግንነት አደባባይ ስማቸው በገነነ ቁጥር በወቅቱ የነበሩ መኳንንት በቅናትና ጥላቻ ይቃጠሉ እንደነበር ይታወቃል። አንዳንዶቹም የዐፄ ዮሐንስ የሥጋ ዘመዶች ሳይቀሩ ለግብፅ ተገዝተው፣ ሀገራቸውንና ንጉሣቸውን ይወጉ ነበር። በጉራሪ ጦርነት ዋዜማ ከግብፅ ጋር ሽር ብትን ይሉ የነበሩት ደጃዝማች ወልደሚካኤል ነበሩ። እኒህ ሰው “እኛ የመኳንንት ዘር ነንና አንገዛም!” የሚል ዕብሪት እንደነበራቸው ይነገራል። ይሁን እንጂ አፄ ዮሐንስ የሐማሴን ሕዝብን ለመያዝ በማለት ደጋግመው አገረ-ገዢ አድርገዋቸዋል። … ግን ሰውየው በዚህ የሚመለሱ አልነበሩም። የግብፅን ጉርሻ ጓጉተው፣ ሀገራቸውንና ንጉሣቸውን ከድተዋል። ይሄኔ ግን አሉላ አይለማመጡም፤ … ከወላዋዮች ይልቅ ጥቂት ታማኞች ይሻላሉ በሚል አፄ ዮሐንስን ያበረታታሉ።
ዐፄ ዮሐንስም “እግዚአብሔር ክንዴን ለማጠንከር የሰጠኝ ልጄ ነው”  ይሉ ነበር። ዐፄ ዮሐንስ ለዚህ ጦርነት ያዘጋጁት ሀይል ሲገመት፣ አንዳንዶች፤ ከ60-70 ሺህ ያህል ይሆናል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ከ60-150 ሺህ ይደርሳል በማለት ይናገራሉ። ዞሮ ዞሮ ይህንን ሁሉ ጦር የሚመሩት ግን በእሳት የተፈተኑት ጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ ነበሩ።
ታዲያ አልቀረም፣ የጉራሪ ጦርነት የካቲት 28 ቀን 1868 ዓ.ም ተጀምሮ ውጊያው ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀና ዘመናዊ ስልጠና ወስዶ፣ በሰለጠኑ የጦር መሪዎች አዝማችነት ከመጣ ሰራዊት ጋር ስለነበር፣ ኢትዮጵያውያኑ የዐፄ ዮሐንስ ወታደሮች ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው ድል አድርገዋል። በዚሁ ጦርነትም የኬቪድ እስማኤል ፓሻ ልጅ የሆነው ልዑል ሐሰን እስማኤል ፓሻ በአሉላ አባነጋ ተማርኳል። አሉላ አባነጋ የጦር መሪዎችን ድል አድርጎ መማረካቸው የተለመደ ገድላቸው  ነው።
እናም ግብፆች እንዳሰቡት የኢትዮጵያን ሰራዊት ማንበርከክ አልቻሉም፤ ይልቅስ እስከዛሬ ድረስ ባሰቡት ቁጥር የሚደነግጡበትን ሽንፈት ተከናንበዋል።… አሉላ አባነጋ “ራስ” ተብለው፣ በንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ አራተኛ የተሾሙትም ይሄኔ ነው።
ይሁንና አሉላ ሕይወት አልጋ ባልጋ የሆነችላቸው ሰው አልነበሩም፤ ብዙ ምቀኛ፣ ብዙ ተገዳዳሪ ነበራቸው። ያ ብቻ ሳይሆን የትዳር አጋራቸው፣ ከእርሳቸው ጋር ለመኖር አሻፈረኝ ስላሉ፣ መለያየት ግድ ሆኖባቸዋል። በኋላም ቀድሞ ደጃዝማች አርአያ ድምፁ ቤት በወጣትነት ታፈቅራቸው የነበረችውን አምለሱን ቢያገቡም፣ ከእርሷ ልጅ አላገኙም። በፍቅር ሲኖሩ ባለቤታቸው በሞት ሲለዩዋቸው በእጅጉ አዝነው እንደነበር ታሪካቸው ይዘክራል። በለቅሷቸውም፡-
አምለሱ ነበረች የራሴ ጌጥ ክብሬ፣
የትከሻዬ ልብስ ጋሻዬና ጦሬ፣
የቤቴ ምሰሶ የቤቴ ብርሃን፣
ዛሬ ፈረሰና ጨለመኝ እኔን፣
ክንዴም ሟሸሸልሽ ደከመ ጉልበቴ።
(መምህር ሞላ ተድላ)
ጀግናም ያለቅሳል። ትዳሩ ሲፈርስ፣ አጋሩ ስትወድቅ!... አሉላ እንደ ናፖሊዮን ፍቅር ያውቃሉ፤… እንደ ጆሴፍ ስታሊን በሚስታቸው ሞት እንባ ያፈስሳሉ። ይህንን ሁለት ጽንፍ - ሕይወትም በሁለት ክንፎቿ ይዛ ትርራለች። ፈሪ ብቻ ሳይሆን የጀግና ዐይኖችም የእንባ ደመና ያረግዛሉ።
አሉላ አባነጋ፣ ባንድ ዐይቸው እንባ፣ በሌላ ዐይናቸው ተስፋ እያነበቡ፣ ንጉሰ ነገስቱን አርክተው፣ ሕዝባቸውን አኩርተው፣ ባንዳዎችን እያሳፈሩ ቀጥለዋል። ዐፄ ዮሐንስም ከመኳንንት ቤት አልመጡም ብለው የሚገባቸውን ክብርና ሹመት አልነፈጓቸውም።… ከንጉሡ ቀጥሎ ያለውን የራስነት ማዕረግ ሲሰጧቸው ብዙዎች አጉረምርመዋል። ይህንን አስመልክቶ መምህር ሞላ ተድላ፣ ሃጋይ ኤርሊክ የተባሉ ፀሀፊን ሀሳብ እንዲህ ጠቅሰዋል፡-
“ለራስ አሉላ አባነጋ ከሻለቃ  ማዕረግ ራስ ወደተባለ ከፍተኛ ማዕረግ ሲሰጥ እጅግ በጣም በአጭር ጊዜ የተሰጠ ሹመትና ክብር በመሆኑ፣ እንዲህ ዐይነት ሹመትና ማዕረግ ደግሞ ብዙ ልምድ ለሌለው (ወጣት) አስተዳዳሪ፤ አንድ ትልቅ ግዛትን መስጠት፤ በተለይም የውጭ ወራሪ ሃይሎች እየተወረወሩ በባሕር በኩል አድርገው የሚገቡትን ግዛት መስጠት፣ በተለይ ከመሳፍንትና መኳንንት ወገን ተወላጅ ላልሆነ ሰው መሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተለመደ በዓይነቱም የመጀመሪያ ክስተት ነበር። ይሁን እንጂ ዐፄ ዮሐንስ ይህን ያደረጉበት በቂና አሳማኝ ምክንያት አላቸው።
በታማኝነታቸውና በጀግንነታቸው ራስ አሉላ አባነጋ የሀማሴን ገዢ ተደርገው መሾማቸው የአካባቢውን ሰዎች አስኮርፎ፣ ወላዋይና ከሀዲ ወደነበሩ ወደ ደጃዝማች ወልደሚካኤል ቢያስገባቸውም፣ የኋላ ኋላ ባንዳዎች በእነ አሉላ እጅ መውደቃቸው አልቀረም። በተለይ የአካለ ጉዛዩ ባላባት ደጃዝማች ባህታ ሐጎስ (አባ ጥመር) ለአሉላ አባ ነጋ ቀንደኛ ጠላቶች ነበሩ።
አሳዛኙ ነገር ይህ አልነበረም። አሉላ አባነጋን ለበዝብዝ ካሳ “ይጠቅምዎታል” ብሎ የሰጠው ደጃዝማች አርአያ ድምፁ ሳይቀር፣ በኋላ አድማ መምታት ጀመረ። የስጋ ዘመዱ ለሆኑት ዐፄ ዮሐንስ የሚያቃቅርና የሚያጠራጥር ወሬ ማቀበሉን ተያያዘው። የልጁን የአምለሰትን ባል፣ አሉላን አሳልፎ ሰጠው። እንደ ይሁዳ ስሞ ከዳው። አብዛኛዎቹ የትግራይ መሳፍንትና መኳንንት “የገበሬ ልጅ ነው” ያሉትን ታላቅ ጀግና አድመው ኮረኮሙት፡፡ የጦር ሜዳው አንበሳ፣ በሳሎን ወሬ አጥንቱ ሰለሰለ። ዐፄ ዮሐንስም ሰው ናቸውና ወሬ ሰሙ፤ አዘኑ፤ ጠረጠሩትና የራስ አሉላ ግዛት የሆነውን ሐማሴንን (ምፅዋና ዙላ ወደቦችን) ለሌሎች ከፍለው ሰጡ። ይህንን ያደረጉት ተቆርቋሪ የሚመስሉ ሰዎች  ነበሩ፡፡ “አሉላ አባነጋ ሥልጣንዎትን ይነጥቅዎታል” በሚል ከውጭ ሰዎች ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና በባህር በሮቹ ያስገቡ የነበረውን የጦር መሳሪያ እንደ ማስረጃ በማቅረብ፣ ለንጉሠ ነገሥታቸው በግ ሆነው ያገለግሉ የነበሩትን ጀኔራል ጥርስ ወስጥ አስገቧቸው። ግን ለሀገራቸውና ለሕሊናቸው መቼም ታማኝ ነበሩ።
ይህ ሁሉ እየሆነ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ባላንጣዎቻቸው ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የሚያሻክራቸው ስራ እየሰሩ፣ አሉላ ግን በሰህጢ በኩፊትና በሌሎችም የጦር ግንባሮች እየተፋለሙ፣ ድል ማስመዝገቡን ተያያዙት። አሉላ ዘምተው፣ አሉላ ለጦርነት ወጥተው ድል ያላዩበት ጀምበር፣ ያላንበረከኩበት መስክ የለም።
ራስ አሉላ በዶጋሊ ላይ ለጣሊያን ያሳዩትም ይህንኑ ነበር። ጥቃት የማይወዱ፣ ሲያታልሏቸው  የማይዋጥላቸው፣ ትዕግስታቸውን እንደቂልነት የሚቆጥሩባቸውን የልባቸውን መንገርና ማሳየት የሚወዱ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጄነራል ናቸው። ስለዚህም እንደ ልማዳቸው የጣሊያን ጦር መሪ የነበረውን ኮሎኔል ክርስቶፈሪስ ከ22 የጦር መኮንኖች ጋር ገድለዋል። 418 ወታደሮችም በአሉላ አባነጋ ጦር ድባቅ ተመትተዋል።…
ቀድሞውንም በሰብቀኞች ወሬ ልባቸው የተከፋው አፄ ዮሐንስ፣ “ያለፍቃዴ- ተዋግቷል” በሚል ከጦሩ ጠቅላይ አዛዥነት አንስተዋቸዋል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ከልቡ የራሱን አድናቆት በግጥም ገልጾላቸዋል። እንዲህ፡-
1. መብቱን ዮሐንስ ለአሉላ ቢሰጠው
እንደቀትር እሳት ቱርክን ገላመጠው
ጣሊያንም ወደቀ እያንቀጠቀጠው
አጭዶና ከምሮ እንደ ገብስ አሰጣው
2. አባነጋ አሉ ካስመራ ቢነሳ
እንደ አንበሳ ሆኖ እሳት እያገሳ
የችግር ምሥጋና ባይወሳ
ቢቸግረው ጣሊያን አለ ፎርሳ ፎርሳ
3. ጣሊያን ሀገርህ  ላይ አልሰማህም ወሬ
የበዝብዝ አሽከሮች እነሞት አይፈሬ
ዘለው ጉብ ይላሉ እንደ ጎፈር አውሬ
4. አባ ነጋ አሉላ የደጋ ላይ ኮሶ
በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተቀምሶ
5. ጣሊያን ሰህጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ
በብረት ምጣዱ በሰሀጢ አደጋ
አንገርግቦ ቆላው አሉላ አባነጋ
6. ተው ተመከር ጣሊያን ይሻላል ምክር
ሰሀጢ ላይ ሆነህ መሬት ብትቆፍር
ኋላ ይሆንልሃል ላንተው መቃብር
ይቺ ሀገር ኢትዮጵያ የበዝብዝ አገር
ምንም አትቃጣ እንዳራስ ነብር
ራስ አሉላ፣ “የራሶች ራስ” የተባሉ፣ በየጦር ግንባሩ በእሳት የተፈተኑ፣ ሀገራቸውን የሚወድዱ፣ ቃላቸውን የሚያከብሩ፣ ለድል የተፈጠሩ ሰው ናቸው።
ራስ አሉላ በአምባላጌው ጦርነት፣ በዐድዋውም ውጊያ ከሀገራቸው ልጆች ጋር ቆመው ተፋልመዋል። ጣሊያኖች “ምኒልክን ይከዳሉ”  ብለው ካሰቧቸው የጦር መሪዎች መካከል ቢሆኑም፣ አሉላ መቼም ቢሆን ከሀገር ጋር ኩርፊያ የላቸውም፡፡ ኤስ ፔተሪ ዲስ በጻፉት መፅሐፍ፤ በዐድዋው ድል ታሪክ አሉላን እንዲህ ገልፀዋቸዋል፡-
“እኚህ መልከመልካም ሰው የኢጣሊያውያን ጠላት በመሆናቸው ልክ ለንጉሠ ነገስታቸው ለአፄ ዮሐንስ ብለው ከግብጣውያንና ከሱዳኖች ጋር በጥላቻና በትጋት እንደተዋጉት፣ ከኢጣሊያውያኑ ጋርም እስከ መጨረሻው በጀግንነት ተዋግተዋል። የሚበራው ዓይናቸው ያስተዋይነትና የቆራጥነት ምልክት ይታይበት ነበር። እንደ ስፓርታውያን በቁጣ ይኖሩ የነበሩት ታላቅና ብልህ ጄኔራል፤ ለህይወታቸው አስደሳች ነገር ያገኙ የነበረው ታላቅ ጦርነት ተደርጎ የክብር ቦታ ሲይዙ ነበር።
ስለ እርሳቸው ጣሊያኖች እንዲህ ብለው ነበር፤ “ይህ ራስ አሉላ ዘወትር መጥፎ ዕጣ ያመጣብናል!”
አሉላ አባነጋን፣ ጠላቶቻቸው በፍርሃት ያስቧቸዋል፤ የጦር ዐውድማዎች በናፍቆት ያስታውሷቸዋል።… ኢትዮጵያ በውለታቸው በፍቅር ልቧ ትዘምራቸዋለች!
አሉላ ለትግራይ አልተዋጉም፣ ባልቻ ለኦሮሚያ፣ ገበየሁ ለአማራ አልዘመቱም!... ሁሉም በልባቸው ይነድድ የነበረው ኢትዮጵያዊነት እንጂ ጎጥ አልነበረም።… አሉላም በኔ ልብ ከሁሉም በላይ ሆነው ይነድዳሉ!... ምክንያቱም አሉላ የኔም ናቸው!...

Read 10025 times