Sunday, 20 March 2022 00:00

ዓለማቀፍ ኤግዚቢሽን ዘርፉ የብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ገቢ ነው ተግዳሮቶችና የፖሊሲ ክፍተቶች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - ለሥራው አመቺ የሆነ የቦታ እጦት ትልቁ ችግራችን ነው
        -የአግሮ ፉድ ኤግዚቢሽን ከማሳ እስከ ጉርሻ ያለውን ፅንሰ ሃሳብ ይዟል     

         ፕራና ኢቨንትስ በአገራችን በአሁኑ ወቅት ትላልቅና ዓለም አቀፍ ኤክስፖዎችንና ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ከሚጠቀሱ ስመጥር ኩባንያዎች አንዱ ነው። ከሰሞኑ የዘንድሮን “ኢትዮ ሄልዝ” ዓለም አቀፍ የጤና ኤክስፖ በስካይ ላይት ሆቴል አካሂዷል፡፡ ለመሆኑ ፕራና ኢቨንትስ በዋናነት በምን ዘርፎች ላይ ነው የሚንቀሳቀሰው? የኩባንያው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? የኤግዚብሽንና ትሬድፌር ዘርፉ ተግዳሮቶችና የፖሊሲ ክፍተቶች ምንድን ናቸው? በአፍሪካና በአካባቢው ደረጃችን ምን ያህል ነው? ምን ያህል የውጭ ኩባንያዎች በኢግዚቢሽኖች ይሳተፋሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከፕራና ኢቨንትስ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወጣት ነብዩ ለማ ጋር በኩባንያውና በዘርፉ ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-
             ፕራና ኢቨንትስ መቼና እንዴት ተመሰረተ?
እንግዲህ ከ”አፍሪካ ቫኬሽን ክለብ” በኋላ ከጓደኞቼ ጋር ብዙ ስራዎችን ሞክረናል። ነገር ግን  ለኔ ቀልቤን የሳበውና ልሰራው የወደድኩት ይህንን ዘርፍ ነው። ይህን ዘርፍ ይበልጥ የወደድኩበት ምክንያት ደግሞ ኮሜርስ አብራኝ ስትማር የነበረች ጓደኛዬ፡- በኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት፣ ማርኬቲንግ ክፍል ነበር የምትሰራው፤ እናም ኤግዚቢሽኖች  ሲዘጋጁ ትጋብዘኝ ስለነበር ሄጄ እጎበኝ ነበር። በምጎበኝበት ጊዜ ታዲያ አዳዲስ የውጭ ኩባንያዎችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በእጅጉ ይመስጡኝ ስለነበር፣ እኔም ኤግዚቢሽን ባዘጋጅ አገር እጠቅማለሁ የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ ከዚያም በዚችው ጓደኛዬ አማካኝነት የፖልትሪውን (የዶሮውን) ኤግዚቢሽን ከሱዳኑ አጋራችን ጋር መስራት ጀመርን፡፡
ይሄ የመጀመሪያው ኤግዚቢሽናችሁ መቼ ነበር የተካሄደው?
እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም ከ16 ዓመት በፊት ነው የጀመርነው፡፡ ያን ጊዜ የሱዳኑ አገራችን ከውጪ 10 ድርጅቶች ይዞ መምጣት ቻለ፡፡ ከአገር ውስጥ 3 ድርጅቶች፣ በድምሩ 13 ድርጅቶችን አሳትፈን ነበር የፖልትሪውን ኤግዚቢሽን ያዘጋጀነው፡፡ ያን ጊዜ ፕራና ከኔ ውጪ ሰራተኛም አልነበረውም፡፡
ቀደም ባለው ዘመን ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት የመንግስት ብቻ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡  ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ጥቂት የግል ኩባንያዎች ናቸው ዘርፉን የተቀላቀሉት፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው?
እኛ ወደ ዘርፉ ስንቀላቀል ስፔሻላይዝድ ትሬድፌሮች ሶስት ብቻ ነበሩ፡፡ በአዲስቴለር የሚዘጋጅ የአውቶሞቲቭ ኤግዚቢሽን፣ በማህበሩ የሚዘጋጅ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽንና ለሌላው  በውጭ ኩባንያ የሚዘጋጅ  የአበባ ኤግዚቢሽን ብቻ ነበሩ፡፡ ከዚህ ውጩ ስፔሻላይዝድ ኤግዚቢሽኖች አልነበሩም። ሶስቱንም ብንመለከት ከአውቶሞቲቭ ኤግዚቢሽኑ ውጭ ያሉት አንዱ በማህበሩ የሚዘጋጅ፣ ሌላው በውጪ አገር ኩባንያ የሚዘጋጅ ነው። ስለዚህ የግል ዘርፉ ተሳትፎ አነስተኛ ነበር። በመንግስትም ደረጃ እየተሰራ አልነበረም፡፡ እኛ ወደ ዘርፉ ከገባን በኋላ ነው ዘርፉ መነቃቃትና መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ እኛን ተከትለው የገቡ ድርጅቶችም ነበሩ፤ አብዛኛዎቹ ሞክረውት አልቀጠሉትም፡፡ አሁን ላይ ጥቂት ድርጅቶች ነን  እየሰራን ያለነው፡፡ ስፔሻላይዝድ ትሬድፌር በመስራት ደረጃ ማለቴ ነው፡፡ በሴክተር ደረጃ 15 ዘርፎችን ፕራና ይሰራል፡፡ በዚህም ቀዳሚ ድርጅት ነን፡፡ እስከዛሬም ባለው ከአንድ ዘርፍ ውጪ የሚሰራ የትሬድፌር ድርጅት፤ የለም እኔ በማውቀው ደረጃ። ሌሎቹም እንደኛ በርካታ ዘርፎች ላይ እንዳይሰሩ የሚያደርገው በዘርፉ ላይ ያለው መጠነ ሰፊ ችግር ነው። የቢዝነስ ማህበረሰቡ በዚህ ደረጃ ሳያስብና ሳያውቀው ቀርቶ ሳይሆን በየዘርፉ ያለው አቅምና የገበያው መጠን በሚታሰበው ደረጃ  አትራፊም አይደለም፡፡ አንድ ኤግዚቢሽን በእግሩ ለማቆመና መሰረት ለመጣል በትንሹ 3 ዓመት መሰራት አለበት፡፡ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ዓመታት በሰሳራ ከስራሽ በኋላ ነው፤ ራሱን ችሎ ትንሽ ማገገሚያና  መንቀሳቀሻ የምታገኚው። ስለዚህ የቢዝነስ ሰዎች ወደዚህ ዘርፍ ሲገቡ ትርፍ አስበው ስለሚገቡና አትራፊ አለመሆኑን ሲገነዘቡ ጥለው ይወጣሉ።
የዘርፉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
የዘርፉ ችግር ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ነገር ግን የመጀመሪያው ችግር የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ የግንዛቤው ችግር በጣም ሰፊና ጠንካራ ነው። እንደነዚህ ዓይነት ኤግዚቢሽኖች ወይም ኹነቶች ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ያለማወቅና ያለመረዳት ክፍተት አለ። ይህ ችግር የሚታየው ደግሞ በህብረተሰቡም፣ በፖሊሲ አውጪዎቹም በአስፈፃሚዎቹም በኩል ነው፡፡ ለምሳሌ  እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህን ዘርፍ የሚመራ የመንግስት አካል አልነበረም። ባለፉት አስር ዓመታት ጮኸን ጮኸን፣ የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ወይም ሁለት ዓመት ሊጠጋ አካባቢ ኮንቬንሽን ቢሮ ተቋቋመ፡፡ ከዛ በፊት ይሄ ነው የሚባል ባለቤት አልነበረውም። በተበጣጠሰ መልኩ የተወሰነውን የንግድ ሚኒስቴር ይይዘዋል፣ ሌላውን ባሀልና ቱሪዝም ይይዘዋል፡፡ ብቻ ወጥነት በሌለው መልኩ ነበር የሚካሄደው፡፡ ይህ የመጀመሪያውና ትልቁ ፈተና ነው፡ ሁለተኛው ነገር “ኢቨንት ማኔጅመንት” እንደ ሙያ የሚቆጠር አልነበረም፡፡ ሙያው ትልቅ እንደሆነ ልምድ እውቀትና ክህሎት እንደሚጠይቅ ብዙ ሰዎች አይረዱትም፡፡ ይሄም በመጀመሪያው ረድፍ ላይ  የሚቀመጥ ፈተና ነው፡፡
ከዚያ ባለፈ የምናየው ችግር የፖሊሲ ነው። ዘርፉ እንዲያድግ የሚደግፍ ፖሊሲ የለም። ስለ ማይስ፣ ወይም ኢቨንት ዘርፍ የሚያወሳ ፖሊሲ አልተቀመጠም፡፡ ጉዳዩን የቱሪዝም ፖሊሲ ውስጥ ለማካተት ተሞክሯል፤ ነገር ግን እዛም ቢሆን በግልፅ ተብራርቶ ተቀምጧል ማለት አይቻልም፡፡ ይህም ዘርፉ እንዳይታወቅና እንዳያድግ በችግርነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የቦታ ችግር አለ፡፡ “ኢትዮ ኸልዝ” ዓለም አቀፍ 6ኛውን የጤና አውደ ርዕይ በስካይ ላይት ሆቴል ለማካሄድ የተገደድነው  በቦታ ችግር ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሚሊኒየም አዳራሽ ነበር የምንሰራው፡፡ አሁን ላይ ሚሊኒየም ተይዟል፡፡ ሚሊኒየም አዳራሽም ቢሆን እንደሚፈርስ ታስቦ የተሰራ እንጂ ለዚህ ሁነት ደረጃውን ጠብቆ የተሰራ አይደለም፡፡ ነገር ግን ትልቅ ስለሆነ ብዙ ድርቶችን ይይዝልናል፣ በርካታ ጉባኤዎችን ማካሄድ እንችላለን፣ ለምዝገባ የሚሆን ቦታ አለው፡፡ ንጹህና በርካታ መፀዳጃ ቤቶች አሉት፡፡ ኤሲ፣ ኢንተርኔት፣ ሳውንድ ሲስተም ስላለው የተሻለ ነው እንጂ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም። እውነቱን ለመናገር ኤግዚብሽን ማዕከል፣ እንኳን ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት ለመጋዘንነትም አይመጥንም፡፡ ከዚህ ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አለ ብትይ…ምንም የለም። አሁንም ስካይ ላይት የመጣንበት ምክንያት ከሌሎቹ ሰፋ ያለው አዳራሽ ይሄ ስለሆነና አማራጭ ስላጣን እንጂ በጣም ውድ ነው፡፡ ካለው የቦታ ስፋት አንጻር የምንክፍለው ክፍያ በጣም ውድ ነው። የተሻለ ሰፋ ያለ አዳራሽ ቢኖረን ተጨማሪ በርካታ ኩባንያዎች እናስገባ ነበር፡፡ አሁን ከፍተኛ ችግራችን ከምንላቸው ለስራው አመቺ የሆነ የቦታ እጦት አንዱ ነው፡፡
ሌላው ችግራችን ደግሞ የከስተምስ ጉዳይ ነው፡፡ ኤግዚቢሽን ሲባል የሚታይና የሚዳሰስ ነገር ይፈልጋል፡፡ ኩባንያዎች ማሽነሪያቸውን፣ ቴክኖሎጂያቸውንና አለን የሚሉትን ሁሉ አምጥተው ማሣየት ይፈልጋሉ፡፡ በተግባር ስራውን  እየሰሩ ለማሳየት ምርቶቻቸውን ማምጣት አለባቸው፡፡ እኛ አገር እቃቸውን ለማስመጣት ህግ አለ፡፡ ተመልሶ እቃው መውጣት አለበት ይላል፡፡ ግን ለሚገባው እቃ የታክስ መጠንና አስር በመቶ ዲፖዚት ማስያዝ አለባቸው፡፡ ይህን ገንዘብ ደግሞ የሚያሲዙት በብር ነው፡፡ ለምሳሌ የ1ሚ ዶላር እቃ ከሆነ የዚያ ታክስ 200 ወይም 300 ሺህ ዶላር ሊሆን ይችላል፤ ያንን መላክ አለባቸው፡፡ ይሄ የትም አገር ላይ የሌለ አሰራር ነው፡፡ ስለዚህ ሰውየው ለምን ማሽነሪዬን አመጣለሁ ይላል። ያንንም አድርጌ አመጣለሁ የሚል ሰው ካለ ገንዘቡን ማስያዝ ያለበት በብር ነው፡፡ ኮንሳይን ለመሆን ደግሞ የሀገር ውስጥ ቲን ቁጥር ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ደግሞ ወይ ኢቨንት ኦርጋናይዘሩ አሊያም ኤጀንቱ ወይም ደግሞ የትራንዚት ቢሮው ነው ይህን ሃላፊነት ወስዶ የሚያደርገው፡፡ ይህ ሲደረግ ሲመለስ በብር ነው የሚመለሰው። ስለዚህ ለሰዎቹ ገንዘቡ በምን ይላካል? የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲያችን ደግሞ ይህን አይፈቅድም። ስለዚህ ያ ኩባንያ ማሽነሪውን አምጥቶ አንድ ሁለት መቶ ካሬ ቦታ ይዞና ብዙ ሺህ ዶላሮች ከፍሎ ብዙ የስራ ቡድኖቹን ማለትም ሲኒየር ኤክስፐርቶቹን የሴልስም የቴክኑኒክም ሰዎች አምጥቶ ኤግዚቢት ማድረግ እየፈለገ ነገር ግን ህጉ ስለማይፈቅድለትና አመቺ ስላልሆነ፣ አሁን እንደምታይው ሶስት በሶስት የሆነች ዘጠኝ ካሬ ሜትር ቦታ ይዞ፣ብሮሸር አስይዞ፣ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ብቻ ልኮ፣ ያ ኩባንያ በሁለት በሶስት ሺህ ዶላር ጉዳዩን ጨርሶ ይሄዳል፡፡
የህጉ አስቸጋሪነት እንደ ሀገር እኛም ማግኘት ያለብንን ጥቅም እያሳጣን ነው ማለት ነው…
እጅግ በጣም!! ትልቁና የመጀመሪያው ነገር ብዙ ማግኘት ስንችል የውጭ ምንዛሬያችንን እንቀንሳለን። ማሽነሪው በአካል መጥቶ የምናገኘውን የቴክኖሎጂ ሽግግር እናጣለን። ማሽነሪ ይዞ ሲመጣና ብሮሸር ይዞ ሲመጣ ያለውን ልዩነት አስቢው፡፡ ማሽነሪው በተግባር እየሰራ ሲያየው የጎብኚው የመግዛት ፍላጎት ይጨምራልኮ! ሶስተኛው ነገር እነዚህ ሰዎች ሲመጡ እውቀትም ሰጥተው ነው የሚሄዱት። ምክንያቱም ሲኒየር ኤክስፐርቶቻቸው ሲመጡ  ሥልጠና ያዘጋጃሉ፤ፕረዘንቴሽን ያቀርባሉ፡፡ በተጨማሪም ከባለሙያዎች ጋር  ቁጭ ብለው ቴክኒካል ነገር ያዘጋጃሉ፡፡ ይህንን እውቀት ማግኘት ስንችል አሁን ላይ ግን የሴልስና የማርኬቲንግ ሰዎች ናቸው የሚመጡትና እንጎዳለን፡፡ የገፅታ ግንባታውንም ጭምር ነው የምናጣው። ከዚያ ባለፈ ደግሞ ለቱሪዝም ቢዝነስ የሚመጡ ሰዎች አለም አቀፍ ጥናት እንደሚያሳየው፤ 60 በመቶዎቹ ተመልሰው ለጉብኝት ይመጣሉ፡፡ ምክንያቱም ለቢዝነስ በሚመጡ ጊዜ ለአጭር ጊዜ አቅደው ነው የሚመጡት። ሲመጡም የመጡበት ቢዝነስ ላይ ይጠመዳሉ፡፡ ያችን አገር ከወደዷት ግን ተመልሰው ይመጣሉ፤ ይጎበኟታል፡፡ እኛም እንደ ኢትዮጵያዊ ብዙ አገር ስንሄድ ይህን እናደርጋለን፡፡ ሌላውም እንደዛው ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ነገር ነው እንደ አገር የምናጣው፡፡
አሁን ዋናው ጥያቄ፣ “ፕራና” ይህን ሁሉ ተግዳሮት በምን ጎኑ ችሎና ተቋቁሞ 16 ዓመታትን ዘለቀ የሚለው ነው፡፡ እስኪ ተሞክሯችሁን አጋራን?
ዋናው ነገር ይዘነው የተነሳነው ዓላማ ነው። እዚህ ኢንዱስትሪ ላይ መስራት አገር መለወጥ መሆኑን ተገንዝበናል። በየዘርፉ ስንሰራ በእያንዳንዱ ዘርፍ ላይ እሴት እንደምንጨምር፣ ትልቅ የአገር ጥቅምና ለውጥ እንደምናመጣ ስለምናምን ነው የቀጠልነው። እያንዳንዱን ትሬድፌር ስንሰራ የሚያስቆሙን እንቅፋቶች ብዙ ናቸው። ለምን እንሰቃያን የምንልበት ጊዜ አለ። ግን ደግሞ አኛ ይህን ያህል ዓመት ደክመን ሰርተን በቃ ብለን ተስፋ ቆርጠን ብንተወው፣ ማን ነው መጥቶ የሚያስቀጥለው ብለን እንጠይቅና ችግሩን ተቋቁመን እንቀጥላለን። ቢያንስ በአንድም በሌላም ቢሆን በገነባነው ፕሮፋይል ኔትወርክ ምክንያት የሚገጥሙንን እንቅፋቶች የምናልፍበት ሁኔታዎች ፈጥረናል። እኛ ይሄ እድል እያለን ተማረርን ከተውነው፣ ሌሎች አዲስ የሚመጡ ሰዎች እንዴት ይሆናሉ ብለን እናስባለን። ሁለተኛው ነገር ለፍተን ይህን ያህል ዓመት እዚህ አድርሰነው ለምን ጥለን እንሄዳለን የሚል ስሜት አለን። አገራችንን ትተን አንሄድም እንደምንለው ሁሉ፣ እኛም እያንዳንዱን ፕሮጀክቶቻችንን እንደ ልጆቻችን ነው የምናያቸው። ልጅ አጠፋ ተብሎ እንደማይጣለው ሁሉ ፕሮጀክቶቹ አክሳሪ ሆነው እንኳን አልጣልናቸውም፡፡ ለምሳሌ አሁን ያለንበት 6ኛው “ኢትዮ ሄልዝ” የጤና ኤክስፖ አራተኛውና አምስተኛው ብዙ ብር አክስሮናል ግን 6ኛውንም አካሄድን፡፡ ለምን? ብር አይደለም ዓላማችን ብዩሻለሁ፡፡ እየከሰርንም  ቢሆን መቀጠላችን በአገራችን ላይ የሚያመጣውን ጠቀሜታ ስለምናውቅ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ጥለነው ብንወጣ አዲስ የሚመጡ ሰዎች ለማስቀጠል እኛ የወሰደብንን ጊዜ ያህል ይወስድባቸዋል። ያንንስ ወስዶ ይቀጥላሉ ወይ የሚለው ጥያቄ ይመጣል። ይህን የምንለው ወደ ኢንዱስትሪው ከእኛ ጋር ገብተው የወጡትን ስለምናስታውስ ነው፡፡
እስኪ በቋሚነት ከምታዘጋጇቸው የኤግዚቢሽን ዘርፎች ጥቂቶቹን አብራሪልኝ?
መጀመሪያ ስንነሳ የምንመርጣቸው ዘርፎች ወሳኝ ሆነው  ገና፣ ማደግና ፕሮሞት መደረግ ያለባቸውን ነው፡፡ አላማችን ያደገን ዘርፍ ማስተዋወቅ ሳይሆን ለሰው ልጅ ጠቃሚ ሆነው ነገር ግን ብዙ ፕሮሞሽን የሚፈልጉትን ዘርፎችን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እኛ የተሰማራንባቸው ዘርፎች የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማዕከል ያደረጉ ናቸው። የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ምንድናቸው? አንደኛው ምግብ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሳይበላ  መኖር አይችልም። ከዚህ አንጻር የመጀመሪያው ፕሮጀክታችን የፖልትሪ(የዶሮ) ኤግዚቢሽን ነበር። በአገራችን ያለውን የምግብ ችግር ለመቅረፍ አንዱና አጭሩ መንገድ ዓለም ላይ ብዙ አገሮች የተከተሉትና ውጤታማ የሆኑበት በጣም በርካሽና በ45 ቀን ውስጥ እንዲያውም አሁን ከዚያም ባነሰ ቀን ውስጥ የሰው ልጅ በቂ ፕሮቲን የሚያገኝበትን ትልቅ እድል የሚያመቻች ዶሮ ነው፡፡ ዶሮ ላይ ብቻ ብለን አላቆምንም፡፡ እሱን አሰፋንና  የእንስሳት ሀብት (livestock)ን ጨመርንበት። የወተትና የስጋ የእሴት ሰንሰለቱን ጨምረን ቀጠልን፡፡ ከዚያ ወደ ሰብል እንግባ አልንና ወደ አግሮ ፉድ ገባን፡፡ ስለዚህ ምግብ ላይ ያለውን እሴት ሙሉ በሙሉ አካትተን መስራት ጀመርን።
እዚህ ላይ የፖልትሪ ሾው የዶሮ ዘርፉን ይይዛል፣ ላይቭስቶክ ሾው የወተትና ስጋውን ክፍል ይይዛል፣ አግሮፉድ ሾው ደግሞ የእህሉን ዘርፍ ይይዛል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ የአግሮፉድ ኤግዚብሽን ከማሳ እስከ ጉርሻ ያለውን ፅንሰ ሃሳብ የያዘ ነው። እዚህ እሴት ሰንሰለት ላይ ያሉትን በሙሉ ማለትም የግብርናውን፣ የግብርና ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂውን፣ የተቀነባበሩ ምርትና አገልግሎቶችን  እንዲሁም  የማሸጊያ የህትመትና የፕላስቲክ ዘርፉን በአጠቃላይ ያካተተ ነው። ምግብ ፕሮሰስ ከተደረገ መታሸግም ስለሚያስፈልገው ማለት ነው።
ሌላው የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ጤና ነው። የጤናው ዘርፍ ላይ መስራት አለብን ብለንም ተነሳን። አሁንም እኔና አንቺ የምንነጋገርበት 6ኛው ዙር ኤግዚቢሽን ላይ ስካይላይት ሆቴል ሆነን ነው። ጤናውን ስናነሳ ሶስቱ ዘርፎች ላይ  በብዛት ትኩረት እናደርጋለን። “Health care” የተሰኘውንና ከጤና ክብካቤ ጋር የተያያዘውን እንዲሁም ከህክምናና ከመድሃኒት ጋር የተያያዘውን ሰንሰለት እንሰራለን። ይህንን በደንብ እየሰራን ጎን ለጎን ከዚሁ ከአኗኗር ዘይቤ (life style) ከምንለው ጋር የተያያዘውንም ጨምረን እንሰራለን ማለት ነው። ሌላው የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት መጠለያ (Shelter) የምንለው ነው። ከመጠለያው ጋር ተያይዞ የሪል እስቴትና የኮንስትራክሽን ኤክስፖዎች ስላሉ እሱ ላይ መግባት አልፈለግንም፤ ግን በዚህ ዘርፍ ያልተነካ ሴክተር አለ። ሰው ቤቱ ከገባ በኋላ ኑሮውን የሚያመቻችበትና የሚያቀልበት የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎች አሉት። ይሄ አልተነካም። ለዚህ “ፊንቴክስ” ኤክስፖን ይዘን መጣን። ፈርኒቸርና ኢንቲሪየር ኤክስፖ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ባልተለመደ መልኩ ሰው ኑሮውን አንዴት ማድረግ አለበት የሚለውን ነገር የሚያሳይ ነው። ከአንድ ወር በኋላ ይካሄዳል።
በአጠቃላይ እኛ እንደነገርኩሽ፤ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ ነው ትኩረታችን፡፡ እነዚህን እየሰራን ነው ያለነው። ሌላው ፕሮሞት መደረግ ያለበት ነገር ግን እስካሁን ትኩረት ያላገኘው የፓኬጂንግ ዘርፍ ነው። ሀገራችን ደግሞ ለዚህ ዘርፍ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ታወጣለች። ነገር ግን አገር ውስጥ ሊሰራ የሚችል አይነት ምርትና አገልግሎት ነው፡፡ እሱ ላይም በደንብ ሰርተናል፡፡ “አሪፍ ፕሪንትና ፓኬጂንግ” ይባላል። ከምግብና መጠጡ ጋር ያለውን ደግሞ “ፕላስት ፕሪንት ፓክ” እንለዋለን። ሌላው የኬሚካል ኢንዱስትሪውም ላይ ሰርተን እናውቃለን። ግን ብዙ አልገፋንበትም።
እንዴት ነው በዓለማቀፉ ገበያ ላይ ራሳችሁን የምታስተዋውቁት? ከውጭ አገራትና ኩባንያዎች ጋርስ እንዴት ነው ትስስርና ግንኙነት የምትፈጥሩት?
በመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ገበያውን ስንወስደው የምንረዳበት መንገድ ነው የሚወስነው። የእኛ ውድድር ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም። የእኛ ውድድር ዓለም አቀፍ ነው። ኢትዮ  ሄልዝን ስናዘጋጅ የሄልዝ ኬርና ሜዲካል ኢግዚቢሽን የትም አገር ይዘጋጃል። ከዚያም አለማቀፍ ብለን ስንመጣ አፍሪካ ውስጥ ይዘጋጃል። ከዚያ ቀረብ ስንልም ጎረቤቶቻችን ኬኒያም ሩዋንዳም ሱዳንም ይዘጋጃል። ስለዚህ ለምንድነው ሰዎች ኢትዮጵያን መርጠው የሚመጡት? ለዚህ ይህ በቂ የሆነ የገበያ መረጃ አደራጅተናል። ዓለም ላይ ያሉት ኩባንያዎች ቀጥር ውስን ነው። በየዘርፉም ይለያያል። እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች አስር ሺህም ይሁን መቶ ሺህ ከሁሉም አገር መረጃ ይደርሳቸዋል። በዓመት ውስጥ አንድ ድርጅት ሊሳተፍ የሚችለው በአማካይ ሶስትና አራት ኤግዚቢሽን ላይ ነው። ትልልቆቹ 10 እና 12 ድረስ ሊሳተፉ ይችላሉ። በአንድ ዓመት ውስጥ ዓለምን ማካለል አይችሉም ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ተመራጭ ሆና ኩባንያዎቹ እንዲመጡ ለማድረግ አንደኛ በመረጃ በኩል የምንሄድበት ስራ አለ። ሁለተኛ በማስተዋወቅ ደረጃም እንሰራለን። ዓለም አቀፍ በሆኑ በየዘርፉ ባሉ መሪ የሚባሉ ኤግዚቢሽኖች ላይ እንሄዳለን። ጀርመን ይዘጋጅ፣ ቻይና ይዘጋጅ ወይም ዱባይ ሄደን አስተዋውቀናል። ህንድ ሄደናል፣ ቱርክ፣ ማሌዢያ፣ ፖላንድ፣ ሩሲያ፣ ዱባይ፣ ኬንያ፣ ግብፅና ሌሎችም ሀገራት ሄደን አስተዋውቀናል። መጀመሪያ የምናደርገው የትኞቹ ሀገራት ናቸው ፖቴንሻል ያላቸው የሚለውን እንለይና አቅማቸውን ከተረዳን በኋላ አንድም ከማህበራት፣ ከግል ዘርፉና ከመንግስት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ሁለትም የሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች ላይ ሄደን በመሳተፍ ፕሮሞት እናደርጋለን። በዚህ አጋጣሚ ከእነሱም ይዘን የምንመጣው አለ። አገራችንንም እናስተዋውቃለን። እኛ እንደዚህ አገር ለማስተዋወቅ ስንኳትን ወጪያችንን ገቢዎች አያወራርድልንም፣ ይጥለዋል። ለመዝናናት የሄድን አድርጎ ነው የሚወስደው። አንዱ ፈተናችንም ይህ ነው። ይህም ቀደም ሲል ካነሳሁልሽ የመረዳት ችግር ጋር የሚገናኝ ነው። ዞሮ ዞሮ እኛ በየአገራቱ እየዞርን አገራችንን በማስተዋወቃችን እስከዛሬ ባዘጋጀናቸው ኤግዚቢሽኖች ላይ 48 የዓለም አገራት ተሳትፈዋል።
አንዳንዶቹ አሁን የኢትዮሄልዝ ላይ እንዳየሽው በብሄራዊ ደረጃ ይሳተፋሉ። በኢትዮ ሄልዝ ህንድና ባንግላዴሽ ብሄራዊ ተሳትፎ አድርገዋል። ባለፈውም በአግሮ ፉድ ኔዘርላንድ፣ ቱርክና ጣሊያን እንደተሳተፉበት አይነት ማለት ነው። ሌሎቹ ደግሞ በኩባንያ ደረጃ መጥተዋል። እስከዛሬ ተሳታፊ ያላገኘነው ከአውስትራሊያ ብቻ ነው። ከአውስትራሊያ ያላገኘነው እኛም ስላልሄድን ነው፡፡ በዚያ ላይ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ትስስርም ደካማ ነው። ከርቀቱም አንጻር ያለው ግንኙነት የላላ ስለሆነ ላነሳሽው ጥያቄ መልሱ አስተሳሰባችን ነው። ውድድራችንም ዓለም አቀፍ ነው። እንደዚህ ከፍ አድርጎ ማሰብና ማሳካት እንደሚቻል አሳይተናል።
ቀደም ሲል ስለዘርፉ ተግዳሮቶች ብዙ ተነጋግረናል፡፡ እንደ ፕራና ኢቨንትስ ችግሩን ተቋቁማችሁ የዘርፉ መሪ ሆናችሁ ቀጥላችኋል። አሁን ከሚመለከተው አካል ድጋፍና ማበረታቻ እያገኛችሁ ነው?
ጉዳዩን በሁለት መልኩ እንየው። አንደኛው ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ብዙ ጮኸን ጮኸን ኮንቬንሽን ቢሮ ተቋቁሟል። ይሄ አንዱ በጎ ነገር ነው። ሌላው ነገር ለውጡ መጣ ከተባለ ጀምሮ ዘርፉ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ መካተቱም አንዱ እሰየው የሚያሰኝ ጉዳይ ነው። ቱሪዝሙ ትኩረትና ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ሲሆን የእኛ ዘርፍ በቱሪዝም ውስጥ የተካተተ ስለሆነ አብሮ ቅድሚያ ያገኘ በመሆኑ በዚህ ደስ ይለናል። ቢዝነስ ቱሪዝም ተብሎ ነው የሚታሰበው። የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም በሂደት የሚፈቱ ናቸውና መልካም ነው።
ሁለተኛው ጉዳይ “MIES” ኢንዱስትሪው ስትራቴጂ ዶክመንት ከIFC ጋር ሆኖ ቱሪዝም ኢትዮጵያ እያለ አድርገናል። ይህ መሆኑ ኮንቬንሽን ቢሮው እንዲቋቋም አግዞናል። ይህ ትልቅ እርምጃ ነው። ይሄ እንዳለ ሆኖ ቅድም የዘርፉ ተግዳሮቶችን ስገልጽ ያልጠቀስኳቸው ፈተናዎች አሉ። እነሱን በመፍታት ደረጃ ምንም አልተሰራም። ኮንቬንሽን ቢሮው ከተቋቋመ የሀገራችን አለመረጋጋትና የመዋቅር ለውጡ ለእንቅስቃሴ አመቺ አልነበሩም። አሁን መረጋጋቶች እየታዩ ስለሆነ መንቀሳቀስ ይጀምራል ብዬ አምናለሁ። ይህንን ለማድረግ እንደ ፕራና ብቻችንን ስለማንችል ሌሎቹም ብቻቸውን ስላልቻሉ በጋራ ሆነን የማይስ ኢንዱስትሪ ማህበር አቋቁመናል። አራት ትሬድፌር አዘጋጆችና ስድስት ኢቨንት አዘጋጆችን በአባልነት የያዘ ነው ማህበሩ። የአባልነት ሥራው ላይ እየሰራን ነው፡፡ ሌሎችም ተካትተውበት ጠንከር ያለ ሆኖ ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ።
ፕራና ኢቨንትስ የት ደርሶ ማየት ነው ህልምህ?
ትልቁ ራዕያችን በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት ኢቨንትና ኤግዚቢሽን አዘጋጆች አንዱ መሆን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ጥሩ መስመር ላይ ነን ብለን እናምናለን፡፡ እንደ መርህም ያስቀመጥነው አዲስ አበባን በአፍሪካ የሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና አውደ ርዕዮች መዲና ማድረግ ነው፡፡ እንደ ፕራና ያስቀመጥነውም ግብ ቢያንስ በዓመት 24 የሚሆኑ ስፔሻላይዝድ ትሬድፌሮችን ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህንን በትንሹ ሞክረነዋል፡፡ በዓመት እስከ አምስትና ስድስት እየሰራን ነው፡፡ ወደፊት ነገሮች እየተመቻቹ ሲሄዱ እውን ለማድረግ የሰው ሀይል እያሰፋን፣ ዘርፎችን እየጨመርን እንሄዳለን፡፡ መሰራት ያለባቸውንም ዘርፎች መርጠን ጨርሰናል። ነገሮች ሲመቻቹ ወደ ትግበራ እንገባለን። ልምዱንም በ45 ቀናት ሶስት የንግድ ትርኢቶችን በመስራት ሞክረናል፤ አቅማችንንም ፈትሸናል። ከዚህ ባለፈ ከኢትዮጵያም ወጥተን ሌሎች የአፍሪካ  አገራት ላይ የመስራት እቅድ አለን። ምክንያቱም በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት የሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ከአውሮፓና ከእስያ በሚመጡ ድርጅቶች የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ ይሄ ትክክል ነው ብለን አናምንም፡፡ የአፍሪካን ገበያ በአፍሪካዊያን መምራትና ማበልፀግ ይቻላል የሚል እምነት አለን፡፡ የኢትዮጵያን ገበያ በኢትዮጵያዊያን መምራት እንደሚቻለው ማለት ነው፡፡ በአፍሪካም ያለን አስተዋፅኦ ያስፈልጋል ብለን ስለምናምን እናሳካዋለን።
በመጨረሻ አልተነሳም የምትለው ወሳኝ ጉዳይ ካለ…..
ትልቁ ጉዳይ የማይስ ኢንዱስትሪው ወይም የኤግዚቢሽኑ ኢንዱስትሪ ጠበብ አድርገን ስንወስደው፣ በዓለም ላይ ትልቅ በጎ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ነው፡፡ ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች ማደግ የቆመ ዘርፍ ነው፡፡ ይህንን ኢቨንት ስናዘጋጅ ከኢቨንት ዘርፉ ይልቅ የጤና ዘርፉ ነው የሚያድገው፤ ኢኮኖሚውም ላይ የሚያመጣው በጎ ተፅኖ ትልቅ ነው፡፡  እንደ እኔ ዘርፉ ገና ያልታና ያልተነካ ሀብታችን ነው። በአፍሪካ ደረጃ ብዙ ተወዳዳሪ የሚያደርጉን አቅሞች አሉ። አንደኛው ገበያችን ነው፡፡ ሁለተኛው የአየር ንብረታችን ነው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠንካራ መሆን ነው። ከመላው ዓለም ጋር በቀጥታ መገናኘታችን ተወዳዳሪ ያደርገናል። አብዛኞቹ ዘርፎች እያደጉ ስለሆነ ኢኮኖሚያችን በፍጥነት ማደግ የሚችል ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ አንጻር እነዚህ ዘርፎች ላይ ብንሰራ ብዙ ገንዘብ ሳናወጣ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ማግኘት የምንችልበት ነው። ቡና 30 እና 40 ሚሊዮን ሰው ተሳትፎበት እስከዛሬ በዓመት 1 ቢሊዮን ዶላር  አላመጣም። በዚህ ዘርፍ ግን በጥቂት ኩባንያዎች ሥራ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን ማምጣት ይቻላል ጀርመንን ብንወስድ በኤግዚቢሽን ጠንካራ ከሚባሉ አገሮች አንዷ ናት። በ2019 ከኤግዚቢሽን  በዓመት 28 ቢሊዮን ዩሮ ማመንጨት ችለዋል፡፡ ሩዋንዳ በቅርቡ ኮንቬንሽን ሴንተር ከፍታ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ቀዳሚ መዳረሻ ሆናለች፡፡ በኢቨንት ማኔጅመንት ትንሽ የምትባል አገር ብትሆንም፣ ሲስተም ስለዘረጋችና ጉዳዩ ስለገባት ነው ይህን ለውጥ ያመጣችው፡፡ ኢትዮጵያም ይሄ ከገባትና የሚያንቁ አሰራሮቿን አሻሽላ ምቹ ሁኔታዎችን ከፈጠረች፣ 10 እና 15 ቢሊዮን ዶላር ከዚህ ኢንዱስትሪ ማመንጨት ብርቅ ላይሆን ይችላል፡፡  ግን ትልቅ ስራ ይጠይቃል፡፡ ዋና ዋና ሴክተሮችን መርጠን ከሰራን በተደማጭነትም በኢኮኖሚም አቅማችንን እናጎለብታለን ብዬ አምናለሁ።

Read 1144 times