Saturday, 19 March 2022 11:11

‘የፈገግታ የሴራ ትርክት’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

"እና የተከሰከሱ ፊቶች በበዙበት ዘመን፣ ትንሹም፣ ትልቁም ካብ ለካብ በሚተያይበት ዘመን፣ ይበልጥ ፈገግ ማለት እንደ መልካምነት ሳይሆን...አለ አይደል... ‘የፈገግታ የሴራ ትርክት’ (ቂ...ቂ...ቂ...) ነገር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ለማለት ያህል ነው፡፡"
             
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የምር ግን ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ግራ ገባን እኮ! ኮሚክ ነገር እኮ ነው...ደህና ወዳጅ ያሉትን ሰው አቀፍ አድርጎ “ደህና ሰነበትክ ወይ?” “ሰዉም ከብቱም ጤና ከረምክ ወይ?” ለመባባል “ምን ያስብብኝ ይሆን?” “አቅፌ ሰላም ብላት በሌላ ትተረጉምብኝ ይሆን!” ልንባባል ምንም ያልቀረን ደረጃ ስንደርሰ አሪፍ ነገር አይደለም፡፡ ቀደም ሲል እኮ እጆቻችሁን አምስት ጊዜ ሦስት መቶ ስድሳ ዲግሪ እያሽከረከራችሁ የምትጨምቁት እሱ፣ የምታቅፏት እሷ፣ እንዴት ነው ለስንት ዘመን ስታደርጉት የቆያችሁት ነገር ድንገት የእናንተ ጠበቅ አድርጎ ማቀፍ የሚያስደነግጠው? ምን አዲስ ነገር መጥቶ ነው?
“ጉንጭ ለጉንጭ ለመነካካት እንኳን ሞክረን የማናውቀው ሰዎች፣ እንዲህ ግራና ቀኝ ግጥም አድርጋ ይዛ አትመጨመጨኝ መሰለሽ!”
“ይሄኔ ዛሯ ተነስቶባት ይሆናላ!”
“አትይኝም! የእውነት ዛር አለባት እንዴ!”
“እኔ እንጃ፣ ብቻ ሳያት አንድ ብቻ ሳይሆን አንድ መቶ ዛር ያለባት ነው የሚመስለኝ፡፡”
እናማ...እናንተ ግጥም አድርጋችሁ የምትመጨምጩ እንትናዬዎች፣ የነገሮች አተረጓጎም እየተለወጠ ነውና ለምኑም ለምናምኑም ሁለቴ እያሰባችሁማ፡፡
“ስማ ያ ማነው የምትለው ያደረገኝን ልንገርህ?”
“አልፈልግም ብልም መንገርህ ስለማይቀር... ንገረኝ፡፡”
“ትንፋሼ እስኪያጥር አቅፎ አይመጨምጨኝ መሰለህ!;
“ታዲያ ምን አለበት፤ ናፍቆቱን ሊገልጽልህ ፈልጎ ይሆናላ!”
“አንተ ምነ ነካህ፣ የምልህን እየሰማኸኝ ነው?”
“የአቅሜን ያህል እየሰማሁ ነው፡፡ እስከሚገባኝ ድረስ ስትተዋወቁ ረጅም ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ አቅፎ ሰላም ቢልህ ምን ችግር አለው?”
“የሆነ ነገር ቢኖር እንጂ መሀል መንገድ ላይ ማቀፍ ምን የሚሉት ነገር ነው!”
“አንተ ሰውዬ፣ ከድራፍት ወደ ጠጅ ዞርክ አንዴ?”
“አቦ አትዘባርቅ፡፡”
“የሁለታችሁ መተቃቀፍ ምን አዲስ ነገር አለውና ነው፡፡ የሚያያችሁ ሰዉ ቋቅ እስኪለው በቀን ሰባት ጊዜ አይደል እንዴ በየሰበቡ ስትተቃቀፉ የምትውሉት!”
“ከዚህ በፊት እንደዚህ ትንፋሽ እስከሚያጥረኝ አይጨምቀኝም ነበራ! እኔ ለራሴ መንምኜ የጠበበኝ ጃኬት ሁሉ ከትከሻዬ ላይ እየተንሸራተተ አስቸግሮኛል... ጭራሽ መጨናነቅ አለብኝ እንዴ!”
“ታዲያ እንደእሱ አትለኝም፡፡ ታዲያ ችግርህ የእሱ ማቀፍ ሳይሆን የትከሻዬ መሳሳት ነው ብለህ ቁርጡን አትነግረኝም!”
“እየው እንግዲህ ነገር ማጣመም ጀመራችሁ!”
“እዚህ ያለሁት እኔ፣ ጀመራችሁን ምን አመጣው!”
የምር ግን...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... እንደ አንድ ግለሰብ የተናገራችሁትን፣ ወይም የሠራችሁትን የወል የማድረግ ነገር ግርም አይላችሁም! በተለይ ደግሞ የተናገራችሁት ወይም ያደረጋችሁት ነገር ለዛኛው ወገን የማይመቸው ከሆነ፣ ብቻ ምን አለፋችሁ፣ ተበድሮም ተለቅቶም ከሆነ ‘ኢንቪዝብል’ ከሚባል አይነት ስብስብ ነገር የማያያዝ የቅሽምና ጥግ አይነት ነገር አለ፡፡
“ለምን ይህን ኮሚቴያችንን ትንሽ ለውጥ ነገር አናደርግበትም?”
“ምን አይነት ለውጥ?”
“ለምሳሌ ማንኛውም አባል አስቀድሞ ለኮሚቴው አሳውቆ ካልተፈቀደለት በስተቀር፣ በራሱ ከስብሰባ ቢቀር በአንድ ጊዜ አምስት ሺህ ብር ይቀጣል የሚል ለምን አንጨምርበትም!”
“ይሄ እንኳን ይበዛል፣ ሰው እኮ ብዙ  ነገር ይገጥመዋል፡፡”
“እሱማ ልክ ነው፡፡ ግን ቸልተኛ እየሆንን እየቀረን የኮሚቴው ሥራ እንዳይዳከም...”
ከንቱ ክፋት ነው፡፡ ከዛ በኋላ ዝም ብሎ በሆዱ እያጉረመረመ የሚያዳምጥ የሚመስል እንጂ ልጄ፣ ህዝቤው ሌላ፣ ሌላ ነገር ነው የሚያብሰለስለው፡፡ አንደኛው...አለ አይደል... “ሁሉም ነገር ቢያቅታቸው አጅሬዎች በዚህ በኩል መጡብን! አሁን ይቺም ስልጣን ሆና ግልበጣ መሞከራቸው ነው!” ሲልላችሁ ሌላኛው ደግሞ... “እኔ ድሮም ጠርጥሬ ነበር፡፡ ተደራጅተው እንደሚዘምቱብን አውቄው ነበር፣” ይልላችኋል፡፡ ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ...አጅሬዎች የሚባሉት የሉም፣ ተደራጅተው ዘማቾችም የሉም! ብቻ የሆነ አንድ ‘ሰብሰብ ያለ’ አይደለም እኛ  ሲ.አይ.ኤም ሆነ ኬ.ጂ.ቢ. ለይተው የማያውቁት ጠላት ነገር መፍጠሩ ‘ጥርሳችንን የነቀልንበት’ ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...
በመታቀፉ ወደተበሳጨው ዜጋችን ለመመለስ ያህል....
“የተበሳጨህበት ሌላ ምክንያት ካለ ንገረኝ እንጂ እኔ ጨመቀኝ፣ ትንፋሽ አሳጣኝ ምናምን የምትለው ነገር አይገባኝም፡፡”
“እባክህ ተወው፣ እኔ እሱን መች አጣሁትና ነው፣ ‹ይሄኔ የሆነ ነገር አዘጋጅቶልኝ ነው እንጂ! ወይ ጥቁር ዶሮ ሦስት ጊዜ ሳይሆን አስራ ሦስት ጊዜ አዙሮብኝ፣ “ስታቅፈው ጨምቀህ ትንፋሽ  ካሳጣኸው የፈለግኸውን ነገር ልታደርገው ትችላለህ  ተብሎ ይሆናል!”
“ከአንተ እንዲህ አይነት አስተሳሰብ አልጠብቅም፡፡”
“ምን አይነት አስተሳሰብ ነው የምትጠብቀው?”
“ማለት ዶሮ ሦስት ጊዜ አዙሮ ምናምን...”
“በቃ፣ በቃ! እሱን ሂድና ለሚሰሙህ ንገራቸው፡፡ ነው ወይስ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን ምናምን መሆንህ ነው!” ይሄን ጊዜ ብልጥ ሰው... የሆነ ምክንያት ፈጥሮ ሽው ነው፡፡
እናላችሁ... ምን ለማለት ነው፣ ትናንት ያለምንም ሀሳብ እንዝናናባቸው፣ እንሳሳቅባችው የነበሩ ነገሮች፣  ዛሬ አዳዲስ ዲክሺነሪ እየተጻፈላቸው፣ “ነብር አየኝ በል!” ምናምን የሚያሰኙ እየሆኑ ነው ለማለት ያህል ነው፡፡
“ሦስቴ እንዴት ዋላችሁ አንዱ ለነገር ነው፣” የሚሏት አባባል አለች፡፡ ተጠራጣሪዎች ነን እኮ! እና ያኔ እንደ ተረት ቢጤ  ትነገር የነበረችው ነገር ዘንድሮ እውነት ሆና አይደለም፣ ሦስቴ እንዴት ዋላችሁ ተብሎ ለአንዱ ጊዜም ሰላምታው ጠበቅ ካለ...አለ አይደል...
“ሰውየው አንድ ያሰበው ተንኮል ቢኖር ነው፡፡”
“ኸረ እባክህ እንደዚህ አይነት ነገር አታስብ! ሞቅ አድርጎ ሰላም ስላለህ ምን? እኔ እኮ ግርም የሚለኝ እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ መጀመሪያውኑ ምን ብሎ ነው የሚመጣላችሁ!”
“እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የሚመጣልንማ ስለሚገባን ነው፡፡”
“ራሳችሁ እያመሳችሁት ዘመን፣ ዘመን አትበሉ!”
“ስማ ፖለቲካህን እዛው ለሚገባቸው ንገራቸው፡፡ የማናውቅ መሰለህ፣ ለምን ንገሩኝ ትላለህ!”
ጎሽ! “ይቺ ናት ጨዋታ!” ነገር የምትመጣው ይሄን ጊዜ ነው፡፡ በእናንተ ቤት ሎጂክ ቅብጥርስዮ ስትሉ ስለ ራሳችሁ ለካስ ሌላ ሎጂክ አለ! ቂ...ቂ...ቂ...
እሷዬዋም ብትሆን እንደው ፈገግ፣ ፈለቅለቅ ያለች እንደሁ... “እሰየው ከልቡ ፈገግ ብሎ ሰላም የሚል ሰው ተገኘ?” የሚባል ሳይሆን፣ 'የፍርድ ውሳኔው' ሌላ ነው፡፡
“ይቺ ሴትዮ ድሮም ደስ አትለኝም፡፡ ይሄ ሁሉ ትህትና ከየት  ያመጣችው ነው?”
“እሷ ድሮም ቢሆን ማንንም ሰው ሰላም የምትለው ስቃ፣ ተፍለቅልቃ ነው፡፡ አሁን ምን አዲስ ነገር ተገኘና ነው!”
“እና፣ በደንብ አይተሀታል? ድሮ የምትስቀውን አሳሳቅ ነበር የምትስቀው?”
“እኔ እንደውም ይበልጥ ከዳር ዳር ፈገግ ብላ፣ በሳቅ ፍክትክት ብላ ነው የማያት፡፡”
“እኮ እኔስ ምን እልኩ፣ ይሄ ሁሉ ፍክትክት ማለት ምን አመጣው ነው የምልህ፡፡ ሴትየዋ ስቃ፣ አሳስቃ የሆነ ተንኮል ልትፈጽም አስባ ነው እንጂ!”
እና የተከሰከሱ ፊቶች በበዙበት ዘመን፣ ትንሹም፣ ትልቁም ካብ ለካብ በሚተያይበት ዘመን፣ ይበልጥ ፈገግ ማለት እንደ መልካምነት ሳይሆን...አለ አይደል... ‘የፈገግታ የሴራ ትርክት’ (ቂ...ቂ...ቂ...) ነገር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ለማለት ያህል ነው።
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 744 times