Saturday, 19 March 2022 11:50

ጐዳናዉ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(6 votes)

   "--ማሕሌትን የመክሊትን ያህል ባልቀርባትም የምንጋራዉ ተመሳሳይ ታሪከ ስላለን ብቻ አዝንላታለሁ፡፡ ማሕሌት ሀሜት ልብሷ ነዉ፤ እሷን እኔ ፊት የሚያማ ሴት ግን የለም፡፡ አብዛኛዉ የቡና ቤት ወሬ በግለሰቦች ታሪክ ላይ የሚሽከረከር ነዉ፡፡ መነሻዉም መድረሻዉም የሌሎች የተሸሸገ ጀርባ ነዉ፡፡ የቡና ቤት ሴት እንደ ሀሜት ከልቧ የምትወደዉ ነገር የለም፡፡--"
            
                 እነሆ ዕጣ ፈንታ ካዛንቺስ የተባለ ሲኦል መንደር ወርዉሮኝ፣ አበሳ የበዛበት የቡና ቤት ኑሮን መግፋት ከጀመርኩ ድፍን ሦስት ዓመታት አለፉ፡፡ የመከኑ ግን ታሪኬ ሲተረተር አብረዉ የሚወሱ (እኔ ለሌሎች ስተርክ ሳንሱር አድርጌ የምዘላቸዉ) ድፍን ሦስት ዓመታት፡፡ ቡና ቤቱ ዉስጥ አብረዉኝ ከሚሠሩት ሴቶች ተገንጥዬ ጥጌን ይዤ ተጎልቻለሁ፣ ግንባሬ ጎትቶ የሚያመጣልኝን ወንድ በቋፍ እየጠበቅኩ፡፡ ጥቂት ተስተናጋጆች ናቸዉ ቡና ቤቱ ውስጥ ያሉት፡፡ የምሸሸዉን ትዝታ የሚጎትት የኩኩ ሰብስቤ ዘፈን ግድግዳው ላይ በተሰቀሉት ስፒከሮች በኩል ጐላ ብሎ ይንቆረቆራል፡፡
ሲጋራዬን እየማግኩ ዘፈኑን ተከትዬ በትዝታ እየተብሰከሰኩ ሳለ፣ የልብ ወዳጄ መክሊት በቡና ቤቱ የጀርባ በር በኩል ዘልቃ እየተጣደፈች መጥታ ጉንጬን ሳመችና፣ ባልኮኒዉ አጠገብ ተሰብስበዉ ለሚያወጉት ሴቶች ለስንብት እጇን አዉለብልባ፣ ቤቱን ለቃ ተሰወረች፤ ያን ታላቅ ዳሌዋን እያዉረገረገች፡፡ አጠገቤ መጥታ ሳለ ነስንሳዉ የሄደችዉ ስርንን የሚበጥሰዉ ሽቶዋ ጠረን ገና በአየር ተጠርጎ ስላልተወሰደ ምቾቴን አጓድሎታል፡፡ መክሊት እዚህ ቡና ቤት ሥራ የጀመረችዉ ከእኔ ቀድማ ነዉ። ጋግርታም ብትሆንም በሰዉ የመወደድ ፀጋን የታደለች ናት፡፡ ቀዝቃዛነቷ ስትፈጠር ጀምሮ የተጣባት ይሁን ዘግይቶ የተከሰተ በዉል አይታወቅም፡፡ ዉበቷ ነዉ ድብርቷን ሸፍኖ ዓለም መኖሯን እንዳይዘነጋ የረዳት፡፡
ይህን ብሽቅ ሥራ እየሠራሁ ረብጣ ገንዘብ አፍሳለሁ፤ ግን ይህ ነዉ የሚባል የአፈራሁት ጥሪት የለም፡፡ የዘወትር ጥረቴ የዕለት ቀዳዳዬን ከመሙላት ዘሎ አያዉቅም። ማለቴ፣ የወደፊት ዕጣዬን በቀቢፀ-ተስፋ የምጠብቅ ሰዉ ነኝ፡፡ ደግሞም፣ መጪዉ ጊዜ ከኖርነዉ ትናንት ጋር ተመሳሳይ ነዉ፡፡ በእርግጥ፣ ማንም የወደፊቱን ጊዜ መተንበይ አይችልም፤ የሕይወት ጉዞ ፈጽሞ የማይተነበይ ነው፡፡ በሕይወት ዉስጥ የሚከናወነዉ ጉዳይ ሁሉ በራሱ መርህ የሚገዛ በመሆኑ የእኔ ሚና ከንቱ ነዉ፡፡ እነሆ ለምሳሌ፣ ከቀናት በፊት የቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ በሠርጓ ዋዜማ፣ በለጋ እድሜዋ በመኪና አደጋ ተቀጠፈች፡፡ ያ ሁሉ ልፋቷ  በሞት ተደመደመ፡፡ እዉነት አሁን እንደ እሷ ያለ መልካም ሰዉ፣ ያን አይነት አሰቃቂ ሞት ይገባዉ ነበርን? ታዲያ እንዴት ሰዉ ሞትን በጉያዉ ተሸክሞ እየሄደ፣ ስለ ነገዉ ፀሐይ እርግጠኛ መሆን ይችላል? የእኔ የኑሮ ርዕዮተ-ዓለም የአሳማ ነዉ፡፡ ይኸን ፍልስፍናዬን ሰዎች ይሳለቁበት ይሆናል። እና ምን ይጠበስ? ዉበቴ እስካልረገፈ ድረስ በልቼ ማደር እችላለሁ፡፡ የወደፊቱን ጊዜ በቀቢፀ ተስፋ የምጠብቅ ደንታ ቢስ የሆንኩት  ከንቱና በስባሽ ፍጡር መሆኔን መገንዘቤ ነዉ፡፡ ይኸ ሐቅ ፀሐይ የሞቀዉ አገር ያወቀዉ ሐቅ ነዉ፡፡ የእኔ የሕይወት አረዳድ ላይ ያሳደረዉ ተፅዕኖ ግን ታላቅ ነዉ፡፡ ይኸን አተያዬ ለሰዎች የማላካፍለዉ የኑሮዬ ርዕዮት ነዉ፡፡ እያንዳንዳችን ፈፅሞ ሌሎች የማይረዷቸዉ የራሳችን እዉነቶች አሉን፡፡
ሥጋዊ ተድላ ወዳድ ነኝ፣ እንደ አሳማ። ለነገሩ የእኔ ኑሮ ዕጣ ሥጋ ለሥጋ አይነት ነዉ። እናም፣ በልቼ እንዳድር ያበቃኝን ሥጋዬን ማዋደዴ የሚያስደንቅ ጉዳይ አይደለም፡፡
ማሕሌት እና ባልኮኒዉ ጋ ተቀምጦ ቢራ ሲጠጣ የነበረዉ ቋሚ ደንበኛዋ (በሰካራምነቱ፣ በምሁርነቱና በለጋስነቱ ዝነኛ የሆነ)፤ ዳንስ ወለሉ ላይ ወጥተዉ በባህር ማዶ ሙዚቃ ተቃቅፈዉ መደነስ ጀምረዋል፡፡ የሁሉም ሰዉ ዐይን እነሱ ላይ ነዉ፡፡ ማሕሌትን የመክሊትን ያህል ባልቀርባትም የምንጋራዉ ተመሳሳይ ታሪከ ስላለን ብቻ አዝንላታለሁ፡፡ ማሕሌት ሀሜት ልብሷ ነዉ፤ እሷን እኔ ፊት የሚያማ ሴት ግን የለም፡፡ አብዛኛዉ የቡና ቤት ወሬ በግለሰቦች ታሪክ ላይ የሚሽከረከር ነዉ፡፡ መነሻዉም መድረሻዉም የሌሎች የተሸሸገ ጀርባ ነዉ። የቡና ቤት ሴት እንደ ሀሜት ከልቧ የምትወደዉ ነገር የለም፡፡ የሌሎችን የተሸሸገ የጀርባ ታሪክ የመቅደዱ ሂደት ተወዳጅ የሆነዉ ሁሉም የወሬ ኤክስፐርት፣ የወሬ ፕሮፌሰር የገዛ ሕይወቱን በከፊልም ቢሆን ተፅፎ ስለሚያገኝበት ነዉ፤ ስለ ሌሎች ማዉራት ስለ ራስ መስማትም ጭምር በመሆኑ ነዉ፡፡   
ከዉጪ ሪዙ የጎፈረ ቀይ ወጣት ገብቶ ፊት ለፊቴ ከሚገኘው ቦታ ላይ ተቀመጠ። ረዥም ነዉ፣ መልከ መልካም፡፡ የሆነ ገፅታዉ ከመስፍን ጋር ይመሳሰላል፡፡ በቅርቡ ቡና ቤቱ ዉስጥ ሥራ የጀመረችዉ ጁሊ (ሁላችንም፣ እኛ ብቻ የምንጠራራበት፣ ደንበኞቻችን የማያወቁት ቅፅል ስም አለን) እነዛን እንደ ኮርማ በሬ ቀንድ ከርቀት የሚታዩትን ጡቶቿን ወድራ (እነዚህ ጡቶቿ ወንድ የምትስብባቸዉ ብቸኛ መግነጢሷ ናቸዉ) ትዕዛዝ ልትቀበለዉ  ወጣቱ ፊት ተገትራለች፡፡ ጎኔ ካለዉ ጠረጴዛ (በግራዬ በኩል) ከተቀመጡት አራት ወጣቶች አንዱ (ፀጉሩን ድሬድ ሎክ የተሠራ።) ይኸኔ፣ የእኛኑ ንጉስ ኃይለስላሴን አምላክ አድርገዉ የሚያመልኩትን ራስተፈሪያኖቹን (ይኸን ሲባሉ ተፈሪ ለምን ተዉ ሳይሉ ቀሩ? እግዜርን አማኝ ናቸዉ ሲባል አልነበረም? ኮርጆ ይሆናል) ተነስቶ ጓደኞቹን ተሰናብቶ በአይኑ ቂጥ ገርምሞኝ ወጥቶ ሄደ፡፡
ፊት ለፊቴ የተቀመጠዉን ሪዛም ወጣት በንቃት መከታተሉን ቀጥያለሁ፡፡ ፊቱ ጥቁር ዉስኪ ከነጠርሙሱ ቀርቦለታል፡፡ ሙሉ ትኩረቱ እነ ማሕሌት ላይ ነዉ፣ ዳንሳቸዉ የመሰጠዉ ይመስላል፡፡ ዐይኖቹን ከዳንስ ወለሉ ትእይንት ላይ ሳይነቅል፣ ሁለተኛ ሲጋራዉን አቀጣጠለ፡፡ ጎኔ የተቀመጡት ወጣቶች የጦፈ ወግ አለሁበት ድረስ ጎልቶ ይሰማል፣ ጆሮዬን ጥዬ ወጋቸዉን በትኩረት ማዳመጥ ጀመርኩ፡    
“…ቆይ ለምንድን ነዉ ግን ሲስ ራስታ ያቺን ልጅ የተዋት? አንድ ሰሞን አብዶላት አልነበር?” ቀጭኑ ወጣት፡፡
“የደንቡን አግኝቶ ይሆናላ፡፡” የዐይን መነፅር የለበሰዉ፡፡
“ምን ባክህ፣ ሲስ መች ይረባል፡፡ ያቺን የመሰለች ልጅ …” ባለ አፍሮዉ ወጣት፡፡ ከፊል የፊቱ ገፅ ብቻ ነዉ የሚታየኝ፡፡  
“ይሄማ ቢሆን አብሯት ይዘልቅ ነበር፣ ተነፍጎ ቢሆን ነዉ፡፡ ሂሂሂ…” ቀጭኑ ወጣት።
“ባክህ ገጭታዉ ነዉ በሳምንቱ ዐይንሽን ላፈር ያላት፡፡” ባለ አፍሮዉ፡፡
“እንዴት አወቅክ?” መነፅር የለበሰዉ፡፡
“ራሱ ነግሮኝ፡፡”
“አይ ሲስ እንዲህ አይነት ሰዉ ነዉ ለካ?” መነፅር የለበሰዉ፡፡  
“ሲስ እኮ እንዲህ ነዉ፣ ዛሬ ከአንድዋ ጋር አግኝተኸዉ ነገ ከሌላዋ ጋር ነዉ፡፡  እሚገርምህ አሁን የያዛትን ልጅ የጠበሳት ከሌላ ካምፓስ ነዉ፡፡” ባለ አፍሮዉ፡፡
“ኧረ ባክህ? እኛ ካምፓስ ያሉትን አዳርሶ ቢሆን ነዋ?” አራዳ እኮ ነዉ ሲስ፡፡ እኔ የእሱን ምላስ ቢሰጠኝ፡፡ ጤፍ እኮ ይቆላል ምላሱ!” ቀጭኑ ወጣት፡፡ ንግግሩን ተከትለዉ ሌሎቹ በሳቅ አወኩ፡፡
“ጋይስ ቢራ ይጨመራ?”  መነፅር የለበሰዉ፡፡ እጁን ከፍ አድርጎ በምልክት ጁሊን ጠራ፡፡   
ፊት ለፊቴ የተቀመጠዉ ሪዛም ወጣት ዐይኖቹን ከነ ማሕሌት ላይ አሽሽቶ ወደ እኔ ሲዞር ዐይን ለዐይን ተጋጨን፣ ቀድሜ ዐይኖቼን ሰብሬ ሲጋራ አቀጣጠልኩ፡፡ ከጎኔ ያሉት ወጣቶች ተባራሪ ወሬ አሁንም በጆሮዬ መስረጉን ቀጥሏል፡፡ በጎረምሶች ክበብ የሚቀደድ፣ ማጠንጠኛዉ ከጭን፣ ከዳሌ፣ ከጡት… የማይዘል፣ ከግልብ እዉቀት የሚቀዳ የቸከ ወሬ፡፡
ማሕሌት እና ሰዉዬዉ አዲስ የተከፈተዉን ዘፈን ምት ተከትለዉ ተቃቅፈዉ መደነሱን ቀጥለዋል፡፡ የማሕሌት ቁመት ከሰዉየዉ ስላጠረ ጎበጥ ብሎ ሊያቅፋት ተገዷል። የዳንስ ወለሉን ትእይንት መታዘቡን ትቼ ሪዙን ወዳጎፈረዉ ወጣት ሳማትር ዳግም ዐይኖቻችን ተጋጩ፣ በአጸፋው ፈገግታዬን ብልጭ አደረግኩለት፡፡ ማሕሌት ዳንሷን አቋርጣ የፊቷን ላብ በአይበሉባዋ እየጠረገች ወደ መቀመጫዋ ተመለሰች፡፡
ከውጭ የገቡ ጥንዶች መጥተዉ ጎኔ ካለዉ ጠረጴዛ ላይ እንደተቀመጡ ሪዛሙ ወጣት ከመቀመጫዉ ተነስቶ ወደ እኔ መጣ፡፡    
“መቀመጥ እችላለሁ?” አለ ፊቴ ቆሞ በትኩረት እያስተዋለኝ፡፡ ድምፁ አስገምጋሚ ነዉ፡፡  
“ይቻላል፡፡” አልኩ፤ ፈገግ ብዬ ፊቴ ወዳለው ሶፋ እንዲቀመጥ እየጠቆምኩ። ሞገሳም ነዉ፡፡ በቁሙ ከአጭር ቀሚሴ የተረፉትን ጭኖቼን በስርቆት ገርምሞ ሶፋው ላይ ተቀመጠ፡፡ ጁሊ ወዲያዉኑ ቀድሞ ተቀምጦበት ከነበረዉ ቦታ ጥሎት የመጣዉን የጠርሙስ ዉስኪ ከነብርጭቆዉ አምጥታ ፊቱ አቅርባለት ተመልሳ ሄደች፡፡
“ብቻዬን መቀመጡን ጠልቼ ነው አንቺ ጋ የመጣሁት፡፡”
“ጥሩ አደረክ፣ ከሰው ጋር መጫወት መልካም ነው፡፡” አልኩ፤ በፈገግታ ተሞልቼ።
“እስክንድር እባላለሁ፡፡”
“ሄለን፡፡” እጅ ለእጅ ተጨባበጥን፡፡ ሄለን የሐሰት ስሜ ነዉ፣ እዉነተኛ ስሜ ግዮን ነዉ።
ታዲያስ? ኑሮ እንዴት ነው?” አለ ወንበሩን ወደ ፊት ስቦ፡፡
“ሁሉም መልካም ነዉ፡፡”
“ካዛንቺስ እጅግ ተለዉጧል፣ ብዙ ድንቅ ነገሮችን ነዉ ያስተዋልኩት፡፡”
“ካዛንቺስ ዉስጥ ምን ድንቅ ነገር አስተዋልክ?”
“ብዙ ነገር፣ ለምሳሌ እንዳንቺ አይነት ዉብ ሴቶች፡፡” አለ በታላቅ ፈገግታ ተሞልቶ። ጥርሶቹ በረዶ የመሰሉ ናቸዉ፡፡
“ሴት የትም አለ፡፡ ቆየህ ካዛንቺስ ከመጣህ?”
“አዎ ረዥም ጊዜ፡፡ አገር ዉስጥ አልነበርኩም፣ ባሕር ማዶ ነበርኩ፡፡”
“የት አገር ነበርክ?”  
“ረዥም አመት አዉሮፓ ነዉ የኖርኩት፤ ሁለት አመት ሆነኝ አገር ቤት ከገባሁ፡፡”  
“ጥሩ አደረግክ፣ ማን እንደ አገር፡፡” ቢራዬን ብርጭቆዉ ላይ ቀድቼ ተጎነጨሁ፡፡
“ያዉ ነዉ እባክሽ፣ የትም ኖርሽ የት ሕይወት ተመሳሳይ ነዉ፡፡” የዉስኪዉን ጠርሙስ አንስቶ ብርጭቆዉ ወገብ ድረስ ቀዳ፡፡
ባዶ የነበረው ቡና ቤት በመሸተኛ ተወሯል፡፡ ከእዚህ ቀደም ከእረፍት ቀናት ዉጪ እንደዛሬዉ ቀን መሸተኛ ተንጋግቶ መጥቶ አያዉቅም፡፡  
ቡና ቤቱ ዉስጥ ከእስክንድር ጋር እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አብረን ከአመሸን በኋላ፣ ቤቱ ለመሄድ ተዋዉዬ ተያይዘን፣ አራት ኪሎ ወደሚገኘዉ አፓርታማዉ አመራን፡፡
*  *  *
የእስክንድር አፓርታማ ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ ሳሎኑ እጅግ ሰፊ ነዉ፡፡ ሶፋ ላይ እንድቀመጥ ጋበዘኝና ካፖርቱን ግድግዳዉ ላይ ሰቅሎ ወደ ውስጠኛው ክፍል ዘለቀ። መስኮቱ አጠገብ የተገተረዉ ትልቅ የመጽሐፍ መደርደሪያ በመጽሐፍ የተሞላ ነዉ፡፡ የዘለቀበት ክፍል የሚገኘው ከሳሎኑ ትይዩ ነው፣ በመሆኑም፣ እራት ለማቅረብ ሲንጐዳጐድ ይታያል፡፡ ሳሎኑ በወጉ የተሰናዳ ቢሆንም በቁስ በመታጨቁ ምክንያት ሳቢነቱ ተጓድሏል፡፡
እስክንድር፣ ለሩብ ሰአት ያህል የተንጐዳጐደበትን ምግብ አቅርቦ ከቀማመስን በኋላ ቀድሜ መኝታ ቤት ገብቼ አልጋው ላይ ሰፈርኩ፡፡ ቤቱ ጠባብ ነዉ፣ በተቃራኒ አቅጣጫ የተሠሩ ሁለት መስኮቶች አሉት፡፡ ፊት ለፊት ግድግዳዉ ማዕዘን ላይ እስክንድርና አንዲት ፈረንጅ ሴት ባህር ዳርቻ ላይ የተነሱት ባለቀለም ፎቶግራፍ ተሰቅሏል፡፡ ፎቶግራፉ ግርጌ ላይ ማሊቡ ደሴት፣ ጁላይ 2005 የሚል ጽሑፍ ተጽፎበታል፡፡
“እየውልሽ ኑሮዬ ይህን ይመስላል እንግዲህ።” አለ እስክንድር መጥቶ፣ አልጋዉ ደርዝ ላይ እየተቀመጠ፡፡  
“ጥሩ ቤት ይዘሀል፡፡”
“ምን ዋጋ አለዉ፣ ሴት ከሌለበት ቤት ብቻዉን…”
“እዉነት ነዉ፣ አብሮነት ጎጆ ያሞቃል።” አልኩ ዐይኖቼን ጣራዉ ላይ እንደተከልኩ። የሰነዘርኩት አባባል በተግባር ያላረጋገጥኩት ግን ብዙዎች ሲናገሩት የሰማሁት እሳቤ ነበር፡፡ ግላዊ እሳቤአችን በአብዛኛዉ በገሀድ ያልፈተነዉን የጋርዮሽ ርእዮት መሠረት ያደረገ አይደል? እስክንድር ልብሱን ለውጦ መጥቶ ጐኔ ተጋደመ። የምሽቱ ፀጥታ ፍፁም ታላቅ ነበር፡፡ የመንደሩ ዉሻ የሚረብሽ የማላዘን ድምፅ ጋብ ብሏል፡፡
“አራት ኪሎ ከመጣሁ አመት ሆነኝ፣ ግን መንደሩን ልወደዉ አልቻልኩም፡፡” የራስጌዉን መብራት ካበራ በኋላ ተቀናቃኙን ደማቅ ብርሃን ደረገመው፡፡
“በሂደት ትወደዉ ይሆናል፡፡” የጠጣዉ ዉስኪ ጠረን ከቀዝቃዛው አየር ጋር ተቀላቅሎ በአፍንጫዬ ይሰርጋል፡፡
“ተስፋ አደርጋለሁ፡፡” መኝታው እንዳልተመቸዉ አይነት ተነቃንቆ ተጠጋኝ፡፡
“አራት ኪሎ ከመግባትህ ቀድሞ የት ነበርክ?”
“ኮልፌ ቤተሰቦቼ ቤት፣ ከዉጭ ከመጣሁ ጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ ቤታቸዉን ተዳብዬ ነበር የኖርኩት፡፡” ድጋሚ ተነቃንቆ ይበልጥ ተጠጋኝና ወገቤን አቀፈ፡፡
“ራስን ችሎ መኖርን የመሰለ ነገር የለም፡፡”
“እዉነት ብለሻል፡፡” እጁን ከወገቤ ላይ አሽሽቶ ወደ ጡቶቼ ሰደደ፡፡
“ትዳር አልሞከርሽም እስካሁን?”
“አዎ፣ የትዳሩን ዓለም እስካሁን አላየሁትም።” አልኩ የዉስጥ ሱሪዬን ዘልቆ የገባ እጁን እያሸሸሁ፡፡
“እንዴት እስካሁን ሳትሞክሪ ቀረሽ?;
“አለ አይደል፣ ትዳር ትርጉም የሚኖረዉ እህል ዉሃ የሚሆንህን ሰዉ ሲያገናኝህ ነዉ። ይኸ ካልሆነ ደግሞ አብሮነት ፋይዳ ቢስ ነዉ፡፡” አልኩ ለጠየቀኝ ጥያቄ አጥጋቢ የመሰለኝን የቅጥፈት ሰበብ ፈብርኬ። መቸስ ሸርሙጣ መሆኔ ባል አሳጣኝ አልለዉ ነገር፡፡ ሸርሙጣነቴ ነዉ እንዲያ በፍቅር እንሰፈሰፍለት የነበረዉን መስፍንን አግባኝ ብዬ አፍ አዉጥቼ እንዳልጠይቀዉ የገደበኝ፤ በራስ መተማመኔ ተንኮታኩቶ፡፡ የእኔ መስፍን የወንዶች ቁንጮ። ልቤ ለፍቅር እጁን የሰጠዉ ለእሱ ነዉ፡፡ ግን፣ እሱ ይኸን አያዉቅም፡፡ ከምንም ነገር አብልጬ እንደምወደዉ አያዉቅም፡፡ ለእሱ፣ እኔ የሥጋ አምሮቱን የሚወጣባት፣ በየዋህነቴ የሚያዝንልኝ (እሱ እንደሚለዉ) ተራ ሴት ነኝ። በልቡ ዉስጥ ከእዚህ የሰፋ ሥፍራ የለኝም። የይሉኝታን እግር ብረት ሰብሬ ከእሱ ጋር እስከ ሕይወቴ ፍፃሜ ድረስ አብሬዉ ልኖር እንደምመኝ አልነገርኩትም። ከእሱ ጋር ስተኛ እንደዛ የምሆነዉ የፍትወት ዛር የተጣባኝ ቅንዝረኛ ስለሆንኩ እንጂ በፍቅሩ አብጄ መሆኑን አያዉቅም፡፡ ቀንደኛ ጠላቴ ይሉኝታ ነዉ፣ ያፈቀርኩትን ሰዉ የእኔ እንዳላደርግ የገደበኝ፡፡ ጠይቄዉስ ቢሆን? ጥያቄዬን ይቀበል ነበር? ምናልባትም ጥያቄዬን ይገፋዉ ይሆናል፡፡ ሸርሙጣን ማን ይመርጣታል፡፡ ሁሉም ወንድ የሚፈልገዉ ገላዬን ብቻ ነዉ፡፡ ይኸን ገላዬን፣ ሁሉም ሳይረግፍ ሊቀምሰዉ የሚራኮትበትን። ከዛስ? ከዛማ ሁሉም ይንቁኛል፣ ምን ቢያስጎመዥ የሸርሙጣ ገላ እፅበለስ ነዉ በሚል ብሂል። አቅፈዉኝ አድረዉ ሲነጋ በመንገድ ሲያዩኝ ሸሽተዉ መንገድ ይለዉጣሉ፡፡ ታዝቤ ዝም እላለሁ፡፡ ሸርሙጣን ማነጋገር የሚያስወግዝ ተግባር ነዉ? ሁሏ ሴትስ ሸርሙጣ አይደለች? ሁሉስ ጨዋ ነኝ ባይ፣ ምሁር ነኝ ባይ ወንድ ዘላ ዘላ የደከማትን ሴት አይደል በጋብቻ ዉል ተብትቦ ቤቱ የሚያስገባዉ? ለብቻ የተሸለመዉ የሚመስለዉስ ሥጋ፣ የሌሎች ትራፊ አይደል? ሸርሙጣ የተለየች ፍጡር ናት? ጣርኩትን የተለያየ ወንድ የሚተኛት ሴት ናት ሸርሙጣ፡፡ ይች ሴት ከሌሎች ሴቶች የምትለየዉ ለሥጋዋ ድርጎ የተኛትን ወንድ ገንዘብ ስለምታሰከፍል ብቻ ነዉ፡፡ ሁሏስ ጨዋ ነኝ ባይ ሴት መሀላ ሽራ ወንድ እንደ ቡታንታ፣ እንደ ቀሚስ፣ እንደ ኮት፣ እንደ ሸሚዝ እየለዋወጠች በሰበብ አስባቡ የተባእት ኪስ ታራቁት የለ፡፡ ሁሉስ ከማን አንሼ በሚል እልህ ወንድ በመለዋወጥ ታላቅ ዝና ካተረፉ የኮሌጅ አሳዎች ጋር አብሮ አልተንዘላዘለም? መንገዱ ነዉ እንጂ ተግባሩ አንድ አይነት ነዉ፡፡
“ገና ወጣት ነሽ፣ ትደርሽበታለሽ።” ያሸሸሁት እጁ መልሶ ዉስጥ ሱሪዬን ዘልቆ ገባ፡፡ መልሼ አልተከላከልኩም፡፡ በመሐላችን ታላቅ ዝምታ ነገሰ፡፡ ገላዬ ላይ የሚርመሰመሱት ጣቶቹ መላ አካሌን እጅግ አግመዉታል፡፡
“ዛሬ ካዛንቺስ ጎራ ባልል ኖሮኮ ይህን የመሰለ ዉበት ያመልጠኝ ነበር፡፡ አይደል እንዴ?” ከንፈሩን አሞጥሙጦ ሊስመኝ ተስቦ መጣ፡፡ ተስገብግቤ የጎመራ ወይን የመሰሉ ከንፈሮቹን ጎረስኳቸዉ፡፡ ከንፈሮቼ አፉ ውስጥ እንደሰም የቀለጡ መሰለኝ፣ ሁለመናዬ በወሲብ ቋያ ነደደ፡፡ ልቤ፣ ስለ አካሌ ዉበት እስክንድር በሚያዥጎደጉደዉ ዉዳሴ ሊቀልጥ ደርሷል። ቁንጅናን ከወንድ አንደበት ማድመጥ ልብን ደስ ያሰኝ የለ፡፡ ከእስክንድር አፍ የሚፈሱት ቃላት ነፍስን ደስ የሚያሰኙ፣ ለጆሮ የጣፈጡ ናቸዉ። እስክንድር ልክ እንደ ታላቅ ባለቅኔ ነበር የሚናገረዉ፡፡ ከተጋደመበት ተነስቶ እላዬ ላይ ተከምሮ፣ ያለ እኔ እርዳታ አጭር ቀሚሴን ቁልቁል ሸለቀቀዉ፡፡ ወርቃማዉ ብርሃን የእርቃን ገላዉን ቅላት አጋኖታል፡፡ ትከሻ ሰፊ ነዉ፡፡ ክንዶቹ ፈርጣማ ናቸዉ። እንደ እቶን የሚፋጅ ገላዉን አቀፍኩ፡፡ አልጋው ላይ ድርና ማግ ሆንን፡፡
* *  *
ያለልማዴ እጅግ አርፍጄ ከእንቅልፌ ነቃሁ። የበጋዉ የፀሐይ ጮራ የመስታወቱን መስኮት ዘልቆ ከብርድልብስ ሾልኮ የወጣ አካሌ ላይ ተኝቷል፡፡ እስክንድር አጠገቤ አልነበረም፡፡ ቤት ዉስጥ ይኖራል ብዬ ጮክ ብዬ ተጣራሁ፣ ምላሽ አልነበረም፡፡ ከአልጋ ላይ ወርጄ እየተጎተትኩ ወደ ሳሎኑ አመራሁ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ከእስክንድር ጋር ወግ ስጠርቅ ስላነጋሁ በእንቅልፍ እጦት መላ ጅስሜ ዝሏል፡፡ ሶፋዎቹ መሐል የተጎለተዉ የመስታወት ጠረጴዛ ላይ ከቦርሳዬ ጎን እስክንድር አኑሮልኝ የሄደዉ የአፓርታማዉ ቁልፍ ተቀምጧል፡፡ ወደ ቴፕ ሪከርደሩ አምርቼ ሙዚቃ ከፍ አድርጌ ከፈትኩና በብርሃን የተጥለቀለቀዉን ሳሎን አቋርጬ ወደ መታጠቢያ ቤት አመራሁ፡፡
መታጠቢያ ገንዳዉ ደርዝ ላይ እርቃኔን ተቀምጬ፣ ፊት ለፊቴ በተሰቀለዉ ግዙፍ መስታወት ዉስጥ ባፈጠጠዉ መልኬ ላይ አተኩሬአለሁ፡፡ በእንቅልፍ እጦት የቦዘዙት ትላልቅ ዐይኖቼ ቀልተዋል፡፡ ብዙ ወንድ ያቀፋቸዉ ጡቶቼ አላንቀላፉም፣ የበረሃ ተራራ መስለዉ ደረቴ መሐል ጉብ ብለዋል፡፡ ከጡቶቼ ዝቅ ብሎ ያለዉ አካሌ እህል በልቶ የሚያድር አይመስልም፡፡ ተፈጥሮ ዐይን አፍዛዥ ዉበትን ባይድለኝም፣ ወንዱን ሁሉ እንደ መግነጢስ ስቦ ወደ እኔ የሚያንጋጋ ግንባር አለኝ፡፡ በእዚህም ምክንያት በህቡዕም ቢሆን በሌሎቹ ሴቶች ስሜ በከንቱ ተብጠልጥሏል፡፡ ሁሉንም ነገር እየሰማሁ ጆሮ ዳባ ልበስ ያልኩ ብመስልም በሁሉም ላይ ቂም መቋጠሬን ግን አያዉቁም፡፡ ወንድ ለመሳብ አቅጄ የምከተለዉ የተለየ ቴክኒክ የለኝም፡፡ ለአለፈ ለአገደመ ሁሉ የለበጣ ፈገግታ ማሳየት አልወድም፡፡ የይስሙላ ኑሮ እጠላለሁ፤ ሁሉ ከልኩ ፈቀቅ ላይል ግብዝነት ምን ይረባል?
ረዥም አንገቴ ስር ሦስት ክርክራቶች አሉ፡፡ ከእሱ ስር ብርቅ ቅርሴ የሆነዉ የእናቴ (ነብሷን ይማር) የወርቅ ሐብል፡፡ ሐብሌን አዉልቄ መስታወቱ ድርዝ ላይ አኖርኩና ዉሃ የተሞላዉ ገንዳ ዉስጥ ገባሁ፡፡
ምሽት ላይ እስክንድር መጣ፡፡ ሳሎን ሶፋ ላይ ተጋድሜ ሴንት ኦፍ ኤ ዉመን  የተሰኘ የባህር ማዶ ፊልም በቴሌቪዥን እየተመለከትኩ ነበር፡፡
“ኦ! ቤቴን ሌላ አድርገሽዉ የለ እንዴ።” አለ ተሸክሞት የመጣዉን በፍራፍሬ የታጨቀ ከረጢት ወለሉ ላይ አስቀምጦ፣ እንደነገሩ ያሰናዳሁትን ቤት ቆሞ በአድናቆት እያስተዋለ፡፡
“እንዴ ታዲያስ፣ ሴት አይደለሁ?” ከተጋደምኩበት ተነስቼ ለእቅፍ የዘረጋቸዉ ክንዶቹ መሐል ተሸጎጥኩ፡፡
ሳሎኑ ዉስጥ የሠራሁትን ራት አቅርቤ በጋራ ከተመገብን በኋላ፣ እስክንድር ገበታዉን እንኳ እስክሸክፍ መታገስ አቅቶት እላዬ ላይ ተከምሮ ድሪያ ጀመረ፡፡ ኪነት የሚጎድለዉ ግን በወሲብ አምሮት አካልን የሚያቅበጠብጥ ድሪያ፡፡ እንደ ልጅ አቅፎ መኝታ ቤት ወሰደኝ፡፡
አልጋ ላይ የእስክንድር ደረት መሐል ተሸጉጫለሁ፣ የገላዉን ምዑዝ ጠረን እየማግኩ፡፡ አብዛኛዉ የሰዉነቴ ክፍል ገላዉ ላይ ነዉ የተኛዉ፣ የአልጋ ላይ ጨዋታ ድካም አዝለፍልፎት፡፡ ጭኖቼን የሚታከከዉ ያልበረደዉ የእስክንድር አካል በሁለመናዬ እሳት ለኩሶ ሊያነደኝ ደርሷል፡፡ እስክንድር ከደረቱ ላይ አሽሽቶኝ በሰፍሳፋ ዐይኖቹ ዐተኩሮ አየኝ፣ የቅንዝር እቶን ዐይነ ዉሃዉ ዉስጥ ይንቀለቀላል፡፡ የማይጠግብ ጉድ። ሁለመናዬ ፍፁም ዝሏል፡፡ በተቃራኒዉ፣ የእስክንድር እጆች በሥራ ተጠምደዋል፣ የማይዳስሱት የሰዉነቴ ክፍል አልነበረም፣ ጡቶቼን፣ ዳሌዬን፣ ጭኖቼን፣ እምብርቴን፣ እፍረቴን … ሰመመን ባህር ዉስጥ እስክገባ ድረስ፡፡ ከዛ፣ ድንገት ከአልጋዉ ላይ አፈፍ አድርጎ አዉርዶ ወለሉ ላይ አስተኛኝና፣ ለእኔ እንግዳ የሆነ ተራክቦ ሊያደርገኝ አመቻቸኝ፡፡
“ኧረ ቀስ ሰዉዬ! ምን ልታደርግ ነዉ? ኖ ኖ! እረፍ! እንደዚህ አይነት ያፈነገጠ ተግባር ደስ አይለኝም!” እጆቹን ከወገቤ ላይ አሽሽቼ አፈፍ ብዬ ተነሳሁ፡፡   
“ይቅርታ አድርጊልኝ?”
“አጥፍተሃል! ቢያንስ ፈቃዴን ቀድመህ መጠየቅ ነበረብህ!”
“ይቅርታ ጠየቅኩሽ እኮ፡፡”
“አዉቀዉ እያጠፉ ይቅርታ መጠየቁ ምን ይረባል! ሴተኛ አዳሪ ስለሆንኩ ብቻ
አንተ የምትሻዉን ሁሉ ሳላቅማማ የምፈፅም አይነት ሴት አድርገህ ስለቆጠርከኝ
ነዉ፡፡”
“አጋነንሽዉ--”
“ምን ማለት ነዉ አጋነንሽዉ!?” አቋረጥኩት፡፡  
“ሸርሙጣ መሆንሽን ግን አትዘንጊ፡፡”
“ብሆንም ክብር ያለኝ ሰብአዊ ፍጡር ነኝ!” እንደ መብረቅ አንባረቅኩበት፡፡
“አፍሽን ዝጊ! ጋጋኖ!”
“ባልዘጋስ? ምን ልታደርግ ኖሯል!?” በኃይል ገፍትሬዉ ተነሳሁና ወለሉ ላይ እዚህና እዚያ የወደቁ ልብሶቼን ሰብስቤ ክፍሉን ለቅቄ ልወጣ ስል፣ ክንዴን አፈፍ አድርጎ ያዘ፡፡ ፊቱ በንዴት ሳምባ መስሏል፡፡
“ሰዉዬ ልቀቀኝ!” ፊቱ ላይ ተፋሁበት። እንደ ነብር ተቆጥቶ ገፍትሮ አልጋዉ ላይ ወረወረኝና በጥፊ ፊቴን ደረገመኝ። የሞት ሞቴን ከወደቅኩበት ተነሳሁና እላዩ ላይ ተከመርኩ፣ ተያይዘን ወለሉ መሐል የተጎለተዉ ጠረጴዛ ላይ ወደቅን። እንደ ዕብድ እያጓራሁ በሹል ጥፍሬ ያልዘነጠልኩት የፊቱ ክፍል አልነበረም። ግንባሩን፣ ዐይኑ ሽፋል አካባቢ፣ አፍንጫዉን፣ ጉንጩን፣ አገጩን፡፡ እጁን ወደ ግንባሩ ሰዶ መድማቱን ሲያረጋግጥ፣ ነብር ሆኖ ከወደቀበት ተነስቶ እየተንደረደረ ወደ እኔ መጣና፣ አናቱን ልፈረክስበት አፈፍ ያደረግኩትን የዉስኪ ጠርሙስ ከእጄ ላይ ቀምቶ፣ መንጋጭላዬን በቡጢ ነረተኝ። የሞት ሞቴን ወደ ሳሎኑ ተፈተለኩና በደመነብስ መስፍንን ላጠቃበት የሚያግዘኝን ቁስ ማማተር ጀመርኩ። ፊት ለፊቴ የተደነቀሩት ቁሶች ሁሉ ባላንጣዬን ለማጥቃት የሚረዱ አልነበሩም፤ ሁሉም እርባና ቢስ የግዑዝ ጥርቅም፡፡ በእዚህ መሐል እስክንድር መለመላዉን እየተንደረደረ መጥቶ እንዳልፈናፈን አድርጎ ፀጉሬን በኃይል ጨምድዶ ሶፋዉ ላይ ገፈተረኝና፣ ቀድሞ ሊፈፅም አቅዶት የነበረዉን ተራክቦ ሊያደርገኝ ግብግብ ገጠመኝ። የሚያዥጎደጉደዉ አፀያፊ ስድብ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ነዉ፡፡
“ሰዉዬ ምን ማድረግህ ነዉ? አቁም!”
ያለኝን ኃይል ተጠቅሜ ገፍትሬ ከላዬ ላይ ለማሸሽ ብፍጨረጨርም ሳይሆንልኝ ቀረ። ፀጉሬን በኃይል ጨምድዶ እንሰሳዊ ግብሩን ሊፈፅም ብርቱ ግብግቡን ተያይዞታል፡፡ ፊት ለፊት ያለዉ ሶፋ ስር የወይን መክፈቻ ወድቆ አየሁ፡፡ የሞት ሞቴን ተንጠራርቼ ወይን መክፈቻዉን በቀኝ እጄ አፈፍ አደረግኩና በአለኝ ኃይል የእስክንድርን ራስቅል በሹሉ በኩል ደጋግሜ ወጋሁበት፡፡ ተዝለፍልፎ ጎኔ ተዘረረ፡፡ የፊቱ ገፅ በደም ተሸፍኗል። የሚያሰማዉ የጣር ድምፅ ነፍስን እጅግ ያሸብር ነበር፡፡ በደመነፍስ ከተዘረረበት ወለል ላይ አቃናሁት፣ በቅፅበት በድን ሆኖ ነበር። የምይዘዉን የምጨብጠዉን አጣሁ፡፡ ደጅ ወጥቼ የድረሱልኝ ኡኡታዬን አቀለጥኩት፣ ኡኡኡኡ!
*  *  *
እነሆ ሕይወት ፈፅሞ ባልተለምኩት ጎዳናዉ አካልቦ አስጉዞ፣ እዚኸኛዉ የዕድል ፈንታዬ ምዕራፍ ላይ ጥሎኛል፡፡ ድፍን ስድስት ዓመታት አለፉ፤ በፈፀምኩት የግድያ ወንጀል ተፈርዶብኝ ዘብጥያ ከወረድኩ። እንደ ወንዝ ባሻኝ ቅያስ ፈስሼ ዓለሜን የማይበት የወጣትነት ዘመኔ፣ ከእዚህ ጠባብ እስር ቤት ሳልወጣ ያከትማል፡፡  
ጠባቡ የእስር ክፍሌ ዉስጥ አልጋዉ ደርዝ ላይ በቀቢፀ-ተስፋ ተሸብቤ ተቀምጫለሁ። ምሬት ሰበብ ሆኖት ልቤ ዉስጥ የበቀለዉ ዉጥን ጎልምሶ ራሴን ለመግደል እንድቆርጥ አድርጎኛል። ሕይወት ከሞት የላቀ ፋይዳ የሌለዉ ከንቱ ጉዞ መሆኑን ልብ ያልኩት፣ ወደ እዚህ እስር ቤት ከተወረወርኩ በኋላ ነዉ፡፡ ራሴን ለመግደል መወሰኔን ስናገር የሚደነግጥ ሰዉ አይጠፋም፣ ምን ያስደነግጠዋል? ሞት ሁላችንም ፈፅሞ የማንሸሸዉ ዕጣ ፈንታችን ነዉ፡፡
የሰዉ ልጅ ተራና ፋይዳ ቢስ ፍጡር ነዉ፤ ከድንጋይ፣ ከዛፍ፣ ከአሸዋ የላቀ ዋጋ የለዉም። መኖር ከሞት የላቀ ግብ የለዉም፡፡ ታዲያ ዘወትር ለመኖር ፍዳችንን የምናየዉ ለምንድን ነዉ? ይኸን ዘወትራዊ ሩጫ የምንሮጠዉ ለዘመናት በቅብብሎሽ የዘለቀ ልማድ ጠፍሮ ስለያዘን ብቻ ነዉ። የእዚህ ልማድ ብቸኛዉ ገፊ ኃይል የሞት ፍርሀታችን ነዉ፡፡ እነሆ አሁን እኔ ይኸን ታላቅ ፍርሀት ድል ለመንሳት ቆርጬ  ይሄን እቅድ አበጅቼአለሁ፡፡
ያቀናበርኩት የመሞቻ ቴክኒክ በቅፅበት እስትንፋሴን ነጥቆ በድን እንደሚያደርገኝ ፍፁም እርግጠኛ ነኝ፡፡ በእኔ ሞት ምናልባት የሚወዱኝ በብርቱ ሐዘን ሊጎዱ ይችላሉ፤ ግን ጊዜ በሂደት ከሁሉም ልብ ላይ እንደሚደመስሰኝ እሙን ነዉ፡፡
ከመኝታዬ ተነስቼ ከዓመት በፊት ደህንነቴን ለመጠበቅ በማሰብ ሲጋራ ከምትሸጥልኝ የእስር ቤቱ ዘብ የገዛሁትን አነስተኛ ካራ ከደበቅኩበት ሥፍራ አወጣሁ። ካራዉ ከማይዝግ ብረት የተሠራ ነዉ፡፡ ሁለመናዬ ልቤ በወለደዉ ድንገተኛ የሞት ቡከን ቢያርደኝም፣ ዉጥኔን ለመፈፀም አላመነታሁም፡፡ ሰዉነቴ በላብ ተዘፍቋል፡፡ የአእምሮዬ ሚዛን በቅፅበት በመቃወሱ ፈፅሞ ከእዚህ ቀደም ሰምቻቸዉ የማላዉቃቸዉ እጅግ አሰቃቂ ድምፆች በጆሮዬ መስረግ ጀምረዋል፡፡ በቀኝ እጄ የጨበጥኩት ካራ በሁለቱም ጎኑ የተሳለ ነዉ፡፡ የሹራቤን እጅጌ ሽቅብ ከሰበሰብኩ በኋላ በያዝኩት ካራ የግራ እጄን አንጓ ጅማት ገዝገዝኩት፣ ደሜ እንደ ዉሃ  መጉረፍ ጀመረ፡፡ ከአፍታ በኋላ በሰዉነቴ ዉስጥ የተከማቸዉ ደም ፈሶ ስለሚያልቅ፣ ያለ ስቃይ በፀጥታ ይህን ዓለም እስከወዲያኛዉ እሰናበታለሁ፡፡

   

Read 1471 times