Saturday, 19 March 2022 12:15

አፍንጮ (Pinocchio)

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

    «አፍንጮ» (Pinocchio) የተባለው የህጻናት ታሪክ ገጸ-ባህሪ፣ ልብ ብለን ካስተዋልነው የሚገርም ነገር አለው፡፡ ስለ ፍጡር ሳስብ፣ ከአዳም ባልተናነሰ ለምን አፍንጮ እንደሚመስጠኝ አላውቅም፡፡ በጄኔቲክስ ሳይንስ ብያኔ ከመዘንናቸው፣ አዳምም፣ አፍንጮም ፍጡር ሳይሆኑ «ሐውልት» ናቸው፡፡ ሁለቱም እንብርት የላቸውም፡፡ ተረግዘውም ተወልደውም የሚያውቁ አይደሉም፡፡
እናት እና እንብርት ባይኖራቸውም ፈጣሪ ግን አላቸው፡፡ አፍንጮን ከጉማጅ እንጨት ጠርቦ ወደ ትንሽ ልጅነት ያበጀው «ጨቡዴ» የሚባል ሽማግሌ ነው፡፡ ፈጣሪ ልጅ አልሰጠው ሲል፣ ከጉማጅ እንጨት ጠርቦ በሐውልት መልክ አሰናዳው፡፡ አዳምን ደግሞ ፈጣሪ ያሰናዳው ከጭቃ አላቁጦ ነው። ጭቃው ላይ እስትንፋሱን እፍ ሲልበት ነብስ ዘራ፡፡ በእብራይስጥ «ሩህ» ማለት እስትንፋስ ማለት ነው፡፡
አፍንጮ ድሮ ህያው ዛፍ ሳለ፣ ተፈልጦ ወደ ጉማጅ እንጨት ከመለወጡ በፊት፣ ይተነፍስ ነበር፡፡ አተነፋፈሱ ግን እንደ ሰው ልጅ አይደለም፡፡ ማታ ካርቦንዳዮክሳይድ በቅጠሎቹ አስገብቶ፣ ቀን ቀን ኦክሲጅን ያስወጣ ነበር፡፡  ፈጣሪ አዳምን ከጭቃ አቡክቶ ነፍስ በእስትንፋስ ዘራበት። የአፍንጮ ፈጣሪ፣ የድሮ እጽዋታዊ አተነፋፈሱን በሰው አተነፋፈስ ለመለወጥ አፍንጫ ሰራለት፡፡ ሁለቱም ፍጡራን ግን በመሰረቱ ሐውልታዊ አቀራረጽ የተጫናቸው ናቸው፡፡
አዳም እንብርት ባይኖረውም፣ እትብታም ልጆች ግን ከአብራኩ አፍርቷል፡፡ አፍንጮ ግን ራሱም እንዳያድግ ልጆችም እንዳያፈራ ሆኖ ተረግሟል፡፡ መሃል ቤት የቀረ ነው፡፡ ወደ ድሮው እጽዋትነቱ አይመለስም፤ ወደ ሙሉ ሰውነትም አያድግም፡፡ መሃል ቤት፣ የሁለቱም ዓለም አምሳያ ሆኖ ቀርቷል፡፡ የሰው ልጆችን ለመሆን የሚያደርገው ሙከራ ሁሉ ከመባከን ውጭ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ እንደ ሰው ልጆች፣ ውሸት ለመናገር ሙከራ በሚያደርግበት ጊዜ አፍንጫው እንደ አንቴና እየተመዘዘ ከቅርጽ ያወጣዋል፡፡ አፍንጫው በዋሸበት ቅጽበት ቢያድግም፣ አስተዳደጉ የዛፍን ጤናማ እድገት የተከተለ ስላልሆነ ቅጠል አያቆጠቁጥም፡፡ አፍንጮ፣ የሰው ልጅም፣ ዛፍም አይሆንም፡፡ ከሐውልት የሚለየው በመንቀሳቀሱና የሰው ልጆችን ቋንቋ በማቀላጠፉ ብቻ ነው፡፡ ቋንቋውን ሲያቀላጥፍ የምናነበው ለሰው ልጆች በተጻፈ የህጻናት መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ይሄም ነገሩን ቁምነገር አድርገን እንዳናካብድ የሚከለክለን ኃይለኛ “አያዎ” ነው፡፡ ፈረንጆቹ፣ ኃይለኛ ጥምዝ ያለውን አያዎ:-  «ኦክሲሞሮን» (Oxy=sharp + moros=foolish) ይሉታል። አፍንጮም ህልውናው ያለው በህጻናት መጽሐፍና የካርቱን ፊልም ውስጥ ነው፡፡ የሰው ልጆች መዝናኛ ከመሆን ያለፈ የራሱ ግብ የለውም።
የአዳም ግብ ግን ከአፍንጮ ይለያል። ራሱ ፈጣሪ መሆን ይፈልጋል፡፡ ፈጣሪው እንዳትበላ ያለውን ፍሬ እባብ አሳስቶት በልቷል፡፡ ከገነትም ተባሯል፡፡ እርግጥ እባብ በቅርቡ በሰጠው አንድ ኤክስክሉሲቭ ቃለመጠይቅ «እኔ የበለስ ፍሬ በልቼ አላውቅም» ብሏል (እየተባለ) ነው፡፡ «እኔ የበለስ ፍሬ እንዲያውም ያስጠላኛል፡፡ በልቼ የማላውቀውን እንዴት ‘ብሉ’ ብዬ እመክራለሁኝ? አይጥ ብሉ ብል የአባት ነው፤ ሊመስል ይችላል፡፡ አዳም የራሱን ኃጢአት እኔ ላይ ሲዘፈዝፍ ይኸው ሰባት ነው ስምንት ሺ አመት አሁን በቅርቡ ይሞላዋል፡፡ ይኼንን እድል አግኝቼ ብሶቴን መተንፈስ በመቻሌ ደስ ተሰኝቻለሁኝ፡፡ ለምሳሌ ተመልከት የ”አፕል” ካምፓኒን ሎጎ፡፡ የተገመጠ የበለስ ፍሬ ነው፡፡ የሎጎው ባለቤት ፍሬውን የገመጠው ማን እንደሆነ ስለሚያውቅ ብቻ ሳይሆን በመገመጡም ኩራት ስለሚሰማው ነው ምልክቱ አድርጎ የቀረጸው፡፡ ተመልከቱኝ እስቲ እኔን፡፡ አሁንም በሆዴ እንደተሳብኩ ነኝ፡፡ እንደ ፈጣሪ ለመሆን የሚያደርጉትንና የሚሰራቸውን ያጡት የሰው ልጆች ናቸው፡፡ አሁን እያደረግን ያለነው ቃለ መጠይቅ ራሱ በእኔ ስም ሌላ የሰው ልጅ ፈጥሮ እየጻፈው ያለ ነው፡፡ እኔ ምንም ውስጥ የለሁበትም» በማለት እንባ እየተናነቀው እንደተናገረ አክቲቪስቶች ገልጸዋል፡፡
አዳም እንብርት እንደሌለው እንዴት አረጋገጥክ? ብሎ የሚጠይቀኝ ሰው፣ የዋህነት የተጠናወተው ነው፡፡ እንብርቱ የተቀበረበትን ስፍራ ስለማላውቅ እንዳይመስላችሁ እንብርት የለውም ያልኳችሁ፡፡ እኔ አዳም እንብርት የለውም ያልኩት በልቶ ስለማይጠግብ ነው፡፡ የፍላጎቱ መጠን በእንብርት ውል የሚታሰር ባለመሆኑ ምክኒያት ነው፡፡ ቢፈልግ እና ቢያገኝ ራሱ መፈለጉን የማያቆም ነው፡፡ እድሜውን ከልክ በላይ ለጥጦ ከኖረ በኋላ ራሱ የሚመኘው በድጋሚ ወጣት ሆኖ መልሶ መኖር መቀጠልን ነው፡፡ የሌሎችን ፋንታ እየኖረ መሆኑን እያወቀም፣ ምንም አይገደውም፡፡ በድጋሚ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ከአሜሪካ ይመጣል፡፡
አፍንጮ ግን ፍላጎቱ ቀላል ነው፡፡ ፍላጎቱ እውነተኛ የሰው ልጅ መሆን ነው፡፡ ደም፣ ስጋና ተስፋ ያለው የሰው ልጅ መሆን። አፍንጫው ብቻ ሳይሆን፣ ቁመቱም፣ እውቀቱም፣ እድሜውም እንዲመነደግ ነው የሚፈልገው። ግማሽ ጉቶ፣ ግማሽ ጨቅላ የሆነው ህልውናው ወደ ሙሉ ሰው እንዲለወጥለት ነው የሚመኘው፡፡
እርግጥ ተንኮለኛው የሰው ልጅም፣ መጀመሪያ አመጽ ሲቀሰቅስ የሚጠይቀው ጥያቄ ቀላልና መመለስ ያለበትም ይመስላል። ባሪያ መሆን አልፈልግም! ነው የሚለው፡፡ እንደ ማንኛውም የሰው ልጅ መብትና ክብር እንዳለኝ ይታወቅልኝ!… ነው የሚለው፡፡
እውቅና ከተሰጠው በኋላ፣ መብቱ ከተረጋገጠለት በኋላ፣ ለሰው ልጅነቱ የሚመጥን ክብር ከተሰጠው በኋላ… ወደ ዋነኛው ጥያቄ ይገባል፡፡ የመነሻው ጥያቄ፣ መደበኛው ገበታ ከመቅረቡ በፊት፣ ሆድ ለማለስለሻ በትንሽ እቃ እንደሚቀርብ ውኃ መሳይ ሾርባ (Clear soup) የመሰለ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ ከተዋጠ በኋላ በቀላሉ የማይዋጠውን ሁለተኛውን ያመጣል፡፡
አፍንጮም የእንጨት ጉቶ በነበረበት ወቅት፣ የሰው ቅርጽ ያለው የታነጸ እንጨት ልሁን ብሎ ተመኘ፡፡ ጨቡዴ እንጨቱን ቀርጾ የሰው ልጅ አምሳያ ይዘት ሲሰጠው… ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ዞረ፡፡ «እውነተኛ የሰው ልጅ ልሁን» የሚል ሆነ ቀጣዩ ጥያቄው፡፡
ችግሩ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እውነተኛ የሰው ልጅ ቢሆን የሚገጥመው መከራ እንጨት ሳለ አልታየውም፡፡ እውነተኛ የሰው ልጅ ቢሆን፣ የአዳም ኃጢያት ድሮ የማይነካው እሱን መነካካት ይጀምራል። የአዳም እንብርት አልባነት ይጋባበታል፡፡ አልጠግብ ባይነቱ። እንጨት በነበረ ጊዜ ዞር ብሎ የማያየው እባብ… ሊያሳስተው ስራዬ ብሎ እየተሳበ ይመጣል፡፡ «ከሰው ስህተት፣ ከብረት ዝገት አይጠፋም» ብሎ እርሱም ያለ ምንም ማቅማማት ይሳሳትለታል፡፡ ከስህተት ወደ ንስሀ፣ ከንስሀ ወደ ስህተት የሚደረገው ማለቂያ የሌለው አዙሪት ይጀምራል፡፡ እራሱ በድሎ ራሱ የማልቀስን ብልሃት ይካንበታል። ከሰው ልጅነት ጋር ለመተባበር ሲል ከቀድሞው እጽዋታዊ ሚዛናዊነቱ ጋር ይጣላል፡፡ ድሮ ዛፍ የነበረው አፍንጮ፣ ሰው የመሆን ህልሙ ቢሳካለት መጥረቢያ አንስቶ ዛፍ ለመቁረጥ መውጣቱ አይቀርም። ኃይለኛ አያዎነቱ ፈጽሞ ላይታየው ሁሉ ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ እቺ የምናውቃት፣ የምናከብራት፣ በሶ መሳይ የቆዳ ቀለም ያላት፣ ባለውለታችን የሆነችው አህያ፣ ኤክስክሉሲቭ ኢንተርቪው ሰጥታ ነበር እየተባለ ነው። በኢንተርቪው ላይ «እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ብዬም አላውቅም፣ ልልም አልችልም» ማለቷ እየተወራ ነው፡፡ ያወሩት አክቲቪስቶች ናቸው፡፡
እና ምስኪኑ አፍንጮ በሚያሳዝን ሁኔታ ሰው ለመሆን ነው የተመኘው፡፡ ዛፍ ሳለ፣ ማንም በመጥረቢያ ግራ ጉንጩን ቢመታው ቀኙን በዝምታ አዙሮ እንደሚሰጠው አይደለም… ሰው በሚሆን ጊዜ የሚከተለው መርህ፡፡ ጉንጭ አልፋ የሆነ፣ የማያልቅ፣ የግራ እና ቀኝ ርዕዮተ አለም የጥፊ ናዳ ውስጥ ነው የሚዘፈቀው፡፡ ወደ ጥንቱ ለምለም ቅጠላማ ዛፍነቴ መልሰኝ በማለት ፋንታ… ‘ሰው ልሁን’ ብሎ መመኘቱን ባሰብኩት ቁጥር ዘወትር ግርም ይለኛል፡፡
አዳምም «እንደ ፈጣሪዬ በአምሳል ብቻ ሳይሆን በግብርም አንድ አድርገኝ» በማለት ፈንታ እንቢተኝነቱን ተመኘ፡፡ እንቢተኝነቱ እንብርት አልባ አደረገው፡፡
ምናልባት፣ የሁለቱም ፍጡራን ስህተት ከአፈጣጠራቸው የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ከአፈር የተሰራ ትቢያ ላይ የፈጣሪን ትንፋሽ ማሳረፍ፤ እንዲሁም፣ በፈጣሪና በተፈጥሮ ሚዛን የተሰራ የእጽዋት ቅሪት የሆነ ጉቶ ላይ የሰው ልጅነትን ህልም ማሳረፍ…. ይሄ ሊሆን ይችላል የችግሩ መሰረት፡፡ የማይመጣጠኑ ነገሮችን መቀየጥ አጥፊ ማንነትን አምጦ እንደመውለድ ይቆጠራል፡፡ ለፍጡሩ ስህተት የፈጣሪውም እጅ በመጠኑ አለበት፡፡



Read 11179 times