Saturday, 26 March 2022 10:16

‘ኩርፊያ በባዶ ሜዳ!’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው... የአንዳንዶቻችን ፍጥነት፣ ምን አለፋችሁ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አሃ ልክ ነዋ... ለምሳሌ የሆነ ጉብታ በዝላይ ወይ ኩሬ ምናምን ለመሻገር መጀመሪያ መንደርደር አያስፈልግም እንዴ! አሁን እዚህ አይታችሁት ነገ ደግሞ ከጋራው ማዶ ስታዩት ወይ እሱ መንፈስ ነው፣ ወይ እናንተ ዶክተር እንትና የሚባሉ ምርጥ የአእምሮ ሀኪም ዘንድ መሄድ አለባችሁ፡፡ ችግር ይኖራላ! ዛሬ ቀስ ብሎ ከመናገሩ የተነሳ ድምጹ በመከራ የሚሰማና “የሰከነ፣ ዝምተኛ፣” የሚባልለት ሰው፣ በሦስተኛው ቀን “እንደው ትንሽ እንኳን ጉሮሮውን አይቆጠቁጠውም!” የሚያሰኝ በአምስት ሰከንድ ሀምሳ አምስት ቃላት የሚተኩስ  ቦተሊከኛ ሲሆን ግራ ይገባላ! አለ አይደል “የዛሬውስ መውደድ እንስፍስፍ አረገኝ...” አይነት ነገር፡፡
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ምነው ከመሬት ተነስቶ የሚያኮርፈን በዛሳ! አሀ...ትናንት ሲያገኘን የእሱ ፈገግታ ስለማይበቃው ከሌላ ለመበደር ምንም የማይቀረው፣ ዛሬ ገና ሲያየን  ፊቱን ድስት ሙሉ እንቆቆ የጠጣ የሚያስመስለው ምን አድርገነው ነው? አሀ...ታዲያ ኑሮ ቢከብደውስ! ለእሱ የከበደው ኑሮ ለእኛ ቀሎናል ያለው ማነው! የጓዳችንን በጓዳችን ቆልፈንበት በአደባባይ ‘ጠዳ፣ ጠዳ’ ብለን ስለታየን በግልምጫ አንስተው የሚያፈርጡን እዳ አለብን እንዴ!
ቀደም ባለው ጊዜ የሆነ ወዳጅ በድንገት ካኮረፋችሁ የሆነ ምክንያት አለው ማለት ነው፡፡ ወይ የሆነች ቆንጆ ነጠቀኝ ብሎ ጠርጥሯችኋል...ወይ ደግሞ ሁለት መቶ ብር በሁለት ወር እመልሳለሁ ብሎ ወስዶ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡
የምር ግን... ሰዋችን በብዙ መልኩ እንደከፋው የምታውቁት መንገድ ላይ ምን ያህሉ ገጽታው እንደዳመነ ስታዩት ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አንዱን አለፍኩት ሲሉት ሌላ አንድ መቶ አንድ  ‘የሚነጅስ’ ነገር ስለማይጠፋ ፈገግ የሚል ሰው ቢቀንስ አይገርምም፡፡
እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ይሄ የአበዳሪና የተበዳሪ ነገር እኮ ስንቱን አቆራርጦታል መሰላችሁ፡፡
“ምነው ደህና አይደለህም እንዴ! ሳይህ የሆነ ነገር የረበሸህ ነው የምትመስለው፡፡”
“ምን እባክህ...እንደውም ወዳንተ ስመጣ ነው ያገኘኹህ፡፡”
ኸረ በህግ! የእናንተ ቤት ያለው ጉለሌ፣ እሱን ያገኛችሁት ወደ አራት ኪሎ በእግሩ ሲያቀጥነው! ወደ አራት ኪሎ እየሄደ ያለው ሰው  በምን አይነት ተእምር ነው ወደ እናንተ ቤት ወደ ጉለሌ እየመጣ ሊሆን የሚችለው! ግን ደግሞ ምን መሰላችሁ...አሁን አሁን ይቺ ሀገራችን ሊሆን አይችልም ያላችሁት ነገር ሊሆን የሚችልባት እየመሰለች ስለሆነ፣ ምናልባት እናንተ ያልደረሳችሁበት ‘የተለየ ጥበብ’ ሊኖር ይችላል ብሎ መጠርጠር ክፋት የለውም፡፡
“ምነው፣ በደህና?”
“አንድ ነገር ላስቸግርህ ነበር፡፡” ምን መሰላችሁ የሆነ ሰው ‘አንድ ነገር ላስቸግርህ ነበር...’ ብሎ ዓረፍተ ነገር ከጀመረ ቀሪውን ክፍል መሙላቱ ከባድ አይሆንም። መጠኑን አታውቁትም እንጂ ያው የፈረንካው ጉዳይ እንደሆነ ታውቁታላችሁ፡፡  እናላችሁ... “እንዴት ቸግሮህ?” “በምን ምክንያት ቸግሮህ?” ምናምን ብሎ መጠየቅ አያስፈልግም፡፡
“ቢበዛ በአስራ አምስት ቀን የምመልስልህ ሦስት መቶ ብር ብታበድረኝ...” ወይ ዘንድሮ በተደጋጋሚ እንደምንሰማው የሆነ ነገር አስነክቷችሁ፣ ወይ የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ ሲቪያችሁን ወፈር ለማድረግ አስባችሁ፣ ብቻ በሆነ ምክንያት ትሰጡታላችሁ፡፡ በአስራ አምስተኛው ወር ፊት ለፊት ስታገኙት...አለ አይደል... ግንባሩ ላይ የተደረደሩት እርከኖች ድንበር ጥሰው አገጩ ስር ደርሰዋል፡፡ አለ አይደል... የማይረሳ፣ ይቅር የማይባል ብቻ ሳይሆን በነፍስ የሚያፈላልግ ግፍ ፈጽማችሁበት ተሸሽጋችሁ የከረማችሁ ነው የሚመስለው፡፡
ታዲያላችሁ... ለሰላምታ ስትዘጋጁ ልክ እንዳላያችሁ ልትጨብጡት የዘረጋችሁትን እጅ እንዳንከረፈፋችሁ ትቷችሁ ያልፋል። እናላችሁ... በእናንተው ያልተመለሰ ሦስት መቶ ብር የሠላሳ ዓመት ወዳጅ ያኮርፋችኋል። እመኑኝ... ሰላም ቢላችሁ እንኳን “ብድሩ አትመልስልኝም እንዴ?” ለማለት የሆነ ነገር አንደበታችሁን ቁልፍ አድርጎ ይይዛችኋል፡፡ እናማ...“ከጓደኛህ መኳረፍ ከፈለግህ ገንዘብ አበድረው፣” የሚባለው ዝም ብሎ አይደለም ለማለት ነው፡፡
“ስማ ይቺን ልጅ በደንብ እወቃት፡፡ እኔ ጁዲ ብዬ ነው የምጠራት...”
“ጆሴፍ እባላለሁ፡፡ ስላወቅሁሽ ደስ ይለኛል...” (ማንም ሰው “ከመቼ ወዲህ ነው ጆሴፍ የሆንከው?” ብሎ ስለማይጠይቅ ችግር የለም፡፡ ግን ይህ መተተኛ ቆንጆ ቆንጆዋን ከየት ነው የሚያገኘው! እኛ በየሁለት ወሩ ጫማ እየጨረስን አልሳካ ብሎናል፣ እሱ ምን እያስነካቸው ነው! እኔ እኮ ያለምንም ምክንያት “ገጠር እያለ ሲመላለስ የሆነ ምስጢር እንዳለው እጠረጥር ነበር! ቂ...ቂ...ቂ....)
“ጁዲ እባላለሁ፡፡ እኔም ስላወቅሁህ ደስ ብሎኛል፡፡;  ስሙኝማ ይሄ ኩዋንተም ምናምን ነገር  ሊያብራራው በማይችለው ሁኔታ አእምሯችሁ ‘ደስ ብሎኛል’ ያለችውን ምን ብሎ ቢተረጉመው ጥሩ ነው... “ደስ ብለኸኛል!”
ታዲያላችሁ... ቀስ በቀስ ከጓደኛችሁ ‘ክሌኦፓትራ’ ተቀራርባችሁ እንደ ብዙ ዘመን ወዳጅ መጫወት፣ መሳሳቅ ትለምዳላችሁ። ‘የፈረንጅ አፍ’ ትንሽ ስለምትሞክር...ሲጠራሩ እንኳን “ጁዲዬ ቢዩቲፉል!” እሷ ደግሞ “ጆሲዬ ሀንድሰም!” ይሆንላችኋል... በትውውቁ ሦስተኛ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ማለት ነው፡፡  እናማ... በመጀመሪያዎቹ ቀናት.... “አንተ ከእኛ ጋር እራት የማትበላው ለምንድነው?” "ጁዲን እንደሚከፋት አታውቅም!” ሲል የነበረ ጓደኛ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው...ያኮርፋል! ራሱ ለመሸለል፣ “እንደኔ አይነቱን ጓደኛ እግራችሁ ሲቀጥን ብትሄዱ አታገኙም!” ብሎ ጉራውን ለመነስነስ አንዴ እራት፣ አንዴ ምናምን ሲል ቆይቶ ጭራሽ አኩርፎ እንትኑን ጣይ እሱ ሆኖ ያርፈዋል! እናላችሁ.... ቀደም ሲል ሰው ለማኩረፍ የሆነች ምክንያት አያጣም ነበር ለማለት ያህል ነው፡፡
ዘንድሮ ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባ ሆኖ የለ...ማህበራዊ ግንኙነታችን ውስጥም ግራ የሚያጋቡ ባህሪያት እየበዙ ነው፡፡ የምር አስቡት እስቲ፣ ለረጅም ጊዜ በጣም በቅርብ በወዳጅነት አብራችሁ የኖራችሁት ሰው፣ ለማንም  የማትነግሩትን ምስጢር ሁሉ ስታወሩት የነበረው ሰው፣ ከመሬት ተነስቶ ጀርባውን ሲያዞርባችሁ ለወሬ አያስቸግርም!
“ስማ ያ እንትና እንዲህ ልውጥውጥ ያደረገው ምንድነው? አይደለም ብዙ ዘመን ልንተዋወቅ፣ ከእነመፈጠሬም አይቶኝ እማያውቅ ነው እኮ የመሰለው!”
“ይህን ያህል ምን ቢያደርግህ ነው!”
“አያኮርፈኝ መሰለህ! ትሰማኛለህ፣ አኮረፈኝ እያልኩህ ነው!”
“የተጋጫችሁበት አለ እንዴ!”
“በጭራሽ! እኔ እኮ እሱ ነው የገረመኝ፡፡ አይደለም ልንጋጭ ሀይለ ቃል ተለዋውጠንም አናውቅ፡፡ ሰው ከመሬት ተነስቶ ያኮርፋል! ለነገሩ ሰዉን ሁሉ ነው ያኮረፈው አሉ፡፡”
“ጎሽ፣ እኔም እንደሱ እንድትለኝ ፈልጌ ነው፡፡”
“አልገባኝም...”
“እኔንም በማላውቀው ምክንያት አኩርፎኝ የምነግረው ሰው አጥቼ ነበር!”
“ጭንቅሌው ጠሽ አለች እንዴ!”
“እሱን ሂድና ዘመዶቹን ጠይቅ፡፡”
“የምሬን ነው እኮ! ወይ ጭንቅላቱ ጠሸ ብላለች ወይ የሆነ የፖለቲካ ቡድን ውስጥ ገብቶ ይሆናል፡፡”
“የአሜሪካው ሪፐብሊካን ፓርቲ ማለትህ ነው?”
“አዎ፣ አንተ ምን አለብህ፣ ቀልድ እንጂ፡፡”
“ቀልድ ሳይሆን እዚህ ያሉት ሁሉ ቦታ ሳይሞላባቸው አይቀርም ብዬ ነው!”
“ስማ የፈለግኸውን ያህል ብትነካካኝ የሚቦተልክልህን ሂድና ፈልግ፡፡ ይልቅ የዚህ የወዳጃችን ነገር...”
እናማ... ለምን ከመሬት ተነስተን ምንም የከፋ ነገር ያላደረጉብንን ሰዎች የምናኮርፍበትን ምክንያት ለማወቅ እንትን ድርጅት ስፖንሰር የሚያደርገው ጥናት አይካሄድልንም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1627 times