Saturday, 26 March 2022 15:47

“ውራጅ”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)


               "-+መኪናዋን ስንመለስም እየነዳት ነበር፡፡ ከእኔ ይልቅ ከመኪናዋ ጋር ክፉ ትዝታ ያለበት ይመስላል፡፡ እኔን ከአልጋው ቤት ከወጣን በኋላ አልነካኝም፡፡ እኔ ደግሞ በተገላቢጦሽ ላቅፈው እፈልጋለሁ፡፡ አልተያዘልኝም፡፡ ያሟልጫል፡፡ ዝም ብዬ አለቅሳለሁ፡፡ የማለቅሰው ለራሴ ነው፡፡--"
              
                ምድርን  ከሰዎች ጋር እጋራለሁ፡፡ ግን፣ አስታዋሽ ካልመጣብኝ መርሳት የምፈልገው ሃቅ ነው፡፡ ልክ እንደዚህ እስክርቢቶ፣  አዲስ ከፋብሪካ የመጣ ያልተነካካ ነገር  ብገለገል፤ እመርጣለሁኝ፡፡ ምርጫዬ ግን አንዳንድ ነገር ላይ አይሟላም፡፡ ባለፈው፣ አንድ ማየት ከማልፈልገው ሰው ጋር መንገድ ላይ ተገጣጠምኩኝ፡፡ የትራፊክ መብራት ሲሻገር፡፡ ደግነቱ በመኪና ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ በፍጥነት፣ ባላየ ለማለፍ ተመቸኝ፡፡ የትራፊክ መብራቱ እግረኛን ነው የያዘው እንጂ ተሽከርካሪውን ለቋል፤ አረንጓዴ በርቷል። አረንጓዴ መብራትን እንደዚህ  ወድጄው አላውቅም፡፡
ለሰላምታ እጁን ሳያውለበልብልኝ አልቀረም፡፡ “ባላየ” ስለሆነ ማለፍ የፈለኩት አፀፌታ አልሰጠሁትም፡፡
ስም ያለው ጥሩ ቡና የሚሸጥበት የሆነ ቤት አለ፡፡ ወደዛ ነው ያመራሁት፡፡ እየሄድኩ የነበረው ወደ ሌላ ቦታ ቢሆንም ሰውዬውን ትራፊክ መብራት ላይ ካየሁት በኋላ ጠንካራ ቡና አስፈለገኝ፡፡ መኪና ስላለኝ ከአንድ ቦታ በቅፅበት ጠፍቼ ሌላ ቦታ መገኘት እችላለሁኝ፡፡ እሱ እግረኛ ስለሆነ እዛው በጎዳናው ጥግ ጥግ ይኳትን። ማየት የማልፈልገው ሰው ነው፡፡ የሞተ የመሰለኝ ሰው፡፡ አለመሞቱ አስደንግጦኛል። የነበረብኝ የቡና ሱስ ብቻ ነው፡፡ እሱንም ትቼው ነበር፡፡ ድንገት አስፈለገኝ፡፡
ቡናውን አይኔን ጨፍኜ ነው ማጣጣም የፈለኩት፡፡ ከቡና በስተቀር ምንም ሱስ የለብኝም፡፡ ቡና በቀን አንዴ… አልፎ አልፎ… በፍጥነት የሚከናወን ከሆነ መጥፎ ልምድ ሊባል አይችልም አይደል? ኡ.ስ.ስ.ፕ እያደረግሁ ብርጭቆውን በከንፈሬ እመጠዋለሁ፡፡
“አንዳንድ ሰው አይሞትም ማለት ነው?” ብዬ አስባለሁኝ፡፡ ባላየው  ኖሮ---- በህይወት እንዳለ   አላውቅም ነበር፡፡ ካየሁት ጀምሮ የሆንኩት ነገር አለ፡፡ ጩ-ኺ ጩኺ ይለኛል። ከመልኩ አስቀድሞ እንዴት ጠረኑ ትዝ አለኝ? ቢታጠብም ባይታጠብም አንዳንድ ሰው ሁሌ ጠረን አለው…፡፡
አይኔን ስገልጥ የሆነ አዲስ ፒክ አፕ መኪና ቡና ቤቱ ፊትለፊት እየቆመ ነው። ከእኔ መኪና አጠገብ  ሲቆም ከእድሜዋ በላይ አስረጃት፡፡ የመኪናዬ እድሜ የራሴን አስታወሰኝ፡፡ ማርጀትም አለማርጀትም በአንድ ላይ እፈልጋለሁኝ፡፡ ማርጀት ይዟቸው የሚመጣቸው ፀጋዎች አሉት። መረጋጋት አንዱ ነው፡፡ የጉርምስና ደም መጥፎ ነው። ሙሉ ማርጀት አልፈልግም፡፡ በተለይ ገላዬ ሳይረግፍ ነው መረጋጋት የምፈልገው፡፡ ረጋ ብዬ እያስተዋልኩ ግን ደግሞ ቀልጠፍ ማለት፡፡ ተመልሶ እንዲመጣ የማልፈልገው ጊዜ አለ፡፡ በተለይ ግን ተመልሶ እንዲመጣ የማልፈልገው ጊዜውን ሳይሆን፣ ከጊዜው ጋር የሚመጡትን አንዳንድ ሰዎች ነው፡፡ መብራት ላይ ያየሁት የዛ ዓይነቱ ሰው ነው፡፡
ግራ ገባኝ፤ ደነገጥኩኝ፤ ግር አለኝ፡፡ ቅድም ትራፊክ መብራቱ ጋር የተውኩት ሰውዬ ነው፣ መኪናውን አቁሞ እየወረደ ያለው። ቶሎ ፉት ማለት የጀመርኩትን ጨልጬ መሮጥ ፈልጌአለሁ፡፡ ግን ደግሞ፣ ለምን አልኩኝ፡፡ የሚያስጠላኝ ሰው መጣብኝ እንጂ በእዳ የሚፈልገኝ አበዳሪዬ አይደለም፡፡ “ቀስ በይ” አለኝ ኩራቴ፤ ከሆነ ጎኔ ብቅ ብሎ፡፡ ኩራቴ፤ ከኔ ዘወትር የማይለየኝ ውጋቴ ነው።
እንደፈራሁት እየተጣደፈ መጥቶ ጨበጠኝ፡፡ ይህ ሰውዬ በማይመላለስበት የምድር አካል ላይ ለመኖር እችላለሁኝ። እጓጓለሁኝ ማለት ሳይሆን ጊዜ ማሳለፍ እችላለሁኝ፡፡ ሞት ሳይናፍቀኝ፡፡
እንደ ማንኛዋም ሴት ትዳር አለኝ፡፡ ደግሞ እንዴት ያለ ደግ ሰው ነው ባለቤቴ። ልጄን እና እኔን ወረት በሌለው ፍቅር የሚወድ ባል፡፡ የበሰለ፡፡ ተምሮ የጨረሰ፡፡ አዳዲስ ነገር እያስተማረኝ የማያስደነግጠኝ፡፡ ትዕግስት እና ትምህርት ያለው፡፡ ትምህርቱን ላቡን አንጠፍጥፎ ያገኘው፡፡ ትዕግስቱን በተፈጥሮ። ማስተዋል የሚችል፡፡ አይዞሽ የሚለኝ፡፡ ሲለኝ ደግሞ የእውነቱን፡፡ ከጎኔ  የማይጠፋ፡፡ ሮብ እና አርብ ሳይሳሳት የሚጾም፡፡ ሃይማኖት ያለው፡፡ ሃይማኖተኛ። በቤተስኪያን ደጃፍ በእግሩ ሲያልፍ አጥሩን ሳይስም የማይቀጥል፡፡ በእግሩ ከሆነ፡፡ መኪና ከያዘ ደግሞ በአንድ እጁ መሪ ሳይለቅ፣ ጎንበስ ብሎ  የሚሳለም፡፡ ሴት ልጁንና እኔን በብዙ የቁልምጫ ስም የሚጠራ፡፡ የማይቆጣ፡፡ ምራቁን ዋጥ ያደረገ፡፡ የማይተፋ የማያቀረሽ።
እጄ  ላይ… ሶስተኛው ጣቴ ላይ፣ በግራ በኩል ያጠለቅሁትን አምስት ግራም ወርቅ እንዲታይ አድርጌ ጠረጴዛው ላይ ክርኔን አሳረፍኩኝ፡፡ የፊቴን ገፅታ በግዴለሽ ፈገግታ አስዋብኩት፡፡ እንደ ድሮው አይደለሁም። እንደሚፈራኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ፊቴን አውቀዋለሁኝ፡፡ የማለብሰውን መልክ ይለብሳል፡፡ “አታውቀኝም አላውቅህም” እንዲልልኝ ነው፤ በዛ ቅፅበት የፈለኩት።  በፊት ለፊት በኩል፡፡ በሚታየው በኩል።  ሆዴ ውስጥ ልቤ  ውስጥ ግን ያለው ሌላ ነገር ነው፡፡ ውስጤ እርብሽ እያለብኝ ነው፡፡
“አሁን አንተ በአርያ ስላሴ የተቀረጽክ ሰው ነህ?” የሚል ንግግር ነው በአንደበቴ የመጣው፡፡
“ሀይሚዬ መብራት ላይ እኮ ሰላም ስልሽ አላየሽኝም” ብሎ ተጠመጠመብኝ፡፡ ብገፈትረውም አልላቀቅ አለ፡፡ የስጋ ግንብ ነገር ነው ሰውነቱ፡፡ አልጮህ ነገር፤ ማፈር ፈፅሞ ያልፈጠረበትን ሰው መሸሽ ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡ ገና ሲገባ መሮጥ እግሬ አውጭኝ፣ ማለት ነበረብኝ ማለት ነው?
በጣም ረጅም ደቂቃ አቅፎኝ ቆየ፡፡ አቅፎኝ በብብቱ ስር  ብቅ ያለውን ፊቴን በእጁ ያሸሸዋል፡፡ ጠረኑ ያው ነው፡፡ ለነገሩ ምን የተቀየረ ነገር አለው? ዘመን ብቻ እሱን ሳያየው አልፎታል፡፡ ቢያየውማ ይለውጠው ነበር፡፡ ያዳክመው ነበር፡፡ ይሰባብርልኝ ነበር። ለኖርኩት ለእድሜዬ ከማም ለበረከተልኝ የሚገባው አክብሮት ከዚህ ዲያብሎስ ይቸረኛል ብሎ ማሰብ ከንቱ ሞኝነት ነው፡፡ አይሰማም ይሄ ሰው፡፡ አይሰማውም፡፡
---- ስልክ የሚደውልልኝ በዛች ቅፅበት አምላክ ቢልክልኝ፣ መንግስተ ሰማይ ከመግባት በላይ በሆነልኝ ነበር፡፡ እንደማይሆንልኝ ግን አውቄአለሁኝ፡፡
“ልቀቀኝ” ብዬ መጮህ ፈልጌአለሁ። የሚጮህበት ሰዐት ግን አይደለም። ቡና ቤት ውስጥ ሰላምታ በአንድ ጓደኛዬ እየተለገሰኝ ስለመሆኑ ነው ታዛቢ የሚያውቀው፡፡ ተመልካች የሚመለከተው መች ገብቶት ያውቃል፡፡ ይሄ ነብሰ በላ ግን ሁሉም ይገባዋል፡፡ እንድምጠላው ያውቃል። እሱ  ቢሞት  አለም  የተሻለ ትሆናለች ብዬ እንደማምን፣ እምነቴም እንዲፈፀም ስጸልይ እንደቆየሁ ያውቃል፡፡ ዲያቢሎስ ነው፡፡ የሰውን መብትና ፍላጎት አያከብርም፡፡ ሰውን አበላሽቶ መስዋዕትነት አስከፍሎ ይሰወራል። ስለ ምንም ነገር ስሜት አይሰጠውም፡፡ ያኔም መጥቶ ተጫውቶብኝ ሲሄድ ፍቃዴን ጠይቆ አልነበረም፡፡  ባህሪው እንደዛ ነው፤ የሰውን ስምምነት አይጠይቅም፤ ያኔም ድሮ ያስገድደኝ ነበር፤ አሁንም ያው ነው፡፡ ጨምቆ አቅፎኝ እንደታረደ ዶሮ ተፍጨርጭሬ እስክጨርስ ጠበቀኝ፡፡
“ዛሬማ ምሳ ሳንበላ አንላቀቅም”
በአንድ እጁ ጥርቅም አድርጎ እንደያዘኝ የራሱን ጥቁር ማኪያቶ አዝዞ፣ ጠጥቶ ጨረሰ፡፡ ጉልበቱ ይገርመኛል፡፡ የሰውን ጉልበት እንደ መቅኒ እየሳበ የሚጠጣ፣ የራሱን ግን የማያስቀምስ ነው፡፡ ድሮም እንደዛ ነበር፡፡ እኔን አዳክሞ እሱ ግን በርትቶ ነበር የምንለያየው፡፡
የሞተ መስሎኝ ነበር፡፡ በሞተ ብዬ ጸልያለሁኝ፡፡ የሞተ ባይመስለኝ ርቄ ከሄድኩበት ሀገር ወደዚህ ተመልሼ ድርሽ አልልም ነበር፡፡ ከባለቤቴ ጋር ስገናኝ የተበላው ጉልበቴ አንሰራራ፡፡ ባህር ማዶ ስደት ላይ እያለሁ ነው ጉልበቴን ያገኘሁት። ጉልበቴን መልሶ የሰጠኝን ሰው አገባሁት። ፈጣሪ የታረቀኝ መስሎኝ ነበር፡፡ አንድም ቀን በድሎኝ አያውቅም፡፡ ከስሪቱ ነው፡፡ ስሪቱ የጨዋ ነው፡፡ በአርያ ስላሴ አምሳል የተፈጠረ ማለት ባለቤቴ ነው፡፡ ክፉ አይደለም፡፡ ስጋ ብቻ አይደለም፡፡ በአጥንቴ ሳለሁ ደረሰልኝ፡፡ ያለቀውን ስጋዬን ይዞልኝ በመጣው ደግነቱ ሞላው፡፡ አገባኝ፡፡ ተስፋ ይዘን ወደ ሀገር ቤት ተመለስን፡፡ ቤት ሰራን። ሰራልኝ፡፡ እሱ ራሱ ነው ግን የማይፈርሰው ቤቴ፡፡ ልጅ ወለድን፡፡ “ወለድሺልኝ” ሲለኝ ይገርመኛል፡፡ እሱ የሰጠኝ እንጂ እኔ አንድም የመለስኩለት የለኝም፡፡
ባለቤቴ እንደዚህ እስኪሪቢቶ ነው፡፡ እየፃፍኩበት ያለው እስኪሪቢቶ ገና አዲስ ነው፡፡ ማንም ተጭኖ ፅፎበት አያውቅም፡፡ እድፍ አይተፋም፡፡ ንፁህ ነው፡፡ ህሊናውም አካሉና ነብሱም፡፡
 አለም ግን እንደዛ አይደለችም፡፡ ወደ ኋላ ወድቆ የተጣለ የመሰለንን ቆሻሻ መልሳ ታመጣለች፡፡ በቡና ቤቱ ውስጥ እጄን እንዳይላወስ አድርጎ የያዘኝ ወድቆ የጠፋ የመሰለኝ  ቆሻሻ ነው፡፡ ቆሻሻ ለካ ይሰወራል እንጂ አንዴ ከተፈጠረ አይጠፋም። ፈርጣማ ክንድና ደስ የማይል ጠረን አለው። በቆሻሻው ውስጥ ራሴን ወድቄ ሳየው የጀመርኩት አዲስ ጎዳና ይጠፋኛል። ዋጋዬ ይረክስብኛል። ድካሜ ይመለሳል፡፡ መከራከር እንኳን ያቅተኛል፡፡ መፍጨርጨር ይሳነኛል፡፡
እየጎተተ ያወራኝ ጀመር፡፡ እየጎነተለ። ማግባቴን ብነግረውም አልደነገጠም።  የፊቱን ቆዳ ለመወጠሪያ በደንብ የሚገለገልባት ሳቅ አለችው፡፡
እየሳቀ “አውቀዋለሁኝ… ግን  አመንሽበት?” አለኝ፡፡
ኡኡ---ብዬ ጮህኩኝ፡፡ ግን ጩኸቴ ከጉሮሮዬ ተሻግሮ አልወጣም፡፡ የሰራ አካላቴ ብቻ ዛር እንደወረደበት ይንቀጠቀጣል፡፡ እያለቀስኩ ነው፡፡ እንባ ግን አይወርደኝም። ማንም የሚያስጥለኝ የለም፡፡ ወደ ባለቤቴ ለመደወል እፈልጋለሁኝ፤ ግን አልችልም። ስልኩ ከነአካቴው ቻርጅ አልቆበት ጠፍቷል።
ከቡና መጭመቂያው ቤት ስንወጣ የመኪናዬን ቁልፍ ከእጄ ተቀብሎ እየሾፈራት ነው፡፡ ትንሽ እንኳን ግር አላለውም፡፡ እኔን እንዳስገደደው መኪናዬንም አስገድዷታል፡፡ እየነዳ የመጣትን አዲስ ፒክ አፕ እዛው ቡና ቤቱ ደጃፍ ጥሏታል፡፡ ድሮ በስህተት ሰው ቆሻሻን ወስዶ የሚጥል ይመስለኝ ነበር፡፡ እውነቱ ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ቆሻሻ ነው ሰውን የሚጥለው፡፡ ሊጥለኝ ይዞኝ እየሄደ ነው፡፡
“ይገርማል መገጣጠም፡፡ የሰው ታሪክና የመኪና” እያለ የመኪናዋን መሪ በአንድ እጁ፣ የእኔን ታፋ በሌላው ይደባብሳል፡፡
“ከማን ነው የገዛሻት እቺን መኪና?” አለኝ፡፡
 ለሚጠይቀኝ ጥያቄ መልስ ያለመስጠት መብቴ፣ በእሱ የራስ መተማመን ብልግና ቀልቡን ተገፏል፡፡
“እቺ መኪና ከአራት ዓመት በፊት የእኔ እንደነበረች ታውቂያለሽ አይደል? አታውቂኝም፡፡ እንዴት ልታውቂ ትችያለሽ?” አሁን እኔን መደባበሱን አቁሞ፣ አንድ እጁን ስልኩን ለመክፈት ተጠቀመበት። ከፍቶ ፎቶ ማንሸራተት ጀመረ፡፡ መርጦ አንድ አወጣ፡፡ እጥረቱ ደስ የማይል ቁምጣ ወጥራ ከታጠቀች ልጃገረድ ጋር አብረው ቆመው የተነሱት ፎቶ ነው፡፡ ከቁምጣው ይልቅ ጡቶቿ የተጋለጡበት መንገድ ያስደነግጣል። ተደግፈው የተነሱት መኪና ባለቤቴ፣ ለእኔ ከሁለት አመታት ቀደም ሲል የገዛልኝ፣ አሁን እሱ እየነዳ ያለችው ናት፡፡
በፍጹም ከባለትዳርና ከአንድ ልጅ እናት የማይጠበቅ ጥያቄ ከአፌ ሲያመልጥ፣ ፈስ እንዳመለጠው ሰው እኔው  መልሼ ደነገጥኩኝ፡፡ መኪና ስለምድ ደጋግሜ ተጋጭቻለሁ፡፡ ግን ይሄንን ያህል በሰራሁት ስህተት ደንግጬ አላቅም፡፡
“ማናት እሷ?” ብዬ ነው የጠየቅሁት፡፡ ያንን ሳቅ ደገመልኝ፡፡
“እዚህ መኪና ውስጥ ስንት ታሪክ ተሰርቷል” ብሎ በድጋሚ ይስቃል፡፡
መወራት የነበረበት ታሪክ ደጉ መሆን ነበረበት፡፡ ደጉ ታሪክ እኔና ባለቤቴ አብረን የሰራነው እንጂ የዚህኛው አይደለም። ረጅሙ ታሪክ ደጉ ነው፡፡ ቆሻሻው ቅፅበታዊው ነው፡፡ የቆሸሸውን ለማጠብ የእድሜ ልክ የፀፀት ፈሳሽ ሳሙና ይፈልጋል። የትሁታኑ ታሪክ በድንገት በአመፅ ተበላሸ። የሆነውን የትኛውንም ነገር የመከላከል አቅም አልነበረኝም፡፡
የባህል ምግብ ቤት ልጋብዝሽ ብሎ ሲያስገባኝ፣ እጄን ለመታጠብ ብዬ በጓዳ በር እንደማመልጥ እያውጠነጠንኩ ነበር። የመኪናዬን ቁልፍ መንጭቄ ለመሮጥ ነበር ሀሳቤ፡፡ በሰው መሃል “ይሄ ሰውዬ ጠላቴ ነው፤ ያደረገኝን አታውቁም” እያልኩ ለመጮህ ነበር ፍላጎቴ፡፡ ግን በሆነ እኩይ ሀይሉ ሸብቦኝ እንዳልላወስ አድርጎ አሰረኝ። እንደሚታረድ በግ ሆንኩኝ፡፡ እጄን ታጥቤ ተቀምጬ መብላት ስጀምር፣ ስጋዬ መንፈሴን አሸነፈው፡፡ በራሴ ቤት  ከሚቀርበው ምግብ ምንም የተለየ ባይሆንም፣ ደጋግሜ ለመጉረስ ተንሰፈሰፍኩኝ፡፡ የባህል ምግብ ቤቱ፣ የባህል መጠጥ አብሮ አቀረበልኝ፡፡ ከቡና ውጭ ምንም ነገር ለወትሮው የማልነካው ሴትዮ፣ በጠባቡ የብርሌ አፍ የቀረበውን ቢጫ እብደት ተስገብግቤ መሻማት ጀመርኩኝ፡፡
የባህል ምግብ ቤቱ የባህል መጠጥ ብቻ ሳይሆን፣ የባህል ጭፈራንም በቅደም ተከተል ያቀርባል፡፡ አንዱ ሃጢአት ሌላኛውን እንደሚጠራ ጋባዤ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በአዲስ እስክርቢቶ አሮጌ ታሪክን በድጋሚ መጻፍ የጀመርኩት እዚህ ነጥብ ላይ ነው፡፡
እንደዛ አይነት እስክስታ መውረድ እንደምችል አላውቅም ነበር፡፡ አላውቅም ሳይሆን ረስቼ ነበር፡፡ መጠጡ ጭፈራውን፣ በቁም ትከሻ መስበቁ፣ በአግድም የሚከተለውን ጭፈራ እንደሚመራ አውቃለሁኝ፡፡
የሆነ ነጥብ ላይ ራሴን ስስቅ ሳወራና ስጫወት ያዝኩት፡፡ የማወራው አብሮኝ ለተቀመጠው የስጋ ግድግዳ ነው። እስቅለታለሁኝ፡፡ የመኪናዬን ቁልፍ መልሶልኛል፡፡ እኔ ግን እግሬን ማንቀሳቀስ አልቻልኩም፡፡ አልፈለኩም፡፡ እንዲያውም እሱ አስታዋሽ፣ አሳቢ መሰለ፡፡
“ቤት ብትደውይ አይሻልም እንዳያስቡ?”
“ምን ብዬዬዬ?” ለምን ብዬ ይመስላል አባባሌ፡፡ መልሶ በራሴ ጓሮ ሲገባ፡፡ አቅፌዋለሁኝ፡፡
የሰው አይን አሁንም አይደርስልኝም፡፡ አያስጥለኝም፡፡ ባያስጥለኝም እየገላመጠኝ ነው፡፡ ሁሉም ሰው የሚያውቀኝ ይመስለኛል፡፡ እንዳያውቀኝ ለማድረግ ብዙ መጨለጥ ነበረብኝ፡፡ ራሴን በመርሳት እነሱ እንዳያስታውሱኝ ማድረግ፡፡
የሆነ ታሪክ ሲያወራልኝ አመንኩት። ይቅር ሁሉ አልኩት፡፡ በምንም በኩል ቢሰላ ሰይጣንን ይቅር ማለት እንደ አማራጭ መቅረብ አልነበረበትም፡፡ ማስተዋያዬ አብሮኝ የለም፡፡ ለካ ማስተዋያዬ አስተዋዩ ባሌ ነው፡፡ ከዚህኛው ጋር በድጋሚ አብረን ተመልሰን የምንሆን ሁሉ መሰልን፡፡ ወደ ስቃይና ሞት እንደመመለስ ነው፡፡ ከሞት በኋላ ደግሞ ወደ አጥንትነት፡፡ እንደገና፡፡
ለባለቤቴ ተመልሼ የማቀርብለት ምክኒያት እንኳን የለኝም፡፡ ስለዚህ ሰውዬ ምንም ነገር አውርቼለት አላውቅም፡፡ የራሴው ቁስል ነው፡፡ የራሴው ቁሻሻ፡፡
ባለቤቴ ስለኔ የሚያስበው እኔ ስለራሴ የማስበውን አይደለም፡፡ ወይንም ከእኔ ስላገኘው ብቸኛ ወንድ ልጁ፡፡ ውራጅ እንዳይደለን ነው የሚያስበው፡፡ የእኔን ታሪክ አያውቅም እሱ፡፡ የሚያውቀው እኔ የነገርኩትን ብቻ ነው፡፡ በቆሻሻ ፍሳሽ ቱቦ ውስጥ ህይወቴን ስጎትት፣ እሱ ዘንድ እንደደረስኩ አያውቅም፡፡ የእሱን ንፁህነት ግን ህይወቴን አስይዤ እወራረዳለሁኝ፡፡ ህይወቴ በዚህ ክፉ አሰናካይ እጅ በቀትሯ ፀሃይ ወድቃለች፡፡
ቀኑ እየመሸ ሲመጣ አሳሳቹ ሃላፊነት አልወስድም ብሎ ካደ፡፡ የካደው የማይደረገውን፣ የማይታሰበውን አድርገን ከወጣን በኋላ ነው፡፡ ሰውነቴ ደንዝዟል፡፡ ግን እሱ ስሜትም አልሰጠኝም፡፡ ሁኔታዬ የደስታ ይመስል ነበር፡፡
ሲመሽ ተለያየን፡፡ ራሱን ከተጠያቂነት አፅድቶ፣ የማይፀዳውን በእኔ ላይ ደፈደፈው። “ራስሽን መግዛት ነበረብሽ” እንደማለት ነው፡፡
መኪናዋን ስንመለስም እየነዳት ነበር። ከእኔ ይልቅ ከመኪናዋ ጋር ክፉ ትዝታ ያለበት ይመስላል፡፡ እኔን ከአልጋው ቤት ከወጣን በኋላ አልነካኝም፡፡ እኔ ደግሞ በተገላቢጦሽ ላቅፈው እፈልጋለሁ፡፡ አልተያዘልኝም፡፡ ያሟልጫል፡፡ ዝም ብዬ አለቅሳለሁ፡፡ የማለቅሰው ለራሴ ነው፡፡
 ቅድም አልወርድም ያለው እንባዬ መንታ መንታ እየሆነ ፈሰሰ፡፡ የለቅሶ ጩኸቴም ተሰማ፡፡ ቡና ቤቱ ጋ ተመለስን። ቤቱ ጨላልሟል፡፡ ተዘግቷል፡፡ እኔን ለመኪናዬ ጥሎ፣ የራሱን መኪና አንስቶ “እደውልልሻለሁ” ብሎ ተለየኝ፡፡
እንደተለመደው ሀገር ጥዬ መጥፋት ፈልጌ፣ እንዴት ተደርጎ እንደሚጠፋ ግራ ገባኝ፡፡ መኪናዬን ጠላሁት፡፡ ወደማይቀረው ቤቴ ተመለስኩኝ፡፡ ባለቤቴ በጎረቤት ተከቦ፣ ጋቢ ለብሶ፣ ባትሪ ይዞ እየጠበቀኝ ነው፡፡ መኪና አቁሜ እግሩ ስር ለመውደቅ አስቤ እፊቱ ደንዝዤ ቆምኩኝ፡፡ የሆንኩትን ሁሉ ከበፊት ጀምሮ እስከ አሁን ምንም ሳልደብቅ ሁሉንም ነገር ነገርኩት፡፡
“ዋናው ደህና መሆንሽ ነው” ይላል ብዬ አልጠበቅሁም፡፡ ሳለቅስ እንዲያዩኝ አልፈለገም፡፡ በተለይ ልጄ፡፡ እንቅልፍ አይወስደኝም ብዬ ነበር፤ ለጥ ብዬ አደርኩኝ።
ግን አውቃለሁኝ፡፡ ውራጅ አለም ውስጥ ነኝ፡፡ ይሄ አዲስ መስሎኝ የጀመርኩት ህይወትም ከእንግዲህ እንከን የሌለበት ሆኖ እንደማይቀጥልም ታወቀኝ፡፡ እኔ የጣልኩትን ማን እንደሚያነሳ እግዜር ይወቅ፡፡ ሰው ቁሻሻን አይጥልም፤ ቁሻሻ ግን ይጥለዋል። ያውም ንፁውን አቆሽሾ። ባለቤቴን የምታነሳው እድለኛ ናት፡፡ ግን ስታነሳው እሱም እንደቀድሞው ሆኖ አይደለም የሚነሳው፡፡ ትንሽ ቆሽሾ ነው። ወድቆ ያነሳውን አቆሽሾ ለመጣል፡፡ የምታነሳው የተባረከች ናት፡፡
እኔ አንሺ የለኝም፡፡ ለማንሳት ብሎ የሚመጣ ወዮለት፡፡ ውራጅ አርጅቶ መጣል አለበት፡፡ እንደማይታደስ እኔ ህያው ምስክር ነኝ፡፡ እኔ ነኝ እራፊ፤ አዲሱ ላይ ተለጥፌ የማስረጀው፡፡ ይሄ እስኪሪቢቶ ራሱ ይሄንን ታሪክ ከፃፈ በኋላ ለደህና ነገር አይውልም። የተፃፈውን የሚያነብም እንደዛው፡፡ እርግማንን የሚያነብ የተረገመ እንዳይሆን ይጠንቀቅ፡፡ ለማይሰማ፤ ምክር  ቅንጦት ነው፡፡ ብክነት፡፡

Read 1234 times