Saturday, 02 April 2022 11:21

ዘመን ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር አዳዲስ የክፍያ ዘዴዎችን ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


             ዘመን ባንክ በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የማስተር ካርድ የክፍያ ዘዴ (MPGS) አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ። ባንኩ ይህንን አገልግሎት ይፋ ያደረገው ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሸራተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፣ ባንኩ ባለፈው የበጀት ዓመት ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነውን ከንክኪ ነጻ የተጓዦች ካርድ በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም መሆኑን አስታውሷል።
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘነበ፤ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ እንዳስታወቁት፤ ባንካቸው አዳዲስና የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸውን የባንክ ቴክኖሎጂዎች በመተባበርና ግንባር ቀደም በመሆን ለደምበኞቹ አገልግሎት በመስጠት ይታወቃል። በዕለቱ ባንኩ ያስተዋወቀው የማስተር ካርድ የክፍያ  አገልግሎት  በድረ-ገፅ የሚከወኑ ክፍያዎችን  ከማስተር ካርድ የክፍያ ዘዴዎች ጋር በማጣመር በዘመን ባንክ በማስተር ካርድና በቪዛ ካርድ ግብይት የሚፈፅሙ ደንበኞች ለደንበኞቻቸው ባሉበት ሆነው በምቾት ክፍያ ለመፈጸም ያስችላቸዋል ተብሏል።
የማስር ካርድ ክፍያ  አገልግሎት ተግራዊ መሆን የባንኩ ደንበኞች ከክፍያ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ተደራሽነታቸው እንዲጨምር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ነው የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ የገለጹት።
የባንኩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አምሃ ታደሰ በበኩላቸው፤ በሰጡት አስተያየት፤ የማስተር ካርድ ክፍያ መስጫ ሁሉም ደንበኞች በሻጮች ዲጂታል ክፍያ መሰብሰቢያ ቀለል ባለ መልኩ መጠቀም እንዲችሉ ማድረጉ ዋነኛ ጠቀሜታው ነው ብለዋል። አቶ አምሃ አክለውም፤ ሆቴሎች፣ የንግድ ሱቆች፣ የጉዞና አስጎብኚ ድርጅቶች፤ አየር መንገዶች፣ የንግድ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲሁም መካከለኛና ትልልቅ ድርጅቶች  ከዚህ የተቀናጀ የኢ-ኮሜርስ አገልግሎት መስጫ መንገድ በእጅጉ እንደሚጠቀሙ አብራርተዋል።
ዘመን ባንክ የማስተር ካርድን የክፍያ መንገዶችን በመጀመር በኢትዮጵያ የዲጂታል ፕላትፎርም አሻራውን ከማሳረፍም ባሻገር በመንግስት የተቀመጠውን የ2025 የዲጂታል ዕቅድ በማሳካትም በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ ጨምረው ገልጸዋል። በዚህ የማስተር ካርድ የክፍያ ዘዴ ማስተዋወቂያ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ የማስተር ካርድ ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ የዘመን ባንክ የቦርድ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።


Read 11455 times