Saturday, 02 April 2022 11:28

“ፊንቴክስ” ዓለማቀፍ ኤክስፖ ሀሙስ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)


             3ኛው "ፊንቴክስ” የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና ግንባታ አጨራረስ ኤክስፖ የፊታችን ሀሙስ መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ያከፈታል፡፡ በፕራና ኤቨንትስና በአፍሪካ ትሬድ ፓርትነርስ በጋራ የሚዘጋጀው ይሄው ኤክስፖ፤ እስከ ሚያዝያ 1 ቀን  2014 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡
የፕራን ኤቨንትስ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ በመግለጫው ላይ እንዳስታወቁት፤ በሀገራቸን ከዘመናዊ አኗኗር ጋር ተያይዞ  ሰዎች ቅንጡ የመኖሪያ ቤቶችን፣ ፈርኒቸሮችንና የቤት አጋጊያጥን የመምረጥ  ከፍተኛ ፍላጎት ቢታይም፤ ዘርፉ ግን ትኩረት ያገኘ ባለመሆኑ ይህን ኤክስፖና ጉባኤ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ትሬድ ፓርትነርስ ዋና ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ በለጠ በበኩላቸው፤ የአለምን የፈርኒቸር ፣የቤት ውበትና የግንባታ አጨራረስ ዘርፍ፤ ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማነፃፀር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ፣ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ አውደ ርዕይና ጉባኤ ላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣በዘርፉ ተዋንያን መካከል ለመቀራረብ ምቹ መድረክ በማዘጋጀት ልምድና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ዘርፉ ትልቅ እምርታን መፍጠሩን  ተናግረዋል ፡፡
በዚሁ የፈርኒቸርና የቤት ውበት የንግድ ትርኢት ላይ ከ60 በላይ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉና ከ4 ሺህ በላይ የንግድ ጎብኚዎች እንደሚመለከቱት የሚጠበቅ ሲሆን በዘርፉ ከተሰማሩት ከሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በተጨማሪም ከቻይና፣ ከቱርክ፣ከማሌዢያና፣ ከጣሊያን የሚመጡ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበትም ታውቋል፡፡ አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ የፈርኒቸር ዕቃ ወደ ሀገር በማስገባት ከደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጄሪያ ፣አንጎላና ሴኔጋል በመቀጠል አምስተኛ ላይ እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት ጥናት ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ የ10 ቢሊዮን ብር ፈርኒቸር ግዢ መፈፀሟን በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአት ልማት ኢንስቲቲዩት የተደረገ ጥናት  ዋቢ አድርገው የገለጹት የኤክስፖው አዘጋጆች፤ በዚህም የአገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ 20 በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው ይህንን የአገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ ከፍ ለማድረግና ኢትዮጵያ ለፈርኒቸር ግዢ የምታወጣውን የውጪ ምንዛሪ ለመቀነስ እንዲህ አይነት አውደ ርዕይዎችና ጉባኤዎች ወሳኝ መሆናቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቁሟል፡፡      


Read 11451 times