Saturday, 02 April 2022 11:30

የአማራ ኢመርጀንሲ ፈንድ” በጦርነቱ ለተጎዱ ሁለተኛ ዙር ድጋፍ 1.7 ሚ ዶላር ማሰባሰቡን ገለፀ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 በመላው አለም ያሉ የአማራ ማህበራትን በስሩ የያዘው “የአማራ ኢመርጀንሲ ፈንድ” ለሁለተኛ ዙር ድጋፍ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ሊደግፋቸው ላቀዳቸው ፕሮጀክቶች 1.7 ሚሊዮን  ዶላር ማሰባሰቡን አስታውቋል፡፡
“የአማራ ኢመርጀንሲ ፈንድ” ይህንን ያስታወቀው ከትላንት በስቲያ ረፋድ ላይ በጣይቱ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ የአማራ ኢመርጀንሲ ፈንድ ዋና ስብሳቢ አቶ ጌታቸው በየነ እንዳብራሩት በመጀመሪያው ዙር በጎንድር በወሎ፣ በአፋር በደሴ፣ በሸዋና በጎጃም በጦርነቱ ለተፈናቀሉ፣ በወራሪው ሀይል መደፈርና ጥቃት ለደረሰባቸው፣ መጠለያ ለሌላቸው ህጻናትና አረጋዊያን የምግብ፣ የአልባሳት፣ የሶሻል ሳይኮቴራፒ ህክምና፣ የመድሃኒት አቅርቦትና ለተደፈሩ ሴቶች የመቋቋሚያ ገንዘብ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰው፤ በአማራ ክልል በህክምና ሙያ ተመርቀው ወደ ስራ ያልተሰማሩ 40 ያህል ዶክተሮችን የውሎ አበል እየከፈለ በወሎና በጎንደር እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር አውስተዋል፡፡
በሚኒሶታ የአማራ ቅርስና ውርስ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ የዚህዓለም መስፍን በበኩላቸው፤ አሁንም በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለው የነበሩት ወደ ቀያቸው ቢመለሱም  ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው ለመግባት የሚያስችል ሁኔታ ላይ አለመሆናቸውን ገልፀው የግድ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ “የአማራ ኢመርጀንሲ ፈንድ” በጎፈንድሚና በመሰል መንገዶች ያሰባሰበውን ገንዘብ ይዞ ወደ  ሀገር ቤት መመለሱን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ከአንድ ወር በፊት በሰቆጣ ዋግህምራ ለሚገኙና የምግብ እርዳታ ለሚሹ  ወገኖች የ2.4 ሚ ብር የምግብ አቅርቦት ማድረጋቸውንና ዛሬና ነገም የ2.4 ሚ ብር የምግብ አቅርቦት ይዘው ሀይቅ ጃራ አካባቢ ለሚገኙ ወገኖች እንደሚደርሱም ተናግረዋል፡፡
“እኔም ለእህቴ” ለተሰኘውና በጦርነቱ በወራሪው ሀይል ለተደፈሩ በርካታ እህቶችና እናቶች የህክምናና የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት 300 ሺህ ዶላር፣ በጦርነቱ የተሰዉ ጀግኖች ቤተሰቦችን ለመደገፍ 150 ሺህ ዶላር፣ በጦርነቱ ተሳትፈው ለተመለሱ ገበሬዎችና የቆሰሉትን ለማሳከምም እንዲሁ፣ ከ50 ሺህ ዶላር በላይ መመደቡን የአማራ ኢመርጀንሲ ፈንድ ሀላፊ  ገልፀው ለመካነ ሰላም ሆስፒታል፣ ባህርዳር ለሚገኘው ፈለገ ሕይወት ሆስፒታልና አፋር ዱብቲ ለሚገኘው ሆስፒታል ለእያንዳንዳቸው የ1 ሚ ብር መድሃኒትና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶች ተገዝተው በቅርቡ እንሚላኩም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 11625 times