Saturday, 02 April 2022 11:30

በህወኃት ታጣቂ ሃይሎች ተስተጓጉሎ የቆየው ለትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ የማድረሱ ሥራ ተጀመረ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(4 votes)

በህወኃት ቁጥጥር ስር የሚገኙ የአፋር ክልል 6 ወረዳዎች ነዋሪዎች ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል
                      
             በህወኃት ታጣቂ ሃይሎች ተስተጓጉሎ የቆየው ለትግራይ ክልል ህዝብ የሰብአዊ እርዳታ የማድረስ ስራ ከሰሞኑን ተጀምሯል።  ከሳምንት በፊት የህወኃት ታጣቂ  ሃይል የእርዳታ አቅርቦት መተላለፊያ የሆነው የአብአላ መንገድ በመዘጋቱ ሳቢያ በአለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ የተላኩ 43 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መሳሪያ ተኩሶባቸው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡ መንግስት ባለፈው ሳምንት ለሰብአዊነት ሲባል እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ፤ ህወኃትም ውሳኔውን እንደሚቀበለው ላያስታውቅና ሳይተገብረው ቆይቶ ነበር።  በትላንትናው ዕለት ግን የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዝ መጀመሩም የተነገረ ሲሆን እስካሁን ወደ 40 የሚጠጉ የእርዳታ እህል የጫኑ ተሸከርካሪዎች ትግራይ ክልል መግባታቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ግጭት የማቆም ውሳኔውን ይፋ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ የመድሃኒት የህክምና መሳሪያዎች ገንዘብና አልሚ ምግቦችን እርዳታ ሰጩ ድርጅቶች በአየር ትራንስፖርት በየዕለቱ ወደ ትግራይ ክልል እያመላለሱ ቢሆንም፣ በየብስ ትራንስፖርት የእርዳታ እህሎች ወደ ክልሉ ለማስገባት የሚደረገው ጥረት በህወኃት ታጣቂ ሃይሎች ተስተጓጉሎ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
የእርዳታ አቅርቦት ዋነኛ መተላለፊያ በሆነው የአብአላ መንገድ ላይ ለቀናት ቆመው የቆዩትና በአለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ ክልል ሊጓጓዙ የተዘጋጁት የእርዳታ እህል የጫኑ 43 የጭነት ተሽከርካሪዎች  ትናንት ወደ ትግራይ ክልል መጓዝ መጀመራቸውን ተከትሎ፣ በአካባቢው በከፍተኛ ደረጃ የተጎዱ እርዳታ ፈላጊ የአፋር ክልል ነዋሪዎች መኖራቸው ተገልጿል፡፡ አለም ዓቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በከፍተኛ ረሃብ እየተጠቃ የሚገኘውን የአፋር ክልል ህዝብ በቸልታ  አልፈው እርዳታውን ለትግራይ ክልል ለማድረስ መጣደፋቸው ተገቢ አለመሆኑን የአፋር ክልል አስታውቋል፡፡
የአፋር ክልል የስራ ኃላፊዎች ለአልዓይን እንደገለፁት እንደ ፍየል በየቦታው ፈሶ በረሃብ የሚሰቃየውን የአፋር ክልል ህዝብ ችላ ብሎ እርዳታውን ለትግራይ ህዝብ ብቻ እናድርስ ማለት ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በህወኃት ታጣቂ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ከሚገኙት የአፋር ክልል 6 ወረዳዎች  ተፈናቅለው በየቦታው የፈሰሱትን በርካታ ወገኖች ዞር ብሎ የሚያያቸውንና እርዳታና ድጋፍ የሚያደርግላቸው  ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል ያሉት የአፋር ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊው አቶ ያሲን ሀቢብ አክለውም፤ ተፈናቃይ ወገኖች በየ ቦታው እየወለዱ እንዲሁም በውሃ ጥምና የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ፣ ለከፍተኛ የጤና ችግር መጋለጣቸው ከእነአካቴው ትኩረት አለመሳቡ  የሚያስገርም ጉዳይ ነው ሲሉም ለአልአይን ተናግረዋል፡፡
የአፈር ሕዝብ እንደሌለው ጉልበትና የዓለም ሚዲያ የለውም ያሉት ኃላፊው፤ ከጤናና ከሰብአዊነት አንፃር ግን አፋር ክልል ላይ የፈለሰውን ህዝብ ጥሎ ማለፍ ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ “በከፋ ችግርና ረሃብ ውስጥ የሚገኘውን የአፋር ህዝብ ጥሎ እያለፈ ትግራይን ብቻ እንርዳ ማለቱ ከእርዳታ ያለፈ ነገር መኖሩን የሚጠቁም አሳዛኝ ተግባር ነው” ብለዋል አቶ ያሲን ሃቢብ፡፡


Read 11593 times