Saturday, 02 April 2022 11:58

ግማሽ ፍቅር፤ ግማሽ ከንፈር - (ምናባዊ ወግ)

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


           አዘውትረው ከሚያመሹባት ‘Sol Dallas’ የምትባል ለሚ ኩራ...ፍየል ቤት አካባቢ ካለች ትንሽዬ ቤት በረንዳ ላይ ጥገኛውን ጠረጴዛ ይዛ ቁጭ ብላለች። ፊት ለፊቷ ያቆማት መኪናውን መሪ ከላይ ሁለት እጆቹን አጋጥሞ እንደጨበጠ በትንሽዬ ፈገግታ ትኩር ብሎ ለአፍታ ታዘባት።
ከሩቅ ሀገር የሚጣራ ግርማ ሞገስ እንደተላበሰች የምታውቅ ሁላ አትመስልም... አቀርቅራ ከተከዘችበት ስልኳ ተፋትታ ቀና ስትል፣ ጠረጴዛዋን በአፍንጫዋ ልትነካ የመወስወስ ያህል ተጠግታት የቆመችው መኪና የእርሱ አሮጌ ቢመር መሆኗን አይታ፣ በዐይኖቿም... በጉንጮቿም... በከናፍሯም አንድ ላይ ፍንድቅድቅ አለች።
ወዳጁ ብቻ እንደሆነች ያውቃል። እንዴት ወዳጁ ብቻ እንደሆነች አይገባውም። ብቻ የተዋወቁ ሰሞን “አስተምርሀለው...” ያለችውን፣ ተስማምቶ “...እሺ” ያላትን ላለመርሳት ከራሱ ተማምሏል።
“...ነገሮችን ከሆኑት በላይ አወሳስበህ እየተረጎምክ ሰላምህን የምታጣውን ነገር እንዴት እንደምትጥል እኔ ሀላፊነቱን ወስጄ አስተምርሀለው... አንዳንዴ ነገሮች የሚመስሉትን ብቻ ናቸው... ሌላ ድብቅ ትርጉም ከጀርባቸው የለም!” ብላው ነው፤ ይኸው አሁን ይሄን ያኽል አንዳቸው በሌላኛቸው ቀን ውስጥ እስኪገዝፉ ድረስ ያደገው ወዳጅነታቸው ዳዴ ማለት የጀመረው።
በእርሷ ቤት ትምህርቷን አጣጥሞ በሚደንቅ ፍጥነት ነፃ እንደወጣ እርግጠኛ እንደሆነች ያውቃል። እርግጠኛ ነው። ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ስታየው ከሚገነፍል ፍንደቃዋ ውስጥ ከወዳጅነት የላቀ ፍቅር ላለማንበብ እንደሚታገል ሊነግራት አይችልም። ምክር ሲያስፈልገው ከቅዱሱ መፅሐፍ “...ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን?” የሚል ጥቅስ እየመዘዘ እራሱን ይገስፃል።
“ተው እንጂ ፊሊጶስ...” እያለ እራሱን ይጎሽማል።
“አንዳንዴ ሰማያዊ አስተማሪ ለምድራዊ ተማሪ አይገባ እንደሁ እንጂ መልዕክቱ ፍፁም፤ ያልተገለጠም የሌለው ነው!” ሲል ተስፋውን እራቅ አድርጎ ይጥላል።
በተቀመጠችበት ከናፍሯን አሞጥሙጣ ቀኝ ጉንጯን ሰጠችው። የከናፍሯ ድርሻ እንደ መሳም ያለ ድምፅ ማውጣት ብቻ እንደሆነ ያውቃል። ነገር ከሆነው በላይ የማይተረጎምበት ወዳጅነት ውስጥ ግርታ ለመፍጠር እንኳ አቅም አጥታ የተሰነቀረች የሰላምታ ድግግሞሻቸው ናት ይቺ... በቃ።
ሊቀመጥበት ያለውን ወንበር ከራሷ ወንበር በስሱ ወደተረፈ ዳሌዋ ጎተት እያደረገች... “ ንገረኝ እስቲ... እንዴት ሆነልህ?” አለችው በጉጉት።
“እህ... ሰላምዬ ደሞ... ቁጭ ልበል እስቲ ቆይ...” አላት ላለመሳቅና ለመኮሳተር እኩል እየታገለ።
መፅሐፉን እንዲያሳትም ድፍን ዐመት ጀንጅና ካሳመነችው በኋላ በስልክ ካገናኘችው አሳታሚ ጋ የከሰዐት ቀጠሮውን ጨርሶ እስኪመለስ አላስቻላት ሆኖ ፣ ቀድማው ከትንሿ ማምሻቸው ቤት በረንዳ ላይ የጠበቀችው።
“አትሟዘዝ እንግዲ... ንገረኝ። አነበብኩት አለህ? ወደደው? ደስ የሚል ሰው ነው ኣ?...” አጣደፈችው።
“ደስ የሚል ሰው ነው።” እየሳቀባት ቀጠለ...
“... ወዶታል መሰለኝ ነገር... ትንሽ ጦልቦኛል ግን ያው... የወደደው ይመስለኛል።”
“እና ምን አለህ? ይታተማል አለህ?...” ፊቷ ላይ በተትረፈረፈ ደስታዋ፣ እንዳልረካች አይነት ግራ እጁን ቀጨም አድርጋ፣ ዐይን ዐይኑን እያየች ጠየቀችው።
“እ... ‘ነገር’ የሚለውን ቃል አብዝቼ እንደምጠቀም... እ... ምዕራፍ ሶስት ላይ ብቻ እንኳን ወደ አስራ ሶስት ጊዜ ‘ነገር’ እንዳልኩ ነገረኝ ይኸውልሽ...”
“ነገረኛ ስለሆንክ እንደሆነ ነገርከው?...” አለችው ሳቋን እየታገለች።
“እ... እንደዛ ነገር...” ብሏት ግንባራቸው እስኪጋጠም ተጠጋግተው፣ አብረው ድክም አሉ...
ሲዋሻት ውስጡ ከመገላበጥ የሚጀምረው መረበሽ እየተጣደፈ፣ ፊቱ ላይ እንደሚሳፈር ከተረዳ ጊዜ ጀምሮ ያገኘው ድኩም መላ እየቧለተ እንድትስቅ ማድረግ ነው። እንድትስቅ አድርጎ ደግሞ በሳቋ መልሶ መሳቅ... ስትስቅ ከፊቱ ላይ የማይባረር መረበሽ ሊኖር አይችልም። አብሯት ሲስቅ ደግሞ ከሚጠብቡ ጨፍጋጋ ዐይኖቹ ውስጥ እውነቱን በሚያንሰፈስፉ ዐይኖቿ እንዳትፈልግ ያዘናጋታል።
አሳታሚው ጎልማሳ የላከለትን ጥራዝ በወጉ እንኳን እንዳላገላበጠው የተረዳው፣ ገና ወደ ቢሮው ገብቶ ከግብዳ ጠረጴዛ ስር የተወሸቀች የእንግዳ ማስተናገጃ ወንበር ላይ ተደላድሎ ሳይቀመጥ ነው። ቀጠሮውንም የያዘለት በአግባቡ እንዳልተገላበጠ በሚያሳብቅ መልኩ፣ ከፊቱ ያስቀመጠው ፅሁፍ ውስጥ ቁምነገር አግኝቶ ሳይሆን የሚወሰወስባትን ሰላም ደውሎ መጀንጀኛ ርዕስ ፍለጋ እንደሆነ ገብቶታል ነገር...
የመታተም እቅድ ኖሮት ስለማያውቅ ብዙም አልከፋውም። የደበረው የሰላሙ ደስታ ላይ ውሀ ላለመቸለስ አሁን እየተወነ ያለው የማስመሰል ድራማ ነው።
ሰላሳ ደቂቃ ከዘለቀ ደጅ ጥናቱ ሀያውን ያጠፋው ጎልማሳው ሰውዬ፣ ስለ ሰላም የጠየቀውን ጥያቄዎች በመመለስ እንደሆነ እያስታወሰ ፈገግ አለና፣ ቀጥሎ ለምትጠይቀው ጥያቄ፣ ከአስሯ ደቂቃ ውስጥ የእውነት የሚመስል መልስ መፈለግ ጀመረ።  
“እ... እና መቼ እናሳትመዋለን አለህ? ብሩ እንደማይቸግረን ነገርከው ኣ? ያው እሱ የሚያስፈልገን ገበያውን ስለሚያውቀው ምናምን እንደሆነ?” አሁን ደስታዋ ወደ መኩራራት ተንጠራርቷል።
“በርግጥ ፅሁፉን ወዶታል ያው... ግን ምን አሪፍ ነገር አነሳ መሰለሽ? መፅሀፉ ላይ ያሉት ብዙዎቹ ገፀ-ባህሪዎች የሌሉ ናቸው... በሌሉ ሰዎች የሚረካ የአንድ ምስኪን ትዝታ ላይ የተንጠለጠለ ጨለምተኛ መልዕክት ነው የሚያስተላልፈው... እና ያው ሰዎች ሲያነብቡት እንደሱ አድርገው ነው የሚስሉኝ... እንደርሱ እንደሆንኩ እንድታውቁ የምፈቅደው ደግሞ ለጥቂት የልቤ ሰዎች ብቻ ነው መሆን ያለበት... አይመስልሽም? እና ‘ሌላ ቆንጆ ነገር ብፅፍልህ ይሻላል፤ ይኼንን እንተወው’ ልለው እያሰብኩ ነው... ሙች ሙች የመታተሙን እቅድ እየተውኩት አይደለም ሰላምዬ...” በስስት እያያት ተንተባተበ...
“እኔን... አስጨነቅኩህ ኣ? ዋናው ፅሁፎችህን ለማካፈል መወሰንህ ነው... የኔ ጎበዝዬ...” እጁን ለቀቅ አድርጋ የሚያግል እጇን አንገቱ ስር አስገባች...
ጋደድ ብሎ በጆሮና በትከሻው መሀል ትንሽ ቆልፎ አቆየው...
“...ይሄንን ጨለምተኛ... የሌለ ሰው... ምናምን የምትለውን ነገር ግን ብትተው ነው እሚሻልህ...” አለች ኮስተር ብላ እጇን እየነጠቀችው...
“ምን ማለቴ እንደሆነ ገብቶሻል ባክሽ... አንዳንድ ሰው ሳይኖር ነው እሚሻለው። ሲኖር የሚያስቀይም ነፍ ሰው አለ ሰላምዬ። እኔ አባቴን የማዝንበት ልጅነቴን በሙሉ ስላልነበረ አይደለም። ያው እንደምታውቂውና ደጋግሜ እንደጎረርኩብሽ መልኳን በመልኬ የቀየረች ጀግና እናት ናት ያሳደገቺኝ። ምንም አልጎደለብኝም። አባቴ እንዳይጠላው እየተገራ ያደገ ልቤን ያስከፋው ባለመኖሩ ሳይሆን ሰልባጅና ጥራጥሬ ሽጣ ያስተማረችኝ ሴትዮ ልታስመርቀኝ በደገሰችው ድግስ፣ ‘እንደ አባት ካልተገኘሁ’ በማለቱ ነው። ኤክሴን የማልወዳት ስለሄደች አይደለም... ‘ለካ ያቺኛዋን የወሰድክብኝ እንደዚህችኛዋ አይነት ድንቅ ልትለግሰኝ ነው’ ብዬ አመስግኜ ሳልጨርስ ተመልሳ መጥታ ስላደፈረሰችው ሰላሜ ነው...” ፊቷ ላይ የነበረው ደስታ ሲከስም እንኳ እስከማያስተውል ድረስ ዝለቱን ዝርግፍ አደረገባት...
“እና ብትሄጂም አይከፋኝም... እግዜሩ የተሻለ ያዘጋጅልኛል ነው?” አለችው፤ አፍንጫዋን ነፍታ ወንበሯን ወደ ኋላ እስከ መጨረሻ እየተደገፈች።
ስታኮርፍ እንዴት እንደሚያፅናናት ያውቃል... ዐይኖቹን አጨፍግጎ ምላሱን እያወጣባት፣ ጎተት አደረገና ግንባሯን ሳም አደረጋት...
ብዙም የተፅናናች አትመስልም... እንዳያስቃት ፊቷን እያዞረችበት...
“ለማንኛውም ወዳጅ አታርቅ... ወዳጅ አስፈላጊ ነገር ነው...” አለችው።
ቀልድ... ቀልድ ያስፈልገዋል... ሳትሄድ መሳቅ አለባት...
“ወዳጅማ ግድ ነው... እንኳን የሰው የእንሰሳ እንኳን ወዳጅ ያስፈልጋል። አልነገርኩሽም? ግቢ ገና እንደገባን...”
ቆንጆ ፊቷን ቀስ አድርጋ አዞረችና ልትሰማው ቀና አለች።
“... ነፍሱን ይማረው ሶል ካሳ ‘sketching’ እያስተማረን፣ አንድ አርብ ቀን ‘ወደ ቤታችሁ ስትሄዱ አንድ መንደራችሁን የሚገልፅ scene ምረጡና sketch አድርጉ’ ብሎ ይልከናል። እናልሽ ሰኞ ስንመለስ ሰፈሩ እዛው ልደትዬ ጋ የሆነ አንድ ቀልድ አዋቂ ጀለሳችን፣ ውሻ ስልክ እንጨት ስር እግሩን አንስቶ እየሸና sketch አድርጎ ከች ይልልሻል። ሶል ካሳ ግራ በመጋባት እያየው፣ ‘ይሄንንማ ከፎቶ አልያም ከስዕል ላይ ነው የወሰድከው’ ይለዋል። ጀለስካ ግግም ብሎ ‘ኧረ ሰክቼው ነው’ ማለት... ‘sketch አድርገኸው እስክትጨርስ እንደዚህ ሆኖ ጠበቀህ?’ ይለዋል፤ ሶል ካሳ ቆጣ ብሎ... ጀለስካ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘የሰፈር ውሻ እኮ ነው... አውቀዋለሁ... ወዳጄ ነው!’... እና ምን ልልሽ ነው? ወዳጅ ሲሆን ውሻም ይቸገርልሻል፤ ይኸውልሽ... ወዳጅማ አስፈላጊ ነው...”
እየተፍለቀለቀች በስሱ በጥፊ አለችው...
“እ... እንዴት እንደምታስቀኝማ ታውቅበታለህ... ለማንኛውም በቃ ልግባ፤ ሰውዬዬም ያው ዛሬ እንደማገኝህ ስለሚያውቅ ከዚህ በላይ ካመሸሁ አፍንጫውን መንፋቱ አይቀርም... እንኳን ተነፋፍቶ ስቆም የሚጨንቅ ሶዬ...” ለመነሳት ተቁነጠነጠች...
ከጥቂት ወራት ወዲህ ሰውዬዋ አብሯቸው ካልተቀመጠ፣ ዘይራው እንኳን የጠገበች ሳይመስላት ነው በግዜ ጥላው የምትሄደው።
እንደ ልማዳቸው ብድግ ብሎ እራቅ እድርጋ የምታቆመው መኪናዋ ድረስ አደረሳትና፣ ገብታ ስትደላደል ጠብቆ የዘጋላትን በር መስታወት ስታንሸራትትለት፣ ወደ ትከሻዋ ስር ዝቅ አለ...
በጣቷ ብቻ ተረክ አድርጋ ስትቀሰቅሰው መኪናዋ ማዜሙን ካቆመበት ይቀጥላል... ምን እየሰማች እንደነበር ለመስማት ጆሮውን ለአፍታ የሚቀስራት ነገር፣ አሁን የሁልጊዜ ልምምዳቸው ሆናለች። ‘ኢንትሮውን’ እየሰማ...
“ታውቀዋለህ ኣ ይሄን ዘፈን?” አለችው ፈገግ ብላ።
“ of course...” አለ አፉን እያጣመመ።
ብዙ ፕሌይ ሊስቷን የሰራው እርሱው እራሱው ነው።
“ለማንኛውም ለዛሬ የደስደስ የምሰጥህ ነበረኝ... ገግመህ ግማሽ አድርገኸዋል... ይኸው እንግዲ...” ብላ ግማሽ ከንፈሩን በከንፈሯ አስነክታ ፈትለክ አለች።
ከቆመበት ሳይነቃነቅ ትንሽ ከቆየ በኋላ፣ እየተንገዳገደ ወደ ጠረጴዛው ተመለሰ። ስልኩን አውጥቶ የመኪናዋን ዜማ ቀጠለው...
“50 ways to leave your lover”ን ከሌላው ጊዜ በተለየ ትኩረት እያዳመጠ ነው...
Paul Simon ቀለል አድርጎ ይወርደዋል...
“...She said why don’t we both
Just sleep on it tonight
And I believe in the morning
You’ll begin to see the light
And then she kissed me
And I realized she probably was right
There must be fifty ways
To leave your lover
Fifty ways to leave your lover...”
ዐይኖቹ ፈጠጡ...
“ምን እያለችኝ ነው?...” አለ በለሆሳስ አጠገቡ ለሌለ ሰው።
አዲስ ውዝግብ የሚያስተናግድበት አቅምና ሰላም እንደሌለው ያውቃል። እንዳይጠይቃት አይነት አካሄድ የሄደችውስ ነገር? “ሰውዬሽ ጋ ሰላም ገባሽ?” ብሎስ እንዴት ነው የሚደውለው?


Read 1429 times