Saturday, 09 April 2022 13:29

“የክልል ልዩ ሀይሎች አወቃቀር ማሻሻያ እንዲደረግበት እናት ፓርቲ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

       በታጠቁ ሀይሎች መካከል የጉልበት መፈታተሽ ፍላጎት፣ ሀገሪቱን  ወደባሰ ትርምስ ሊያስገባት እንደሚችል ስጋቱን የገለፀው እናት ፓርቲ፤ የክልል ልዩ ሀይሎች አወቃቀር ተገምግሞ አፋጣኝ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠይቋል።
“ጉልበትን የመፈተሽ ፍላጎትና የጠላትነት ፖለቲካ ውድቀት እንጂ ውጤት አላመጣም አያመጣምም!” ያለው  ፓርቲው፤ “በቅርቡ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አሞራ ቤት ቀበሌ፣ ልዩ ቦታው አውራ ጎዳና የተፈጠረው ድርጊት የጉልበት መፈታተሽ፣ ፀብ ያለሽ በዳቦ አባዜ ነው ሲል ተችቷል።
ይህ ክስተት አዝሎት የመጣው አደጋ ጥልቀት ያለው በአፋጣኝ መፍትሄ ካላገኘ ሀገሪቱን በሌላ የግጭት አዙሪት ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን አበክሮ ያስገነዘበው  እናት ፓርቲ፤ የፌደራሉ መንግስቱ የከፋ ችግር ከማጋጠሙ በፊት ለጉዳዩ ተኩረት ሰጥቶ መፍትሄ እንዲያበጅ ጠይቋል።እናት ፓርቲ - Home | Facebook
“በሁለት ወንድማማች ማህበረሰቦች መካከል አሁንም በአቅመ ቢስ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ቤንዚን አርከፍካፊነት የከፋ እልቂት እንዳይፈጠር ያሰጋል” ያለው እናት ፓርቲ በፖለቲከኞች በኩል የሚደረጉ የቃላት ውርወራዎች ፣ዛቻዎች እንዲሁም በአቅራቢያ አካባቢዎና ከፍተኛ የሚባል የታጠቀ ሀይል ጭምር የማስፈር እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ መሆኑ ጉዳዩን የበለጠ አስጊ ያደርገዋል ብሏል።
ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን የከፋ ጉዳት ለመከላከል የፌደራል መንግስቱ ሊመጣ ያለውን ችግር በልኩ ተረድቶ ማዕከላዊነትና ሚዛናዊነቱን ጠብቆ አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ እንዲሁም፤የዜጎችን ሰላም የማስከበር ቀዳሚ መንግስታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ፓርቲው ጠይቋል።
በተጨማሪ ብልፅግና በውስጡ ያለውን ችግር በሩን ዘግቶ እንዲፈታ፤የክልል መንግስታት ለሚናገሯቸው ቃላት እንዲጠነቀቁና ህዝብን ወደ እርስ በእርስ ጥርጣሬ ከሚወስዱ ቃላትና ድርጊቶች እንዲታቀቡ፤ የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና ፣የሀገር ሽማግሌዎችም የገላጋይነትና የማስታረቅ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስቧል እናት ፓርቲ፡፡ እናት ፓርቲ - Home | Facebook
ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤የፌደራል አወቃቀሩ የብዙ ችግሮች ምንጭ ነው ብሎ እንደሚያምንና አማራጭ የፌደራሊዝም ስርዐት ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባ ይህ እስኪሆን ቢያንስ የክልል ልዩ ሃይሎች አወቃቀርን በጥናት ገምግሞ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ካልተቻለ በአሁኑ አካሄድ ዳግማዊ ጥቅምት 24 ሩቅ እንዳልሆነ አመላካች ነው ብሏል።
“ህዝብ ጠላት እየተፈለገለት፣ግንባር እየተቀያየረ የጦርነት አዙሪት ውስጥ መኖር ይበቃዋል” ያለው እናት ፓርቲ፤ ማንኛውም ችግር በውይይትና በንግግር ሊፈታ ያገባዋል ብሏል በመግለጫው።

Read 11035 times