Saturday, 09 April 2022 13:33

መንግስት የሰብአዊ መብት የማስከበር ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ ግጭቶችና በሚፈፀሙ ጥቃቶች ዙሪያ የምርመራ ሪፖርት በማውጣት መንግስት የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስድ ቢጠየቅም፣ ቸልተኝነት በመስተዋሉ በሀገሪቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከወትሮው በተለየ እየተባባሱ መምጣታቸውን ያመለከተው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) ፤መንግስት የሰብአዊ መብት የማስከበር ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ሲል ወቅሷል።
ከሰሞኑ በአማራና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ከተፈጠረው ግጭት ባሻገር በኦሮሚያና በሲዳማ ክልል አዋሳኝ አካባቢ እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን በተፈጠሩ ግጭቶች የሰዎች ህይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን አመልክቷል።
ኢሰመጉ በኦሮሚያ ክልል በሲዳማ ክልል በሚዋሰኑባቸው በሲዳማ ክልል ጭሬ ወረዳ ሀሌላ ቀበሌ  ባለፈው መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች የሲዳማ ተወላጅ የነበሩ አንድ የሀገር ሽማግሌ በመገደላቸው ምክንያት፣ በአካባቢው ግጭት መፈጠሩን የኢሰመጉ ሪፖርት ያስረዳል። ይህ ግጭት ወደ አጎራባች ቀበሌዎች ተሰራጭቶ በአጠቃላይ የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 15 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን፣በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን ፣ነዋሪዎችም አካባቢያቸውን ለቀው መፈናቀላቸውን  ሪፖርቱ ያመለክታል።
በሌላ በኩል፤ በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ሰገን ወረዳ፣ በተለያዩ ቀበሌያት በተፈጠረ ግጭት በርካታ ቀበሌዎች እየተቃጠሉና የሰው ህይወት እየጠፋ እንደሚገኝ ኢሰመጉ መረጃዎች እንደደረሱት ፤እንዲሁም በደቡብ ኮንሶ ዞን አማሮ ልዩ ወረዳ ከጉጂ ዞን የተነሱ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት፣ የ3 ሰዎች ህይወት ማለፉን ጠቁሟል።
እነዚህ ግጭቶችና ጥቃቶች እንዲያበቁም ለመንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም፣ እስካሁን ውጤት አለመገኘቱን ያወሳው መግለጫው፤ አሁንም የክልል መንግስታትና የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ፣የሀገር ሽማግሌዎች ሰላም ለማምጣት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል። በተጨማሪም የፌደራል መንግስቱ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሀላፊነትና ግዴታውን ያለማወላወል እንዲወጣ ኢሰመጉ አሳስቧል።


Read 11009 times