Saturday, 09 April 2022 14:39

የእነ አምነስቲ ሪፖርት “ሚዛናዊነት የጎደለውና ለአንድ ወገን ያደላ ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)


            አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች ከሰሞኑን ምዕራብ ትግራይ ላይ  በጋራ ያወጡት  በወልቃይት ላይ ትኩረቱን ያደረገው ሪፖርት፤ የአገሪቱን ሉአላዊነት የሚዳፈርና ሚዛናዊነት የጎደለው ለመሆኑ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ሰለሞን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ፤ ከእኚሁ ምሁር ጋር ተቋማቱ ባወጡት ሪፖርት ዙሪያ  አጭር ቆይታ አድርጋለች።

                አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች ከሰሞኑ  “የዘር ማፅዳት” ተፈፅሟል ያሉበትን የምዕራብ ትግራይ ሪፖርት እንዴት አገኙት?
ሪፖርቱን እንደተመለከትኩት፤ ሚዛናዊነት የጎደለውና ለአንድ ወገን ያደላ ሪፖርት ነው። እነዚህ ሁለት ዓለም አቀፍ ተቋማት ቀደም ሲል በተለያዩ ጊዜያት ጥናት አድርገናል  ብለው ያወጧቸው ሪፖርቶች አሉ። ለምሳሌ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም  ሂዩማን ራይትስ ዎች ከኢትዮጵያ  ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር ባወጡት ሪፖርት፤ የህወኃት የሽብር ቡድን ብሔርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ መፈጸሙንና በህወኃት መዋቅር ውስጥ የነበሩ አመራሮች በቀጥታ ተሳታፊ እንደነበሩ ገልጾ ነበር። ከጥቅምት 27 ቀን 2013 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ  በማይካድራ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ መፈፀሙን ያመላከተው የተቋሙ ሪፖርት፤  ከ600-1000 የሚጠጉ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውንም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በተጨማሪም የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት፤ የትግራይ ሃይሎች፣ የአማራ ክልል ገብተው በቆዩባቸው ጊዜያት ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከል በሲቪሎች ላይ ግድያና አስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን መፈፀማቸውን  ይፋ አድርጓል። የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ውሰጥ ገብተው በቆዩባቸው ጊዜያትበርካታ ንፁሃንን ከመግደላቸውም ባሻገር ታዳጊ ሴቶችን በቡድን መድፈራቸውን አመልክቶ ነበር:: ቡድኑ እነዚህን ወንጀሎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን አረጋገጥኩ ብሎ ሪፖርት ሲያቀርብ፣ ድርጊቱ ዘር የማፅዳት ወንጀል ስለመሆኑ መግለፅ እንኳን አልፈለገም ነበር። ይህም ሪፖርቱ ለአንድ ወገን ያደላና ሚዛናዊ አለመሆኑን የሚያመለክት ነው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቀደም ሲል ተመሳሳይ ጥናት በማድረግ ሲያወጣቸው በነበሩ ሪፖርቶች ላይ  አሁን እንደተገለፀው አይነት ያልተለመዱ  ምክረ ሀሳቦችን ነበር። የአሁኑ  ሪፖርት ምን  የተለየ ነገር ኖሮት ነው ምክረ ሃሳቦችን እንዲያካትት የተደረገው?
ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ነው።  አሁን ሁለቱ ዓለም አቀፍ  ድርጅቶች በጥምረት ያወጡት  ሪፖርት ወገንተኝነት የሚታይበትና ፍፁም ሚዛናዊነት የጎደለው ነው። ቀደም ሲል እነዚህ አለም አቀፍ ድርጅቶች አውጥተዋቸው በነበሩ ሪፖርቶች ላይ የህወኃት ታጣቂ ቡድን ለወራት ተቆጣጥሯቸው በነበሩት የአማራ ክልል አካባቢዎች ላይ የጦር ወንጀል ነው ሊያሰኝ  የሚችል ወንጀል መፈፀማቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች መገኘታቸውን በመጠቆም፤ መንግስት በጉዳዩ ላይ ምርመራ በማካሄድ ወንጀሉን የፈፀሙ ወገኖች ለፍርድ እንዲቀርቡ  ከማሳሰብ የዘለለ ነገር  አላሉም ነበር። የጅምላ ጭፍጨፋ፣ አስገድዶ መድፈርና ዝርፊያ መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ያለው ቡድኑ በጉዳዩ ላይ ሪፖርት ከማቅረብ የዘለለ ድርጊቱን ፈጽመዋል ባላቸው ወገኖች ላይ መወሰድ ስለሚገባው እርምጃ አንዳችም ነገር ሳይል ቆይቶ፣ አሁን በወልቃይትና አካባቢው ተፈፀመ ባለው የዘር ማፅዳት ወንጀል መነሻነት፣ ከዚህ ቀደም ባልተለመደና በተለየ ሁኔታ የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ስፍራው  እንዲገባ እንዲሁም የፋኖ አደረጃጀቶች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡና ትጥቅ እንዲፈቱ የሚለውን ምክረ ሃሳብ ማቅረብ፣ የድርጅቶቹን ወገንተኝነት የሚያሳይና ገለልተኝነታቸውን ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነው።
እነዚህ ተቋማት በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እንደ ፋኖ ያሉ አደረጃጀቶች ሊፈርሱና የያዙትን ስፍራ ለቀው ሊወጡ ይገባል የሚል ምክረ ሀሳብ የማቀረብ ማንዴት አላቸው ወይ?   
ከሁለተኛው ጥያቄሽ ልነሳና ተቋማቱ ምክረ ሃሳብ ብለው ባቀረቡትና የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሀይል ወደ ስፍራው ገብቶ፣ ይሰማል በሚለው ሃሳብ ውሰጥ እጅግ አደገኛና የተቋማቱን ፍላጎትና ግብ በግልፅ የሚያሳይ ሴራ ይንፀባረቃል። የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሀይል አንድ ሀገር ውስጥ ገብቶ ሰላም ለማስከበር የሚችልበት አሰራርና መመሪያዎች አሉት። አንድ ሀገር ማዕከላዊ መንግስቱ ችግርን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ሲያጣ፣ መንግስት ሲዳከምና የዜጎች ህይወት አደጋ ላይ ሲወድቅ ነው። የሚሰማው  በእኛ ሀገር ሁኔታ ግን ይህ አልሆነም። አሁንም፣ አገሪቱ ጠንካራ መንግስት ያላት  ናት  እንኳንስ ለራሷ የውስጥ ጉዳይ ይቅርና በሌሎች ሀገራት ሊቃጣባት የሚችለውን ማንኛውንም ችግር ለመቋቋም  የሚያስችላት አቅም ያለት አገር ነች። ከራሳችን አልፈን በሌሎች የአፍሪካ አገራት ሰላም የማስከበር ተግባር ላይ መሰማራታችን ይታወቃል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ሰላም አስከባሪ ሀይል መግባት አለበት የሚል ምክረ ሀሳብ ማቅረብ፣ ከቀልድነት የዘለለ ነገር ሆኖ አይታየም። ሌላው እነዚህ ተቋማት ያቀረቡት ምክረ ሃሳብ፣  እንደ ፋኖና ሚሊሽያ ያሉ አደረጃጀቶች ትጥቅ እንዲፈቱና የያዟቸውን ቦታዎች እንዲለቁ መጠየቅ የአንድን ሉአላዊት ሀገር  ህልውናን መዳፈርና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው። የራሷ ጠንካራ መንግስት ባላት አንዲት አገር፣ የወሰን ጉዳይ ውስጥ ገብቶ መፈትፈት፣ የተቋማቱ ፍላጎት ሌላ እንደሆነ የሚያመለክት ነው።ተቋማቱ ነፃና ገለልተኛ  አለመሆናቸውንም  በግልፅ የሚያሳይ  ነው።
ሪፖርቱ ለአንድ ወገን ያደላ  እንደመሆኑ፣ በህዝቦች መካከል ሰላምና እርቅ ከመፍጠር ይልቅ ለበቀል ስሜት የሚገፋፋ ይሆናል ብለው የሚሰጉ ወገኖች አሉ? የተጀመረውን የሰላም ጥረትም የሚያደናቅፍ አይመስልዎትም?
ሪፖርቱ ተጠያቂነትን ለአንድ ወገን ብቻ የሰጠና ሌላኛውን ወገን ከተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ ያለመና፣ ግልፅ አድሏዊነት  የሚታይበት ሪፖርት ነው። ይህ ደግሞ በህዝቦች መካከል ሰላም እንዳይፈጠርና ህዝቡ ለበቀል  እንዲነሳሰ የሚያደርግ ነው። እንዱን ወገን ለማስደሰትና ፍላጎትን ለማስፈጸም እንዲህ አይነት ጥላቻን የሚያቀጣጥልና ለበቀል የሚያነሳሳ ረፖርት ማቅረብ፣ እጅግ አደገኛ አካሄድና በህዝቦች መካከል እንዲፈጠር የሚፈለገውን ሰላምና እርቅ የሚያርቅ ነገር ነው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሁናዊ አቋምና ብቃቱን እንዲሁም ገለልተኛነቱን እንዴት ያዩታል?
እንደሚታወቀው ኢሰመኮ ቀደም ሲል በተለያዩ ጫናዎች ውሰጥ ሆኖ የሚሰራና በገዢው መንግስት ተፅዕኖ ስር የወደቀ ተቋም ነበር። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተቋሙ የሚያወጣቸውን አንዳንድ ሪፖርቶች ስንመለከት፣ ከመንግስት ተፅዕኖ ለመላቀቅ እየሞከረ እንደሆነ እናያለን። ለምሳሌ ተቋሙ ያቀረበው የ2013 ዓ.ም የሰብአዊ መብቶች ሪፖርት ላይ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በህገወጥ መንገድ በዘፈቀደ የሚፈፀሙ ግድያዎችን ይፋ አድርጓል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋዜጠኞችን ዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ማዋል፣  ማሰርና  ማዋከብ እየጨመረ መምጣቱንም  ሪፖርት አድርጓል። ይህ  ሁኔታ ተቋሙ ሙሉ በሙሉ ነፃና ገለልተኛ ሆኗል ባያስብልም ፣ወደዚያ ጉዞ መጀመሩን አመላካች ነው። ነገር ግን አሁንም ተቋሙ ሙሉ በሙሉ ከገዢው መንግስትም ሆነ ከውጭ  ኃይሎች ጫናና ተፅዕኖ ነፃ ነው ለማለት አያስደፍርም።


Read 7489 times