Print this page
Sunday, 10 April 2022 00:00

ሲዶርፍ በአዲስ አበባ መግለጫ ይሰጣል

Written by  ግሪም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

     67ኛዋን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ይዞ መጥቷል

       ከዓለማችን የእግር ኳስ ኮከቦች አንዱ የሆነው ክላረንስ ሲዶርፍ ነገ በሸራተን አዲስ ጋዜጣዊ መግለጫ  የሚሰጥ ሲሆን 67ኛውን የአውሮፓ ሻምፒዮን ሊግ ዋንጫ ወደ አዲስ አበባ ይዞ እንደመጣ ታውቋል፡፡ ሄንከን ኢትዮጵያ ዝነኛውን የእግር ኳስ ተጨዋች ወደ አዲስ አበባ ያመጣው እግር ኳስ አፍቃሪዎች ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በቅርበት እንዲመለከቷት በማሰብ ሲሆን ነገ በሚካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ለክላረንስ ሲዶርፍ የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያቀርቡበት እድል ተፈጥሯል፡፡ ሄንከን ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጋር በመስራት 13 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በ13 አገራት ይዞ በመዘዋወር ለጉብኝት አብቅቷል።  በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተጨዋቾች አንዱ የሆነው ሲዶርፍ ከ3 የተለያዩ ክለቦች ጋር አራት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን በማሸነፍ ብቸኛው ነው፡፡ በ1995 እኤአ ላይ ከሆላንዱ አያክስ ጋር፤ በ1998 እኤአ ከስፔኑ ሪያል ማድሪድ እንዲሁም በ2003 እና በ2007 እኤአ ከጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል፡፡
ትውልዱ በሱሪናሚ፤ ፓራማሪምቦ የሆነው ሲዶርፍ አሁን 46ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በተጨዋችነት ዘመኑ ከ1992 እስከ 2004 እኤአ  በሆላንድ፤ በጣሊያንና በስፔን በሚገኙ ታላላቅ ክለቦች  ውስጥ  ከ654 በላይ ጨዋታዎችን አድርጎ 107 ጎሎችን ያስቆጠረ  ሲሆን  ከ1994 ጀምሮ በሆላንድ ብሄራዊ ቡድን ለ14 ዓመታት ሲያገለግል በ87 ጨዋታዎች 11 ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ደግሞ በ2014 እኤአ የጣሊያኑን ኤሲ ሚላን፤ በ2016 እኤአ የቻይናውን ሼንዘን፤ በ2016 እኤአ ላይ የስፔኑን ዲፖርቲቮ ላካሩኛ የመራ ሲሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ በ2018 እና 2019 እኤአ ላይ የካሜሮንን ብሄራዊ ቡድንን አሰልጥኗል፡፡

Read 4063 times