Saturday, 09 April 2022 15:26

ከጉልበተኛ አትወዳጅ፤ ወይ ስንቅህን ይበላብኻል፤ አሊያም ከእነአካቴው ይበላኻል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ጥንት ጠዋት ደራሲ ከበደ ሚካኤል፣ በታሪክና ምሳሌ መጽሐፋቸው የመከሩን ዛሬም ፋይዳው ኃያል ነው። እነሆ፡-
 “አንድ ቀን ብረት ድስት ፣ ሸክላ ድስትን አለው።
እኔን ነው በሁሉም መልክህ የሚመስለው
 ወንድሜ ነህ እኮ ባታውቀው ነው አንጂ  
ከዛሬ ጀምሮ እንሁን ወዳጅ።
እኔን እንደመቅረብ  መሸሽህ ለምነው?
አካሌ አካላትህ፣ የኔ ቤት ያንተም ነው።
አሁንም በል ተነስ ፍቅራችንም ይጥና፤
ሽርሽር እያልን እንናፈስና።
መፋቀራችንን ይይልን ሰው ሁሉ፤
የማንተዋወቅ ለምን ነው መምሰሉ።
አጥቂ ቢመጣብን ዘሎ የሚማታ
እኔ እሆንሀለሁ ሀይለኛ መከታ።
ለፀሀይ ለአቧራው እየሆንኩህ ድንኳን፤
 እደግፍሀለሁ ቢያደናቅፍህ እንኳን፤
በደካማነቱ ቅር እያለው ሆዱ
ተነሳ ሸክላ ድስት አንድነት ሊሄዱ፤
አንድ መቶ እርምጃ እንደተራመዱም
ድንገት ተጋጩና አቶ ብረት ድስት
ረግተው ሲቆሙ ያላንዳች ጉዳት።
የሸክላ ድስት ግን በፈራው ጎዳና፤
ተሰብሮ ወደቀ እንክትክት አለና።
ወዮ እንኳ ለማለት ጊዜ ሳይደርሰው፤
የገሉ ስባሪ ምድርን አለበሰው።
እንዲያው ሰው ያላቻው እየተንጠራራ፤
ለመሻረክ ሲያስብ ከበላዩ ጋራ።
መቼም አይጠፋና ከሀይለኛ ግፍ፤
ከጉዳት በስተቀር ምንም አያተርፍም።
ሰዎች ከሰው ጋራ ሸሪክ ስትሆኑ
አቅማችሁን በፊት አይታችሁ መዝኑ፡፡
*   *   *
 የምንፈጥረው ማናቸውም ወዳጅነት አቅማችንን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። አቅማችን ስንል አንድም የኢኮኖሚ አንድም የፖለቲካ ማለታችን ነው። ምነው ቢሉም? ፖለቲካ የኢኮኖሚ ጥርቅም ነፀብራቅ ነው ይሏልና። (politics is the concentrated form of economics) ዛሬ የዘይት ዋጋ የት ድረስ እንዳሻቀበ ለማንም ኢትዮጵያዊ ፤ ስላገራችን ፖለቲካ-ኢኮኖሚ አይኑን ሳያሽ፣ ጠጉሩን ሳያክ እቅዱን መናገር ይችላልና፣ የግድ “አዋቂ ቤት” መሄድ አይኖርበትም! ማሰብ ካለብን ለሌሎቹም ቁሳቁሶች ሰንሰለታዊ ዝምድና ነው።
(Domino Effect እንዲል ፈላስፋው!) የኢኮኖሚ ጠበብት በብርቱ መጨነቅ ካለባቸው አሁን ነው። በጦርነትም፣በረሀብም የምናሳፍርበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ አሁን “የአብዬን  እከክ ወደ እምዬ  ልክክ” የምንልበት ሰዓት አልፏል!
አሁን እንደ ዲዮጋን በቀን ፋኖስ አብርተን የሰው ያለህ የምንልበት ሰዓት አይደለም። ሰው አለ። ያለንን የሰው ሀይል በአግባቡ የሚጠቀም ሰው ግን የለም።  ከቀልቡና ከአገሩ የሆነ ሰው ያስፈልገናል! የተማረ ልባም ሰው ያሻናል። “ካንጀት ካለቀሱ እምባ አይገድም” በሚለው ተረት የሚያምን፣ ሁነኛ ሰው በብዛት ሊኖረን ግድ ነው። የተማረው ሰው መሰደዱ ማብቃት አለበት። No more brain-drain የሚል ትውልድ መበርከት አለበት።
“ምነኛ ታድሏል የሰነፍ አእምሮ
አንኳን መማር ቀርቶ ፊደል ሳያጠና
ሁሉንም ያወቀ ይመስለዋልና!
አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
ይሉናል ከበደ ሚካኤል። ያንን ሁሉ ታሪክና ምሳሌ ፅፈው የሚሰማ ሲጠፋ ምን ያድርጉ?
ሌላ የገነነ ሽብር፣የፖለቲካ ሽርክነት እንኳን እንከን ነው። በተለይ የፖለቲካ ሽርክነቱና ወዳጅነቱ ከመንግስት ጋር ሲሆን ከባድ ፈተና አለበት። በየትኛም መስፈርት ቢታይ መንግስት ትልቅ ነው። ትልቁ ዓሳ ትንሹን ዓሳ መብላቱ አይቀሬ ሀቅ ነው። ስለዚህ ከመንግስት ጋር ስንወዳጅ፣ የአብርሃም የሳራ ቤት ነው ብለን ከሆነ ቢያንስ የዋሀ ነን! የዋህነት ደግሞ ያጸድቅ እንደሆነ እንጂ ከመበላት አያድንም! ለጊዜው የሞቀን ጉያ ውሎ አድሮ ልባችንም፣ልብሳችንም ሲሳሳ ብርድ ይመታናል። ለበሽታ ያጋልጠናል! ስለዚህ ስንወዳጅ እንጠንቀቅ! ስንቀራረብና ቀለበት ስናስር ልብና ልቦና ኖሮን ይሁን።  “ከጉልበተኛ አትወዳጅ፤ ወይ ስንቅህን ይበላብኻል፤ አሊያም ከእነአካቴው አንተኑ ይበላኻል” የሚለው ተረት አደራ የሚለን ይሄንኑ ነው!

Read 12124 times