Wednesday, 13 April 2022 17:23

ለዕውቀትም ለኃላፊነትም … ውጤታማነት - በጎ ሕሊና

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በየመስሪያ ቤቱ የተለጠፉት ቅንነት፣ ታማኝነት፣ አለማዳላት፣ ግልፅነት ... የሚሉት ፅንሰ-ሃሳቦች በጎ ሕሊና መገለጫዎች ናቸው። አንድ ሕብረተሰብ ወይም ሃገር እነዚህ ነገሮች ከበዙለት ሁለንተናዊ እድገቱ በሰላም ላይ ተመሥርቶ ይቀጥላል፡፡ ባለዕውቀቱና በሃላፊነት ላይ ያለው ደግሞ በጎ ሕሊና ኖሮት ሕዝብን ካገለገለ ያቺ ሃገር በእውነት ዕድለኛ ነች፡፡
እንደሚታወቀው ዕውቀት የዕድገት መሠረት ነው፣ ሃይልም ነው፡፡ በአግባቡ ካልተያዘ ደግሞ ዕውቀት ያስታብያል፣ እንዲህ ያለው ሃላፊነት ላይ ካለ ደግሞ ሕዝቡን ከማገልገል ይልቅ የራሱንና የሚመስሉትን ጥቅም የሚያስቀድም ይሆናል፡፡
ሲጀመር ግንኙነቶች የተገነቡት በበጎ ሕሊና ላይ ተመስርተው ነው፡፡ ባልና ሚስት የተጣመሩት እኮ ግለኝነታቸውን ትተውና በፍቅር ሆነው ቤተሰብ ለመመስረት ነው፡፡ ሕብረተሰቡ ደግሞ ሌሎችን #ከእኛ እናንተ በዕውቀትም በልምድም ትሻላላችሁና ምሩን; ብለው ግለሰቦችን ሃላፊነት ላይ ያስቀመጡት በጎ ሕሊና መርቷቸው ነው፡፡
በጎ ሕሊና ቀስ-በቀስ ሲዳከም ግን ከተጋቢዎች አንዱ /አንዷ/ ውሉን ማፍረስ ይጀምራሉ፣ ሃላፊነት የተሰጣቸውም ሰዎች ሁሉንም ማገልገል ይተውና፣ ራሱን ወይም ጥቂቶችን ብቻ መጥቀም ያዘወትራሉ፡፡
ቅንነት በትዕቢት ይተካል፣ ታማኝነት በውሸትና በማስመሰል ይለወጣል፣ ግልፅነት በሴራ ይተካል፣ በአጠቃላይ አድልዎ ሥፍራውን ይረከባል፡፡ ይህን የንቅዘት ሁኔታ ባለ ዕውቀቱ በችሎታው ተጠቅሞ ይሸፋፍነዋል፣ የዳቦ ስም ያወጣለትና አሳምሮ ያስተዋውቀዋል፣ በተለይ ደግሞ ኃላፊነት ላይ ያሉት ከተጨመሩበትማ መዋቅራዊ ቅርፅ ይይዝና፣ ከላይ እስከ ታች ድረስ ይሰበካል፡፡ ሕዝብም እውነት ይመስለውና ይከተላቸዋል- ለጊዜውም ቢሆን፡፡
እንደ ዕድል ሆኖ ግን ሕብረተሰብ በጎ ሕሊና ያላቸውን ጥቂት ባለዕውቀቶች አያጣም፡፡ እነዚህም በብርቱ ድካም ሕዝቡን ማንቃታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በተፃራሪው በምቾት ላይ (Comfort Zone) ያሉት ለምሳሌ የትምህርት ሥርዐቱን በማዳከም ብቁ ትውልድ (ምክንያታዊ ትውልድ) እንዳይፈጠር ይሟሟታሉ፤ ሕዝቡን በቋንቋው ወይም በብሔሩ ባስ ሲልም፣ በጎሳው ላይ ብቻ የሙጥኝ እንዲልና ሃገራዊ የአንድነት ስሜቱ እንዲጠፋ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡ በአንድ ምሳሌ እንመልከት፡፡ የወባ ትንኝ በመጀመሪያ ዙር የኬሚካል ርጭት ተረፈረፉ፤ ጥቂቶችም የተረፉት ትንኞች መድሃኒቱን እየለመዱት በመጨረሻም ኬሚካሉን ሊቋቋሙት ቻሉ፤ ስለዚህም አዲስ የወባ መድሃኒት መስራት አስፈለገ፡፡
የወባ ትንኞቹ ልምምድ ደመ-ነፍሳዊ ነው፤ ሰው ግን ተገዳዳሪነቱ በንቃት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የመጀመሪያው ዙር ትውልድ የተሸነፈበት ዘመን ቢረዝምም፣ ለሚቀጥለው ትውልዶች ግን ይህ እያነሰ ነው የሚመጣው፤ምክንያቱም የአሸናፊነት ዕውቀት ይከማቻል! (Cumulative Knowledge) በጎ ሕሊና እንደገና ያብባላ!!
በጎ ሕሊና ሊተኛ ይችላል፤ ጨርሶ ግን አይጠፋም፤ በጎ ሕሊና ከእንስሳነት ይልቅ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስተሳስረን ጥብቅ ገመድ ነው፡፡
በጎ ሕሊና ያለው አያጠፋም፣ አይሳሳትም ማለት አይደለም፤ ሆን ብሎ ለራሱና ለወገኖቹ ሲል ግን ጭልጥ ያለ ስህተት አይፈጽምም፡፡ በጎ ሕሊና ያለው ሰው እሺ ባይ ነው፤ ከጥፋቱ ቶሎ የሚመለስና የሚታረም ነው፣ ታራቂም ነው፡፡ አዋቂነት የሚለካውም በዚህ እኮ ነው፡፡ (An intellectual is a person who makes a few mistakes and rectifies them immediately).
አለም በጎ ሕሊና ባላቸው ሰዎች ዕድገት አሳይታለች፡፡ በሕክምና በኩል፣ በኢንጂነሪንግ በኩል (መንገድ፣ ሕንፃ፣ ግድብ ……. ግንባታ) በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (ሬዲዮ፣ ስልክ፣ ቴሌቪዥን፣ ኢንተርኔት ……..) በግብርና ቴክኖሎጂ፣ በሕዋ ምርምር በሥነ-አዕምሮ ዕውቀት ….. ወዘተ.
እነዚህ ዕውቀቶች ሰውን ከድካም አሳርፈዋል፤ ምርትን አሳድገዋል፤ ኑሮን አዛምነዋል፤ የበሽታን አደጋ ቀንሰዋል፤ የጨለማን (የማይምነትን) ግርዶሽ ቀድደው ከጎጂ ልማዳዊ ነገሮችና ከአካባቢያዊ ክፉ ልማዶች አላቅቀዋል፡፡ ትሩፋታቸው ተዘርዝሮ አያልቅም፤ እነዚህ ሁሉ የበጎ ሕሊና ውጤቶች ናቸው፡፡
በጎ ሕሊና ያለው ሰው አንዳንድ ጊዜ ሊመጣ ያለን የሩቅ አደጋ አስቦ ከወዲሁ መፍትሔ ያዘጋጃል፡፡ አንዱ ሊቅ በንግግሩ ወቅት እንዲህ አለ፡- የራይት ወንድማማቾች ጥሩ ነገር አስበው አይሮፕላን ሰሩ፤ ሌላው ደግሞ ቆይቶ ቆይቶ አይሮፕላኑ ቢበላሽስ ብሎ (ክፉ!) አሰበና ፓይለቶቹን ለማዳን አስቦ ፓራሹት ሰራ፡፡
አያችሁት! በጎ ህሊና ከተፈፀመ ክፉ ነገር ብቻ አይደለም የሚያስመልጠን፣ ሊመጣ ካለውም አደጋ ጭምር ነው እንጂ፡፡ ይህ አይነት በጎ ሕሊና (Good conscience) ይብዛልን!  


Read 1338 times