Friday, 15 April 2022 16:18

ትናንቴ ተከተለኝ

Written by  አድሃኖም ምትኩ
Rate this item
(2 votes)

አለሌ ነበርኩ። ከህንድ እስከ እብድ የቀረኝ የለም የምል አለሌ። የተኛኋቸው ሴቶች ጠቢቡ ሰለሞን ከተኛቸው የሚያንሱ አይደለም፤ አልቆጠርኳቸውም እንጂ።
ጀንጅኜ መዳረሻዬ ማራኪ ሆቴል ነው። ሆቴሏ ሸጎጥ ያለች  ሰዋራ ስፍራ ነች፤ ከመኖርያዬ በርቀት የምትገኝ። አስተናጋጆቹ ምቹ ናቸው። በእርግጥ ጉርሻ ምቹ የማያደርገው የለም። ፈረንጁና መስኪ የሚባሉ አስተናጋጆችን የበለጠ አውቃቸዋለሁ።
 ጠብ እርግፍ ብለው ያስተናግዱኛል፤ በእርግጥ መስኪ የምትባለው ትንሽ ተለቅ ትላለች።
ፊት ከሰጠሁት ይጎነትለኛል ብላ ይሁን፣ ተፈጥሮዋ ሆኖ ይሁን፣ ነፍፍ ቺክ ስለማመላልስ ይሁን፣ ስለማጨስ ወይም ስለምጠጣ ይሁን፣ እኔ’ንጃ ብቻ አትስቅልኝም፤ አትኮሳተርብኝም።
ፊቷ ወጣትነትን  ቢሸኝም ውበቷ ግን እንዳለ ነው። መስኪ ምንም ያህል ቲፕ ብሰጣት አመሰጋገኗም ሆነ አስተያየቷ አይለይም፤ ተመሳሳይ ነው።
ክላሴ ውስጥ አጭሼ፣ ጠጥቼ፣ ቀብጬ  ሹልክ ብለን በጓሮ እንሄዳለን። በሌላ ቀን ሌላ ይዤ እመጣለሁ፤ አዲስ። ሁሉንም እንደ ሙዳቸውና እንደ ፍላጎታቸው እይዛቸዋለሁ። ላጤነቴ፤  በነፃነት ታየው አልታየው ብዬ  ሳልሳቀቅ  ለመቅበጥ አግዞኛል።  ጓደኞቼ ሁሉ  ሲያገቡ፤ የቤተሰቦቼ የአታገባም ውትወታ በበረታበት ወቅት ሶልያና የምትባል ልጅ ተዋወቅኩ።
ባገኘኋት በሁለተኛው ቀን ወደ ገደለው ለመግባት ሞክሬ ነበር፡፡ ግን  አልተሳካልኝም።  በውስጤ "ስንቷ እንደ አንቺ አካብዳ፣ መጨረሻ ላይ እጇን ትሰጣለች" ብዬ ፈገግ ስል "ምነው?" አለቺኝ። "እርጋታሽ ደስ ይላል" አልኳት፡፡
"ውስጤ እንደላዬ የተረጋጋ እንዳይመስልህ" አለቺኝ።
"ይሆናል ግን ውስጥም ላይም አንድ ላይ ከመንቀዥቀዥ ይሻላል" አልኳት፤ ከንፈሯን ገለጥ አድርጋ፣ ሳቅኩኝ አይነት አለቺኝ፡፡
"በነገራችን ላይ አንተም ረጋ ያልክ ነህ" አለቺኝ... ስስቅ። "ውስጥህ ወዲህ ወዲያ ስለሚል ነው እርጋታህ ያልታወቀህ" አለችኝ።
"ይሆናል" አልኳት፡፡
ሶልያና  የበዛ እርጋታ አላት፥ እርጋታዋ ይረብሸኛል፤ ከደስታ ይልቅ ለድብርት አጋልጦ ነው  የሚሰጠኝ።
አብሬያት የምሆነው የምፈልገውን እስካገኝ ብቻ ነበር።  
ትፈልጋለች ብዬ የማስበውን እነግራታለሁ። ሲኒማ እጋብዛታለሁ፤ ትያትር ትጋብዘኛለች፡፡ ከንፈሯ ጋ ሳልደርስ ቀናቶች ነጎዱ፡፡
በጭራሽ የወሲብ ወሬ ለማውራት አታመችም። ወሲብ ነክ ከተወራ ለመቀጠል ፊቷ አይጋብዝም። ወሲብ ነክ ወሬ ካወራሁ  ለይሉኝታ እንኳን ፈገግ አትልም። መንፈሳዊ ጉባኤ ትጋብዘኛለች። ለእሷ ደስ እንዲላት አንዳንድ አሰልቺ፣ አንዳንድ ማራኪ ስብከቶችን እሰማለሁ።
ቀልቧን ለመግዛት መንፈሳዊ መፅሃፍ እያነበብኩ፤ "በጉዳዩ ላይ ሰፊ እውቀት አለኝ" ወሬ ሳወራት ቀልቧ ሲሳብ፣ ወሬው ሲጥማት አያለሁ።
ሳይታወቀኝ የኔን መንገድ እየተውኩ፣ በእሷ መንገድ መመላለስ ቀጠልኩ።
ከሌሎች ስለተለየች  ይሆን፣ እንደምፈልገው አለመሆኗ ይሆን፣ የምፈልገውን ስላልሰጠቺኝ  ይሆን፤ ብቻ ቀልቤን ገዝታዋለች።
ውሎዋን ስራዬ ብዬ እከታተላለሁ። ካልተደዋወልን ይታወቀኛል። እንቅስቃሴዋ እየገባኝ መጣ። ሳላገኛት  የት እና ምን እያደረገች እንደሆነ መገመት ቻልኩ።
ከደወለችልኝ ስግብግብ ብዬ አነሳለሁ። በሂደት መንገዷ ምቾት ሰጠኝ። ከተመላለስኩበት መንገድ በተሻለ ይሄኛው መንገድ ጣፈጠኝ፡፡ የድሮ አመሌ ውል ሲለኝ፣ ቺኮች ውልብ ብዬባቸው ሲደውሉ ሳላቅማማ የድሮ ስልክ ቁጥሬን  ቀየርኩ።
የትላንት የውድቀት መንገዳችንን ካልቀየርነው ለለውጣችን ሳንካ ይሆናል።
አሁን ፈልጌ መፅሃፍ ቅዱስ አነባለሁ፤ እፆማለሁ ጉባኤ እከታተላለሁ። መንፈሳዊ ጉዞ እሄዳለሁ።  ከሶሊያና ጋር እንፋቀራለን። የትላንት መንገዴን አልተረኩላትም፤ ለዛሬው ማንነቴ ግን  መሃንዲሷ እሷው ናት።
ለአምላኬ ስንቴ በእሷ ምክንያት ምስጋና እንዳቀረብኩለት። የትላንት ህይወቴን እንዴት አሁን እንደማልወደው። ስለ ሴት አውልነት ሲነሳ ምንም ሃሳብ አልሰጥም፤ ያ ዘመን ያሳፍረኛል።
ሶልያና አንድ ቀን ስትፍነከነክ መጣች፡፡ ምነው? ስላት፤ "እቴቴ ስራ አገኘች" አለቺኝ።
"የት?"
"ባንክ"
በቀላሉ ፍንክንክ የምትል አይደለችም፤ የእናቷ ጉዳይ ግን ስስ ጎኗ ነው። ብቻዋን ስላሳደገቻት ይሁን ሁሉ ነገሯ ስለሆነች ይሁን-- ብቻ ስፍስፍ ትልላታለች።
ምን እንደምትሰራ አላውቅም። በትምህርት ብዙ ያልገፋች ስለሆነች፣ የት እና ምን ትሰራለች ብዬ አልጠየኩም፤ እሷም ስራ ነች አልመጣችም፣ ስራ ቀረች ነው እንጂ የትና ምን እንደምትሰራ ነግራኝ አታውቅም።
በጥንጡም በግዙፉም ወሬዎችዋ መሃል  እቴት ሳትል አትውልም።
"የድሮ ስራዋስ?" ስላት።
"ውይ የድሮ ስራዋን እኮ አትወደውም፤ ግድ ሆኖባት እንጂ" አለቺኝ።
 ስለ እኔ እንዳወራቻትና እንደወደደቺኝ  የነገረቺኝ እለት እንዴት ደስ እንዳለኝ።
"ባሻዬ" ብላ ቴክስት አደረገችልኝ።  ደስ ስላት እና ስትቀልድ ባሻዬ ነው የምትለኝ።
"ከእቴት ጋ እንደምንመሳሰል ነግሬህ አውቃለሁ? ኣ?" ስትለኝ
"ሁሌ" ብዬ የሳቅ ስቲከር ላኩላት።
"እንደ እሷ ቆንጆ ነኝ ግን" ብላ ፎቶዋን ላከችልኝ።
ማመን አልቻልኩም፡፡
ክው! ድርቅ አልኩ፡፡
የላከችልኝን ፎቶ አገላብጬ አየሁት፤ አልቀየር አለ። የማራኪ ሆቴል አስተናጋጅ መስኪ፣ የሶሊያና እናት ናት፤ ሁለቱ አብረው ሆነው እና አንድ የመስኪን ማራኪ እንግዳ መቀበያ ጋ የተነሳችውን ፎቶ ላከችልኝ።
ውስጤ ታወከ።
ያ ሴት አውል አብርሃም፤ ያ በየጊዜው ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሴቶች የሚያጋድመው፣ የሚያጨሰው አብርሃም፤ ያ በጥሩ አይን አይታው የማታውቀው አብርሃም፤ የአንድ ልጇ ሶሊያና እጮኛ ነኝ ብሎ ፊቷ እንዴት ይቆማል??
ትላንቴ  ተከተለኝ። እግዜር በተፀፀትንበት ትላንታችን ይቀጣናል እንዴ? ስንቴ ያመሰገንኩበት ጉዳይ መጨረሻው እንዴት እንደዚህ ሆነ??
የማደርገው ጠፋኝ። ጠፋሁ። አንዳንድ ትላንት፣ ትላንት ላይ ብቻ አይቆምም።


Read 1190 times