Print this page
Friday, 15 April 2022 16:32

እናት ኢትዮጵያ - ለልጇ ትግራይ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“ይኸውልሽ ልጄ ስሚኝ
አይጣልምና መቼም  የእናት ምክር
 ጎጇችንን ስንተክል ያኔ በደግ ዘመን
አንቺ ነበርሽ አንዷ ምሶሶውን ያቆምሽ
ጫካውን መንጥረሽ  ጋሬጣውን ደልድለሽ
መካነ ጎጆውን የጠቆምሽ፤
ይረሳል  ወይ ልጄ?
መሰረቱን ስንጥል  ያወጋነው ስንቱን
ለስልጣኔው የሰጠሁሽ ብኩርናውን
አደራ ያልኩሽ ቀዬውን
ይረሳል ወይ ልጄ?
በየጎሬው ዘምተን ግዳይ የጣልነውን
 ክንዳችን ፈርጥሞ  ባህርም ተሻግሮ  
ከምስራቅ በደቡብ በኑቢያም በሮም
ስማችን ገኖ ስንንጎማለል
እንደአምበሳና ደቦል
ይረሳል ወይ ጊዜው?
ጥንት ነገስታት ሲፈራረቁ
ባንቺ ሆኖ የዙፋን ርስቱ
እንዴት ይረሳሻል የበረከት ዘመኑ
ከጎተራችን አልፎ  የተረፍንበት ለጎረቤቱ፤
እንዴትስ ይረሳል?
የአለም ትንግርት ቃልኪዳናችን
ተባብረን የቀረጽነው ታሪካችን
የአንድነት የፍቅር  መለያችን፤
እንዴት ይረሳሻል ልጄ?
የገጠመንስ መከራ
ድርቁ ሲመታን ሲራቆት ቤታችን
ያነባነውን በባዶ ሆዳችን፣
ጠላት ደፍሮ ሲያሳድደን
በየዱሩ በየዋሻው ሳንለያይ- ስንንገላታ የኖርነውን
ይረሳል ወይ ልጄ?
በአድባራት በገዳማት
ከቅዱሳን ሰማዕታት
ጾም ጸሎት ይዘን ለፈጣሪ አቤት ብለን
በስግደት በሱባኤ ተማጽነን
ያሳለፍነው ጊዜን
ትዝ ይበልሽ ልጄ፤
ጉራማይሌ ቢሆንም መልካችን
እንደሳንቲሙ አይነጣጠል ዕጣፋንታችን
በሺ ዘመናት ጉዟችን
አንድ ነበር የጎጆ መጠሪያችን
አንድ ነው መለያ ሰንደቃችን
አንድ ነበር የታሪክ ገጽታችን
ትዝ ይበልሽ ልጄ፤
 አብረን የቆረስነው አምባሻ
የጠጣነው ቡና
ተውበን በሹሩባ-የጨፈርነው አሸንዳ
ትዝ ይበልሽ ልጄ፤
የገነባነው መቅደስ ያበጀነው መሶብ
የጠለፍነው ጥለት
ሺ ዘመናት ቢጓዙ የማይደበዝዝ
መሬት ቢቆፈር  የሚመሰክር
የናትና ልጅ ቀለማችን፡፡
ታዲያ ምነው ማኩረፉ -ራቅ ራቅ ማለቱ
አይሻልም  መነጋገር!?
ምንስ ችግር ቢኖር፤
ስትርቂ አያስችለኝም ልጄ
ይቀዘቅዛል ቤቴ
ግልገሏን እንዳጣች ላም  ባር ባር ይላል ሆዴ
ላንቺም አይበጅሽም መንገዱ
ከአብራኮቼ መነጠሉ
ከደምወስጋ ክፋዮችሽ መለየቱ
ያስችልሻል ግን ልጄ?
ተገልሎ ለብቻ መኖሩ
እንደሽፍታ ተገንጥሎ ማድፈጡ
የብቻ ጎጆ መቀለሱ
ያስችልሻል  ግን?
እንደ ባዳ መተያየት- እንደ ባላንጣ ጎረቤት
የተጋሩትን ማዕድ ረግጦ መውጣት
ያስችልሻል ግን?
ወጥተን የገባንበትን በር ዘግቶ
ወላጅ ሳይሞት የውርስ ኑሮ
የነ ዘራይ ደረስ የነ አሉላን ዕዳ ይዞ
ጀርባን ሰጥቶ ጉዞ …. ያዋጣል ግን?
እኔ ግን እልሻለሁ ልጄ
የትላንቱ ውጣ ውረድ
ድልና ሽንፈት -ኮሶና ወይን መጋት
መሰረት ነውና  ለነገው ረዥም ጎዳና
ተደማምጠን እንለፈው የዛሬን ፈተና
አምርረሽ አትራቂ  ጨክነሽ በእናትሽ አትቁራጪ
የክብሪት እንጨት አትሁኚ
ተይ እልሻለው ልጄ…ተይ
የበላችበትን የሰበረች እንዳትባይ
ከቤት የራቀ ተንከራታች እንዳትሆኝ
የእናት ሆድ አዝኖብሽ ከልጆቿ ለይታ
ባሳደገ ልቧ
እንዳይደርስሽ ርግማኗ
ተይ ተመለሺ
ሻንጣዎችን ሁሉ መልሺ
የተንጠለጠለ ልብሽን አረጋጊ
ዳኛም አያስፈልገን በኔናንቺ መሃል
ማንስ ያውቅና ጓዳዬን  ካንቺ በላይ
ማንስ ያውቅና ገመናሽን ገመናዬን    
ማነውስ ልባችንን የሚያነብ ገብቶ ከኛ በላይ
ተይ እልሻለሁ ልጄ ተይ
ባዳ ሳናስገባ እንፈታዋለን  ነይ ከጎጆ
በሃገር ባህል ከኦዳው  ስር  ተቀምጠን ሸንጎ
ይውጣልሽ ተናገሪው
የውስጥሽን ሳታስቀሪው
ቤተኛ ነን የምንሰማው
ምንጊዜም የእናት ሆድ አይጨክንም
ይቅርታሽን ለመቀበል ዝግጁ ነው
እጆቿን ለማቀፍ እንደዘረጋች ነው
ግቢ ልጄ
በእልፍኙ ጠላው ዳቦው ሽማግሌው
ሙሉ ነው.. ቆመውም እየጠበቁሽ ነው፡፡”


Read 1448 times
Administrator

Latest from Administrator