Saturday, 16 April 2022 13:49

“የጃኖ ባንክ አደራጆች ቢሮአቸውን ዘግተው ጠፉ” የሚለው መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ወሬ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       ጃኖ ባንክ ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ሊቀየር ነው ተብሏል
                          

               የጃኖ ባንክ አደራጆች “ቢሮ ዘግተው ጠፉ" ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያ ሲናፈስ የነበረው ሀሰተኛ ወሬ ነው ሲሉ የባንኩ አደራጆች ያስተባበሉ ሲሆን ጃኖ ባንክ ከባንክነት ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ሊቀየር በሂደት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ከአስር ዓመታት በፊት የአዳዲስ ባንኮች ምስረታ እንዲቆም መደረጉንና ከአራት ዓመት  ወዲህ በመጣው ለውጥና ምቹ ሁኔታ ተቋርጦ የነበረው የአዳዲስ ባንኮች ምስረታ መቀጠሉን ያስታወሱት አደራጆቹ፤ ጃኖ ባንክም ይህንን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ መደራጀት መጀመሩን  የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ መንገሻ አድማሱ (ረ/ፕ) ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ባንኩ በጥሩ ሁኔታ መደራጀት በጀመረ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰቱንና ለአራት ወራት ያህል ምንም እንቅስቃሴ ሳያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ እንዲያም ሆኖ የባንኩ አደራጆች ጥረታቸውን በመቀጠል በተለያዩ የክልል ከተሞች በመዘዋወር  ባለሀብቶችን ቃል በማስገባት ባንኩን በማደራጀት ሥራቸው መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በወቅቱ በሀገራችን በተከሰተው የሰሜኑ ጦርነትና የህግ ማስከበር ዘመቻ ባለሀብቶቹ ለባንኩ ማደራጃ ሊያውሉት ቃል ገብተው የነበረው ገንዘብ ወደ ህልውናው ዘመቻው መዞሩን ተከትሎ፣ በወቅቱ ማስገባት አልቻሉም ነበር ያሉት የአደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ በዚህ መሃል ግን ብሔራዊ ባንክ አዲስና አስደንጋጭ መመሪያ ማውጣቱን ይገልጻሉ፡፡
ቀደም ሲል ባንክ ለማቋቋም የሚጠየቀው 500 ሚሊዮን ብር ብቻ  የነበረ ቢሆንም፣ ብሔራዊ ባንክ ለአዳዲሶቹ ባንኮች 5 ቢሊዮን ብር ለነባሮቹ ደግሞ 7 ቢሊዮን ብር እንዲሆን በማዘዙ ነገሮች ከእቅዳችን ውጭ ሆኑ ይላሉ፡፡ጉዳዩ አስደንጋጭና ያልተጠበቀ ቢሆንም ጃኖ ባንክን ጨምሮ 8 በመደራጀት ላይ ያሉ ባንኮች ጊዜው ተራዝሞ ሁሉም የሚችለውን ይሞክር በሚል ለብሔራዊ ባንክ ቢያመለክቱም ጥያቄው በብሔራዊ ባንክ ተቀባይነት አለማግኘቱን አስረድተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ፈቃደኛ ያለመሆንን ተከትሎም ለጃኖ ባንክ ምስረታ የተሰበሰበው ገንዘብ እንዲሁ ከሚቀር ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት  በመቀየር ተንቀሳቅሶ አቅም ካዳበረ በኋላ ወደ ባንክነት የመቀየር እድል ይኖረዋል በሚል ይህንን ጥያቄ ማቅረባቸውን ፕ/ር መንገሻ ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጂ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ሲዘገይ በቦሌ መድሃኔአለም አካባቢ ለነበረን ቢሮ ያለ ውጤት ኪራይ መክፈሉ አሳሳቢም አክሳሪም በመሆኑ ከሶስት ሳምንት በፊት ሌላ ቢሮ በመክፈት ነባሩን ቢሮ መዝጋታቸውንና አዲስ ቢሮ የማደራጀት ሂደት ላይ እንደነበሩ ገልፀው በዚህ መሃል ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ “አደራጆቹ ቢሯቸውን ዘግተው ጠፉ” የሚል ወሬ መናፈሱን አስታውቀዋል።
“ቢሮ ስትቀይሩ ለምን አላሳወቃችሁም” በሚል ለፕ/ር መንገሻ ጥያቄ  አንስተንላቸው ሲመልሱም፤ ይህን ዘግተን አዲሱን ቢሮ ካደላደልን በኋላ ይፋ ለማድረግ በሂደት ላይ እያለን ነው ወሬው መናፈስ የጀመረው” ብለዋል፡፡ “አደራጆች ቢሮ ዘግተው ጠፉ” ተብሎ በተናፈሰው ወሬ በጣም ማዘናቸውን የገለጹት ፕ/ሩም ሆኖም አክስዮን የገዙ ሰዎች ገንዘባቸው በተለያዩ ባንኮች በዝግ አካውንት የተቀመጠና በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ካልሆነ ማንም ሊያዝበት እንደማይችል ግልጽ በመሆኑ ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ በመግለፅ የተሰበሰበው ገንዘብ ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ለመቀየር የሚውልና አሁን በብሔራዊ ባንክ ያለው ተቀባይነት የመፈቀድ ያህል ተስፋ እንዳለው አብራርተው የሚጠብቁት ብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ብቻ  መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ፕ/ር መንገሻ አክለውም፤ አሁንም ቢሆን ለጃኖ ባንክ አክስዮን የገዛ ማንኛውም ሰው “ገንዘቤ ይመለስልኝ” የሚል ከሆነ ህጋዊ ጥያቄ  አቅርቦ፣ ገንዘቡን መውሰድ ይችላል” ብለዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ አሁንም ጃኖ ባንክ ወደ ማይክሮ ፋይናንስ  ተቋምነት ይቀየር ሲባል ሁለት ሶስተኛው አባል የተስማማበት መሆኑንና ብሔራዊ ባንክም ይህንን ተመልክቶ አቅጣጫ መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡
ጃኖ ባንክ ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት እንዲቀየር ፈቃድ ለማግኘት የባንኩ አክሲዮን ገዢዎች በአካል ተገኝተው በጠቅላላ ጉባኤ እንዲወሰን ብሔራዊ ባንክ ማዘዙን ተከትሎ፣ አደራጆቹ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ ያስታወቁት ፕ/ር መንገሻ ጠቅላላ ጉባኤው የሚካሄድበት ቀንና አድራሻ በሚዲያ እንደሚገለጽ ባለአክስዮኖችም በትዕግስት እንዲጠብቁ እንጠይቃለን ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡


Read 334 times