Saturday, 16 April 2022 14:02

ሸማቹን መፈናፈኛ ያሳጣው የዋጋ ንረት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

  • የምግብ ዋጋ ግሽበቱ ባለፉት 10 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሻቅቧል፡፡
   • የኢትዮጵያ ወርሃዊ የዘይት ፍላጎት 79 ሺ637 ቶን ነው
    • በቀጣዮቹ 3 ወራት በየወሩ 150 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ዕቅድ ተይዟል፡፡
             
በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ላይ በየዕለቱ የሚታየው ጭማሪ ህዝቡን ለከፍተኛ ችግር እየዳረገው እንደሚገኝና የምግብ ዋጋ ግሽበቱ ባለፉት 10 ዓመታት ታይቶ በማታወቅ ሁኔታ ማሻቀቡ ተገለፀ። በአሁኑ ወቅት የምግብ ዋጋ ግሽበቱ 37.6 በመቶ ደርሷል፡፡ መንግስት የተፈጠረውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ለማሻሻል ጣልቃ እንዲገባና የዋጋ ንረቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠብ ተጠይቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሚታየው እጅጉን የተጋነነ የዋጋ ንረት፣ የንግዱ  ዘርፍ ምንም ተቆጣጣሪና ሃይ ባይ እንደሌለው የሚያመለክት መሆኑን የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፤ ሸማቹ ማህበረሰብ በነጋዴው በሚደረግበት አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ክፉኛ እየተሰቃየ ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ይታገስ ሙሉቀን ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ አብዛኛው ማህበረሰብ የሚያገኘው ገቢና የኑሮ ሁኔታ ሊጣጣምለት ባለመቻሉ ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል፡፡ ለችግሩ እንደመነሻ ምክንያት በበርካታ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የሚገለፀው የነዳጅ ዋጋ መጨመርና የዶላር ምንዛሬ ማሻቀብ ቢሆንም፣ ይህ ሆኔታ አሁን ተግባራዊ እየሆነ ካለው የመሰረታዊ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪና የአገልግሎት ዋጋ ማሻቀብ አንጻር ስንመለከተው የሚመጣጠን አይደለም ብለዋል -ባለሙያው፡፡
ሸማቹ ማህበረሰብ እየደረሰበት ካለው የዋጋ ጭማሪና የኑሮ ውድነት ሊታደገው የሚችለው መንግስት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ያሉት ዶ/ር ይታገስ፤ ይህም ለነጋዴው ማህበረሰብ የልብ ልብ በመስጠት መረን አልባና ስግብግብ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል። አያይዘውም፤ አገራት  ማህበረሰቡን ከእንዲህ አይነት ችግር ለመታደግ  የሸማቾች መብት ጥበቃ ህግ አውጥተው እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያም ይህንኑ ህግ አውጥታ ካፀደቀች ዓመታት ቢቆጠሩም፤ ለተግባራዊነቱ የሚደረግ አንዳችም እንቅስቃሴ  ግን የለም ብለዋል፡፡ ሸማቹ መብቱን ለማስከበር፣ መንግስትም ህጉን ከማውጣት በዘለለ ለተግባራዊነቱ የዘረጋው ተቋማዊ አደረጃጀት አለመኖር፣የነጋዴው ማህበረሰብም እጅግ የበዛ ስግብግበነት፣ ለዚህ ከፍተኛ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት አብቅቶናል ብለዋል ዶ/ር ይታገስ፡፡
ገበያውን እንዲቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው የመንግስት አካል፣ በነፃ ገበያ ስርዓት ስም እየተፈፀመ ያለውን ብዝበዛና ስርዓት አልበኝነት፣ እጥረት ሳይኖር እጥረት ያለ በማስመሰል ከሸማቹ የተጋነነ ዋጋ የሚጠይቁት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር አድርጎ አስተማሪ እርምጃ ሊወስድ ይገባል። መንግስት ከዛቻና ማስፈራሪያ ወጥቶ ዕለት ከዕለት እየጨመረ ለሚሄደው የዋጋ ንረት መቆሚያ ልጓም ሊያበጅለት ይገባል ብለዋል፡፡
መሰረታዊ  የምግብ ሸቀጦች ከሆኑት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የዘይት ምርት ዋጋ በአገራችን ታሪክ ከዚህ ቀደም ተደርጎ በማታወቅ ሁኔታ እጅግ በከፍተኛ መጠን ጭማሪ እያሳየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከውጭ አገር የሚገባው 5 ሊትር የታሸገ  ዘይት ከ970 ብር በላ እየተሸጠ ነው፡፡
የዘይት አስመጪነት ፍቃድ አውጥተው በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተመዘገቡና የሱፍና የአኩሪ አተር ድፍድፍ ከውጪ አገር በማስገባት አገር ውስጥ አጣርተው ሙሉ በሙሉ ያለቀለት የምግብ ዘይት ምርትን ለገበያ የሚያቀርቡ ከ2900 በላይ አስመጪዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ አስመጪዎች ድፍድፍ ዘይቱን በበቂ መጠን የሚያገኙ ባለመሆኑ ምርታቸውን በበቂ ሁኔታ ለገበያ ለማቅረብ አልቻሉም፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የድፍድፍ የምግብ ዘይት ዋጋ መናር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና፣የሃይል መቆራረጥ ለምርቶቹ በበቂ ሁኔታ ለገበያ አለመቅረብ ተጨማሪ ምክንያቶች ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡ ይህ ችግር ባለፈው ዓመት ተመርቀው ወደ ማምረት ተግባር የገቡትና አገር አቀፍ የዘይት ፍጆታን ከግማሽ በላይ ለመቅረፍ ያስችላል የተባሉትን የፋቤላ እና የዲ ደብሊው የዘይት ፋብሪካዎች የሚመለከት ነው፡፡
የዘይት ምርት እጥረትን ለማሻሻል መንግስት በየጊዜው የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ ቢገለፅም በምርት አቅርቦቱ ላይ የታየ ለውጥ አለመኖሩ ይነገራል፡፡ መንግስት ባለፈው የካቲት ወር በዘይት ምርት ስራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች 250ሺ  ዶላር መፍቀዱ ቢነገርም፣ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የዘይት ገበያ  ቀውስ ለማረጋጋት አልተቻለም፡፡
የምግብ ዘይትን ዋጋን ለማረጋጋት በቀጣዮቹ 3 ወራት 150 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የታቀደ ሲሆን 12.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በአስቸኳይ ሁኔታ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉ ተገልጿል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የምግብ ዘይት ፍላጎት በ2013 በጀት ዓመት 955 ሺ 600ቶን ወይም በወር 79ሺ 637 ቶን ደርሷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የቅባት እህሎችን ጨምቀው በሚያጣሩ 25 መካከለኛና መለስተኛ ኢንዱስትሪዎች ማምረት የተቻለው 4ሺ905 ቶን ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የምግብ ዘይት ፍላጎት 6.2 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ግሽበቱ አገሪቱ በአስር ዓመታት ውስጥ አይታው በማታውቀው ሁኔታ 37.6 በመቶ ደርሷል፡፡ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበቱ ደግሞ ወደ 20.8 በመቶ አድጓል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓመታት የነበራት የተዛባ የንግድ ስርዓት፣ጦርነትና አለመረጋገት፣ የብር ዶላርን የመግዛት አቅም ማሽልቆል የውጭ ንግዱ መቀዛቀዝ ለችግሩ መከሰት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱም ተጠቅሷል። አገሪቱ በዓመት ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዕቃዎችን ከውጭ አገር የምታስገባ ሲሆን 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ የሚያወጡ ምርቶችን ወደ ውጪ አገር ትልካለች፡፡
የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ለዋጋ ንረቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የሚገልጹት ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ፋሲል ታመነ፤ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት ወደ ምርት እንዲገቡና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መጠን ለመቀነስ የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደምሳሌ የሚጠቅሱት ከዓመታት በፊት በአገራችን በስፋት የነበሩት አነስተኛ የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካዎች እንዲያድጉና በተሻለ መልኩ ምርቶቻቸውን አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በተፈጠረው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ላይ መንግስት  ጥብቅ አቋም ሊኖረው ይገባል የሚሉት አቶ ፋሲል፤ ለይስሙላ የሚመስሉ የሸማቹን ብሶት ያላገናዘቡ አካሄዶች የትም አያደረውሱም ብለዋል፡፡
መንግስት በተለይ መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ሸቀጦችን በተመለከተ አስፈላጊውን የገበያ ጥናት በአጭር ጊዜ ውስጥ አድርጎ ዝርዝር የመሰረታዊ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የዋጋ ተመን በማውጣት ለህዝቡ ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል፤ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ብቅ እያሉ ከመዛትና ከማስፈራራት የዘለለ ተጨባጭ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል ባለሙያው፡፡
የኢትዮጵያ ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የሸማቹን ማህበረሰብ መብትና የነጋዴውን ግዴታ እንዲሁ፣ የመንግስት ኋላፊነት በሚዘረዝርብት አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 23 እንደሚመለከተው፤ ያልተገባ የንግድ እንቅስቃሴ ሲኖርና የሸማቹን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲፈጠር መንግስት ተገቢ እርምጃዎችን በመውሰድ በነጋዴው ማህበረሰብ የሚፈፀሙ ያልተገባ የእቃ ክምችትንና መደበቅን መቆጣጠር፣ ገበያ ላይ እጥረት ያለባቸውን ዕቃዎች ለህዝቡ በይፋ ማሳወቅ፣ ዕቃዎቹን በሚደብቁ ላይ ህጋዊ እርምጁ መውሰድና መሰረታዊ በሆኑ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ ዋጋ መወሰን እንደሚገባው ይደነግጋል፡፡



Read 11562 times