Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 06 October 2012 12:16

በገቢ መዳከም የሚሸጡ ታክሲዎች በርክተዋል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የታክሲ ቀጠና ለማንም አልበጀም እየተባለ ነው

የአዲስ አበባ የታክሲ ገቢ በመቀነሱና የመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ በመወደዱ የታክሲ ባለንብረቶች መኪናቸውን እየሸጡ ሲሆን በቀጠና ብቻ ተወስነው መስራታቸውና ቀለም ለውጠው ወደ ሌላ የስራ መስክ እንዳይገቡ መከልከላቸው ታክሲዎቻቸውን ለመሸጥ እንዳስገደዳቸው ይናገራሉ፡፡ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎችም ይሸጣል የሚል ወረቀት የለጠፉ ሚኒባሶች ታይተዋል፡፡ በመገናኛ ድልድይ ስር 18 ሚኒባስ ታክሲዎች ለሽያጭ ዝግጁ ነበሩ - ባለፈው ሳምንት፡፡

በሌላ በኩል በስራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት በርካታ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች በታክሲ እጦት ለእንግልት እንደተዳረጉ በምሬት እየገለፁ ነው፡፡ አንዳንድ የታክሲ ሾፌሮች፤ የትራንስፖርት ችግሩ የተፈጠረው ብዙ ታክሲዎች ከስራው እየወጡ በመሆናቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

መገናኛ ድልድይ ስር ያገኘናቸው የታክሲ ባለንብረት  አቶ ሙሉጌታ ጋረደው፣  ታክሲዎች በቀጠና ስምሪት ስር መሆናቸው ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት እንዲፈጠር ከማድረጉም በላይ ገቢያችንንም ጐድቶታል ይላሉ፡፡

የዛሬ 7 አመት ሚኒባስ ታክሲያቸውን እንደገዙ የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ፤ ያኔ የትም ተዘዋውሮ መስራት ስለሚቻል ገቢው ጥሩ እንደነበር፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋም እንዳሁኑ አለመወደዱን ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ግን ገቢው ሞቷል ይላሉ፡፡ እንደፈለጉ ዞር ዞር ብለው ባለመስራታቸው እንደቀድሞ ጥሩ ገቢ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ በዚያ ላይ  የመለዋወጫ ዋጋ ውድነት ማነቆ ሆኖባቸዋል፡፡ መኪናው ሲበላሽባቸው ለረጅም ጊዜያት እቤታቸው ለማቆም ይገደዱ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻ ግን አልቻሉም፤ ታክሲያቸውን ለመሸጥ ወሰኑ፡፡ አሁን መገናኛ ድልድይ ስር ይሸጣል የሚል ወረቀት ከለጠፉ ሚኒባሶች አንዱ የአቶ ሙሉጌታ ነው፡፡

በሜክሲኮ አካባቢ ያገኘናቸው አቶ ደረጄ ውብሸትም ታክሲያቸው ላይ ይሸጣል የሚል ወረቀት ለጥፈዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲናገሩም፤  የታክሲ ስራ በመሞቱ የመኪናቸውን ቀለም ቀይረው ለመጠቀም ቢሞክሩ በመከልከላቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አንድ ታክሲ ከተሰጠው ቀጠና ውጪ አይሰራም፤ ኮድ 3 መኪኖች ግን ነጭ ቀለም በመሆናቸው ብቻ ሲፈልጉ ከተማ የታክሲ ድጋፍ ሠጪ አሊያም ክ/ሀገር ፤ሲያሰኛቸው ደግሞ የመ/ቤት ሠርቪስ ሆነው ይሠራሉ፡፡ ይሄም ጥቅሙ ብዙ ስለሆነ ቋሚ የታክሲ ሾፌሮችም እነሱን ይመርጣሉ›› ብለዋል፡፡

አንዳንድ ባለንብረቶች ታክሲን ቀለም ለውጦ ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ መለወጥ የሚከለክለውን ደንብ ይተቻሉ - ሌሎች ባለሃብቶችን የሚያርቅ አሰራር በመሆኑ የትራንስፖርት ችግሩን ያባብሰዋል በማለት፡፡

 

Read 3166 times Last modified on Saturday, 06 October 2012 12:23