Saturday, 16 April 2022 15:32

"በእኔ ቤት"ን በወፍ በረር ቅኝት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  "ይህ ድርሰት፥ በኢትዮጵያ የክርስትና ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም፥ ጋዜጠኛ በረከት “to give voice to the voiceless”/ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን ነው በመቃብር ቤት ታፍኖ ያለውን የሊቃውንቱን ሕመምና ስቃይ፤ አጥንታቸው ድረስ የዘለቀውን ሐዘንና እንባ በመረዳት በብዕሩ ድምጽ ሊሆናቸው ሲሞክር ያየነው፡፡--"
                የመጽሐፉ ርዕስ ፦ በእኔ ቤት
                የገጽ ብዛት፦ 181 (መግቢያን ሳይጨምር)
                የመጽሐፉ ደራሲ፦ በረከት ዘላለም
                ዳሰሳ አቅራቢ፡- እንደቸርነትህ


           ይህን መጽሐፍ ለማንበብ ምክንያት የሆነኝ፥ ጥላሁን ግርማ አንጐ የሚሰኝ ወጣት «በእኔ ቤት» ስለተሰኘው ልብወለድ በማሕበራዊ ገጹ ላይ መጻፉ ነው፡፡ ይኸውም፥ «ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ዓለማዊው ስፍራ የገባችበትን የሙስና ድር አንድ ለ14 ዓመታት ያህል በመቃብር ቤት እየኖረ፤ ሥራ ለመቀጠር ደጅ እየጠና፤ ለሙስና የሚከፈል ገንዘብ ለማጠራቀም ስለተከፈለ ፍዳ አነበብኩ።» ሲል ጽፎ ተመለከትኩ። ወጣት ጥላሁን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለው ዘር ላይ የተመሠረተ መሳሳብ ከልብወለዱ መረዳቱንና ኦርቶዶክስ ባረጀና ባፈጀ መዋቅራዊ አስተዳደር መባጀቷ እንዳሳዘነው ጨምሮ ገልጾ ነበር፡፡ ሐሳቡንም ሲቋጭ፥ እነዚህ ሲሰራባቸው የቆዩ ያፈጁ ልምዶች/Status Quo በዓለማዊውም ሆነ በመንፈሣዊው ዓለም ለተጠየቅ የተፈቀዱና ሊፈተሹ የሚገባቸው መሆናቸውን ጠቁሞ ነበር፡፡ በዚህ መነሻነት መጽሐፉን ገዝቼ ማንበብ ጀመርኩ፡፡
ከሁሉ በፊት በመጽሐፉ የመግቢያ ገጽ (IV) በጥራዙ ያለው ሀሳብ በሙሉ ልብወለድ ስለመሆኑ እና ተጨባጭ ማህበራዊ መነሻ እንዳለው መገለጹ፣ ይህ ነገር እውነተኛ ነው ወይንስ ልብወለድ የሚል ጥያቄ ላነሳንና ለምናነሳ መጠነኛ ምላሽ ለማግኘት የሚያስችለን መስሎ ይሰማኛል። የቋንቋ ጥራት፣ የሀሳብ ጥልቀትና የታሪክ አወቃቀሩን በተመለከተ ዳዊት ወንድምአገኝ (ዶ/ር)ን ጨምሮ አንጋፋ የምንላቸው አድንቀው ጨርሰዋልና ብዙ ለማለት አልደፍርም፡፡
እንደመነሻ፥ የፈጠራ ታሪኩ ከመጀመሩ በፊት ስለምን አዲስ ቅኔ ለታሪኩ እንደተቆጠረ፤ የአንጋፎች የሥነ ግጥም ሥራ ስለምን እንደገባና የእግርጌ ማብራሪያዎች ስለምን እንደተሰናዱ ተገልጿልና በዚህም ላይ ተጨማሪ ማለት አይጠበቅም፡፡
በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን የተሰጡ አስተያየቶችን በመመርኮዝ፥ በውስጡም ያለውን የሐሳብ ሰንሰለትና የቋንቋ ጥራት በማጤን ከተማ ውስጥ እንደ አደገና የመጀመሪያ ሥራው እንደሆነ ወጣት ድርሰቱ የይድረስ ይድረስ የተከወነ እንዳልሆነ መመስከር ይቻላል፤ የነገረ ፈጅ ያህል መስመር በመስመር ታስቦበት የተከተበ ነው፡፡ ምክንያቱም፥ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የት ነች? ምን እየተሠራባት ነው? ለምን? በእነማ? ቀጣይ እጣዋስ ምን ሊሆን ይሆን? ሊሉ ለወደዱ ጠቅለል ያለ ምላሽ የሚሰጥ፥ ላላሉት ወገኖች ደግሞ ጥያቄ ፈጥሮ እግረመንገዱን የምላሽ አቅጣጫ የሚያመለክት ሥራ ነው፡፡ ይኸውም፥ ሐሳብን በተሟላ መልኩ ለመረዳት በመሰረታዊነት የሚያግዘው የ5W1H (አምስቱ የደብሊው እና አንዱ የኤች መጠይቅ)፥ ከጊዜ ቦታና ሁኔታ ጋር ስምሙ ሆኖ መከተቡ የሚደነቅ ይሆናል። ለእንዲህ አይነቱ የታሪክ አይነት የሐሳብ ይዘቶችን በምክንያትና ውጤት እያጀቡ መመልከትና ማመልከት በጋዜጠኝነት እንደተመረቀና እየሰራበት እንደሚገኝ ባለሙያ፥ ከአርስቶትል ጀምሮ እስከ ቶማስ አኲናስ ድረስ የተቀመጡትን ሕጎች ለማክበር የሄደበትን ርቀት ተመልክቻለሁ፡፡ በተጨማሪ፥ አንባቢ በድርሰቱ ፍጻሜ ፈራጅነትን ተጋብዟልና፥ በወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች ዘንድ መሰረታዊው ታሪክን የማንጸሪያ ሕግ 5W1H መከበሩ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ተረድቼዋለሁ፡፡
ድርሰቱን ተመርኩዞ ዋለልኝ መንግስቴ በሚሰኝ የብዕር ስም የሚጽፍ/የምትጽፍ (ጾታ ባለመታወቁ እርሳቸው እያልን ለመቀጠል እንገደዳለን) አንዳንድ ነገሮችን ለማንሳት እንደሚወዱ ያተቱበት ጽሑፍ ጥሩ ዕይታ የሰነቀ ነውና ከሌሎች አስተያየቶች ጋር እየተዛነቀ ቢቀርብ መልካም ይሆናል፡፡
ዋለልኝ፥« የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጥንታዊነቷ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ያሳስበኛል። እርሷን ሊያግዙ የሚችሉ መልካምና ገንቢ ሐሳቦች እንዳይንሸራሸሩ በማወቅ ወይም ባለማወቅ አቅባለች፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በአዕምሯአቸው በሳል የሆኑ አባላትና ልጆቿን አውግዛለች፤ አሳዳለችም፡፡ እንደ ግለሰብ ይህ ያሳዝነኛል፡፡ በዚህ ልብወለድ ውስጥ የሚገኘው ተውሕቦ የተሰኘ ገጸ ባሕርይ እንደታዘበው በጥቅማ ጥቅም፣ በዘመድ አዝማድ፣ በወንዜ ልጅነትና በመደለያ (ጉቦ) የሚሠራው ሥራ እየተንሰራፋ መሄዱ ይህችን ድንቅ የዕምነት ቤት ምን ያህል እያዋረዳት እንዳለ እንመለከታለን።» ይላሉ፡፡ ይኸውም፥ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፉትን፣ The Unresponsiveness of the Late Medieval Church: A Reconsideration መሰል ጽሁፎች ያነበበ የኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ከመካከለኛው ዘመን የአውሮፓ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ጋር የሚያመሳስላትን ነገር ያገኛል፡፡ የሃይማኖት አባት የፈረንሳይ ይሁን የጣልያን በማለት በዘር መቧደንና ቤተ ክርስቲያንን በድሎት ለመኖርና ለሀብት መሰብሰቢያነት መጠቀም የካቶሊክን ቤት ክፉኛ አምሶ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ማለፉን ያስታውሰል፤ በማለት በማስረጃ ያስረግጣሉ፡፡
የአቶ ዋለልኝ ሐሳብ እዚህ ላይ ቢቆይ፥ አነጋጋሪ በሆነው በዚህ ልብወለድ ላይ፥ ዮሴፍ ፍስሃ ሰውነት የሚሰኝ ወጣት (የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ይመስለኛል) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚስተዋል የአስተዳደር በደል፣ የሊቃውንት ለቅሶና እንባ በሥነ ጽሑፍ እስከአሁን በአግባቡ እንዳልቀረበና ጋዜጠኛ በረከት ዘላለም ግን ገንዘብ የሌላቸው ሊቃውንት ለመቀጠር ምን ያህል አፈር እንዲበሉና እንዲለብሱ እንደተፈረደባቸው በቅርብ የሚያውቀውን ሐቅ በልብወለዱ እንዳገኘ በማሕበራዊ ገጹ ላይ አብራርቷል፡፡
በድርሰቱ ላይ ግላዊ ዳሰሳውን ያሰፈረው ዮሴፍ፥ (በገጽ 64) “አንደበተ ርቱዕ ጩሉሌዎች” የሚለውን መነሻ በማድረግ በብዙ አድባራት፥ «የፈለገ ደጅ ብትጸና፣ የአለቃ እግር ብትስም፣ የፈለገ ወድቀህ ብትነሳ፣ በፈጣሪ… በእመ ብርሃን… ባዛኝቱ እያልክ ብትለምን፤ በአምላክ ሀልዎት እናምናለን የሚሉ… ግን በተግባር ፈጽሞ በአምላክ ሀልዎት የማያምኑ ቀሚስ ለባሾችና ጠምጣሚዎች የሰው ልመናና ለቅሶ የሚሰሙበት እንጥፍጣፊ ርኅራኄ የላቸውም።» ሲል ጽፏል፡፡ “ለምን?” ከተባለም የበረከት መጽሐፍ እንደሚገልጽልን፤ «ከሌለህ የለህም!» ነው በማለት የአሠራሩን መደምደሚያ ያነሳል። በደላላ ደብተራዎች በኩል የሚተመን ገንዘብ ላዘጋጀ ግን እንደ ገንዘቡ መጠን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ፥ ከከፍተኛ አንስቶ ዝቅተኛ ደመወዝ እስከሚገኝባቸው አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ከቢሮ ሥራ እስከ ቀዳሽ አወዳሽነት አማርጦ መቀጠር መቻሉ የዘመኑ ሐቅ መሆኑን ጠቅሷል። ይኸውም፥ በካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን simony እየተባለ በአውሮፓ ምድር የቤተ ክርስቲያን ሥራና ሹመት በገንዘብ እንደሚሸጥና እንደሚገዛ በ1992 በJoseph Lynch የተጻፈው The Medieval Church የሚሰኘው ድፍን አውሮፓ የሚስማማበት የታሪክ መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ወደየት እየሄደች እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡
በመጽሐፉ (ገጽ 21) በአንድ መሪጌታ ተወክሎ የቀረበው ጩኸት እንደገለጸው፣ የሌብነት አሠራሩን የማያውቁትና ያልተገለጠላቸው፤ በቅንነት ተመርተው በሙያቸው የሚቀጠሩ የመሰላቸው የዋህ ሊቃውንት፣ በጩኸት "ሙስናን እናጋልጣለን" ያሉ እንደሆን “በሰርቆ አደሮች’’ ከቢሮና ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ተንጠልጥለው መውጣት እጣቸው መሆኑን ዮሴፍ ያትታትል፡፡
ወደ ዋለልኝ ምልከታ ስንመለስ፥ የቤተ-ክርስቲያኒቱ አባቶች ኃላፊነትና የሥራ እንቅስቃሴ ሌላው የሚያጠያይቅና ከልብወለዱ ተወስዶ ብዙ ሊያነጋግር የሚያስችል ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም ቅን የቤተ-ክርስቲያን ወዳጆች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ብዙ ነገሮችን ውጠው እስከአሁን አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በአስተዳደር ለማገዝ የሚቋቋመው የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ፣ በየቦታው ያለበት ፈተና ይህ ነው፡፡ ይኸውም ተውሕቦን ሲያብከነክነው በግልጽ እናያለን፡፡
በዚህ ዘመን ያለውን የሌብነት ፈተና ለመረዳት ልብወለዱ ከተራ ፈጠራነት አለፍ እንደሚል የሚያስረዳው ዮሴፍ ፍሥኃ፥ «ስንቶች የሚገባቸውን እንዳያገኙ ገፍተናቸው ወደ ሌላ ቤተ እምነት ሄዱ? ለምንድን ይሆን የአቋቋሙ ሊቅ መሪጌታ ተውሕቦ ሥራ ለማግኘት የሌላ ቤተ እምነትን ሲቀላውጥ የነበረው? አንደ ግብዙና ወሬ አቀባዩ ዲ/ን አካሉ በአብነት ትምህርት የደከሙትን፤ ከቤተ ክርስቲያን የተገፉ፤ የሚበሉት ያጡ ምስኪን ሰዎችን በምን ሞራላችንስ “ሌላ ቤተ እምነት እየሠራችሁ ነው፤ መናፍቅ ናችሁ!” ለማለት የምንደፍረው? በችግራቸው ጊዜ ያልደረስን ሰዎች በችግር ምክንያት ለሚወስዱት ውሳኔ የመፍረድ ሞራል መሠረት ከየት አገኘነው? በቤተ ክርስቲያን የሚገባቸውን ቦታ በማጣት ስንቶቹ ሊቃውንት ጎዳና አዳሪ ሆኑ? ስንቱ በብስጭት ሰካራምና ጫት ቃሚ አጫሽ ሆኑ?» የሚሉ ጥያቄዎች እንደተነሱበት አስፍሯል፡፡ ለዚህም ይመስላል በአ.አ.ዩ የአዕምሮ ሕክምና መምህሩና የ"አለመኖር" መጽሐፍ ደራሲ ዶ/ር ዳዊት ወንድምአገኝ፤ «በተጎዳ ማህበረሰብና በላሸቁ ተቋማት ውስጥ የራስንና ራስን ማግኘት ምን ያክል የውስጥ ሙግት እንደሆነ ያሳያል። ከሁሉ በላይ አንድ ከተሜ (ደራሲው) የሀገሬውን የእምነት ስርዓት፤ የነዋሪውን ወግና ባህል፤ የጉዳቱን ልክ፤ የመረመረበት ደርዝ ‘ይበል በረከት!’ ያስብላል፡፡» ሲል በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ ሐሳቡን ያሰፈረው፡፡
በሌላ ሐሳብ ዋለልኝ፥ (ገጽ 158) ን መነሻ በማድረግ (አከራካሪነቱ ባለበት የሚቀመጥ ሆኖ) “አባቶች ይገለገሉበት ስለነበረ ጥበብ” በልብወለዱ መነሳቱ ጥሩ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ በዚህም፥ «ሥር ማሽነት እና ቅጠል በጣሽነት ከማሕበረሰብ በባሕል በኩል የሚተላለፍ መድኃኒት የመፈለግ ሂደት ሆኖ ሳለ፣ ቅኑን ከደጉ መለየት በማይችሉ ዘንድ የጅምላ ማጥላላት እየደረሰበት መንፈሣዊ ድንቁርና እንዲስፋፋ ሆኗል፡፡ በዚህ ረገድ ተውሕቦ የተሰኘ ገጸ ባሕርይ፥ የባሕል ሕክምና የፈጣሪ ጸጋ መሆኑን በግልጽ በማመን የሳትነውን ያስረዳናል፡፡» ሲሉ አረዳዳቸውን ያሰፍሩና ባሕላዊ መድኃኒትን መጥላትና ማጥላላት አላዋቂነት መሆኑን የነገረን ሥራ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ምክንያቱንም፥ «ዘመኑ የሚያደንቃቸው የ Phytomedicine ባለሙያዎች ስንት ድንበር አቋርጠው የሀገራችን የመንደር መድኃኒት አዋቂዎች ደጅ አልጠፋ ማለታቸውን ማን እስኪነግረን እንጠብቃለን?» ብለው በማጠየቅ፡፡ በልብወለዱ ይኸው ምልከታ በመጉላቱ ይመስላል «በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዉስጥ ያለውን እምቅ የእውቀት ሀብት የሚያሳይ ሥራ!» ሲል ሐኪም እና የድጓ አዋቂው ሊቀ ጠበብት ዘለዓለም ይርጋ (ዶ/ር) በማሕበራዊ ገጹ ጽፎ የምናነበው፡፡
በሌላ በኩል፥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የበርካታ መንፈሣዊ ዩኒቨርስቲና ኮሌጆች ባለቤት መሆን ስትችል በዚያው የቆሎ ትምህርት ቤትነት ደረጃ ላይ መገኘቷና ባሉበት የሚረግጡ የጉባኤ ቤቶች ባለቤት ሆና መቅረቷ እንዲያስቆጭ የሚያደርግ ልብወለድ መሆኑን ዋለልኝ በትንተናቸው አሳይተዋል፡፡ ይኸውም፥ «በመንፈሣዊ ትምህርት ላይ የተመረኮዙ የጤና፣ የእርሻ፣ የዕደ ጥበብ፣ ማህበራዊ እና መንፈሣዊ ጉዳዮችን የማማከር አገልግሎት በብቁና ልዩ በሆነ ደረጃ ልትሰጥ ስትችል፤ ያንን አለማድረጓ ሌላው የሚስቆጨኝ ጉዳይ ሲሆን… ተውሕቦ (በገጽ 144) ባለው አቅም ይህንን ማድረጉ፥ ልብወለድ ቢሆንም ቁጭትን የሚክስ ነው፡፡» በማለት፡፡
የመጽሐፉን የሴራ አወቃቀር በተመለከተ፥ ተውሕቦ በተደጋጋሚ የDilemma Theory ማረጋገጫ እስኪመስል ድረስ በተዘባረቀ አስጨናቂ ሀሳብ ላይ እንዲዋልል ሲገደድ እናያለን። ነገሩንም፥ «ወደ ፈተና መግባት ሰልችቶኛል፡፡ እንደመግባቴ ግን ዛሬም የመጣብኝን ፈተና በአግባቡ መወጣት ይኖርብኛል፡፡» ይላል፡፡ ይኽንኑ የሐሳብ ሰንሰለት በጥልቀት በመታዘብ ይመስላል «በመቃብር ቤት ውስጥ ከአንድ አስርት በላይ የቆየው ወጣት በዋዛ የሚሸነፍ መንፈስ አልነበረውም። ነፍስና ሥጋውን የሚያፋልም ፈተና ተፈትኖ እየወደቀና እየተነሳ ይጓዛል፡፡ የመቃብር ቤቱ ድቅድቅ ጨለማ ነገን እንዳያይ አይከለክለውም።» ሲል ስለ ገጸ-ባሕርዩ ውጣ ውረድ በአ.አ.ዩ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ረ/ፕሮፌሰር ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) ሐሳቡን ጽፎ የምናነበው፡፡
የመጽሐፉን ማጠቃለያ አስመልክቶ፥ የታሪኩ መቋጫ እንቆቅቅልሽ በመሆን ለአንባቢዎች የቤት ሥራ ተደርጎ መሰጠቱ እኔ በግል የተስማማኝ ቅርጽ ነው፤ ተውሕቦ የወሰነውን አንባቢ አይወስንለትምና፡፡ ሁሉም እንደየንቃቱ፣ ግንዛቤና አረዳዱ ምን ሊወስን እንደሚችል ለመታዘብ የሚረዳ ምዕራፍ ነው፡፡» የሚለውን የዋለልኝን ሐሳብ በመደገፍ የፍልስፍና እና የሥነ-መለኮት ተመራማሪና መምህሩ ዮናስ ዘውዴ፤ «መጽሐፉ ነገሮችን በልኬትና በአግባቡ እንድናይ የሚረዳ ነው።» ሲል የሚያሞካሸው፡፡
ወንድማችን በረከት በልብ ወለድ መልኩ ለመግለጽ የሞከረው የገሀዱ ዓለም ነጸብራቅ እንደ አንገብጋቢ ጉዳይ ተቆጥሮ የሊቃውንቱ የሰቆቃ ሕይወት በአግባቡ እንዳልተጠና የጻፉት በርካታ የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፥ ሊቀ ጠበብት ዘለዓለም ይርጋ (ዶ/ር) ግን «አስተዳደራዊና ሥነ-ምግባራዊ ብልሽቶች የፈተና ምንጭ መሆናቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያስረዳ ሥራ ነው፡፡ ከንባብ በኋላ በልቦለዱ ውስጥ የታመቁት ሀሳቦች አደባባይ ወጥተው ለውይይት መነሻ መሆናቸው መሰረታዊ ይመስለኛል፡፡» በማለት ነገሩ ከልቦለድነት ያለፈ መሆኑን የሚጠቁም ሐሳብ አስቀምጧል፡፡
ይህ ድርሰት፥ በኢትዮጵያ የክርስትና ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም፥ ጋዜጠኛ በረከት “to give voice to the voiceless”/ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን ነው በመቃብር ቤት ታፍኖ ያለውን የሊቃውንቱን ሕመምና ስቃይ፤ አጥንታቸው ድረስ የዘለቀውን ሐዘንና እንባ በመረዳት በብዕሩ ድምጽ ሊሆናቸው ሲሞክር ያየነው፡፡ መጽሐፉ በሥነ-ጽሑፍ፣ በወንጀል ምርመራ፣ በጋዜጠኝነት፣ በሥነ-መለኮት እና ሌሎችም ማሕበራዊ ዘርፎች ላይ ላሉ ተማሪዎች ለጥናትና ምርምር ሥራ እንደ መነሻ ሆኖ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችልም ልንገነዘብ እንችላለን።
መጽሐፉ፥ ሁሉም ራሱን እንዲያይና እግረ-መንገዱን የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ የሚያሳስብ እንደሆነ በደራሲው የማሕበራዊ ገጽ ላይ ከሚንሸራሸሩ ሐሳቦች መመልከት የሚቻል ሲሆን እውቀት፣ ሥርዓትና ትውፊት በቸልታ ከመጥፋታቸው በፊት መገናኛ ብዙኃን በግልጽ ጉዳዩን ለውይይት ቢያቀርቡት አሁንም የረፈደ እንዳልሆነ አስተያየት ከሰጡ ሰዎች የመደምደሚያ ሀሳብ ለመታዘብ ይቻላል፡፡
ለመጠቅለል ያህል፥ ይህንን መጽሐፍ ላስነበበን ወንድማችን በረከት ዘላለም፣ ረጅም እድሜና ጤናን እመኛለሁ፡፡ ያላነበባችሁ መጽሐፉን እንድታነቡት እጋብዛለሁ። በቀጣይ ጊዜያት ማሕበረሰብን በእውቀትና በምልከታ ከፍ የሚያደርጉ የሕይወት ነጸብራቆችን በልብ-ወለዳዊም ሆነ ኢ ልብ-ወለዳዊ በሆነ መልኩ እንዲያስነብበን እንመኛለን፡፡

Read 1948 times