Saturday, 23 April 2022 14:30

“ከህልም ዓለም ውጡ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


          "እባካችሁ፣ እባካችሁ ጊዜው ሳይረፍድ፣ አስራ አንደኛው ሰዓት የምትሉት ድንገት ከች ሳይልባችሁ ከህልም ዓለም ውጡና ወደ እውነተኛው ዓለም ተመለሱ! ለእናንተም፣ ለትውልድም፣ ለሀገርም የሚበጀው ይኸው ብቻ ነው፡፡--"
             
           እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ ለመሆኑ እንዴት ከርመሀል?  ቀዬውስ፣ ሰዉስ ከብቱስ ደህና ነው ወይ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ... ዛሬ ተለየህብኝ።
አንድዬ፡- ተለየህብኝ! ተለየህብኝ ነው ያልከኝ? ምነው፣ምነው ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አጠፋሁ እንዴ አንድዬ?፣
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ አሁንስ ምኑንም ሳልደብቅ እውነቱን፣ የሚሰማኝን መናገር አለብኝ፡፡ አዎ፣ አጥፍተሀል፡፡ አጥፈተሀል ብቻ ሳይሆን አስቀይመኸኛል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንዴ አንድዬ! ይህን ያህል ምን ባጠፋ ነው፡፡
አንድዬ፡- እኔ ጠባዬን አሳምሬ፣ ተሽቆጥቁጬ የረሳችሁትን ሰላምታ ሳቀርብልህ ተለየህብኝ ትለኛለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደው አፌ እንዳመጣ ስለተናገርኩ ነው እንጂ ምን ቆርጦኝ፣ እንዴት ብደፍር ነው የማስቀይምህ! በአሁኑ ጊዜ ከአንተ ሌላ ማን አለንና ነው!
አንድዬ፡- እየው እንግዲህ፡፡ ርዕስ ልታስለውጠኝ እየሞከርክ ነው፡፡ እኔ እንዲህ ሞቅ አድርገህ ሰላም ስላልከኝ ደስ ብሎኛል ትለኛለህ ስል፣ አንተ ግን ጭራሽ ተለየህብኝ አልከኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ስማ ምስኪኑ፣ ወደራሴ ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ዛሬ አመጣጥህ መቼም በሰላም ነው አይደል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በሰላም ነው አንድዬ፣ ለዚች ቀን ስላበቃኸን ምስጋና ለማቅረብ ነው፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ! እንደው ደግ ደጉን አንዳንዴ ብቻ የምታደርጉት ቢሆንም፣ ተመስገን ስትሉኝ እኮ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ሊለኝ አይገባም እንዴ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እ...እሱ አንድዬ፣ እሱማ...
አንድዬ፡- ግዴለም፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ግዴለም ተወው፡፡  ሌላ ጊዜ መክረህ ትመጣና መልሱን ትነግረኛለህ፡፡ ይልቅ አሁን አንድ ቁም ነገር ልንገርህ፡፡ ይፈቀድልኛል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንዴት እንዲህ ትላለህ? ጭራሽ እኔ ነኝ ፈቃጅ?
አንድዬ፡- እሺ፣ አንተ ባትልም እንደፈቀድክልኝ እቆጥረውና፣ ለምን መሰለህ እንደዛ ሞቅ ያለ ሰላምታ ያቀረብኩት?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንዴ አንድዬ፣ ልጆችህ ነና! ስለምትወደን ነዋ!
አንድዬ፡- አሁን ስላልከው እርግጠኞች ናችሁ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ስለምኑ አንድዬ?
አንድዬ፡- እንደምወዳችሁ እርግጠኞች ናችሁ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ለዚህ ምን ጥያቄ አለውና! ደግሞስ እኛን ያህል የምትውደው ማን አለና ነው!
አንድዬ፡- ጎሽ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ጎሽ! አንዳንዴ ግርም የምትሉኝ ለዚህ ነው እኮ። በሁሉም ነገር ለራሳችሁ አንደኛ ደረጃ ነው የምትሰጡት፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አሁን የቀን ክፉ ጥሎን ነው እንጂ ለዚህ ምን ጥያቄ ይኖረዋል!
አንድዬ፡- ጥሩ፣ እንዲህ ስለራሳችሁ ማሰባችሁ ክፋት የለውም፣ ሌላውን ዝቅ እስካላደረጋችሁ ድረስ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ፣ እኛ ማንንም ዝቅ አናደርግም፡፡
አንድዬ፡- እሱን እንኳን ተወው! ይልቅ እንደዛ አብዝቼ ሰላምታ ያቀረብኩት ለምን እንደሆነ ልንገርህ... ፈራኋችሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- ግዴለም ምስኪኑ ሀበሻ ረጋ በል፡፡ በትንሽ ትልቁ ደንግጣችሁ እንዴት ይሆናል!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እስከዛሬ እንዲህ የሚያስደነግጥ ነገር ተናግረህ አታውቅም እኮ አንድዬ! ልቤ ጦሽ ልትል ምንም አልቀራትም እኮ!
አንድዬ፡- ጉድ እኮ ነው! ለምንድነው ልብህ ጦሽ የምትለው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ደንግጬ ነዋ አንድዬ! ፈራኋችሁ ስትል ደንግጬ ነዋ!
አንድዬ፡- ታች ወርደህ እሱ ነው ልቤን ጦሽ ያደረጋት ብለህ ልትከሰኝ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ...
አንድዬ፡- ቆይ፣ ቆይማ ምስኪኑ ሀበሻ። እንደው ለስንት ጊዜ ግርም ሲለኝ የኖረ ነገር አለ፡፡ ለምንድነው ለሁሉም ነገር ሰበብ የምትፈልጉት?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አልገባኝም አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- የሆነ ነገር ሲበላሽ ራሳችሁ ሃላፊነቱን እንደመውሰድ ሁልጊዜ የምታሳብቡት ሰው ወይም ነገር የምትፈልጉት ለምንድነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እኔ ምን ብዬ አንተ ላይ አሳብባለሁ?
አንድዬ፡- አሁን ስለ እኔ አይደለም እያወራሁ ያለሁት፡፡ አጠቃላዩን ነው የተናገርኩት፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ተወው፤ እኔ ነኝ ጥፋተኛው፤ እንደማትመልስልኝ እያወቅሁ እንዲህ አይነት ጥያቄ መጠየቄ፡፡ ይልቅ ፈራኋችሁ ማለት ምን ያስደነግጣል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ያስደነግጣል እንጂ... አይደለም አንተ ብለኸው ሌላ ምድር ላይ ያለ እንደዛ ቢል እንኳን ያስደነግጣል፡፡
አንድዬ፡- እኮ፣ አስረዳኛ ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እኛ ምን አቅም አለንና ነው የምናስፈራው? ለራሳችን በስንቱ ነገር ፈርተን ሟምተን ልናልቅ ምንም አልቀረንም እኮ!
አንድዬ፡- ምስኪን ሀበሻ፣ እናንተ ፈራችሁ ማለት እኮ አታስፈሩም ማለት አይደለም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እኮ እንዴት አንድዬ? አቅም እኮ የለንም!
አንድዬ፡- እሱን እኮ ነው የምልህ። ምስኪኑ ሀበሻ፣ ትልቁ አደጋ አቅም ሳይኖራችሁ ማስፈራታችሁ ነው፡፡ ...ለምን በለኛ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ለምን አንድዬ፣ ለምን?
አንድዬ፡- ምንም ነገር ለማድረግ አትመለሱማ! አቅም ሳይኖር አቅም ካለው በላይ መሆን ሲያሰኛችሁ ለምን አታስፈሩም?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ግዴለህም፣ እዛ ደረጃ አልደረስንም፡፡
አንድዬ፡- እናንተማ ምኑን አውቃችሁት። ስታዩት ነው እኮ ማወቅ የምትችሉት፡፡ አይደለም ሌላው ምድር ላይ ያለው ቀርቶ እኔው ራሴ ልደርሰበት ያልቻልኩት ህልም ዓለም ውስጥ ገብታችኋል፡፡ ደግሞ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እውነታውን ክዶ በህልም ዓለም እንደሚኖር ፍጡር አደገኛ የለም፡፡  ለምን አትለኝም?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ለምን አንድዬ?
አንድዬ፡- ምክንያቱም ድርጊቶቹ ሁሉ፣ ውሳኔዎቹ ሁሉ የሚወሰኑት ባለው የእውኑ ዓለም ላይ ሳይሆን በሌለው የህልም ዓለም ላይ ተመስርተው ስለሆነ ነው፡፡ ለዚህ ነው አሁን አሁን ብዙዎቻችሁ ሀገራችሁን በቅጡ መያዝ ሳትችሉ ዓለምን የተቆጣጠራችሁ ዓይነት የሚያደርጋችሁ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህማ ጭራሽ  እርስ በእርስ መፎካከር ጀምራችሁልኛል፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ ተረዳኸኝ ወይስ የባሰውኑ አደናገርኩህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አሁን ስታስረዳኝ ነው ትንሽ፣ ትንሽ እየተገለጠልኝ የመጣው፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ፣ እንደው ቢሆንም፣ ባይሆንም ትንሽዬ የመፍትሄ ሀሳብ ላቀርብ ይፈቀድልኛል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- እባካችሁ፣ እባካችሁ ጊዜው ሳይረፍድ፣ አስራ አንደኛው ሰዓት የምትሉት ድንገት ከች ሳይልባችሁ ከህልም ዓለም ውጡና ወደ እውነተኛው ዓለም ተመለሱ! ለእናንተም፣ ለትውልድም፣ ለሀገርም የሚበጀው ይኸው ብቻ ነው፡፡ በል፣ ምስኪኑ ሀበሻ ደህና ሁን፤ ሰላም ግባ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን፡፡
መልካም የትንሳኤ በዓል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 652 times