Monday, 25 April 2022 06:17

የእስከዳር ግርማይ “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” ዳሰሳ

Written by  በቴዎድሮስ አጥላው
Rate this item
(0 votes)

መንደርደሪያ
“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው” በሦስት ክፍሎች የቀረበ የ20 ወጎች ስብስብ ነው፡፡ ደራሲዋ እስከዳር ግርማይ እንደምትነግረን፤ እነዚህ ሃያ ተኩል ወጎች “በተለያየ ጊዜ ያለፈችባቸው ስሜቶች ነጸብራቅና ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ያጋጠሟትን ኹነቶች በማስታወሻ የማስፈር ልምድ ውጤቶች” ናቸው፡፡
በርግጥም ወጎች ቅፅበታትን ቀርፆ ማስቀሪያ፤ እንዳይዘነጉ፣ እንዲነገሩ አንድም ለትምህርታችን አንድም ለትውስታችን፣ አንድም ለግርምታችን ይረዳን ዘንድ እንዲቀረሱ ተላላፊ ስሜቶቻችንን፣ ሐሳቦቻችንን፣ መረዳቶቻችንንና ግራ መጋባቶቻችንን ከማይቆመው ጊዜ ላይ ነጥቀን የምናስቆምባቸው መሳሪያዎች ናቸው፡፡ እስከዳር ማስታወሻ በመያዝ ልማዷና በመጻፍ ሥጦታዋ ታግዛ የአርበኝነት፣ የመጠቃት፣ ጥቃትን ያለመቀበል፣ የግትርነት፣ የአቋመ ጽኑነት፣ የጠያቂነት፣ ከዚህ ሁሉ በላይ የተግባራዊ በጎ ሰውነት አፍታዎቿን ጽሑፍ በተባለ ጊዜን ማጥመጃ መረብ አጥምዳልናለች፡፡
ወጎች በባሕርያቸው መደበኛ ኢ-ልቦለዶች ከሚባሉት እንደ የምርምር ጽሑፍና ጋዜጣዊ ጽሑፍ ካሉት ኮስታራ ዘውጎች በተለየ ልሎች ናቸው፤ ከማረጋገጫነታቸው ይልቅ መጠየቂያነታቸው ይበረታል፤ ከመደምደሚያነታቸው ይልቅ ኅሠሣነታቸው፤ ከጥናታዊነታቸው ይልቅ ግላስተያየታዊነታቸው ይጎላል፡፡ ወጎች “እንዲህ ነው” ወይም “እንዲህ መሆን አለበት” ብሎ መበየኛዎች አይደሉም፤ መጠየቂያዎች፣ መፈተሻዎች፣ መመርመሪያዎች፣ ማሳያዎች፣ መዘከሪያዎች፣ መመስከሪያዎች ናቸው፡፡
የእስከዳር ወጎች ከዳር እስከዳር መገረም፣ መደነቅ፣ መታዘብ በወለዳቸው ጥያቄዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ ከገዢው ርእስ  ከ“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው” ጀምሮ ቋንቋን፣ ልማድን፣ እምነትን፣ ባህልን፣ አስተሳሰብን ይጠይቃሉ፤ ይሞግታሉ፡፡ እውነት ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው፣ በዘውግ ፈርጆ እንደየዘመኑ ያሻውን ምንትነት የሚሰጠው ወገኑ ነው? ወይስ የሚሳደድባት የእትብቱ መቀበሪያ ምድሩ? “ከገዛ አገሩ በገዛ ወገኑ የሚፈናቀለው፣ የሚታረደውና የሚሳደደው ወገኔ፣ ከዓመታት በኋላ የሚናፍቀው አገሩን ነው ወይስ ክልሉን?” … ይህንን እና የመሳሰለውን ጥያቄ ማስረጃ ጠቅሰው ከመመለስ ይልቅ ወደ አንባቢው ልብ የሚልኩ ወጎች ናቸው በዚህ መጽሐፍ የተካተቱት፡፡
ሦስቱ ክፍሎቹ እና ማጠንጠኛዎቻቸው
ልጆቼ ቆሎ ፈጆቼ
ከርእሱ በመነሣት ስለ ልጆቿ የሚተረክበት ክፍል መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ በእርግጥም እስከዳር ከልጆቿ ከአቤል “አባቴ” እና ከሊያ/ “ሚሚ” ጋር የተገናኙ አጋጣሚዎችንና የእሷን አፀፋዎች የሚያሳዩ ሦስት ተረኮችን የያዘ ክፍል ነው። ይህ ክፍል በእርግጥ ዓበይት ጉዳዮቹ ሚሚና አቤል ናቸው ወይ ብለን ብንጠይቅ፣ የምናገኘው “አይደሉም” የሚል ምላሽ ነው።
አቤል እና ሚሚ በዚህ ክፍል ለቀረቡ የእስከዳር ጥያቄዎች፣ ሙግቶችና ትዝብቶች መባያዎች ናቸው፡፡ በሚሚ ጥያቄዎች መነሻነት አባባሎቻችንን ትጠይቃለች፤ ኢትዮጵያውያን ወላጆች ከወላጆቻቸው ወይም ከባህላቸው ወይም ከሰፈራቸው የወረሷቸውን ድርጊቶች፣ አባባሎች፣ ባህሎች ጭምር ተረድተው ነው ወይ ወደ ልጆቻቸው የሚያወርዱት? “እኔን” “ጠላትሽን” የመሳሰሉትን የድንገቴ ስሜት አጸፋዎቻችንን ወይም እንደ በዚያ በበጋ ያሉ የልጆች ዝማሬዎቻችንን ተጠየቃዊነት የመጠየቅም ሆነ ለልጆቻችን የመመለስ አቅም ወይም ሐሳቡ ራሱስ አለን ወይ? የሚሉ ዐይነት መብሰልሰሎቿን እስከዳር በነሚሚ አስታካ ታቀርብልናለች፤ ታሳስበናለች፡፡
ልጆቻችን ደንቀፍ ሲያደርጋቸው “እኔ ልደፋ” የምንልበትን ከአባባሉ ሥር የተሰወረ ጥልቅ ፍቅር መግለጽ እንችላለን? ወይስ ያፍ ልማድ ሆኖብን ነው ቃሉ የሚያመልጠን?
በዚህ ክፍል ውስጥ እስከዳር ከልጆቿ እና ከባሏ ጋር ባላት ግንኙነት መነጽርነት ራሷን ትመዝናለች፤ አቤልን ለምን “ኩሩ ኢትዮጵያዊ” ብለህ የኢንስታግራም መገለጫህ ላይ ጨመርክ ብላ ወጥራ እየያዘችው፣ ራሷን ትታዘባለች፤ ከአቤል ትማራለች፡፡ ባሏ ልጆቹ ብቻቸውን እንዲቆሙ ሲፈቅድ እሷ “አሳይልሻለሁ” የምትልበትን ፉከራዋን ትታዘበዋለች። “Essay” የሚለውን ሥያሜ ለእስከዳር ዐይነቶቹ ጽሑፎች መጥሪያነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመበት ሚሼል ደ ሞንታኝ፣ ወግ “ራስን ፈልጎ ማግኛ” መሣሪያ - a tool for self-discovery – ነው ይላል፡፡ “በወጎቼ (በጽሑፎቼ) ስለሌሎች ነገሮች ሳይሆን ስለራሴ ለማሳወቅ ነው የምሞክረው” ይላል፡፡ እስከዳር ወጎቿን ራሷን ለመተዋወቅ ጭምር ስትጠቀምባቸው አይቻለሁ፡፡
እኛና እነሱ፣ ኢትዮጵያዊነት ሲፈተን
ርእሱ የሩድያርድ ኪፕሊንግን አወዛጋቢ ግጥም We and They ያስታውሳል፤ ወይም ደግሞ ድህረ ቅኝ አገዛዝ የምንትነት ትንተና ማጠንጠኛ የሆነውን Us vs them ወይም Othering እየተባለ የሚታወቀውን ማስተንተኛ ያስታውሰናል፡፡
እኛ ሌሎችን እንዴት እናያለን፣ ሌሎችስ እኛን እንዴት ያዩናል?
ሌሎች የሚያዩን እኛ ራሳችንን በምናይበት መንገድ ነው፣ እነሱንስ የምናያቸው ራሳቸውን በሚያዩበት መንገድ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ጉዳዩ ያሳስበናል፡፡
ወይም ከራስ ወገን ውጭ ያለውን በተለየ ዐይን የማየት፣ ከመሰሎች ጋር የመሰባሰብ፣ በአንድ ወይም በሌላ መለኪያ የማይመስሉንን እንደ ስጋት፣ ሲከፋም እንደጠላት የማየትን የዚህ የነቃ የዘረኝነት ዘመን አባዜ ያስታውሰናል፡፡
ታዲያ እስከዳር በዚህ ርእስ ሥር ያካተተቻቸው ሰባት ወጎች፣ ይሄን የእኛ እና እነሱ አስተሳሰብ ማጠንጠኛቸው ያደረጉ ይሆኑ? አዎን አብዛኞቹ ወጎች ለራሳችን ባለን ግምት ወይም እኛ ስለሌሎች ባለን ግምት እና በእውነታው መሀል ያ ልዩነቶች ላይ ያተኩራሉ፡፡
እስከዳር “ምድረ ቀደምት” በሚለው ስላቋ ታጅባ እኛ ስለራሳችን ያለንን ግምት፣ “እነሱ” በተባሉት ውጭ አገር ተመልካቾቻችን ዐይን ታሳየናለች፤ በሚዛናቸው ስንቀመጥ ውሃ ማንሳት አለማንሳታችንን ታስመለክተናለች።
በሰባቱ ታሪኮች ውስጥ (“ነበር” የሚለው ለየት ቢልም እንኳ) አገሩን፣ ሰዉን፣ የሀበሻውን ስፍራ፣ ዐመሉንም ጭምር ሀገርን እንደ መመልከቻ፣ ወገንን እንደ መመዘኛ ትጠቀምባቸዋለች። ባለሺሻዎቹ የአሜሪካ ሀበሾች፣ ለመልእክት ምላሽ የማይሰጡት ዘመዶቿ፣ የከሸፉት ሀበሾች እነሱ ካለቻቸው ጋር (መንገድ ላይ ትርዒት እያሳየ ምጽዋት ከሚሰበስበው የፈረንጅ ተመጽዋች ጋር ሳይቀር) ይነጻጸራሉ፡፡
እነሱ እንዴት ያዩናል? ለሚል ጥያቄያችን በብዙዎቹ ተረኮች ምላሽ ትሰጣለች፣ በአስረጂ ምሳሌዎች የተደገፉ፡፡ ያየችውን በጎ ነገር ትመሰክራለች ብላ የተማመነችባት ፈረንሣይዊት ጓደኛዋ “ኢትዮጵያ ለቀበጥ ልጆቿ ጥሩ ማስፈራሪያ እንደሆነቻት ስለኢትዮጵያ በጎ ሊነገርበት በታቀደው መድረክ ላይ መናገሯ፣ ኢትዮጵያን እንደ የቤት ሠራተኛ አምራች እና ላኪ የሚያስቆጥሩት ተደጋጋሚ አጋጣሚዎች፣ እሷንም በቤት ሠራተኞቻቸው ዐይን የሚያዩት ሰዎች ሁሉ ምሳሌዎቿ ናቸው፡፡
ይህንን ሁሉም ለእኛው ለራሳችን፣ ኢትዮጵያ እንደ ቅንድባችን አልታይ ብላን አለልክ ለምንኩራራባት ወገኖቿ፤ “እኔ ከቆምኩበት ሥፍራ የቤት ሠራተኛዋን አገራችሁን ላሣያችሁ; ብላ፣ የመዋረዷ፣ የሐዘኗ፣ የቁጭቷ ተጋሪዎች ታደርገናለች፡፡
አንድ ጊዜ አንድ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ተማሪዎቹን እያየ፤ “አያችኋቸው ጥቁሮቹን” አላቸው፤ ሁሉም ተነሥተው ወደ መስኮቱ አንጋጠጡ፤ እርስ በርስ እንደመተያየት፡፡ እነሱ ጥቁሮች አልነበሩም፡፡ (የባሻ አሸብር ባሜሪካ ዕጣ እስኪደርሰን እና ሁላችንም በእነሱ በአንድ ዐይን እንደምንታይ እንዘነጋለን፡፡)
እስከዳር ወላጅ ሆና ዘንጣ ሊያ ት/ቤት ሄዳ የሚደርስባት ይኸው ነው፡- “ሁላችሁም የቤት ሠራተኞች፣ ያውም መጸዳጃ ቤት አጠቃቀም የማታውቁ፣ ቶሎ የምታብዱ ዜጎች ናችሁ” የሚል ዐይነት ምላሽ ነው የሚገጥማት፡፡
በእነሱ ዐይን እኛ “እነሱ” ነን፡፡ በአንድ ብራንድ ሥር የምንታወቅ፣ ጎራ አስለይቶ የሚያባላን ልዩነታችን፣ መናናቃችን፣ መጨቋቆናችን፣ መጨራረሳችን… ለጥቅማቸው አስፈላጊ እስካልሆነ ድረስ እውቅና የማይሰጥልን የአንድ ኢትዮጵያ የተባለች ፋብሪካ ውጤት ነን፡፡ እስከዳር ከዚህ ጋር ነው ትግሏ፤ እኛ ዲምቢልቢ ያስቀረጸው ምስል ላይ ያለነው ዐጥንታችን የወጣ፣ የተቀቀለ ንፍሮ የምንናፍቅ ረሃብተኞች ብቻ አይደለንም፤ ለዓለም የምናበረክተው፣ የምናስተዋውቀውና የምንሸጠው የተፈጥሮ፣ የባህልና የፈጠራ ሀብት ያለን ነን ብላ ብቻዋን የምትታገለው - ፊታውራሪዋም፣ ፈረሰኛዋም፣ እግረኛ ሠራዊቷም፣ ስንቅ አቀባይዋም፣ ደጀኗም ራሷ ሆና የምትፋለመው ከእንዲህ ያለው የለየለት ፍረጃ እና ከጣጣዎቹ ጋር ነው፡፡
“ነበር”-  እዚህ ክፍል ውስጥ ለየት ከሚሉት ሁለት ወጎች አንዱ ነው፤ ነበር በእንባ የተጻፈ የአትላንታው ቴዎድሮስ ዳኜ እረፍት ከልብ ያልወጣ ሐዘን የተከተበበት ሥራ ነው፡፡ የተጻፈበት ስልት በራሱ ጸሐፊዋን የተሰሟትን ድብልቅልቅ ስሜቶች የተከተለ፣ አንባቢው ላይ ጭምር እውን እና ሕልሙን፣ እውነት እና ምኞቱን ያደበላለቀ ስልት ነው፡፡
እኛው ነን
ሰፋ ያለውን ክፍል የያዘ ዋናው “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” የሚለውንም ወግ ያካተተ የዐሥር ወጎች ማደሪያ ነው፡፡ የዚህ ክፍል መቋጠሪያው ከጌትነት እንየው ግጥም ተመርጠው የተወሰዱ ሥንኞች ናቸው፡፡ የዚህ ክፍል ዋናው ጉዳዩ ሥፍራ ፍለጋ፣ በወገን መሀል ባይተዋርነት፣ ዐመድ አፋሽነት ቢሆንም እንደ ርእሰ ጉዳይ በርካታ ጉዳዮች ተነሥተውበታል፡-
በአንድ ወገን በቀደሙት ክፍሎች የተነሡ መብሰልሰሎች ምሣሌዎቻቸውን፣ መባያ ታሪኮቻቸውን እየቀየሩ ተጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡ (ራስን በሌሎች ዐይን ማየቱ፣ ከሌሎች ጋር ማነጻጸሩ፣ አርበኝነቱ…)
እስከዳር ከምን ከምን፣ ከማን ከማን እንደተሠራች በተለያዩት ወጎች ውስጥ ተመልክቶበታል፤ (በተለይ “አድዋ ትናንትና ዛሬ” የዚህ ምሥክር ነው)
ሠራተኛዋ እስከዳር፣ በጎ አድራጊዋ እስከዳር፣ ሎቢይስቷ እስከዳር፣ ዐመድ አፋሽዋ እስከዳር፣ የክብር ቆንስላዋ እስከዳር፣ የማያድግ አራሚዋ፣ የሰው ሕይወት ከርካሚዋ እስከዳር በወጎቹ ተመሥለዋል፡፡
የ“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው” መለዮዎች
ምን የተለየ ጠባይ አየሁ
ኢ-መደበኛ ወግነት/ ሥነ ጽሑፋዊነት
ወጎች መደበኛ እና ኢ-መደበኛ ተብለው በጥቅሉ ሊከፈሉ ይችላሉ - ለአጥኚ እና ለተማሪ እንዲመች ሲባል፡፡ መደበኛው በአጻጻፉ ኮስታራ ነው፤ አዛዥነት (ኦቶሪቴቲቭ) አለው፤ በአንጻራዊነት ከጸሐፊው ስሜት የጸዳ ነው፡፡ ለዚህ በምሣሌነት ቅድም የጠቀስኳቸውን ጥናታዊ ጽሑፎች እና ጋዜጣዊ ጽሑፎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ የእስከዳር ወጎች ኢ-መደበኛ ወይም ፋሚሊያር የሚባሉትን ዐይነት ወጎች ናቸው - ታሪክን አዋዝቶ ማቅረብን፣ ስሜቶችን እና አመለካከቶችን መደባለቅን እና ሥነ ጽሑፋዊነት ማላበስን ከሚፈቅደው ወገን ልንመድባቸው እንችላለን፡፡
በተለይ ሥነ ጽሑፋዊነት ወይም ምናባዊነት ላልኩት አስረጅ ላቅርብ፡፡
ከሃያዎቹ ወጎች የአብዛኞቹ አጀማመር የተለየ ነው፤ ወጎቹ መንደርደሪያ አቅርቦ ቀጥታ ወደ ጉዳዩ/ታሪኩ ከመግባት ይልቅ ቀልብ በሚስቡ አኔክዶቶች/ ክፍለ ታሪኮች ይጀምራሉ። ድንገተኛ አገባባቸው አንባቢን ይማርካሉ። ይበልጥ በፈጠራ ድርሰቶች ላይ ጥቅም ላይ የሚውል ስልት ነው፡፡
ብዙዎቹ ታሪኮች ውስጥ አሁንም በፈጠራ ድርሰቶች ውስጥ የምናዘወትረው የምልሰት /ፍላሽባክ ሥልት የመረረ የከረረውን ወግ ሁሉ ስሜት ለማዋዛት፣ ሐሳቡንም ለማጉላት፣ ወጉንም ለማዳበር አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡
የፊልም ሠሪነቷ ተፅዕኖ/ አስተዋፅዖ የታየባቸው ወጎች እና የመጽሐፉ ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ “ዋካንዳ ለዘላለም ትኑር” በፋስት ፎርዋርድ ሥልት ሽው ሽው እያሉ የሚያልፉ 8 ተረኮችን እያንደረደረ ከ2004 እስከ 2018 ያጓጉዘናል፡፡ “መውጫ” ደግሞ የመጻሕፍት ልማድ አይደለም፡፡ ኢንትሮ እና አውትሮ የሲኒማቶግራፊው አላባዎች ናቸው፡፡ እስከዳር “መግቢያ” ባለችው ኢንትሮዋ እና በመጋቢ ሐዲስ እሸቱ “ቀዳሚ ቃል” የመጽሐፏን መሠረት አጠናክራ፤ በኃይለ መለኮት “ማሳረጊያ” እና “የመግቢያ መውጫ” ባለችው አውትሮዋ በወጎቿ በወጉ የዳበረ መቋጫዋን ትሰጠናለች፡፡ ሥለዚህ የሲኒማቶግራፊን ሥልቶች ሳይቀር ወደ ወግ ዓለም መጋበዟ መለዮዋ ሊሆን ይችላል፡፡  
የመግቢያን ነገር ካነሳን የመጽሐፉ መሠረት ከተጠናከረባቸው አላባዎች አንዱ ወደ ዋናዎቹ ክፍሎች ልንዘልቅ ስንል የምናገኘው የማያ አንጄሎ ሁለት አርኬዎች ድርድር ነው፡፡ እስከዳር የመረጠቻቸው አርኬዎች የወጎቹን በዚህ ቅርፅ፣ በዚህ ጊዜ፣ በዚህ ስብስብ፣ በዚህ አገር እና በዚህ ርእስ መታተም ለምን ዓላማ ብሎ ለሚጠይቅ ፍንጭ የሚሰጡ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ማያ አንጄሎን መጥራቷ ብቻ ከወጎቿ ምን እንድንይዝላት እንደፈለገች ይጠቁማል። እስከዳር ስለምን ይህን ጻፈች ለሚል ፍንጭ ሰጪ ናቸው ካልኳቸው አርኬዎች ሁለተኛውን ለዚህ ጽሑፍ እንዲያገለግል እንዲህ ተርጉሜዋለሁ፡
በቃል ጥይት ብታቆስሉኝ፣
ባይን ሠይፍ ብትበልቱኝ፤
ቢገድለኝ እንኳ ጥላቻችሁ
እኔ እንዳየር እነሣለሁ፡፡
ግለታሪካዊ ወግነት
የእስከዳር ታሪክ በእነዚህ ሃያ ወጎች ተበጣጥሶ ተተርኳል፡፡ ሙሉ ታሪኳን ላይይዝ ቢችልም ከወልድያ እስከ ባህሬን፣ ከልጅነት እስከ ወላጅነት፣ ከቤት ሠራተኛነት እስከ የክብር ቆንስላነት እና እውቅ ሞዴልነት የደረሰ ምንትነቷን ያስተዋውቀናል፡፡ ለምሳሌ “አደይ እናነይ/አረጋሽ” እና “ሪቮሉሽኒስቱ” ውስጥ ልጅነቷን፤ አሁንም “ሪቮሉሽኒስቱ” እና “ዋካንዳ ለዘላለም ትኑር” ውስጥ ወጣትነቷን፤ እንዲሁም “ልጆቼ ቆሎ ፈጆቼ” ክፍል ውስጥ እና ሌሎቹም ወጎች ውስጥ እናትነቷን እና ሌሎች የምንትነቷን ክፍሎች እናገኛለን፡፡
ስለዚህ እዚህ ተወልጄ፣ እዚህ አድጌ፣ እዚህ ደረስሁ እያለች በዘመን ቅደም ተከተል ባትተርክባቸውም፣ ከንባቤ በመነሣት እነዚህን ወጎች ግለታሪካዊ ወጎች ብዬ በይኛቸዋለሁ፡፡
የጎን ታሪኮች
ደራሲዋ ስልቷንም እንዳሰበችበት በሚያረጋግጥ መልኩ አስቀድሞ ከጠቃቀስኳቸው የሥልት ሙክረቶቿ በተጨማሪ፣ “በነገራችን ላይ” በሚል ልክ እንደ ጨዋታ የቀጠለችበት አተራረክም አላት፡፡ እነዚህ የጎን ታሪኮች የዋናው የወግ ክፍል ተቀጥላዎች ሆነው የገቡ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ፤
የእስከዳር ወጎች ወደ ደራሲዋ መግቢያ በሮች ናቸው፤ በሸዋ በር፣ ወይ በኳሊ በር፣ በእንኮዬ በር፣ በባልደራስ በር፣ በእቴጌ በር፣ በፊት በር ወይ በጓዳ በር ይግቡ ብላ ደራሲዋ አንባቢዋን ወደ ልቧ እና ወደ አእምሮዋ፤ ወደ አፍታዎቿ እና ወደ ኑሮዋ፤ ቨርጂኒያ ዉልፍ “Moments of Being” ወደምትላቸው የሕይወቷ አፍታዎች የምትጋብዝባቸው በሮች ናቸው፡፡ ላንባቢዎቿ ምናባዊዎቹን ሳይሆን እውናዊዎቹን ቁዘማዎቿን፣ መብሰልሰሎቿን፣ ጥያቄዎቿን፣ ኀሠሣዎቿን፣ መረዳቶቿን እና መኮናፈዞቿን፣ መብሰል እና ማረሮቿን፣ መደሰት መከፋቶቿን፣ አንክሮ ተዘክሮዎቿን ገበታ ዘርግታ፣ ሽክና ሞልታ ብሉልኝ ጠጡልኝ የምትልባቸው ናቸው፡፡
አስቀድሞ እንዳልኩት ወደ ውስጥ መመልከቻዎቿም ናቸው፤ ራስን መመልከቻ፣ ማግኛ እና መመዘኛ መሣሪያዎቿ ናቸው፤ እኛን ብቻ ሳይሆን ራሷንም ወደ ራሷ ማዝለቂያዎቿ ናቸው፤ መዝለቋ ደግሞ መንቂያዋ ሆኖ አገልግሏታል፡፡ ካርል ዩንግ እንደሚለው፤ “ርእይሽ ጥርት የሚለው ወደ ውስጥሽ ማየት የቻልሽ እንደሁ ብቻ ነው፡፡ ውጭ ውጭውን የሚያይ ያልማል፤ ውስጥ ውስጧን ያየች ትነቃለች፡፡”
“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?”፤ የእህት አርበኛ እስከዳር ግርማይ የንቃት ውጤት ነው።
(በ27/5/14 የመጽሐፉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የቀረበ)


Read 1361 times