Monday, 25 April 2022 06:23

በስቅለቱ ቀን

Written by  ደራሲ፡- ሊዮኒድ አንድሬዬቭ ተርጓሚ፡- ዐቢይ ጣሰው
Rate this item
(1 Vote)

  በአሰቃቂው ቀን፤ ሁሉን አቀፍ ኢ-ፍትሀዊነት በተፈፀመበት …ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ወንበዴዎች መሐል በጎለጎታ በተሰቀለበት …በዛች ዕለት የእየሩሳሌሙ ነጋዴ ቤን-ቶቪት፣ ከጠዋት ጀምሮ እጅግ ከባድ የጥርስ ህመም አሞት ነበር፡፡ ህመሙ በዚያች ቀን ዋዜማ፤ አመሻሹ ላይ ነበር የጀመረው፡፡ የቀኝ መንጋጋው፤ ከክራንቻው ቀጥሎ ያለችው ጥርስ ትመስለዋለች፡፡
ምላሱ ጥርሱን ስትነካ ትንሽ ነበር ያመመው። ከእራት በኋላ ግን ህመሙ አልፎለት ጭራሽኑ ረስቶት ነበር፡፡ በዕለቱ ያረጀ አህያውን በጠንካራ ወጣት አህያ ለውጦት ስለነበርና በደስታ ስለተዋጠ፣ ለጥቃቅን ነገሮች እምብዛም ዋጋ አልሰጠም።
ማታ ሲተኛ ጥሩ እንቅልፍ ነበር የወሰደው። ሊነጋጋ ሲል ግን አንዳች ነገር ይረብሸው ጀመር፡፡ የሆነ ሰው ለአስቸኳይ ጉዳይ እየነዘነዘ እንደሚጠራው አይነት፡፡ ቤን-ቶቪት በንዴት ጦፎ ከእንቅልፉ ሲነሳ  ጥርሱን እየመዘመዘው ነበር፡፡ ምዝመዛው በመቦርቦርያ እንደሚፈለፍል ያህል የከፋ ነበር፡፡ የትላንቷ ጥርስ ትሁን ከእርሷ ጋር ሌሎች ጥርሶች ተዳምረው ይመሙት እርግጠኛ ሊሆን አልቻለም፡፡ ብቻ  አሁን ቤን-ቶቪት መላ አፉን ጨምሮ ጭንቅላቱ ሳይቀር በከፍተኛ ህመም እየተወቀረ ነው፤ አንድ ሺ የጋሉ ምስማሮች እያኘከ እስኪመስለው ድረስ። ከማሰሮው እፍኝ ውሃ ሲጠጣ፣ ህመሙ ትንሽ ጋብ አለለት፡፡  
ቤን-ቶቪት ጋደም አለ፤ ወጣቱን አህያ እያስታወሰ፡፡ ጥርሱን ባያመው ኖሮ ምን ያህል ደስተኛ ይሆን እንደነበር  አሰበ። መተኛት ፈለገ። የጠጣው ውሃ ሞቅ ያለ ነበር፡፡ ከአምስት ደቂቃ በኋላ የጥርስ ህመሙ ዳግም እጥፍ ድርብ ሆኖ ተቀሰቀሰ። ቤን-ቶቪት ቁጭ ብሎ እንደ ፔንዱለም ደፋ ቀና እያለ መናጥ ጀመረ፡፡ ፊቱ ተጨረማመተ፤ እንደ ጨረጨሰ ሽማግሌ የተሸበሸበም መሰለው፡፡ ከአፍንጫው ጫፍ ላይ አንዲት ዘለላ ላብ  ተንጠለጠለች፡፡ ፊቱ ግርጥት አለ።
በማሰሮ ውስጥ እንደሚናጥ ወተት ከንበል ቀና እያለ፤ ጎለጎታንና በእርሷ የተሰቀሉትን ሶስቱን ልታይ፤ ከዚያም በታላቅ ፍርሃትና ሐዘን መልሳ ልትጨልም የተፈረደባትን ፀሀይ ቀደምት ጨረር ተቀበለ፡፡
ቤን-ቶቪት ጥሩ እና መልካም ሰው ነበር። ኢ-ፍትሐዊነትን አምርሮ የሚጠላ፡፡ ባለቤቱ ከእንቅልፏ ስትነሳ አስደሳች ያልሆነ ነገር ነገራት። እንደምንም አፉን ከፍቶ፤ በህመም እያጓራ እንዲሰቃይ እንደተፈረደበት ቁስለኛ ቀበሮ ብዙ ወቀሳ ሰነዘረባት፡፡ ባለቤቱ ተገቢ ያልሆነውን ወቀሳ በትዕግስት አሳለፈችው።  ከክፉ ልብ የመነጨ አይደለምና፡፡ በርካታ ማስታገሻዎች ሰጠችው፡፡ በአፉ እንዲይዘው ቅርንፉድ፤ ጊንጥ የተዘፈዘፈበት ጠንካራ መጠጥ፤ ሙሴም ከሰበረው የፅላት ስባሪ። ቅርንፉዱን ሲይዝበት ትንሽ ቢሻለውም ብዙም አልቆየም፡፡ ህመሙ ዳግም ሲመጣ ክፉኛ አይሎ  ነበር፡፡
ከህመሙ እፎይታ ባገኘባቸው ጊዜያት ሁሉ ቤን-ቶቪት በወጣቱ አህያ ትውስታ ይጽናናል፤ ስለ አህያው ያልማል። ህመሙ ዳግም ሲቀሰቀስበት ያጓራል፤ ባለቤቱን ይሳደባል፤ ህመሙ በዚህ ከቀጠለ ጭንቅላቱን ከአለት ጋር አጋጭቶ እንደሚያፈርሰው ይዝታል፡፡
ከቤቱ ጣርያ ላይ ወጥቶ ከአንድ ጥግ ወደ ሌላ ጥግ መንጎራደድ ጀመረ፡፡ ሰው እንዳያየው ወደ መንገዱ በኩል ወዳለው ጣርያው መጠጋት አፍሯል፤ እንደ ሴት ጭንቅላቱን በሻሽ ግጥም ተደርጎ ታስሯል። ልጆች ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ በተደጋጋሚ እየመጡ ይነግሩታል፡፡ ለአፍታ ዝም ብሎ ፊቱን አጨማዶ ያዳምጣቸዋል፡፡ ብዙም ሳይቆይ በንዴት መሬቱን በእግሩ እየደበደበ ያባርራቸዋል፡፡ ቤን-ቶቪት መልካም ሰው ነው፤ ልጆችም ይወዳል፡፡ ነገር ግን በማይረባ ነገር እየረበሹ አበሳጩት፡፡
ከመንገዱ ዳርና ከጎረቤት ጣሪያ ላይ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው፣ እንደ ሴት ሻሽ ማሰሩን በግርምት ማየታቸው ረብሾት ከጣሪያው ላይ ሊወርድ ሲል ባለቤቱ፤
“ተመልከት፣ ወንበዴዎቹን  እየወሰዷቸው ነው፡፡ ምናልባት ሐሳብህን ከህመሙ ላይ ሊወስዱት ይችላሉ” አለችው፡፡
“ባክሽ ተይኝ፡፡ ስቃይ ውስጥ እንዳለሁ አይታይሽም?” ቤን-ቶቪት በንዴት ለባለቤቱ መለሰላት፡፡
ነገር ግን በባለቤቱ ንግግር ውስጥ ትንሽ እውነት ቢገኝ፣ለጥርስ ህመሙ ማስታገሻ ከሆነኝ ብሎ ወደ ታጠረው መንገድ ሳያስበው አመራ፡፡ ጭንቅላቱን ወደ አንድ ጎን ጥሎ፤ አንድ አይኑን ጨፍኖ፤ በአንድ እጁ ጉንጩን ደግፎ፤ ሊያለቅስ ቋፍ ላይ እንዳለ ሰው፤ ሊገረፍ እንደተዘጋጀ ልጅ፣ ፊቱ በፍርሃት ተወጥሮ፣ መሬት መሬቱን አቀርቅሮ እያየ ነበር የሚራመደው፡፡
በጠባቡ መንገድ እጅግ በርካታ ሰዎች ስርዓት የለሽ በሆነ ሁኔታ ዳገቱን እየወጡ ነበር፤ አቧራ ለብሰው ያለማቋረጥ ይጮሃሉ። ከመሃከላቸው በተሸከሙት መስቀል የጎበጡ ወንበዴዎች አሉ፤ ከላያቸው ላይ የሮማውያን ወታደሮች አለንጋዎች እንደ ጥቁር  እባብ ይወናጨፋሉ። ከወንበዴዎቹ አንደኛው፤ ነጣ ያለ ፀጉር ያለው፤ በደም የተጨማለቀና የተበጣጠሰ ካባ የለበሰው ድንጋይ አደናቅፎት ይወድቃል፡፡ ይኼኔ ጩኸታቸው በረታ፤ ሕዝቡ እንደቀለም ባህር የወደቀውን ሰው ሊያፍነው ጎረፈ፡፡ ቤን-ቶቪት ድንገት  በህመሙ ተርገፈገፈ፤ የሆነ ሰው የጋለ መርፌ ጥርሱ ውስጥ ሸቅሽቆ ያዟዟረበት መሰለው። አጓርቶ ከመንገዱ አጥር ወጣ-ተናዷል፡፡ በፍርሃት ተርበድብዷል፡፡
“እንዴት አባታቸው ነው የሚጮኹት!” አለ በቅናት፤ጤነኛ ጥርሶች ያጀቧቸውን አፋቸውን እያሰበ፡፡ እርሱ ቢሆን ምን ያህል ከእነርሱ በበለጠ አፉን ከፍቶ እንዴት እንደሚጮህ ባሳያቸው፡፡ ይህ ሃሳቡ ህመሙን ይበልጥ ስላባባሰው የተጀቦነ ጭንቅላቱን እያርገፈገፈ ጮኸ፤ “ኡኡኡ…”
“የታወረ ይፈወሳል ይላሉ” አለች፤ ከአጥሩ በመለስ የቀረችው ባለቤቱ፡፡ በሮማውያን ስጋ ዘንጣይ አለንጋ፣ ከወደቀበት ተነስቶ በዝግታ  እየተጓዘ ወዳለው ኢየሱስ፣ ትንሽዬ ድንጋይ አንስታ ወርውራበታለች፡፡
“በርግጥ…ታዲያ የጥርስ ህመሜን መፈወስ ነበረበት” ሲል በምጸት መለሰላት።  ብስጭትጭት እያለው “አቧራውን እንዴት ነው ያነሱት ጃል! እንደ ከብት መንጋ ጃል! በዱላ መባረር ነበረባቸው! ከዚህ ውሰጅኝ ሳራ!”
ሚስትየዋ ትክክል ነበረች፤ ትዕይንቱ ቤን-ቶቪትን በትንሹም ቢሆን አሽሎታል። ወይም ቅርንፉዱም ሊሆን ይችላል ያሻለው። በስተመጨረሻ እንቅልፍ ጥሎታል፡፡ ከእንቅልፉ ሲነቃ የጥርስ ህመሙ ሙሉ በሙሉ ለቆታል። በቀኝ መንጋጋው በኩል ብቻ ትንሽ ትንሽ ይጠዘጥዘዋል። ሚስቱ ህመሙ ምንም ማለት እንዳልሆነ ነገረችው፡፡ ቤን-ቶቪት በደስታ ፈገግ አለ። ሚስቱ ምን ያህል ገራገር ልብ እንዳላትና ለእርሱ መልካም ነገሮችን መንገር ምን ያህል እንደምትወድ ያውቃል፡፡
ቆዳ ፋቂው የቤን-ቶቪት ጎረቤት ሳሙኤል መጥቶ፤ አዲሱን አህያ ሊያዩ ከቤት ወጡ። ሳሙኤል፣ ጎረቤቱ ስለራሱና ስለአህያው በኩራት የሚነግረውን እያዳመጠ ነበር፡፡
ከዚያ በጉጉዋ ሳራ ጠያቂነት ሶስቱ የተሰቀሉትን ለማየት ተያይዘው ወደ ጎለጎታ ወጡ፡፡ በመንገዳቸው ላይ ቤን-ቶቪት ለሳሙኤል ትላንት ስላመመው የቀኝ መንጋጋውና እንዴት ህመሙ ሌሊት እንደቀሰቀሰው በዝርዝር ነገረው፡፡ ህመሙ እንዴት እንደነበር ለማሳየት ፊቱን የሰማዕት አስመስሎ፤ ዐይኖቹን ጨፍኖ፤ ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡ ቤን-ቶቪት ማጓራቱን ሲጨምር ሳሙኤል ጭንቅላቱን በሃዘኔታ ነቅንቆ  “እህ፤ እንዴት ያለ ከባድ ህመም ነው ባክህ!” አለው፡፡
ቤን-ቶቪት በሳሙኤል ምላሽ ተደሰተ። ታሪኩን ደገመለት፡፡ በዚህም ሳያበቃ ወደ ኋላው መለስ ብሎ ቆይቶ በግራ መንጋጋው በኩል አሞት ስለነበረው ጥርስ መተረክ ጀመረ፡፡ ሞቅ ባለው ወሬ እንደተመሰጡ ጎለጎታ ደረሱ፡፡ በዚያ አሰቃቂ ቀን እንዳትወጣ የተፈረደባት ፀሃይ፣ ራቅ ካሉት ጋራዎች ጀርባ ከጠለቀች ቆይታለች። በምዕራቡ የሰማይ ግርጌ ቀይ ሐምራዊ መስመር እየተንቀለቀለ ነበር-ልክ መሬት ላይ እንደፈሰሰ ደም፡፡ መስቀሎቹ ከዚህ ትዕይንት ዳራ ጨለማ ውስጥ በድንግዝግዙ ቆመው ይታያሉ፡፡ ከመሃከለኛው መስቀል ስር ነጭ የተንበረከኩ ምስሎች እዚህም እዚያም ተሰባጥረው ይታያሉ።
ተሰባስቦ የነበረው ህዝብ ከተበተነ ቆይቷል። ቅዝቃዜ እየጀመረ ነበር። የተሰቀሉትን ሰዎች ለአፍታ አየት አድርገው፤ ቤን-ቶቪት ሳሙኤልን ይዞት በቀስታ ወደ ቤቱ አቅጣጫ አዞረው፡፡ ወደዚህ ሲመጡ በተለየ መልኩ  የንግግር አዋቂነት ስሜት ተሰምቶታል፡፡ እናም የጀመረውን የጥርስ ህመሙን ታሪክ መጨረስ አማረው። ቤን-ቶቪት ፊቱን የሰማዕት አስመስሎ፤ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ድራማዊ በሆነ መልኩ ያቃትታል፤ሳሙኤልም በሃዘኔታ ጭንቅላቱን ይነቀንቅ፣ አሁንም አሁንም የሃዘኔታ ድምጽ ያሰማ ነበር፡፡ ከጥልቁ፤ ከረከሰው ሸለቆ፤ እጅግ ርቆ በቁጣ ከሚንቀለቀለው አምባ የጨላለመ  ምሽት ወጣ፡፡ ጨለማው የምድርን ታላቁን ወንጀል ከሰማይ ዕይታ ለመሸፈን የፈለገ ይመስላል፡፡
("በስቅለቱ ቀን እና ሌሎች ተረኮች" ከሚለው የዐቢይ ጣሰው መጽሐፍ የተወሰደ)





Read 1079 times